የፓሪሱ የአውሮጳ እና የአፍሪቃ መንግሥታት ጉባኤ እና ውጤቱ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 29.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የፓሪሱ የአውሮጳ እና የአፍሪቃ መንግሥታት ጉባኤ እና ውጤቱ

የመሪዎቹን ውሳኔ መቀበላቸውን የዩ ኤን ኤች ሲ አር ሃላፊ ፊሊፖ ግራንዲ ገልጸው የስደተኞችን ቁጥር መቀነስ ብቻ አጠቃላዩን ችግር መፍታት እንደማይችል አስታውቀዋል። ከዚያ ይልቅ እቅዶቹ የስደተኞቹ መነሻ በሆኑ ሀገራት ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንባቸው ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ እድገቶች እውን የሚሆኑባቸውን መንገዶችም እንዲያካትት አሳስበዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:30
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:30 ደቂቃ

በኒዠር እና በቻድ ማመልከቻዎች የሚጣሩባቸው ማዕከላት ይቋቋማሉ።

የፈረንሳይ የጀርመን የኢጣልያ እና የስፓኝ መሪዎች ፣ አውሮጳ ሳይመጡ አፍሪቃ ሆነው ለሚያመለክቱ ከለላ ሊያገኙ ይገባል ለሚባሉ ስደተኞች ተገን መስጠት ያስችላል ባሉት አዲስ መርህ ተስማሙ። የአራቱ የአውሮጳ ሀገራት መሪዎች ትናንት ፓሪስ ፈረንሳይ ውስጥ ከሦስት የአፍሪቃ ሀገራት መሪዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ ባወጡት መግለጫ አዲሱ መርህ ተገን ማግኘት የሚገባቸው ሰዎች በህጋዊ መንገድ ወደ አውሮጳ እንዲሰደዱ ያስችላል ብለዋል። አዲሱ እቅድ ፋይዳው እና ትችቱ የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን የሚቃኛቸው ጉዳዮች ናቸው።

የአራት የአውሮጳ እና የሦስት የአፍሪቃ አገራት መሪዎች ትናንት ፓሪስ ፈረንሳይ ያካሄዱት ጉባኤ ዓላማ ህገ ወጥ ለሚሉት ስደት ዘላቂ መፍትሄ መሻት ነበር። ከአውሮፓ የፈረንሳይ የጀርመን የኢጣልያ እና የስፓኝ እንዲሁም ከአፍሪቃ የሊቢያ የኒዠር እና የቻድ መሪዎች በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮጳ የሚደረግ ስደትን በዘላቂነት ለማስቆም ከለላ ማግኘት የሚገባቸውን ስደተኞች የመለየቱ ሥራ አፍሪቃ ውስጥ እንዲካሄድ ተስማምተዋል። በመሪዎቹ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ በወጣው መግለጫ መሠረት የስደተኞች ዋነኛ መሸጋገሪያ በሆኑት በኒዠር እና በቻድ የተ መ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ዩ ኤን ኤች ሲአር የተገን ማመልከቻዎቻቸውን የሚያጣራባቸው ደህንነታቸው የተጠበቀ ማዕከላት ይቋቋማሉ። የነዚህ ማዕከላት መቋቋም ሰዎች እጅግ

አደገኛ ከሆኑት የባህር እና የበረሃ ጉዞዎች እንዲቆጠቡ ያደርጋል የሚል እምነት አለ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከጉባኤው በኋላ በሰጡት አስተያየት የአውሮጳ መንግሥታት እቅዱ እንዲሳካ የበኩላቸውን ድጋፍ ያደርጋሉ ሆኖም ትልቁ ትልቁ ሥራ ትክክለኛውን እና የኤኮኖሚውን ስደተኛ ለይቶ ማወቁ ትልቁ ሥራ ነው ብለዋል። 
«ፈረንሳይ አንዳንድ ሃሳቦችን አቅርባለች። የተመ የስደተኞች ጉዳይ መርጃ ድርጅት ይሳተፋል። እኛም የእነዚህን ስደተኞች የወደፊት ህይወት እናመቻቻለን ።ይህ ሊሆን የሚችለው ግን በሊቢያ አድርገው የአውሮጳ የባህር ጠረፎች ለመድረስ የሚሞክሩትን የኤኮኖሚ ስደተኞች እና ትክክለኛዎቹን ስደተኞች በግልጽ መለየት ስንችል ብቻ ነው።»
አውሮጳውን ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በባህር የሚመጡባቸውን ስደተኞች ላይ የሚወስዷቸውን እርምጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከሩ ነው። በቅርቡ ኢጣልያ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ስደተኞችን ከባህር ላይ እንዳይታደጉ ከልክላለች የሊቢያ የብህር ጠረፍ ጠባቂዎችም በኢጣልያ ባህር ኃይል እርዳታ  ከሊቢያ በጀልባዎች የሚነሱ ስደተኞችን ወደ ተነሱበት እየመለሱ ነው። የትናንቱ ጉባኤም ስደተኞችን ለመገደብ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው። ግን ለም አሁን? የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ  በዚህ ወቅት ላይ ጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጠው የተደረገባቸው ምክንያቶች አሉ ይላል።
ከጎርጎሮሳዊው 2014 አንስቶ ከሱዳን ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ ግጭቶችን እና ልዩ ልዩ በደሎችን ሸሽተው በሜዴትራንያን በረሃ እንዲሁም ባህር አቋርጠው ወደ አውሮጳ ለመሻገር ከሞከሩ መካከል ቁጥራቸው ከ 14 ሺህ በላይ የሚሆኑት ህይወታቸው አልፏል። ካለፉት ስምንት ወራት ወዲህ የሜዴትራንያንን ባህር አቋርጠው ኢጣልያ መድረስ የቻሉ ስደተኞች 125 ሺህ ይሆናሉ። በዚሁ ጊዜ ውስጥ በተመሳሳይ ጉዞ የሞቱ እና የደረሱበት ያልታወቀው ቁጥር 2400 እንደሚደርስ ዩ ኤን ኤች ሲአር አስታውቋል። ይህ አስደንጋጭ ሁኔታ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ ሲያሳስብ መቆየቱን የሚናገረው ዩ.ኤን.ኤች ሲ አር፣የሰባቱ ሀገራት መሪዎች በትናንቱ ጉባኤ ያሳለፉትን ውሳኔ አወድሷል።

የዩ ኤን ኤች ሲአር ቃል አቀባይ  ሴሲል ፖይ ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት መሪዎቹ የተፈራረሙበት ሰነድ የስደተኞችን ክብር ደህንነት እና መብት ከግምት ውስጥ ማስገባቱ አበረታች ነው ብለዋል። «ሰነዶቹ ስደተኞች በአካባቢያያዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በክብር ሊያዙ እንደሚገባ እና ጥበቃም እንደሚያስፈልጋቸው በግልጽ ማሳወቃቸው አበረታቶናል። ለስደተኞች መብትም እውቅና መስጠቱ እንዲሁ።» ፖይ እንዳሉት የእቅዱ ሀሳብ ሰዎች ወደ አውሮፓ እንዳይመጡ ማስቆም ሳይሆን በጣም አደገኛ የሆኑትን የሰሀራ እና የሜዲቴራንያን ባህር ጉዞዎች እንዳይጀምር ተስፋ ማስቆረጥ ነው ። እስካሁንም ድርጅታቸው ስደተኞች ተገን ሊጠይቁ የሚችሉባቸው አማራጭ ህጋዊ መንገዶች እንዲኖሩ እና የሰፈራ እድሎች እንዲሰጣቸው ሲወተውት መቆየቱን አስታውሰው እቅዱ ስደተኞች ለአደገኛ ጉዞ እንዳይጋለጡ ይረዳል ብሎ ድርጅታቸው እንደሚያስብ ተናግረዋል። የመሪዎቹን ውሳኔ በደስታ መቀበላቸውን የዩ ኤን ኤች ሲ አር ሃላፊ ፊሊፖ ግራንዲ ገልጸው የእቅዱ ዓላማ የሆነው ወደ አውሮጳ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞችን ቁጥር መቀነስ ብቻ አጠቃላዩን ችግር መፍታት እንደማይችል አስታውቀዋል። ከዚያ ይልቅ እቅዶቹ የስደተኞቹ መነሻ በሆኑ ሀገራት ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንባቸው ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ እድገቶች እውን የሚሆኑባቸውን መንገዶችም እንዲያካትት አሳስበዋል። በዚሁ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የቻዱ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ሀገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ አፍሪቃውያን መሠረታዊው ችግር እንዲጤን አሳስበው ነበር።
«ወጣት አፍሪቃውያን ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በረሀ እንዲያቋርጡ የሚገፋቸው ምንድን ነው? በሜዴትራንያን ባህር በኩል አውሮጳ የመድረስ እድላቸው አናሳ ነው። ምክንያቱ ድህነት፣ሥራ አጥነት፣እና ደካማ ትምሕርት ነው። እነዚህን ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን። እነዚህ ጉዳዮች በከፍተኛ ደረጃ ሊጤኑ ይገባል።»

ጉባኤው በወራት ውስጥ ከተካሄዱት መሰል ስብሰባዎች እጅግ ውጤታማ ተብሏል። አዳዲሶቹ እርምጃዎች ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስወጡም ሆነ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ግልጽ አይደሉም። ሆኖም በቅርቡ ወደ ቻድ እና ኒዠር መልዕክተኞች እንደሚሄዱ ተነግሯል። ከረዥም ጊዜያት አንስቶ ስደተኞች ወደ አውሮፓ የሚሻገሩባቸውን መንገዶች እያጠበቡ የመጡት የአውሮጳ መንግሥታት ስደተኞች እንዳይመጡባቸው ለሚተባበሩ የአፍሪቃ መንግሥታት የልማት እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው።ባለፈው ዓመት የአውሮጳ ህብረት ኒዠር ስደተኞችን ከሀገርዋ የማታስወጣ ከሆነ 10 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 12ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጣት ቃል ተገብቶላታል። ይህን መሰሉን እርምጃ ኦክስፋም እና አክሽን ኤይድ የተባሉት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በማስፈራራት የሚፈፀም ሲሉ ክፉኛ ተችተዋል።  አሁን የሚወሰዱት እርምጃዎች አውሮጳ ስደተኛ የሚያስፈልጋት መሆኑን ፈጽሞ የዘነጉ ናቸው ይላሉ ድርጅቶቹ ። የክፍለ ዓለሙ ህዝብ ቁጥር ወደፊት እየቀነሰ ሲሄድ ለማህበራዊ ክፍያዎች እና ለጡረታ የሚከፍል ገንዘብ ያጥራል የሚሉ ስጋቶች ያሉባት አውሮጳ ከዚህ እርምጃ ተጠቃሚ እንደማትሆን ነው ድርጅቶቹ የሚናገሩት። ኢጣልያ ብቻ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት 1.6 ሚሊዮን የውጭ ዜጎች ያስፈልጓታል።  ስዎች በሜዴትራንያን ባህር በኩል እንዲሰደዱ ታበረታታላችሁ ተብለው የተወቀሱት እነዚሁድርጅቶች የአውሮፓ ህብረት የስደተኞች ስቃይ ከማባባስ እንዲቆጠብ ጠይቀዋል።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች