የፓሪሱ የአየር ንብረት ዉል ዕጣ ፈንታ እና ትራምፕ | ጤና እና አካባቢ | DW | 30.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የፓሪሱ የአየር ንብረት ዉል ዕጣ ፈንታ እና ትራምፕ

ዘመነ ሥልጣናቸዉን ከጀመሩበት ጊዜ አንስተዉ ያልለወጡት ነገር የለም።  «የአየር ንብረት ለዉጥ» «መቋቋም» በሚለዉ፤ «የቤት ዉስጥ ጥቃት ሰለባዎች» «የወንጀል ሰለባዎች» ተብሏል፣ «ለስደተኞች መብት የዉጭ ርዳታ» «በብሔራዊ ደሕንነት መከላከል ርዳታ» ፤ «የንፁሕ ኃይል መዋዕለንዋይ ፍሰት» «የኃይል መዋዕለ ንዋይ ፍሰት» ብቻ በሚል ተቀይሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:31

የሚጠበቀዉ የዶናልድ ትራምፕ አቋም፤

 የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከስያሜዎች አንስቶ ለዉጦችን እያደረገ ነዉ። በዚህ አላበቁም አነጋጋሪዉ ፕሬዝደንት፤ የአሜሪካን የአካባቢ ጥበቃ ተቋም ስለአየር ንብረት ለዉጥ ያሰፈራቸዉን መረጃዎች ከድረ ገጹ እንዲሰርዝ ትዕዛዝ የሰጡት ሥልጣናቸዉን በይፋ በተረከቡ በቀናት ዉስጥ ነዉ።

ለምርጫ ቅስቀሳ ከሚያደርጉበት ጊዜ አንስተዉ የአየር ንብረት ለዉጥ አለ መባሉን እንደማያምኑ፤ አልፈዉ ተርፈዉም የዓለም ሙቀት ጨምሯል ስለሚባለዉም ምንም የተጨበጠ ነገር እንዳላዩ በይፋ ሲናገሩ ተደምጠዋል። በዚህም ምክንያት እወደዋለሁ ያሉትን የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ኢንደስትሪ ማስፋፋት እንዲሁም የተዘጋዉን መክፈት፤ አሜሪካ የፈረመችዉን የፓሪስ ስምምነትን መሰረዝ፤ እና ተያያዥ ርምጃዎችን መቀልበስ በመጀመሪያዎቹ አንድ መቶ የሥራ ቀናት የሚያከናዉኗቸዉ ተግባራት መሆናቸዉን ለደጋፊዎቻቸዉ እንዲህ በዝርዝር ቃል ገብተዉ ነበር።

«ባራክ ኦባማ መጥፎ እንደመሆናቸዉ ሂላሪ ክሊንተን ደግሞ የባሱ ይሆናሉ። ከዚህ በፊት ከነበረዉ በባሰ በአሜሪካዉያን ሠራተኞች እና በአሜሪካን የኃይል ዘርፍ ላይ የተከፈተዉን ጦርነት ያባብሱታል። የአሜሪካን የአካባቢ ጥበቃ ተቋምም እያንዳንዱን የሕይወታችንን እና የኃይል ምንጭ መስክ እንዲቆጣጠረዉ ያደርጋሉ።  በመቶ ቀናት ዉስጥ ተግባራዊ የማደርገዉ ዕቅድ የሚከተለዉ ነዉ፤ በኦባማ አስተዳደራዊ ዉሳኔ የተዘጉ ሥራዎችን መልሰን እናያቸዋለን። የአየር ንብረት ተግባራዊ ዕቅድን ጨምሮ የአሜሪካንን ሚናም ሁሉ እንፈትሻለን፤ የድንጋይ ከሰሉን ዘርፍ እንታደገዋለን፤ እመኑኝ እንታደገዋለን፤ እነሱን ሰዎች እወዳቸዋለሁ፤ ግሩም ሰዎች ናቸዉ። የፓሪሱን የአየር ንብረት ዉል ስምምነት እንሰርዛለን፤ ለተመድ የዓለም የሙቀት መጨመር መርሃግብር የሚከፈለዉን የዩናይትድ ስቴትስ የግብ ከፋዮች ዶላር በሙሉ እናስቆማለን።»

አሁን ዶናልድ ትራምፕ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ናቸዉ፤ ያሉትንም በተግባር ማድረግ ጀምረዋል። ይህ አቋማቸዉ በሀገራቸዉ ብቻ ሳይሆን በመላዉ ዓለም ዓይን ዉስጥ ከቷቸዋል። እሳቸዉ ግን ለዚህ ቁብ አልነበራቸዉም፤ የላቸዉምም። በርቀት ሲናገሩት የከረሙትን በቡድን ሰባት ሃገራት ጉባኤ ላይ ጉዳዩን ደግፈዉ መፍትሄ እንዲወሰድ ፓሪስ ላይ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም ተሰማምተዉ ኋላም በየግላቸዉ ዉል ለመግባት በወሰኑት በስድስቱ የኃያላን መንግሥታት መሪዎች ፊት እንደዘበት ደገሙት። ከባህር ማዶ ሆነዉ በመገናኛዉ ስልት አማካኝነት ያስተጋቡት የነበረዉ አቋማቸዉን በክብ ጠረጴዛ ከአቻዎቻቸዉ ጋር ተገናኝተዉ በመነጋገር ይለዉጡት ይሆናል የሚል ተስፋ ቢጤ ያላቸዉም አሁን ከባለፈዉ ሳምንት ዓርብ እና ቅዳሜዉ የጣሊያኗ ደሴት ሲሲሊ የቡድን ሰባት ጉባኤ በኋላ እርማቸዉን ያወጡ መስለዋል። እርግጥ ነዉ የፓሪሱን ስምምነት በቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ዘመነ ሥልጣን ሀገሪቱ ተቀብላለች። መቀበሏ ለአካባቢ ተፈጥሮ የሚቆረቆሩትን ወገኖች ሁሉ በወቅቱም ጮቤ አስረግጧል። የዓለማችን ግንባር ቀደም ከሆኑት ከባቢ አየር በካይ ሃገራት ዋነኛዋ በመሆኗ። ከሌላ ፕላኔት የመጡ የሚመስሉት የትራምፕ አቋም ግን ያንን ዘመነ ፍሰሀ ብዙም አላሰነበተዉም። እንደዉም የድላቸዉ ዜና ሲሰማ ማራካሽ ሞሮኮ ላይ ይካሄድ የነበረዉ የዚህ ዓመቱ የተመድ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ጉባኤ መደናበር ታይቶበታል። ከሰሞኑም የታየዉ የዚሁ ተመሳሳይ ነዉ።

G7 Gipfeltreffen Donald Trump spricht mit Angela Merkel und Beji Caid Essebsi

የቡድን ሰባቱ ጉባኤ ገጽታ

በቡድን ሰባት ጉባኤ ላይ ከተገኙት መካከል የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የአየር ንብረት ለዉጥን አስመልክቶ በጉባኤዉ ላይ የተደረገዉ ዉይይት እንዳላስደሰታቸዉ ስብሰባዉ ከተካሄደበት ከታኦሚና ቅዳሜ ዕለት በይፋ ነዉ የተናገሩት።

«የአየር ንብረትን በሚመለከተዉ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተደረገዉ ዉይይት በጣም አስደሳች እንዳልነበረ አለመናገሩ አስቸጋሪ ነዉ የሚሆነዉ። እዚህ ጋር አንድ ሁኔታ አለ፤ ስድስት፣ ወይም የአዉሮጳ ኅብረትን በዚያ ላይ ከወሰድን ሰባት እንሆናለን። ይህም ማለት  ከዩናይትድ ስቴትስ በኩል በፓሪሱ ስምምንነት መቀጠል ያለመቀጠሏ ጉዳይ እስካሁን ግልጽ የተደረገ አቋም አልታየም።»

ዘ ጋርዲያን እንደዘገበዉ ከቡድን ሰባቱ ጉባኤ በኋላ የዶናልድ ትራምፕ በአየር ንብረት ለዉጥ ስምምነቱ ላይ ያላቸዉ አቋም ግልፅ እንዳልሆነና በመጪዉ ሳምንትም ሊለይለት እንደሚችል ነዉ የተነገረዉ።

ከቡድን ሰባቱ ስብሰባ በኋላ ፕሬዝደንት ትራምፕም ይህን ጉዳይ አስመልክተዉ በቲዊተር ላይ ባሰፈሩት መልዕክታቸዉ «የፓሪስን ስምምነት በተመለከተ በሚቀጥለዉ ሳምንት የመጨረሻ ዉሳኔዬን አደርጋለሁ።» ሲሉ አስፍረዋል። የመከላከያ ሚኒስትራቸዉ ጀምስ ማቲስ እሁድ ዕለት በCBS ቴሌቪዥን ለአየር በበቃዉ ቃለመጠይቃቸዉ ላይ የአየር ንብረት ለዉጥን አስመልክቶ የትራምፕ አስተዳደር ያለዉን አቋም ሲጠየቁ ምንም እንኳን ይህ በቀጥታ የእሳቸዉ የሥራ ኃላፊነትን የሚመለከት እንዳልሆነ ቢጠቁሙም አስተያየታቸዉን ግን እንዲህ ሰጥተዋል።

«እንደሚታወቀዉ ይህን በተመለከተ የተሻለ መመሪያ እንዲኖር ዉይይት እየተካሄደ ነዉ። የአየር ንብረት ለዉጥን በሚመለከት የተወሰነዉ ዉይይትም ብራስልስ ላይ ተደርጓል። ፕሬዝደንቱም ቢሆኑ ግልጽ ነበሩ፤ ሌሎች አቻዎቻቸዉ እና ሌሎች ሃገራት ከዚህ አቋም ላይ የደረሱት ለምንድነዉ የሚለዉን ለማወቅም ጉጉት አላቸዉ። እናም ፕሬዝደንቱ የስምምነቱን አዎንታዊ እና አሉታዊ ገፅታዎች ከተረዱ በኋላ ፕሬዝደንቱ ፍጹም ግልጽ እንደሚሆኑ እኔ እርግጠኛ ነኝ። እርግጥ እዉነቱን ለመናገር ይህ በእኔ የሥልጣን ደረጃ ያለ ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን በመከላከያዉ ዘርፍ በሞቃት የአየር ጠባይ ዉስጥ እንደምንሰራ ግልጽ ነዉ።»


«መሬት እናታችን ናት፤ ሌላ መተኪያ ልናገኝላት አንችልም።» እንዲህ እያሉ በአደባባይ የዘመሩት የፕሬዝደንት ትራምፕ አዲስ መመሪያ በቀድሞዉ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ለአካባቢዉ ነዋሪዎችና ለተፈጥሮ ስጋት መሆኑን ከግምት በማስገባት የተዘጉ የነዳጅ ማዉጫ፤ እና የድንጋይ ከሰል ማምረቻ አካባቢዎች መከፈታቸዉን ተቃዉመዉ ካፒቶል ሂል ድረስ የተጓዙት የኮሎራዶ ነዋሪዎች ናቸዉ። እነዚህን ሰልፈኞች ያስተባበራቸዉ የ16 ዓመቱ ሹተስካት ማርቲነስ ለእናት መሬት ጥንቃቄ እንዲደረግ በሚያደርገዉ ቅስቀሳ የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ተሳክቶለታል።

«ለምናምንበት ነገር መታገል ትልቅ ነገር ነዉ፤ ይህ ታላቅ ሰልፍ ነዉ። ሰዎች ኃይል አላቸዉ። ቀጣይ አራት የትራምፕ የስልጣን ዓመታት ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ መገመት ነዉ። ሰዎች መንግሥታችን ለሚያደርጋቸዉ እንቅስቃሴዎች ከእንግዲህ አብሮ አይቆምም።»

በኮሎራዶ ሮኪ ተራራዎች ላይ እምቅ ሃብት አለ፤ የነዳጅ ዘይት እና የጋዝ ክምችት። የትራምፕ አስተዳደር በሰጠዉ የይለፍ ፈቃድ ምክንያትም ይህን ለማዉጣት ታዲያ መሬቱን በድማሚት እየፈነቀሉ እንቅስቃሴዉ ተጀምሯል። ይህ ነዉ እነ ማርቲነስን አስቆጥቶ አደባባይ ያስወጣቸዉ።

«ሥራቸዉን ማከናወኑ አልተሳካላቸዉም። የሰዎችን ጤና የመጠበቅ ኃላፊነታቸዉን አልተወጡም። ከከርሰ ምድር ሀብቱን ሊያወጡ የሚንቀሳቀሱትን ኩባንያዎች በየሰዉ ቤት ጓሮ፣ በትምህርት ቤቶችና በሃኪም ቤቶች አካባቢ የቁፋሮዉን ሥራ እንዲያከናዉኑ ፈቅደዋል፤ ይህም የቅሪተ አጽም ዉጤት የሆነዉ ነዳጅ የኮሎራዶ ነዋሪዎችን ጤና በሚያቃዉስ መልኩ እየቆፈሩ እንዲያወጡ ፈቅደዋል። እኛም እዚህ የምንገኘዉ ይህ አይሆንም ለማለት ነዉ።»

ለተፈጥሮ ተገቢዉ ክብካቤ ካልተደረገ ዉጤቱ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ከትንሽነቱ እየሰማ ያደገዉ ወጣት ከኋላዉ በርካቶችን አስከትሎ የሀገሪቱ መንግሥት መናገሻ ድረስ በመሄድ ድምጹን ማሰማቱ፤ የብዙዎቹን ፍላጎት የገለጸ ነዉ ቢባልለትም ፕሬዝደንቱ ምን ያህል ትኩረት ሰጥተዉት ይሆን የሚለዉ ግን ከጥያቄ የሚያልፍ አይደለም።

እሳቸዉ ለምርጫ ቅስቀሳቸዉ ያሰሙት ንግግር መቀስቀሻ ብቻ ሆኖ እንደማይቀር የተከለከሉትን ሲፈቅዱ አሳይተዋል፤ በቡድን ሰባቱ ጉባኤ በተለይም ከመሰሎቻቸዉ የምዕራቡ ዓለም መንግሥታት መሪዎች ጠንከር ያለ ክርክር ከገጠማቸዉ በኋላ ምን ያህል በአቋማቸዉ ወደፊት ይገፉበታል የሚለዉን የሚመልሰዉ በመጪዉ ሳምንት ይፋ አደርገዋለሁ ያሉት ዉሳኔያቸዉ ነዉ የሚሆነዉ። እንዲያም ሆኖ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸዉ ወቅት እንደዛቱት እያንዳንዱ ሀገር በፈቃደኝነት ወደከባቢ አየር የሚለቀዉን ሙቀት አማቂ ጋዝ መጠን የመቀነስ ዉሳኔ የሚያጥፉ ከሆነ፤ አሜሪካ ከስምምነቱ ለመገለል ሦስት ዓመታት መጠበቅ ይኖርባታል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ተንታኞች ይህ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ የሚካሄድበትን ወቅት ያደርሰዋል የሚል እምነት አላቸዉ። እናም በዚህ ምርጫ ትራምፕ ዳግም መመረጥ ከተሳካላቸዉ ብቻ ይሆናል በአቋማቸዉ ከፀኑ ያሉትን ተግባራዊ ማድረጉ የሚሳካላቸዉ። በተቃራኒዉ ደግሞ ከዚህ ሌላ አማራጭም እንዳለ ያስባሉ፤ ትራምፕ ሀገራቸዉ በፓሪሱ ዉል ፀንታ እንደምትቆይ ያረጋግጡና ያንን እዉን የሚያደርጉ እርምጃዎችን ግን ላይወስዱ ይችላሉ ሲሉም ይገምታሉ። ያም ሆነ ይህ ምዕራባዉያን አቻዎቻቸዉ በጀመሩት መንገድ መቀጠላቸዉ እንደማያጠራጥር እያሳወቁ ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic