1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፍቅር ጓደኛ መተዋወቂያ መተግበሪያዎች ፤ ጥቅምና ጉዳታቸው

ልደት አበበ
ዓርብ፣ የካቲት 22 2016

ሰዎች ይፋቀራሉ፣ ሲልም ትዳር ይመሰርታሉ። አንዳንዶች የትዳር አጋራቸውን የሚፈልጉት በዘመናዊው መንገድ - ኦንላይን ላይ ነው። «ጥሩና ጊዜ ቆጣቢ ነው» የሚሉ እንዳሉ ሁሉ መጥፎ ጎኑ የሚያመዝንባቸውም አሉ። የሀገር ውስጥም ይሁኑ የውጭ ሀገር የፍቅረኛ ማገናኛ መተግበሪያዎች መሠረታዊ የሆኑ መረጃዎችን ይጠይቃሉ። ይሁንና ሁሉም ሰው ሀቀኛ አይደለም።

https://p.dw.com/p/4d3R2
 Tinder የተባለው መተግበሪያ
«ጥሩ እና ጊዜ ቆጣቢ ነው» የሚሉ እንዳሉ ሁሉ መጥፎ ጎኑ የሚያመዝንባቸውም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።ምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/IMAGO

የፍቅር ጓደኛ መተዋወቂያ መተግበሪያዎች

ዮናስ ዛሬ የትዳር አጋሩ የሆነችው ፍቅረኛውን የተዋወቃት አንድ ሀገር በቀል የወንድ እና የሴተ-ላጤዎች ማገናኛ መተግበሪያ ላይ ነው። እዛም ላይ በነበረው ተሞክሮ በጣም ደስተኛ ነው።  ከ2015 አንስቶ እዛ ላይ ከተዋወቃት ፍቅረኛው ጋር ትዳር መስርተው አብረው እየኖሩ ይገኛሉ። ሁለቱ ግን እንዴት እንደተዋወቁ ቤተቦቻቸው አያውቁም።  « ስለዚህ በግልፅ ለማውራት ለእኛ ማህበረሰብ ከባድ ነው። በተለይ በእድሜ ተለቅ ላሉት ይከብዳል። ጓደኞቻችንም አያውቁም።» ይላል። በዚህም ምክንያት በነፃነት እንዲያወራን ዮናስ ትክክለኛ ስሙ አይደለም። በኦንላይን ሰው መተዋወቅ «በተለይ ለሴቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል» የሚለው ይሔው ወጣት የመረጣትን ሴት እስኪያገኝ አንድ ዓመት ያህል ፈጅቶበታል።  እስከዛ ድረስ ከተለያዩ ሴቶች ጋር ይፃፃፍ እንደነበር አልሸሸገም።  በዚህም ምክንያት መተግበሪያው ላይ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እንዳሉ እንዲገነዘብ ረድቶታል።   «  ትዳር ፈልጎ የሚመጣ ወይም የምትመጣ ሰዎች ቢኖሩም በዛው ልክ ደግሞ ብዙ አይነት ሰርጎ ገብ አለ። ስለዚህ ጥንቃቄ በደንብ ይደልጋል።

ፍቅር ከአርባ ምንጭ ኩዌት ድረስ

አበራ ብለን የምንጠራው ወጣትም  ትክክለኛ ስሙን በራዲዮ ባንገልፅ ይመርጣል። የዛሬ የትዳር አጋሩን የተዋወቃት ኦንላይን ላይ ነው። ግን ለዚህ ብለው የተዘጋጁ መተግባራዎች ላይ ሳይሆን ፌስ ቡክ ነበር። « ሁለታችንም የራሳችን የሆነ  ፎቶ እንኳን ገፃችን ላይ አልነበረንም» የሚለው ወጣት ፍቅራቸው እንዴት ከዜሮ እንጀመረ ገልፆልናል። « በአጋጣሚ ፌስ ቡክ እጠቀም ነበር። ስሟ የሴት ስለነበር እንደ ወንድም እና ሴት እናወራ ነበር። የሆነ ጊዜ ፎቶ ተቀያየርን፤ ከዛ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ  በቪዲዮ እየተደዋወልን እናወራ ነበር።» ምንም እንኳን ሁለቱም በወቅቱ በአካል መገናኘት ቢፈልጉም  እድሉ ግን አልነበራቸውም። ይህም አበራ የሚኖረው አርባ ምንጭ ከተማ እሷ ደግሞ የምትኖረው ከሀገር ውጪ ኩዌት ስለነበረ ነው።  « ሁሉንም በግልፅ ተነጋገርን፣ ቃል ተግባባን፣ ተማመንን ከዛ በኋላ ወደ ትክክለኛ ፍቅር ገባን» ይላል። ሁለቱ ፍቅረኛሞች ቢግባቡም ቤተሰብ እና ጓደኞቹን ማሳመኑ ቀላል አልነበረም። 30 ዓመት የሆነው አበራን «መቼ ነው የምታገባው» እያሉ ይወተውቱት የነበሩ ወላጆቹን ፍቅረኛ እንዳለው የነገራቸው እሷን ገና በአካል ሳያገኛት ፣ እሱ እንደሚለው «ከተዋወቃት  ከስድስት ወር በኋላ ነበር።»  ከዛም ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ከ 9 ወራት በኋላ ተገናኙ። ምንም እንኳን ቤተሰቡ እና ጓደኞቹ  ስጋት ቢኖራቸውም የትውውቁ መጨረሻ ስኬታማ ሆኗል። « ከተጋባን አንድ አመታችን ነው። እሷም አሁን እርጉዝ ናት። በፍቅር አብረን ተሳስረን፣ ተቻችለን አንድ ላይ ነው ያለነው።

«100 ሺህ ብር ጠየቀችኝ»

ወጣት ሥዩም ግን እንደ አበራ እና ዮናስ አልቀናውም።  ሀገር በቀል የወንድ እና የሴተ ላጤዎች ማገናኛ መተግበሪያ ላይ የገጠመውን እንዲህ ሲል ገልፆልናል። « ለአንድ ዓመት ያህል በሰላም ከቆየን በኋላ መጨረሻ ላይ ተለያየን» ሥዩም ለመለያየታቸውም የሚጠረጥረው አንድ ምክንያት አለ። የባንክ ሠራተኛ መሆኑን አውቃ የቀረበችው ሴት የገንዘብ ጥያቄ ነው። « 100 ሺህ ብር ስጠኝ አለችኝ። » የሚለው ሥዩም ልጅቷም እንደማይሰጣት ስታውቅ መጥፋት እንደጀመረች እና በግልፅ እንኳን ሳይወያዩ እንደተሰወረች ይናገራል።

የተለያዩ የመተዋወቂያ መተግበሪያ ምልዕክቶች
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መተግበሪያዎን በመጠቀም ሰዎች ይተዋወቃሉምስል Sina Schuldt/dpa/picture alliance

የሀገር ውስጥም ይሁኑ የውጭ ሀገር የፍቅረኛ ማገናኛ መተግበሪያዎች እንደ  ፍላጎት፣ ሐይማኖት ፣ እድሜ፣  ፃታ እና ሌሎች መሠረታዊ የሆኑ መረጃዎችን ይጠይቃሉ። ይሁንና ሁሉም ሰው ሀቀኛ መረጃዎችን ይሰጣል ማለት እንዳልሆነ በፍለጋው ስኬታማ የሆነው ዮናስም ያውቃል። ስለሆነም ለሌሎች ወጣቶች ቢተገብሩ የሚለው ምክር አለው። « ትልቁ ነገር በአካል ከመገናኘት በፊት በስልክ ማውራት፤ ከዛ በቪዲዮ ማውራት» ያስፈልጋል።  ይላል። ስለ እዛ ሰው ጊዜ ሰጥቶ መረጃዎችን ማጣራት እንዳለባቸውም ይመክራል።«በአካል ሲገናኙም ካፌ ላይ ቢሆን ይመረጣል » ይላል። አበራ ደግሞ መተግበሪያዎቹን ለሚጠቀሙ ወጣቶች ግልፅ መሆንን ይመክራል። እንደዛ ከሆነ እሱ እንደሚለው ጥቅሙ ያመዝናል። « በተፈጥሮ ደፍረው ፊት ለፊት ማውራት የማይችሉ ወንድም ሴቶች አሉ ፤ እነሱም እንደቀልድ እንደ ጨዋታ ይግባባሉ። ከዛም ወደ ፍቅር ይገባል። በአካል ያገኙትን ፍቅር በኦንላይን ያገኛሉ። አንዳንድ የታደሉ ያገባሉ» ይላል። የአፋሩ ወጣት ሥዩም ግን ዳግሞ ተመልሶ እዛ መተግበሪያ ላይ ሴት ለመተዋወቅ  አልሞከረም። ዛሬ ላይ «ከባህላችንም ውጪ ነው» እንዲል አድርጎታል። « የአጭበርባሪዎች መንደር ነው ብዬ ትቼዋለሁ። ሲጀመር ከባህላችን ውጪ መኖር ጥሩ አይደለም። ፈጣሪ ይመስገን መጨረሻ ላይ ወደ ባህሌ ተመልሼ ቤተሰቤ የሚያውቃት ጓደኛ ያዝኩኝ። በእጮኝነት ነው ያለሁት። » በማለት ደስተኛ እንደሆነ ገልፆልናል። 

«ከንፋስ የፈጠነ ከውኃ የቀጠነ ፍቅር ይዞኛል»

ሌሎች ተሞክሯቸውን በፁሁፍ ያካፈሉንም ወጣቶች አሉ። Aziz ከሀረር  «ብዙ ጊዜ እነዚህ የመተዋወቂያ መተግበሪያዎች (dating app) ትክክለኛ ፆታቸዉን በደበቁ ሰዎችና ራሳቸዉ ግልፅ ባላደረጉ ሰዎች የተሞላ ነዉ።  ለምሳሌ የተለያዩ dating app ለመጠቀም ሞክሬያለሁ። የፍቅር አለያም የትዳር አጋር ለማግኘት  ምን ያክል እዉነታ አላቸዉ ብዬ በምጠቀማቸዉ ጊዜ መተግበሪያው ላይ የማገኛቸዉ ሰዎች  ፍቅር ወይም ትዳር ሳይሆን ፍላጎታቸዉ  ጥቅምን ያማከለ ነዉ  ለምሳሌ ገና መግባባት እየጀመርኩ እያለ የሚያቀርቡልኝ ጥያቄ ስለ በይነመረብ ንግድ (digital business) ነዉ ? ዕዉቀቱ እንደሌለኝ በምነግራቸዉ ጊዜ የተለያዩ ድራለማቀፍ ማገናኛዎች (link) እየላኩ የበይነመረብ ንግድ ጀምር በተለይ ስለ bit coin ሊያስረዱኝና 1 bit coin ብገዛቸዉ  ትርፋማ እንደምሆን ከማግባባት ዉጭ የተለየ ግንኙነት ገጥሞኝ አያዉቅም! »

Symbolbild Dating App | Lovoo Parship Tinder Lovescout24
እንደ ሎቮ ፓርሺፕ እና ቲንደር ያሉ መተግበሪያዎች ታዋቂዎቹ ናቸው።ምስል Andreas Franke/picture alliance

Endris  «እኔ እየተጠቀምኩ ነበረ በጣም ጥሩ ነው ።ጥሩ ጓደኛሞችም አግኝቼበታለሁ። ስጠቀምም የነበረው tinderን ነበረ በጣም ብዙ መልእክቶች ይላኩልኝ ነበረ ። ሁሉም ሰው ሙሉ ቀን online ስለሚሆን ነው መሰለኝ ብዙ መልዕክቶች ይደርሰኝ ነበረ እና እዛ ፍቅረኛ ብቻ አይደለም የሚፈለገው ጥሩ ጓደኞችም ያስተዋውቃል ግን ትኝሽ ስራ ያስፈታል። ከቲክቶክ የበለጠ እሱ ነበረ የሚያታልለኝ አሁን አልጠቀመውም።»

በቡሄ ያበደ ሆ ሲል ይኖራል «ስለ መተዋወቂያው መተግበሪያ ትንሽ ልበላቹ ። እኔና ባለቤቴ በእንዲህ አይነት መንገድ ነው የተገናኘነው። ይሄንን መተግበሪያ የጠቆመችኝ ካናዳ ያለች አክስቴ ነበረች። ከዛ መተግበሪያን አውርጄ እንደ አጋጣሚ አንድ ቸኮሌት የሆነች ያሁኗን ባለቤቴን አገኘኋት እሷ እዚው አዲስ አበባ ነበረች እኔ ደሞ አየር ላንድ ። እና ውሃ አጣጬን አግንቼ መፃፃፍ ጀመርን ከዛ ተግባባን ጊዜ ሳናባክን ሽማግሌ ላኩኝ ወደ ትዳር አለም ተቀላቀልን ይሀው አሁን የሁለት ልጅ አባት ሆኛለሁ።»