የፍራንክ ተገልጋይ ሃገራት ችግር | ኤኮኖሚ | DW | 17.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የፍራንክ ተገልጋይ ሃገራት ችግር

የአፍሪቃ ሃገራት ከቀድሞይቱ ቅን ገዥ ከፈረንሣይ በፊናንስ እንደተሳሰሩ መቀጠል ለልማት እንቅፋት ሆኗል።

አፍሪቃ ውስጥ የፈረንሣይን ቅኝ ግዛት ዘመን ቅርስ ያህል ስር ሰዶ የቆየ የባዕድ ተጽዕኖ አይገኝም። ፈረንሣይ በምዕራብና ማዕከላዊው አፍሪቃ ከነጻነት በኋላም በመጀመሪያ በፍራንክና ከዚያም በኤውሮ አማካይነት የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿን የፊናንስ ስርዓት ትቆጣጠራለች። 14 የአካባቢው ሃገራት እንግዲህ በፈረንሣይ የምንዛሪ ፖሊሲ ላይ ጥገኞች ናቸው። አንድ ኤውሮ በቀድሞዎቹ ቅን ግዛቶች 656 ፍራንክ እንዲቀየር ቋሚ የምንዛሪ መስፈርትም ተቀምጧል።

ይህ CFA-Franc በመባል የሚታወቀው ምንዛሪ ታዲያ ተቺዎች እንደሚናገሩት ለቀድሞዎቹ የፈረንሣይ ቅኝ ግዛቶች ልማት መሰናክል መሆኑ አልቀረም። በመሆኑም ለምዕራብና ማዕከላዊው አፍሪቃ ሃገራት ከእስካሁኑ የፊናንስ ስርዓት በመላቀቅ የራስ ምንዛሪን መፍጠሩ ግድ እየሆነ ነው የመጣው። ይህ እንደመሆኑም መጠን ከሣምንት በፊት የፍራንክ ተገልጋይ የሆኑት ሃገራት የፊናንስ ሚኒስትሮች ዳካር ላይ ሲሰበሰቡ አንድ ዕርምጃ ተጠብቆ ነበር። በነገራችን ላይ CFA የሚለው አሕጽሮተ ቃል ሲተረጎም የፈረንሣይ የአፍሪቃ ቅኝ ግዛቶች ማለት ነው።

ወደ ፊናንስ ሚኒስትሮቹ ስብሰባ መለስ እንበልና ከኤውሮ ጥገኝነት መላቀቁ ወይም አዲስ የምዕራብ አፍሪቃ ምንዛሪ መፍጠሩ ዓቢይ የውይይት ርዕስ ይሆናል ተብሎ ነበር የታሰበው። ግን አልሆነም። ውይይቱ በአንጻሩ በአካባቢው ሃገራት የኤኮኖሚ ትስስር ላይ ያተኮረ ሆኖ ተገኝቷል። በነገራችን ላይ በ 14ቱ የማዕከላዊና ምዕራባዊው አፍሪቃ ሃገራት በሁለት ማዕከላዊ ባንኮች አማካይነት ሁለት ዓይነት የፍራንክ ምንዛሪዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ።

Geldumtausch in Westafrika

ስድሥት የማዕከላዊው አፍሪቃና ስምንት የምዕራባዊው አፍሪቃ ሃገራት የነዚህ ምንዛሪዎች ተገልጋዮች ናቸው። የምዕራባዊው አፍሪቃ የፍራንክ የምንዛሪ አካባቢ ቤኒንን፣ ቡርኪና ፋሶን፣ አይቮሪ ኮስትን፣ ጊኒ ቢሣውን፣ ማሊን፣ ኒጀርን፣ ሤኔጋልና ቶጎን ይጠቀልላል። የማዕከላዊው አፍሪቃ ስብስብ ደግሞ ጋቡንን፣ ሬፑብሊክ ኮንጎን፣ ቻድንና ማዕከላዊት አፍሪቃ ሬፑብሊክን ጭምር ያቀፈ መሆኑ ነው።

የሁለቱ አካባቢዎች የወረቀት ገንዘብና ሣንቲሞች ደግሞ የተለያዩ ሲሆኑ የሚያገለግሉትም በየራሳቸው አካባቢ ብቻ ነው። እንበል የማዕከላዊው አፍሪቃ ገንዘብ በምዕራቡ አካባቢ አይሰራም። በተገላቢጦሽም እንዲሁ! ይህ ዛሬ ጊዜው ያለፈበትና በአካባቢው የኤኮኖሚ ትብብር ረገድም እንቅፋት ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ለዚህም ነው ለውጥ አጣዳፊ ሆኖ መገኘቱ!

መለስ ብሎ ለማስታወስ ፈረንሣይ ለተወሰኑ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ ምንዛሪውን የፈጠረችው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በ 1945 ዓ-ም ነበር። ታዲያ ምንም እንኳ ማዕከላዊ ባንኮቹ በካሜሩንና በሤኔጋል ተቀማጭ ቢሆኑም አሁንም ከፈረንሣይ ተጽዕኖ የተላቀቁ አይደሉም። የጀርመን የኤኮኖሚ ዘርፍ የአፍሪቃ ማሕበር አፈ-ቀላጤ ሚሻኤል ሞነርያህን እንደሚሉት እነዚህ ሃገራት ዛሬም በፈረንሣይ የፊናንስ ፖሊሲ ላይ በጣሙን ጥገኞች ናቸው።

« ፈረንሣይ እርግጥ እንደ ለጋሽ አገር ተጽዕኖ ማድረግ ትችላለች። እና እንደፈለግነው ካልሆናችሁ ወደፊት ዕርዳታችንን አታገኙም ለማለት ምንም የሚያዳግታት ነገር የለም»

ይህን ግፊት ደግሞ አፍሪቃውያኑ ሃገራት ሊቋቋሙት አይችሉም። የአውሮፓ የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ኦኢሲዲ እንደሚያመለክተው ፈረንሣይ በዓለም ላይ መንግሥታዊ የልማት ዕርዳታ በማቅረብ ረገድ ሶሥተኛዋ ታላቅ አገር ናት። ከዕርዳታዋ ከግማሽ የሚበልጠው፤ ማለትም 53 በመቶው የሚፈሰውም ወደ አፍሪቃ ሃገራት ነው። ለዚህም ነው የፍራንክ ተገልጋይ ሃገራት የፊናንስ ሁኔታ በፈረንሣይ ውሣኔ ላይ ጥገኛ የሚሆነው።

እንግዲህ የምንዛሪዎቹን ዕጣ በተመለከተ የፈረንሣይ ሚና በጣሙን ከፍተኛ ነው። ይህም በየጊዜው በሚወሰዱ ዕርምጃዎች በጉልህ ታይቷል። ለምሳሌ ያህል በጎርጎሮሳውያኑ 1994 ዓ-ም የፍራንክ ዋጋ በፈረንሣይ ግፊት ሲያቆለቁል አቅሙ በግማሽ እንዲቀንስ መደረጉ ይታወሳል። ፈረንሣይ ይህን ያደረገችው ዕርምጃው ለምንዛሪው ተገልጋይ ሃገራት ልማት ይበጃል የሚል ምክንያት በመስጠት ነበር።

ለማንኛውም ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ኤውሮ ስራ ላይ ሲውል CFA-Franc ም ከርሱው እንዲተሳሰር ይደረጋል። ይህም በዳካሩ ባምቤይ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ-ሐብት ተመራማሪ የሆኑት ሱሌይማን እንዳኜ እንደሚሉት ብርቱ ተጽዕኖ ማስከተሉ የተሰወረ ነገር አይደለም።

«የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ በኤውሮ መስፈን የፈረንሣይን መንግሥት የፊናንስ ተግባርም ተረክቧል። እናም የፍራንክ ተገልጋይ የሆኑት አፍሪቃውያን ሃገራት በውጭ ንግድ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪም ሆነ የማዕካዊ ባንኮቻቸውን ወርቅ የሚያስተዳድረውም እርሱው ነው»

ከዚህ ጥገኝነት የተነሣ የ CFA ሃገራት እንዴት ከኤውሮ ተጽዕኖ ሊላቀቁ እንደሚችሉ በየጊዜው ሃሣብ መሰንዘሩ አልቀረም። ለምሳሌ ያህል የምዕራብ አፍሪቃው የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ የኤኮዋስ ሃገራት ከአራት ዓመታት በፊት በ 2009 ኤኮ የተሰኘ የራሳቸውን ምንዛሪ ለማስፈን መስማማታቸው ያታወሳል። ዓላማውም ኤኮን በመላው የምዕራባዊው አፍሪቃ የፍራንክ ተገልጋይ ሃገራትና በሰባት የኤኮዋስ ዓባል መንግሥታት ውስጥ ስራ ላይ ማዋል ነበር።

ይህ እርግጥ ችግርም አላጣውም። ዕርምጃው ለምሳሌ የማዕከላዊ አፍሪቃን የፍራንክ ተገልጋይ ሃገራት የሚያገል ነው። ለነዚህ ሃገራት የሚቀረው ምርጫ ምናልባትም በፍራንክ መቀጠል፤ አለበለዚያ ደግሞ የራስን ምንዛሪ መፍጠር በሆነ ነበር። ለማንኛውም የኤኮዋስ ውሣኔ ከዚያን ወዲህ ብዙም ሲነሣ አልተሰማም። ጉዳዩ እንደማያዋጣ ታውቆ ተድበስብሶ እንዲቀር የተደረገ ነው የሚመስለው። የደቡብ አፍሪቃውን ዊትወተርራንድ ዩኑቨርሲቲ ባልደረባ ኮአኩ ኮፊን የመሳሰሉ ታዛቢዎች እንደሚሉት ብዙ ሲወራ እንጂ ሃሣቡን ዕውን ለማድረግ አንዳች የረባ ነገር ሲደረግ አልታየም።

ስለዚህም ኤኮ ሕያው በመሆኑ ተሥፋቸው የመነመነ ነው። እርግጥ የጊኒው የኤኮኖሚ ባለሙያና ምንዛሪውን ገቢር በማድረጉ ጉዳይ የተቋቋመው የአዋቂዎች ኮሚቴ የውጭ አማካሪ አሱማ ካማራ ለየት ያለ አመለካከት አላቸው። ካማራ ፕሮዤው ወደፊት እየተራመደ ነው፤ ከአሁኑ በኤኮዋስ ሃገራት የሚሰራበትን የጋራ የውጭ ቀረጥ ታሪፍን በመሳሰሉ ጉዳዮች ብዙ ዕርምጃ ተደርጓል ባይ ናቸው።

« ሌላው ቀጣይ ዕርምጃ ኤኮዋስ አስፈላጊውን የኤኮኖሚ መዋቅር ማዳበሩ ነው። በዚሁ የዕርምጃውን ተጽዕኖ ቀድሞ ለማየት ሲቻል ይህም በውሣኔ አደራረግ ሂደት ላይ የሚጠቅም ነገር ነው። እናም ሰዎች ለምን ፕሮዤውን አምኖ መቀበል እንደሚከብዳቸው በፍጹም አይገባኝም። ምንም እንኳ ብዙ ችግሮች ከአሁኑ መወገዳቸው የሚታወቅ ቢሆንም»

ለ CFA-ፍራንክ ተገልጋይ ሃገራት ምናልባትም ይህንኑ ምንዛሪ እንደያዙ በመቀጠል ከኤውሮ ትስስር መላቀቃቸው አንድ ተጨማሪ መፍትሄ ሊሆን ይችላል። ግን ይህ አማራጭ ፍራንክ ተገልጋዩ ሃገራት ብቻ ሊጠቀሙበት የሚችሉ በመሆኑ አልተፈለገም። በአንጻሩ ሌሎቹንም ሃገራት ጭምር የሚጠቅምና ማንንም የማያገል መፍትሄ ለማግኘት ነው የሚጣረው። አሱማ ካማራ እንደሚሉት በዚህ ላይ ደግሞ ብዙ ውይይት በመካሄድ ላይ ነው። እርግጥ በቅርብ ጊዜ ለውጥ ይገኛል ተብሎ አይጠበቅም።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic