1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፌዴራል ዋና ኦዲተር የምርመራ ግኝት ለፓርላማ ቀረበ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 11 2016

በ2015 ዓ. ም ከ124 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መሰብሰብ የነበረበት 14.1 ቢሊዮን ብር አለመሰብሰቡን የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ። ዋና ኦዲተር ባለፈው ዓመት እንዲሰበሰብ አስተያየት የሰጠበት 443 ሚሊዮን ብር እና 23 ሺህ ዶላር አብዛኛው ተመላሽ ሳይደረግ፣ ተገቢውም ርምጃ ሳይወሰድ መቅረቱን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4hCqG
Äthiopien Parlament Addis Abeba
ምስል Solomon Muche/DW

በ2015 ዓ.ም ከ124 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች 14.1 ቢሊዮን ብር አልተሰበሰበም ተባለ

በ2015 ዓ. ም ከ124 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መሰብሰብ የነበረበት 14.1 ቢሊዮን ብር አለመሰብሰቡን የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ።  ዋና ኦዲተር ባለፈው ዓመት እንዲሰበሰብ አስተያየት የሰጠበት 443 ሚሊዮን ብር እና 23 ሺህ ዶላር አብዛኛው ተመላሽ ሳይደረግ፣ ተገቢውም ርምጃ ሳይወሰድ መቅረቱን ገልጿል። በ73 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና በ15 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች 2.1 ቢሊዮን ብር ከግዥ አዋጅ፣ ደንብ እና መመሪያ ውጪ ግዢ መፈፀሙንም አመልክቷል። የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የማዕድን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ የፋይናንስ እና የክዋኔ ኦዲት የአሠራር ጉድለት የታየባቸው መሥሪያ ቤቶች መሆናቸውንም ዋና ኦዲተር ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ዘገባ ጠቅሰዋል። 

የሪፖርቱ ዝርዝር ምን ይዛል?

የፌዴራል ዋና ኦዲተር  የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የ 2015 በጀት ዓመት የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት እና የክዋኔ ኦዲት ዘገባን ዛሬ ለሕዝብ እንደራሴዎች ሲያቀርብ ምርመራ ከተደረገባቸው ተቋማት አብዛኞቹ ጉድለት ተገኝቶባቸዋል ተብሏል።

በዚህም ከአዋጅ፣ ደንብ እና መመሪያ ውጪ እንዲሁም ያለ ጨረታ ግዥ መፈፀም፣ በመሥሪያ ቤት ውስጥ ለሌሉ እና ከሥራ ለተሰናበቱ ሠራተኞች ደሞዝ መክፈል፣ ክፍያን በወቅቱ አለመፈፀምን የመሳሰሉ ችግሮች ተገኝተዋል።

በሌላ በኩል 19.2 ቢሊዮን ብር ለመሥሪያ ቤቶቹ ከተመደበ በኋላ ገንዘቡ ሥራ ያልተሰራበት ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ይህንን ያደረጉትም ዋና ዋናዎቹ የገንዘብ ሚኒስቴር - 8 ቢሊየን ብር፣ ጤና ሚኒስቴር - 2 ቢሊየን እና ግብርና ሚኒስቴር - 1.2 ቢሊዮን ብር ናቸው።

ከ124 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መሰብሰብ የነበረበት 14.1 ቢሊዮን ብር አለመሰብሰቡ፣ በገቢዎች እና ጉምሩክ ኮሚሽን ሥር ባሉ 20 ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች መሰብሰብ የነበረበት 6.4 ቢሊዮን ብር ኤሊሰበሰብ አለመቻሉንም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ያቀረቡት ዘገባ ያሳያል። አስተያየት ከሰጡ የምክር ቤት አባላት መካከል በጀት ከተመደበ በኋላ ጠያቂ ያለ በማይመስል ሁኔታ እንደሚባክን ገልፀዋል።

የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ ዋና ዋና ግኝቶች

ዋና ኦዲተር "የሕዝብ" የሚባለው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሬድዬ እና ቴሌቪዥን አገልግሎቱ "ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚሰጠው ጊዜ አናሳ እና የተለየ ሀሳብ ያላቸው የሲቪክ እና የሙያ ማህበራትን ተገቢ ትኩረት የማይሰጥ" መሆኑን ጠቅሶ እንዲታረም አስተያየት ሰጥቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፦ ፎቶ ከማኅደር
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፦ ፎቶ ከማኅደርምስል Solomon Muchie/DW

ለወሎ ተርሸሪ ኬር ሆስፒታል የህክምና እና ማስተማሪያ ሆስፒታል ማሰሪያ በውጭ ሀገር በሚገኙ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች ይሸጣል የተባለ ኩፖን መጥፋቱን፣ በሀገር ውስጥ የተሰበሰበ ብዙ ገንዘብም ወደ ባንክ አለመግባቱን አመልክቷል።

ሃምሳ አመት የሞላው የማዕድን ሚኒስቴር እስካሁን የማዕድን ሀብት እና ልማት ፖሊሲ እንደሌለው፣ ተቋሙ ለናሙና ወደ ውጪ የሚልካቸው ማዕድናት "ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የላቸውም" በሚል በዚያው ቀልጠው እንደሚቀሩም ተጋልጧል።

"ኦዲተሮችን በጥቅም ለመደለል የሞከሩ የአንድ የኒቨርሲቲ [ስሙ ያልተጠቀሰ] የማኔጅመንት አባላት በሙሉ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ" መደረጉን የጠቀሰው ዋና ኦዲተር  የሥራ ተቋራጮች የያዙትን ሥራ ሳያጠናቅቁ እና አፈፃፀማቸው ሳይታይ በጨረታም ሳይወዳደሩ እንደሚሰሩ፤ ለአብነትም ሁለት ስማቸው ያልተጠቀሰ ድርጅቶች የ 10.2 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት በዚህ ሁኔታ ሥራ እንደያዙ በክዋኔ ኦዲቱ ተመላክቷል። ዘገባው በሀገሪቱ የሀብት አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ችግር ያለ መሆኑን ያሳየ መሆኑን በመጥቀስ አንድ የምክር ቤት አባል የምክር ቤቱ ፋይዳ ላይ ጥያቄ አንስተውበታል።

የዋና ኦዲተር ዘገባ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ  ሚኒስቴር የበዛ የአሰራር ግድፈታ ከታየባቸው ውስጥ ዋናው መሆኑን፣ ዜጎችን በማንገላታት የሚታወቅ የተባለው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት "በግለሰብ ስም የሒሳብ ቁጥር ከፍቶ ገቢ እንደሚሰበስብና፣ በዓመቱ ከሰበሰበው ውስጥ ያለ ስልጣኑ "ለትርፍ ሰዓት ክፍያ እና ለሠራተኞች ስጦታ" በሚል ማባከኑ በዘገባው ተመላክቷል።

ተቋሙ ከዚህ አልፎ " ዜግነት የማጣራት ሥራውን በልምድ የሚያከናውን፣ ውሳኔው ዜግነትን በሚያጣራው ግለሰብ መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ እና ወጥ የሆነ አሠራር የማይከተል" በመሆኑ እርምጃ እንዲወሰድበት ዋና ኦዲተር አስተያየት ሰጥቷል።

ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ከግኝቱ በመነሳት እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክትትል በማድረግ በቀጣይ ችግሮቹ ይቀረፋሉ ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ