የፓሪሱ ጥቃትና የዓለም መሪዎች አስተያየት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 08.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የፓሪሱ ጥቃትና የዓለም መሪዎች አስተያየት

አወዛጋቢ ምፀታዊ ምስሎችን በሚያወጣው ሻርሊ ኤብዶ በተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ የፓሪስ ቢሮ ውስጥ ትናንት በታጣቂዎች የተፈፀመው ግድያ በአብዛኛው የዓለም ክፍል እየተወገዘ ነው ።

የዓለም መሪዎች ፖለቲከኞች ጋዜጠኞች የሃይማኖት መሪዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ባስተላለፉት የሃዘን መግለጫ ጥቃቱን አረመኔያዊ ሲሉ አውግዘውታል ። ትናንት ምሽት በተለያዩ የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ ከተሞች በርካቶች አደባባይ በመውጣት በከባድ መሳሪያዎች የተገደሉትን ሰዎች አስበዋል ።
ፊታቸውን በጭንብል የሸፈኑ ታጣቂዎች ፓሪስ ፈረንሳይ የሚገኘውን ሻርሊ ኤብዶ የተባለውን ጋዜጣ ቢሮ ትናንት በሃገሩ ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ቀን አካባቢ ሰብረው በመግባት በእሩምታ ተኩስ በ 10 የጋዜጣው ሠራተኞችና በ2 ፖሊሶች ላይ የፈፀሙት ግድያ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት የሚከበርበትን ምዕራቡን ዓለም ክፉኛ አስቆጥቷል ። የዓለም መሪዎች ለፈረንሳይ በላኩት የሃዘን መግለጫ ጥቃቱን በእጅጉ አውግዘዋል ። አብዛኛዎቹ ግድያውን የዴሞክራሲ ማዕዘን በሆነው ሃሳብን በነፃ መግለፅ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ሲሉ ነው የገለፁት ። በየጀርመን ፕሬዝዳንት ዮአሂም ጋውክ ለፈረንሳዩ ግድያውን አውግዘው ከአሁን ወዲያ ለነፃነት ለሰብዓዊ መብቶችና ለዴሞክራሲ ያለመታከት መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በበኩላቸው ጥቃቱ በፈረንሳላይ ላይ ብቻ የተፈፀመ አይደለም ብለዋል ።«ፍፅም ተቀባይነት የሌለው ይህ ጥቃት በፈረንሳይ ዜጎችና በፈረንሳይ የሃገር ውስጥ ደህንነት ላይ ብቻ የተሰነዘረ አይደለም ።የነፃና ዴሞክራሲያዊ ባህላችን አስኳል በሆነው ሃሳብን በነፃ በመግለጽ መብትና በፕሬስ ነፃነት ላይ ጭምር የተፈፀመ ጥቃትን ያሳያል ።ይህ ደግሞ በምንም ዓይነት መንገድ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም ። »

ጥቃቱን የሚያሳምም እና አረመኔያዊ ሲሉ ነው ያወገዙት የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ኬምረን ያወገዙት ። የፈረንሳይ ህዝብ ሽብርን ለመዋጋትና የፕሬስ ነፃነትን ለማስጠበቅ በሚያካሂደው ትግል መንግሥታቸው ከጎኑ እንደሚቆምም ቃል ገብተዋል ።የተመድ ዋና ጸሃፊ ባን ኪሙን የመከፋፈል ዓላማ ይዞ ለተነሳው ለዚህ ጥቃት መንበርከክ አይገባም ሲሉ አሳስበዋል ።

«እጅግ አስከፊ ተቀባይነት የሌለው በጭፍን የተፈጸመ ወንጀል ነው ። በዴሞክራሲና በመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት የማዕዘን ድንጋዮች ላይ የተሰነዘረ ቀጥተኛ ጥቃት ነ ው ። የአሰከፊው ጥቃት ዓላማ መከፋፈል ነው ። በዚህ ወጥመድ ውስጥ መውደቅ የለብንም ። ይህ በህብረት የምንቆምበት ወቅት ነው ።በዓለም ዙሪያ ሃሳብን በነፃ ለመግለፅ እና ለመቻቻል እንዲሁም በከፋፋይና በጥላቻ ኃይሎች ላይ ጠንክረን መነሳት ይገባናል ።»በጥቃቱ ለተገደሉት ቤተሰቦች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ለቆሰሉት ደግሞ መልካም ምኞታቸውን ያስተላለፉት ባን የፈረንሳይ ባለስልጣናት ኃይላቸውን በሙሉ በመጠቀም ወንጀለኞቹን በአስቸኳይ ለፍርድ ያቀርባሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም አስታውቀዋል ።

የአውሮጳ ህብረት ፓርላማ ደግሞ የአፀፋዊው እርምጃ ስሜታዊ እንዳይሆን አስጠንቅቋል ። የፓርላማው ፕሬዝዳንት ማርቲን ሹልዝ ከፕሬስና ሃሳብን በነፃ ከመግለፅ ነፃነት ጋር መከባበርና መቻቻልም መሰረታዊ እሴት መሆኑን አስታውሰው የሚወሰደው እርምጃ ስሜታዊ ሳይሆን በሰላምና የአውሮጳን እሴቶች የሚያስጠብቅ ሊሆን ይገባል ብለዋል ።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም የተፈፀመው ጥቃት ሃሳብን በነፃ ከመግለፅ ሊያግድ እንደማይችል ተናግረዋል ።

«ጥቃቱ በጋዜጠኞች በነፃ ፕሬሳችን ላይ የተፈፀመ ፣ መሆኑ እነዚህ አሸባሪዎች ምን ያህል የነፃነት ፍራቻ እንዳላቸው ያሳያል ።ሆኖም እኔ የምተማመንበት ነገር ቢኖር ከፈረንሳይ ህዝቦች ጋር የምንጋራው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ እምነት ጥቂቶች በፈፀሙት ትርጉም በሌለው ጥቃት ሰበብ መታፈን የሚችል አይደለም። »
በአሰቃቂው ግድያ ልባቸው የተነካ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሃዘናቸውንና ጥቃቱ ያሳደረበቸውን ስሜት አደባባይ በመውጣት ሲገልፁ ነው ያመሹት ።በምስራቅ ፓሪስ ጥቃቱ በተፈፀመበት አቅራቢያ በሚገኘው «ፕላስ ደ ላ ሪፐብሊክ» በተባለው ስፍራ በርካቶች ወረቆቶች እስክሪብቶ ዎችና እርሳሶችን ከፍ አድርገው በመያዝ ለመገናኛ ብዙሃንና ለንግግር ነፃነት ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል ። «ሻርሊ ነኝ »እያሉ ጥቃቱን ያወገዙ በርካታ ሰዎች በበርሊን ጀርመን በለንደን ብሪታኒያ በስፓኝ ማድሪድ በቤልጂግ ብራሰልስ ተመሳሳይ ድጋፋቸውን ገልፀዋል ። በአንፃሩ በኢራቅና በሶሪያ የሚንቀሳቀሰው ራሱን እስልማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ቡድን አንድ ተዋጊ ጥቃቱን አወድሶ ይህ የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አይሆንም ብሏል ።

ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic