የፍልስጤም ጥያቄ፦ የእስራኤልና የአሜሪካ ተቃዉሞ | ዓለም | DW | 26.09.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የፍልስጤም ጥያቄ፦ የእስራኤልና የአሜሪካ ተቃዉሞ

የአባስ መስተዳድር አላማ-ግብ ምንም ሆነ-ምን የዓለም አቀፉን ድርጅት ሕግ ደንብ የጠበቀነቱ ሊያነጋግር አይገባም።የፍልስጤሞች ጥያቄ ኦባማ ካይሮ ድረስ ሔደዉ ከተናገሩት ጋር መጣጣሙን ለማወቅም አስተንታኝ አያስፈልገዉም።ጥያቄዉ ከራሳቸዉ ከፍልስጤሞች ሲመጣ ፕሬዝዳት ኦባማ በሁለት ዓመት እድሜ ዘጠና ዲግሪ ዞረዉ ጥያቄዉን የመቃወማቸዉ ።

default

26 09 11

ፍልስጤሞች እንደገና ጠየቁ።አረቦች ዳግም ደገፏቸዉ።እስራኤል አሜሪካኖች ልክ እንደ ቅድመ ሥልሳ ሰወስት ዓመቱ፥ ልክ እንደ ሥልሳ ሰወስት ዘመን ሒደቱ የፍልስጤሞችን የነፃነት ጥያቄ ተቃወሙ።የተቀሩት መንግሥታት ሁኔታም ሐቅን፥ ከጥቅም፥ የራስ አቋምን ከዛቻ-ፍራቻ አላተመ።የዓለም ማሕበር ሕግ-ደንብም አንደ አድራጊ ፈጣሪዎቹ እሳቤ እንደገና ተተረጎመ።የዳግም ጥያቄ-ድጋፍ ተቃዉሞዉ መነሻ የዓለም ሕግ አተረጓጓም መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

ቅዳሜ-ሕዳር 29-1947 ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።ብሪታንያ ለሰላሳ አመታት ያሕል የገዛችዉ ፍልስጤም ለሁለት ተገምሶ በአንደኛዉ ገሚስ አይሁዶች መንግሥት እንዲመሠርቱ የሚጠይቀዉ የዉሳኔ ሐሳብ የአዲሱን የዓለም ማሕበር አባላት ማወዛገብ ከመጀመረ ሰነባበተ።ግዛቱን ለሁለት መከፈሉን የሚቃወሙት አረቦች እና የራሳቸዉን ነፃ መንግሥት ለመመሥረት የሚፈልጉት አይሁዶች የቅኝ ገዢዋን የብሪታንያን ድጋፍ ለማግኘት መሯሯጥ፥ መሻኮት፥ መገዳደል፥ ከጀመሩ ደግሞ ከርመዋል።

ሁለቱ ወገኖች ወደለየለት ጦርነት ለመግባት ሁለት ነገር ይጠብቃሉ።የዚያን ቀኑ ዉሳኔ-አንድ፥ የብሪታንያ ጦር ከዚያ ምድር ለቅቆ መዉጣቱን-ሁለት።ኒዮርክ ከቀኑ አስር ሰዓት።በዋሽንግተኖች ጥረት-ግፊት፥በለንደኖች ድጋፍ፥ በሞስኮዎች ፍቃድ ከሁለት ዓመት በፊት የተመሠረተዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በእስካሁን ታሪኩ ያልደገመዉን ልዩ ዉሳኔ ለማፀደቅ የሰዓታት እድሜ ነዉ የቀረዉ።

የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ሰወስት ቀን የተከራከረ፥ የተወዛገበበትን የዉሳኔ ሐሳብ በድምፅ ከማፅደቁ በፊት የመጨረሻዎቹ ተናጋሪዎች መልዕክት እያደመጠ ነዉ።የፍልስጤም አረቦቹ ተወካይ ጀማል ሁሴይን በርግጥ አዲስ አገር አላሉም።የአረብ መንግሥታት ተወካዮች፥ እራሳቸዉም ባለፉት ጥቂት ቀናት ያሉትን እንደገና ደገሙት።«ይሕ ጠቅላላ ጉባኤ የፍልስጤም ግዛት ለሁለት እንዲከፈል በድምፅ ከወሰነ» ዛቱ ሰዉዬዉ።ብሪታንያዎች አካባቢዉን እንደለቀቁ የፍልስጤም አረቦች በአረብ መንግሥታት ድጋፍ ዉሳኔዉን በመቃወም ዉጊያ ይገጥማሉ።»

ጀማል ነብይ አልነበሩም።ከሃያ ሰባት አመት በፊት ያሉት ግን አልቀረም።

NO FLASH Benjamin Netanjahu UN Vollversammlung 2011

የ1948ቱ የአረብ-እስራኤሎች ጦርነት፥የግብፅ እና የእስራኤል፥ የብሪታንያና የፈረንይ ወይም የሲዊስ ካናል ጦርነት፥ የ1967ቱ ወይም የስድስቱ ቀን ጦርነት፥ የዮም ኪፑር ወይም የ1973ቱ ወይም አራተኛዉ የአረብ-እስራኤሎች ጦርነት፥ የእስራኤል ጦር የዮርዳኖስ ወረራ፥ የእስራኤል ጦር የሊባኖስ ወረራ፥ የፍልስጤሞች ሽምቅ ዉጊያ፥ የፍልስጤሞች የሽብር--- ጥቃት ብቻ ሰላም የሚነገር-የሚሰበክበት ግን ሠላም የማያዉቀዉ ያ ምድር ያፍታዋንም ሠላም እንደተሰናበታት-ዘመን ሔዶ ሌላ ዘመን ተተካ።

ለእስከ ያኔዉ ያሰባት ዓመት።ከሃያ-ሰባት ዓመት በፊት ሐምሳ-ስድስት የነበረዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሐገራት ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።ድርጅቱ የዚያን ዕለት ለተሰየመዉ ጉባኤዉ ከ1947 ወዲሕ የማያዉቃቸዉን ሕዝቦች ተወካይ ጋብዟል።ያሲር አረፋት።
ሕዳር አስራ-ሰወስት 1974።

«ወደናንተ የመጣሁት፥ ክቡር ፕሬዝዳንት፥ (ባንድ እጄ) የወይራ ዝንጣፊ ፥ በሌላዉ የነየፃነት ተዋጊ ጠመንጃ ይዤ ነዉ።የወይራ ዝንጣፊዉ ከእጄ እንዲወድቅ አታድርጉ።የወይራ ዝንጣፊዉ ከእጄ እንዲወድቅ አታድርጉ።»

የያኔዉ የፍልስጤም ነፃ አዉጪ ድርጅት ሊቀመንበር ያሉትን ሲሉ ያኔ የነበሩ እንዳሉት የጉባኤዉ አዳራሽ ከአፍ-እስከ ገደፉ ጢም ብሎ ነበር።ሰወስት ወንበሮች ግን ባዶ ነበሩ።«እስራኤል» ይላል-ከወንበሩቹ ፊት ለፊት ባለዉ ጠረጼዛ ላይ የተፃፈዉ ስም።

ከሃያ-ሰባት አመት በፊት ግን አይሁዶችም ፍልስጤሞችም እኩል ሐገር አልባ ነበሩ።የሁለቱም ተወካዮች እኩል እንግዶች፥ እኩል ተናጋሪዎች ነበሩ።የፍልስጤም አረቦቹ ተወካይ ጀማል ሁሴይን ዛቻ የተሞላበት ንግግር እንዳበቃ ተከታዩ ተናጋሪ ቀጠሉ።ሞሼ ሻሬት ናቸዉ-የአሁዶች ተወካይ።ክቡር ፕሬዝዳት አሉ ወደ ጠቅላላዉ ጉባኤ ፕሬዝዳት ወደ ብራዚሊያዊዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እያዩ።

«የአይሁድ ሕዝብ አብላጫ ቁጥር ባላቸዉ አረቦች እንዲጨቆን ለሚደረገዉ ሙከራ እጅ አይሰጥም።» በርግጥም አይሁድ እጅ አልሰጠም።ያሲር አረፋት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት የ1973 ቱ ወይ አራተኛዉ የአረብ እስራኤሎች ጦርነት ባበቃ በመንፈቁ ነበር።

በዚያ ጦርነት እስራኤል አሸነፈ እንጂ አልተሸነፈም።ወደፊትም እንደምናሸንፍ እርግጠኞች ነን አሉ የያኔዋ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ጎልዳ ሚር።ግን ከጦርነት ድል ደስታ የለም።

«ሌላ ተጨማሪ ዉጊያ ቢደረግ እንደምናሸንፍ ፍፁም እርግጠኞች ነን።ይሁንና መላዉ አለም የተማረዉን እኛም ተምረናል።ጦርነቱን ብታሸንፍ እንኳን የምትከፍለዉ ዋጋ አለ።ልጆቻዉን ያጡ እናቶችን፥ወላጆቻቸዉን ያጡ ሕፃናትን፥ባሎቻቸዉን ያጡ ወጣት ሚስቶችን ሳይ ጦርነትን ብናሸንፍ እንኳይ የሚያስደስት ነገር እንዳልሆነ እገነዘባለሁ።»

በወዲያኛዉም ወገንም መቶ ሺሕዎች አልቀዋል። ሚሊዮኖች ተሰደዋል።ሚሊዮኖች-አባት፥ ባል አልባ ቀርተዋል።የእልቂት-ፍጅቱን አዙሪት ለማስቆም አብነቱ በርግጥ ሠላም ነበር።ሠላም ግን የለም።


ዩናይትድ ስቴትስ የፍልስጤምን ግዛት ለሁለት ገምሶ በአንደኛዉ ግማድ አይሁዶች ነፃ መንግሥት እንዲመሥረቱ የሚጠይቀዉን የዉሳኔ ሐሳብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያፀድቀዉ ያልፈነቀለችዉ ድንጋይ አልነበረም።ጉባኤዉ ሊደረግ ዕለታት ሲቀሩት ፕሬዝዳት ሐሪ ኤስ ትሩማን ራሳቸዉ በጉባኤዉ ላይ የሚካፈለዉን የሐገራቸዉን የመልዕክተኞች ጓድ መሪ ሔርሼል ጆንሰንን ቢሯቸዉ ድረስ አስጠርተዉ «ረቂቁ ካልፀደቀ አሳር ይገጥመናል» በማለት አስጠንቅቀዋቸዉ ነበር።

የትሩማን መስተዳድር ሌሎች አባል መንግሥታትን በማግባባት፥በብድር በመደለል፥ በማስፈራራት፥ በማባበልም አብዛኛዉን ዓለም ከጎኑ አሠለፈ።ጠቅላላዉ ጉባኤ ረቂቁን ዉሳኔ በሰላሳ ሰወስት የድጋፍ በአስራ-ሰወስት የተቃዉሞ፥ በአስር ድምፅ-ተአቅቦ አፀደቀ።አረቦች-ሰማይ የተደመረመሰባቸዉ ያክል ደነገጡ።አዘኑ።ለእስራኤል ባንፃሩ የመንግሥትነት መሠረት ተጣለ።አይሁዶች ፈነደቁ።

«በዚያ ምሽት» አሉ የአይዶችን የነፃነት ትግል በበላይነት የመሩትና የመጀመሪያዉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ቤን ጉርዮን «መጨፈር አልቻልኩም።መዝፈን አልቻልኩም።የሚጨፍሩ የሚዘፍኑትን አይነበር።እና ሁሉም ወደ ጦር ግንባር የሚዘምቱ ይመስላሉ እያልኩ አስብ ነበር።»

ባሁኑ ዘመን የቤን ጉርዮንን መንበር የያዙት ጠቅላይ ሚንስትር ቤን ያሚን ኔታንያሁ፥ ያኔ ድፍን አይሁድን ያስፈነደቀዉን፥ እስራኤል የተመሠረተችበትን ረቂቅ-ዉሳኔ ያፀደቀዉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤን በቀደም ወቀሱት።

«ከዓመት-አመት እስራኤል እየተነጠለች ፍትሕ በጎደለዉ ብይን የምትወገዘዉ እዚሕ ነዉ።የተቀሩት ሐገራት በሙሉ ከደረሰባቸዉ ዉግዘት ይልቅ እስራኤል በተደጋጋሚ ተወግዛለች።ከሃያ-ሰባቱ ጠቅላላ ጉባኤ ሃያ-አንዱ በመካከለኛዉ ምሥራቅ የምትገኘዉን ብቸኛይቱን ዲሞክራሲያዊት ሐገር የሚያወግዝ ዉሳኔ አሳልፏል።ይሕ የተባበሩት መንግሥታት አሳዛኝ ገፅታ ነዉ።ይሕ ግራ-አጋቢ ድራማ ነዉ። ድርጅቱ እስራኤልን እንደ መጥፎ ገፀ-ባሕሪ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ለእዉነተኛ መጥፎ ገፀ-ባሕሪያት የመሪ ተዋኝነት ሚና ይሰጣቸዋል።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እስራኤልን የሚጎዳ አያሌ ዉሳኔ አሳልፎ ይሆናል።ገቢራዊ የሆነ ግን የለም።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት እስራኤል የማትፈቅደዉ ብዙ ረቂቅ ዉሳኔዎች ቀርበዉለታል።የዩናይትድ ስቴትስን ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን አልፎ የፀደቀ የዉሳኔ ግን የለም።

ከትሩማን እስከ ኦባማ የተፈራረቁት የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች ለእስራኤል የማይነጥፍ ዙሪያ መለስ ድጋፍ የመስጠታቸዉን ያክል እስራኤልን ከአረቦች በተለይም ከፍልጤሞች ጋር ለማስታረቅ እንደሚጥሩ ያልተናገሩ፥ ያላስታወቁ ያልዛቱበት ዘመን የለም።ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ በ 2009 ካይሮ ድረስ ተጉዘዉ የተናገሩትም ከትሩማን እስከ ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ የነበሩ ቀዳሚዎቻቸዉ ያሉትን በዘመኑ ቋንቋ ከመድገም ያለፈ አልነበረም።

NO FLASH Obama UN


«በመፈናቀል ሕመም ከሥልሳ አመታት በላይ ተሰቃይተዋል።ብዙዎቹ ምዕራባዊ ዳርቻ፥ ጋዛ እና በጎረቤት ሐገሮች በየስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ሆነዉ፥ በሕይወታቸዉ ሙሉ ማየት ያልቻሉት ሠላምና ፀጥታ ይሰፍናል ብለዉ ለብዙ አመታት ጠብቀዋል።በሐይል የመያዝን ዉርደት በየዕለቱ ይቀምሱታል።ሥለዚሕ የፍልስጤም ሕዝብ የሚኖርበት ሊታገሱት ሊታገሱት የሚገባ እንዳልሆነ ግልፅ ነዉ።ፍልስጤሞች ለክብራቸዉ፥ ለመፃኤ እድላቸዉና ለራሳቸዉ መንግሥት ምሥረታ ላላቸዉ ጉጉት አሜሪካ ጀርባዋን አትሰጥም።»

ኦባማ ካይሮ ላይ ያሉትን ካሉ በሕዋላ ለነበረዉ ድርድር መቋረጥ ዋና ምክንያቱ እስራኤል በሐይል በያዘቻቸዉ የፍልስጤሞች ግዛቶች የአይሁድ ሠፈራ መንደሮች መገንባቷን አለማቆሙዋ እንደሆነ ፍልስጤሞች በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

የፍልስጤሙ ፕሬዝዳት ማሕሙድ አባስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለፍልስጤሞች የነፃ መንግሥትነት እዉቅና እንዲሰጥ የጠየቁትም ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት በአሜሪካ ሸምጋይነት ሃያ-አመት የተደረገዉ ድርድር ያመጣዉ ዉጤት የለም በሚል ነዉ።

«የተከበሩ ፕሬዝዳት እንደ ፍልስጤም መንግሥት ፕሬዝዳትና እንደ የፍልስጤም ነፃ አዉጪ ድርጅት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሊቀመንበርነቴ ለጠቅላላ ጉባኤዉ ንግግር ከማድረጌ በፊት፥ ከሰኔ አራት 1967 በፊት በነበረዉ ድንበር ላይ፥ ርዕሠ-ከተማዉን እየሩሳሌም ላደረገ የፍልስጤም መንግሥት እዉቅና እንዲሰጥ ለድርጅቱ ዋና ፀሐፊ ለባን ጊ ሙን ማመልከቻ ማስገባቴን ማሳወቅ እፈልጋለሁ።»

ሃያ-አመት የተደረገዉ ድርድር ለእስራኤል የሚፈለገዉን ሠላምና ፀጥታ፥ ለፍልስጤሞች፥ ፕሬዝዳንት ኦባማ ያሉትን ክብርና ነፃነት እንዳለመጣ ከጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ወይም ከፕሬዝዳንት ኦባማ በላይ የሚያዉቅ የለም።ኔታንያሁ ግን ዛሬም በሃያኛ አመቱ የሰላም እጄን እዘረጋለሁ-አሉ በቀደም።

«በተለይ ፍትሐዊና ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ለምንሻዉ ለፍልስጤም ሕዝብ እጄን እዘረጋለሁ።»

ማሕሙድ አባስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለፍልስጤም የነፃ መንግሥትነት እዉቅና እንዲሰጥ ሲጠይቁ ጥያቄዉ ባጭር ጊዜ ገቢር እንዳማይሆን ያዉቁታል። ምናልባት እነ ሆሲኒ ሙባረክን ከሥልጣን ያስወገደዉ የአረብ ሕዝብ አመፅ የእሳቸዉን አስተዳደር ከመመነቃቀሩ በፊት የሕዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር አስበዉ ሊሆንም-ይችላል።

የአባስ መስተዳድር አላማ-ግብ ምንም ሆነ-ምን የዓለም አቀፉን ድርጅት ሕግ ደንብ የጠበቀነቱ ሊያነጋግር አይገባም።የፍልስጤሞች ጥያቄ ኦባማ ካይሮ ድረስ ሔደዉ ከተናገሩት ጋር መጣጣሙን ለማወቅም አስተንታኝ አያስፈልገዉም።ጥያቄዉ ከራሳቸዉ ከፍልስጤሞች ሲመጣ ፕሬዝዳት ኦባማ በሁለት ዓመት እድሜ ዘጠና ዲግሪ ዞረዉ ጥያቄዉን የመቃወማቸዉ ሰበብ ምክንያት በርግጥ ያጠያይቃል።

«እና ለብዙ አስርታት የቆየዉን ግጭት ለማስወገድ አቋራጭ መንገድ እንደሌለ አምናለሁ።ሰላም ጠንካራ ሥራ ነዉ።ሰላም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉሳኔና መግለጫ አይመጣም።»

ዩናይትድ ስቴትስ አንደ ተባባሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች፥ እንደ ዓለም መሪ፥ እንደ እስራኤል የቅርብ ወዳጅ የዘወረችዉ የአርባ-ዘመኑ ጦርነት፥ የሃያ-አመቱ ድርድርም ሠላም አላመጣም።የፍልስጤሞች የነፃ መንግሥትነት ጥያቄም ኦባማና ኔትንያሁ እንዳሉት ሠላም አያመጣም።ሠላም-ከየትና እንዴት ይመጣል? ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ
Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች