የፓሪሱ ግድያና የጀርመን የፀጥታ ሥጋት፣ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 09.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የፓሪሱ ግድያና የጀርመን የፀጥታ ሥጋት፣

ከትናንት በስቲያ ፓሪስ ውስጥ፣ በተፈጸመው የሽብር ተግባር ሳቢያ ፣ ድንጋጤ፣ ንዴትና ሐዘን ተፈራርቀዋል። ሻርሊ ኤብዶ የተባለው አሥቂኝ ስዕሎችን («ካርቱንስ»)መሠረት ያደረገ የምፀትና ሥላቅ መጽሔት በሚዘጋጅበት ማዕከል አሸባሪዎች ሰተት ብለው ገብተው

በጥይት 12 ሰዎችን ከገደሉና 11 ካቆሰሉ ወዲህ፤ ጀርመን ያ ዓይነቱ አሸባሪ ተግባር በምድሯ ሊፈጸም እንደሚችል በማሰላሰል ሥጋት አድሮባታል። ስለሆነም በአንዳንድ፣ ከሻርሊ ኤብዶ «ካርቱን» እየተዋሱ ያሳትሙ በነበሩ ፤ የጋዜጣ ድርጅቶች አካባቢዎች፣ ፀጥታ አጠባበቅን ለማጠናከር ፤ ፖሊሶች በብዛት ነው የተሠማሩት። ከፓሪሱ የሽብር ተግባር ወዲህ ጀርመን የፀጥታዋ ይዞታ ይበልጥ አሳስቧታል።

የጀርመን የጸጥታ ጉዳይ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሆነ ጀርመን ከሥጋት እንድትላቀቅ የሚያደርግ ሁኔታ የለም። በፓሪስ የደረሰውን ዓይነት አሸባሪ ተግባር ፈጽሞ መከላከል እንደማይቻል የፀጥታ ጉዳይ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ በብሪታንያው የሊድስ ዩንቨርስቲ የወንጀል ጉዳይ ተመራማሪ አንድሪያስ አርምቦርስትም ተመሳሳይ አስተያየት ነው የሠነዘሩት።

«ያን የመሰለው ጥቃት ፈጽሞ እንዳይደርስ አስተማማኝ መከላከያ የለም። ያም ሆኖ የጸጥታ አጠባበቅ ርምጃዎቹ ነጻነትንና ሌሎች እሴቶችን የማይሸረሽሩ መሆን ይኖርባቸዋል። እናም ክፍተት የማይታይበት የጸጥታ ቁጥጥር ተፈላጊ ይሆናል። እንደሚመስለኝ ፣ አሸባሪዎች፤ ወይም የተጠቀሰውን ዓይነት ተግባር ለመፈጸም የሚዘጋጁ ሰዎች እስካሉ ድረስ፤ ነጻነት ባለው ሕብረተሰብ መካከል፣ ምንጊዜም የጭካኔ ግድያ የመፈጸም አጋጣሚ ይኖራቸዋል።»

ጀርመን ውስጥ በመጋቢት 2003 ዓ ም፤ አንድ የኮሶቮ-አልባንያዊ ፤ ፍራንክፈርት አይሮፕላን ማረፊያ በወሰደው አሸባሪ ተግባር 2 አሜሪካውያን ወታደሮችን በጥይት መግደሉ የሚታወስ ነው። ጀርመን አሁን ያሠጉኛል የምትላቸው IS በሚል ምሕጻር ለሚታወቀው አክራሪ እስላማዊ ንቅናቄ ለመዋጋት ሶሪያና ኢራቅ ደርሰው የተመለሱትን «ወግ አጥባቂ ሳላፊስቶች » ነው። ቁጥራቸው ወደ 600 ገደማ የሚገመተው እነዚሁ በአክራሪነት የሚጠቀሱት ሰዎች ሊጥሉ ይችላሉ የሚለው ሥጋቷ ከፍ ያለ ነው።

በበርሊን የሚኖሩት የስነ ልቡና ባለሙያና የእሥልምና ጉዳዮች ተመራማሪ አህመድ ማንሱር እንዲያውም አልፎ -አልፎ « የጀርመን ዜጎች የሆኑ ጂሃዲስቶች» እየተባሉ የሚጠቀሱት ወገኖች ቁጥር ከ 1500-2000 እንደሚደርስ ነው የገለጡት። ወደ ሶሪያ በመዝመት በእርስ በርሱ ጦርነት ከተሳተፉት መካከል 180 ገደማው ተመልሰው ጀርመን መግባታቸው ነው የሚነገረው። ፔተር ናውማን የተባሉት ሌላው ስለአካራሪነት ምርምር የሚያደርጉት ባለሙያ ቁጥራቸው ከተጠቀስው መካከል እጅግ አደገኞች የሚሰኙት 10 ከመቶው አይበልጡም ባይ ናቸው።

በሻርሊ ኤብዶ ማዕከል ደም እንዲንጣለል አድርገዋል ተብለው ከሚጠረጠሩት ሁለቱ የአልጀሪያ ዝርያ ያላቸው ወንድማማች መካከል፤ አንደኛው ፣ ኢራቅ ውስጥ በጂሃድ ጦርነት የሚሳተፉ ሰዎች በቅስቀሳ ይመለምል እንደነበረና በዚህ ሳቢያ ተከሶ እ ጎ ኣ በ 2008 ፤ የ 3 ዓመት እሥራት ተበይኖበት አንድ ዓመት ከመንፈቅ ብቻ ታሥሮ መለቀቁ ተነግሯል። ይሁንና ያን መሰሉ የእሥር ተመክሮ ይበልጥ አካራሪነትን የሚያጠናክርበት ሁኔታ መኖሩን በለንደን የጸጥታ ይዞታ ጉዳይ ባለሙያ ራፋኤሎ ፓንቱቺ እንዲህ ብለዋል።

«ይህን መሰል ሁኔታ ሲያጋጥም በአንድ በኩል በቀጥታ እሥር ያጋጠመውን ሰው ለመሆን የሚሹ ሰዎችን ነው የሚያፈራው። የተሣካ ተግባር ነው ብለው ያንኑ ራሳቸው ለመፈጸም ይነሣሣሉ። በሌላ በኩል ጉዳዩን በረጅሙ ሲያጤኑት፤ ሰዎች ድርጊቱን አዲስ የማጥቂያ ዘዴ አድርገው ይመለከቱታል። አሁን በተግባር የታየ ነው ብለውም በአርአያነት ይወስዱታል። »

የዓለም አቀፍ የፀጥታ ጉዳይ ምርምር ተቋም Royal United Services Institute(RUSI) ሥራ አስኪያጅ ፓንቱቺ፤ በፓሪስ የተፈጸመውን የሽብር ተግባር ፣ እንደ በጎ አርአያ በመመልከት ተፈጻሚ ለማድረግ የሚሚክሩ ሰዎች አይታጡም ባይ ናቸው። በሻርሊ ኤብዶ ላይ የተፈጸመውን ድርጊት አክራሪ የሆኑ ሙስሊሞች አስመስጋኝ ተግባር አድርገው ነው በማሕበራዊ የህዝብ መገናኛ ዘዴዎች አስተያያታቸውን ያንጸባረቁት። ነፍሰ ገዳዮችንም ጀግኖች ናቸው በማለት አድንቀዋቸዋል። IS በሚል ምሕጻር የሚታወቀው በሦሪያና ኢራቅ የሚንቀሳቀሰው ኃይልም ለራሱ ፕሮፖጋንዳ እያዋለው ነው።

የጀርመን የፀጥታ ባለሥልጣናት ፣ አሁን 260 ያህል ሰዎች ለጸጥታ አሥጊነታቸው እንደማያጠራጥር ነው የገለጹት። አሁንም ራፋኤሎ ፓቱቺ---

«ምን ማድረግ ይቻላል? የገረረ አቋም የያዙ ፣ ሥልጠናም ያገኙ ሰዎች በማህበረሰብ ውስጥ እስካሉ ድረስ አንዳንዴም የግንኙነት መሥመር እስከዘረጉ ድረስ ፤ ጉዳዩ ለረጅም ጊዜ የሚያሳስብ ነው የሚሆነው። የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎችም አክራሪዎችን ለመለየት ሰዎችን በጥሞና እስከመከታተል ይደርሳሉ። ለጥቂት ጊዜ በእሥራት ላይ የነበሩ ወይም ተመሳሳይ ወንጀል የፈጸሙ የአደጋው መሥመር የት ላይ ነው ? ስለዚህም፤ ፀጥታ አስከባሪዎች ተመልሰው ፣ ተጠርጣሪዎቹ አክራሪዎች፤ ጦር መሳሪያ ወይም ተመሳሳይ ነገር እንደሌላቸው እርግጠኞች መሆን ይሻሉ።

ተክሌ የኋላ/ማትያስ ፎን ሃይን

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic