የፌስቡክ ውዝግብ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 25.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የፌስቡክ ውዝግብ

አገልግሎቱን የሚጠቀሙ ሰዎች እንደ አንድ ሀገር ዜጋ ቢቆጠሩ በዓለም በህዝብ ብዛት ቀዳሚ የምትባለውን ቻይናን ያስከንዳል፡፡ ከ14 ዓመት በፊት በዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ማደሪያ ውስጥ ሲጠነሰስ ለ400 ግፋ ቢል ለ500 ሰዎች የታለመ ነበር፡፡ ዛሬ በቀን ብቻ 1.4 ቢሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:50

የግል መረጃ እና ፌስቡክ

ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትስስር መፍጠሪያ በሚል የተሰራው ፌስቡክ የተሰኘው ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ አሁን መንግሥታት በተለይም አምባገነኖቹ እና ጨቋኞቹ ክፉኛ የሚፈሩት ሆኗል፡፡ ፌስቡክን በዋናነት ለመረጃ መለዋወጫነት በመጠቀም የሚቀሰቀስ አብዮት ስልጣን ጭምር ሲያሳጣ አይተዋልና እርሱን ለመቆጣጠር አሊያም ጭርሱን ከአገልግሎት ውጪ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ 
ኃያልነቱ ከዓመት ወደ ዓመት እየገዘፈ የመጣው ፌስቡክ ቤት ግን ከሰሞኑ የተጫረው እሳት አልበርድ ብሏል፡፡ ጭርሱኑ የፌስቡክ ጠንሳሹን ማርክ ዙከበርግን በአሜሪካ ኮንግረስ እና ሴኔት አባላት ፊት ቀርቦ ቃሉን እንዲሰጥ አስገድዶታል፡፡

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲጠቀሱ ለብዙዎች ቀድሞ የሚታወሳቸው ፌስቡክን እንዲህ ውጥንቅጥ ውስጥ ያስገባው የብሪታንያው ካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ መምህር ለጥናት በሚል ከተጠቃሚዎች ላይ የሰበሰበው መረጃ ያመጣው መዘዝ ነው፡፡ አሌክሳንደር ኮጋን የተባለው የ28 ዓመቱ መምህር ለሚሰራው ጥናት እንዲያግዘው ባዘጋጀው አፕልኬሽን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የተለያዩ ጥያቄዎች እንዲመልሱለት ጋብዞ ነበር፡፡ የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ባደረገው ማጣራት ግብዣውን ተቀብለው ጥያቄዎችን በመመለስ የተሳተፉ ሰዎች ቁጥር 300 ሺህ ይጠጋል፡፡ 

የመላሾችን ግላዊ መረጃ ከፌስቡክ አድራሻቸው እግረመንገዱን የሰበሰበው መምህሩ ይህንኑ አሳልፎ ካምብሪጅ አናላቲካ ለተባለ ድርጅት ይሰጣል፡፡ ካምብሪጅ አናላቲካ የመላሾችን ብቻ ሳይሆን ከእነርሱ ጋር በፌስቡክ የተጎዳኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ግላዊ መረጃ ያለፍቃዳቸው ወስዶ በማከማቸት ለሚፈልገው ዓላማ ማዋሉ ነው የውዝግቡ መነሻ፡፡ በዚህ ግላዊ መረጃ የመሰብሰብ የተጠቁ ሰዎች እስከ 87 ሚሊዮን እንደሚደርሱ ፌስቡክ አስታውቋል፡፡

ያለተጠቃሚው ዕውቅና በእንዲህ አይነት ሁኔታ የተከማቸ መረጃ ለምን ተግባራት እንደሚውል በኔዝርላንዱ ቫግኒገን ዩኒቨርስቲ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምህር የሆኑት ዶ/ር አያሌው ካሳሁን ይተነትናሉ፡፡ “ለምሳሌ አበበ፣ ከበደ እና በቀለ የእኔ ጓደኞች ከሆኑ፣ እነዚያ ሶስት ሰዎች ደግሞ ያንተም ጓደኞች ከሆኑ፣ ስለእኔ የፖለቲካ አመላከከት በለው የዕለተ ተዕለት ኑሮዬ የሚታወቅ ከሆነ አንተ እና እኔ ተመሳሳይ ጸባይ አለን የሚለውን ነገር መገመት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አንተ እና እኔ ጓደኞቻችን ተመሳሳይ ሰዎች ወይም አንድ አይነት ሰዎች ናቸው፡፡  እና ይሄ አይነት የመረጃ ትንተና ለምሳሌ ለፖለቲካ ልትጠቀመበት ትችላለህ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው የሚጠቀሙበት ለምሳሌ መንግስታት የሚጠቀሙበት ለምሳሌ ሽብር ፈጣሪዎችን ለመያዝ ወይም ደግሞ ወደ ሽብር ፈጠራ ሊገቡ ይችላሉ የሚሉ ሰዎችን አስቀድሞ ለመግኘት [ነው]፡፡

እኔ አንተ ተመሳሳይ ጓደኞች ካሉን፣ ስለ እኔ ጸባይ ከታወቀ፣ ለምሳሌ እኔ ትክክለኛ ሰው ካልሆንኩ አንተም ትክክለኛ ሰው አይደለህም የሚለውን ግምት መውሰድ ይቻላል፡፡ እና እነዚያን መረጃዎች በሙሉ በማጋጨት አንደኛ ስለእያንዳንዳችን ያለውን መረጃ ማግኘት ይቻላል፡፡ ሁለተኛ እያንዳንዳችን በምን ዓይነት መንገድ ነው የተገናኘነው? clustering የሚባል አለ፡፡ እነማን እነማን አይነት ሰዎች ናቸው አንድ አይነት ጸባይ ያላቸው?፣ profiling የሚባል ነገር አለ፡፡ ምን አይነት ሰዎች ናቸው ለእንደዚህ አይነት ድርጊት ሊገፋፉ የሚችሉ የሚለውን መረጃ ጨምቆ ማውጣት የሚቻለው፡፡”

 መረጃዎችን በመሰብሰብ እና በመተንተን የፖለቲካ ማማከር አገልግሎት የሚሰጠው ካምብሪጅ አናላቲካ በመሪዎች ምርጫ ላይ ሳይቀር ተጽዕኖ እስከማሳደር ተጉዟል የሚሉ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ ግልጽ ማስረጃ ባይገኝም ድርጅቱ የሰበሰባቸውን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ግላዊ መረጃዎች ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ መዋሉን የሚያመላክቱ ዘገባዎች ለንባብ በቅተዋል፡፡ ዶ/ር አያሌው ከፌስቡክ የተገኘ መረጃ በምን መልኩ ሊተነተን እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ 

«አሁን ፌስ ቡክ ላይ የተፈጠረው ምንድነው እኔ ለምሳሌ አንድ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠቴ የታወቀ ከሆነ፣ የእኔ ጓደኞች አራት ካሉ፣ እነዚያ አራት ጓደኞች ያሉት ሌላ ሰው ካለ፣ ምናልባት ያ ሰው ወደ እኔ አይነት አዝማሚያ ሊወስደው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ድምፅ በመስጠት በፖለቲካ አዝማማያው ወደ እኔ ሊመጣ ይችላል በሚለው ግምት እዚያ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ማን ማን ላይ በቀላሉ ድምፅ ሊሰጡ ይችላሉ የሚሉትን ሰዎች ዝርዝር በቀላሉ ይታወቃሉ ማለት ነው፡፡»  

በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር አናሳነት እና የኢንተርኔት አገልግሎት ተደራሽነቱ ውሱን መሆን እንዲህ አይነት ችግሮች ለሀገሪቱ በአሳሳቢነት እንዳይወሰዱ አድርጓቸዋል፡፡ የአሜሪካ አይነት የምርጫ ሂደት ለኢትዮጵያ በልምድም፣ በአሰራርም ሩቅ መሆኑ ደግሞ የፌስቡክ ተጽዕኖ ያለውን ድርሻ ያኮሰመነው አስመስሎታል፡፡ ሆኖም ድርጅቱ በኢትዮጵያ ጎረቤት ኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ጭምር እጁ እንዳለበት መነገሩ ብዙዎችን አንቅቷል፡፡

የብሪታንያው ዘ ጋርድያን ጋዜጣ ያነጋገራቸው አንድ የቀድሞው የድርጅቱ ኃላፊ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት የአገልግሎታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሀሳብ ማቅረባቸውን መናገራቸው ደግሞ ጉዳዩ ይበልጥ ወደ ኢትዮጵያ አቅርቦታል፡፡ በኦሃዩ ዩኒቨርስቲ በዲጂታል መገናኛ ብዙሃን ላይ ጥናቱን እያካሄደ የሚገኘው አቤል አስራት ይሄ የፌስቡክ የመረጃ ጥሰት ጉዳይ «በደንብ ሊያሳስበን ይገባል» ይላል፡፡ 

Facebook Datenschutz Internet Symbolbild Flash-Galerie

«በደንብ ሊያሳስበን ይገባል ምክንያቱም እንደ አንድ ሀገር የራስህ ሉዓላዊነት አለህ፡፡ አሁን ያለንበት ዘመን ደግሞ ያንን ሉዓላዊነትህን ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ የሚያስቀምጥበት ነው፡፡ እና ለምሳሌ የኬንያ ምርጫ ላይ የዚያ የካምብሪጅ አናሊቲክስ የስፖንሰር ማስታወቂያ ማስደረግ ችሎ ነበር፡፡ በኬንያ ምርጫ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ የተለየው ምክንያት አንድ መንግሥት ያለው የፖለቲካ ቁጥጥር እና ሁለት ደግሞ ሰው ኦንላይን ከፍሎ ያንን ዓይነት ተጽዕኖ የመፍጠር መንገድ ስለሌለው ነው እንጂ ውጭ ሀገር ካለው ከዳያስፖራው ወይንም መክፈል የሚችል ሰው በዚያ በኩል የሚያገኘውን መረጃ ተጠቅሞ ለማንኛውም አጀንዳ እና ዘመቻ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡»  

አቤል መረጃዎች ላልተገባ አላማዎች ሊውሉ እንደሚችሉ በምሳሌ ሲያስረዳ የኢትዮጵያን እንቅስቃሴ በቅርበት የሚከታተሉ የግብፅ ኃይሎችን በምሳሌነት ይጠቅሳል፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ያለውን የብሔር ተኮር ውዝግብ እና ውጥረት የሚመለከቱ እንደዚህ አይነት ኃይሎች የእዚህ ሀሳብ አቀንቃኝ እና ተቀባይ ለሆነው የኅብረተሰብ ክፍል የሚፈልጉትን መልዕክት ለማስተላለፍ ሊጠቀሙበት ይችላሉ ይላል፡፡ ለእዚህ በማነጻጸሪያነት የሚያነሳው ደግሞ በአሜሪካ ለሪፐብሊካን ደጋፊዎች ሲቀርብ የነበረውን መረጃ ነው፡፡ 

እነዚህ ደጋፊዎች ያምኑታል ተብሎ የሚጠበቅ ነገር ግን ሀሰተኛ ዜናዎች ተለይቶ ይቀርብላቸው እንደነበር በማስታወስ በኢትዮጵያም ተመሳሳዩ ሊፈጸም እንደሚችል ይገልጻል፡፡ ለዚህ ደግሞ የቴክኖሎጂው ያለከልካይ፣ እንደልብ በሁሉም እጅ መገኘት የየሃገራቱን አውድ የሚረዳ ግለሰብ እንዳሻው ነገሮችን እንዲያዛባ ዕድል ይሰጣል ይላል፡፡ እንዲህ አይነት ዓላማ ያለው ግለሰብ ካምብሪጅ አናላቲካ የመሳሰሉ ድርጅቶች ያከማቹትን መረጃ ተጠቅሞ የፈለገውን በቀላሉ መፈጸም እንደሚችል ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ 

የተጠቃሚዎች መረጃ ከፌስቡክ ተወስዶ እንደዚህ አይነት ተቋማት እጅ እንዲገባ ምክንያት የሆነው ፌስቡክ ከዓመታት በፊት ለአፕልኬሽን (መተግበሪያ) ሠሪዎች ሰጥቶት በነበረው ዕድል ምክንያት እንደሆነ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ የኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ባለሙያው አብዱራዛቅ አብራር የመተግበሪያዎች (አፕልኬሽኖች) ሠሪ ነው፡፡ ፌስቡክ እርሱን ለመሰሉ ባለሙያዎች ሰጥቶት ከነበረው ዕድል ጀርባ ያለውን ምክንያት ያብራራል፡፡   

«Apllication Programme Interface (API) ይባላል፡፡ ሁሉም ኩባንያዎች አላቸው፡፡ እና ምን ያደርጋሉ? ከሆነ ዓመት በኋላ ከተጠቃሚዎቻቸው ላይ የሰበሰቡትን መረጃ ለሌላ ሦስተኛ አካል መጠቀም እንዲችሉ [ፈቀዱ]፡፡ እነዚህ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች በዋናነት የሚፈልጉት መረጃ ለመሰብሰብ ነው፡፡ ሰው ምን ያስደስተዋል? ምን ላይ ይከፋል? የሚለውን መረጃ ለመሰብሰብ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ወደ ራሳቸው አገልግሎት ሰውን ለመሳብ ነው፡፡ መተግበሪያ የሚሠሩ ሰዎች ለምሳሌ ከተጠቃሚዎች ፌስቡክ ገጽ ጋር ማገናኘት ይፈልጉ ይሆናል፡፡ እና በጎርጎሮሳዊው 2014 እና 2015 ላይ ፌስቡክ የሰበሰበውን መረጃ ሌሎች መተግበሪያ የሚሠሩ ሰዎች መጠቀም እንዲችሉ ፈቀደ፡፡ ተጨማሪ መረጃ ለመሰብሰብም ነው፡፡ ብዙ ተጠቃሚዎች እንዲጨምሩለትም ነው፡፡ ለምሳሌ ቫይበር እናውቃለን፡፡ አንዳንድ ሰው ቫይበር ይጠቀማል፡፡ ፌስቡክ ግን አይጠቀመም፡፡ በቫይበር ላይ ሆኖ ሰውን ወደ ፌስቡክ እንዲገባ ለማድረግ ማለት ነው፡፡ የሦስተኛ ወገን መተግበሪያ እየተጠቀመ ነገር ግን እዚህ ጋር ፌስቡክም የሚባል አገልግሎት አለ ብሎ ወደ ፌስቡክ እንዲሳብ ማለት ነው፡፡»

የዲጂታል መገናኛ ብዙሃን አጥኚው አቤል ፌስቡክ የተጠቃሚዎችን ግላዊ መረጃዎች የአሳልፎ የሚሰጥባቸውን መንገዶች ያስረዳሉ፡፡ «እኛ መጀመሪያውኑ ከፌስቡክ ጋር ስምምነት ስንደርስ በብዛት አናነባቸውም፡፡ ያሉት ስምምነት ከ30 ሺህ ቃላት በላይ ነው፡፡ በአማርኛ አማራጭ ኖሮህ፣ ተረድኸው አይደለም ለዚያ ስምምነት [ፍቃድህን] የምትሰጠው፡፡ ያ ሙሉ ለሙሉ ፌስ ቡክን ያንተን መረጃ ለሶስተኛ ወገን እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡ ሁለተኛው መንገድ ደግሞ እነዚህ እንደካምብሪጅ ያሉ ድርጅቶች ደግሞ የሚሰሯቸው ጌሞች አሉ እና እነሱ ጌሞች ከፌስቡክ መተግበሪያ ጋር ሲዋሃዱ ፌስቡክ በዝርዝር አይመለከታቸውም ነበር፡፡ እና ሰው ያንን ተጭኖ ሲጠቀም ከእነሱም ጋር የጓደኛህን አድራሻ እና መረጃ የመሰብሰብ ፍቃድ ይሰጣቸዋል፡፡”

የቫግኒገን የዩኒቨርስቲው ዶ/ር አያሌው « ፌስቡክ ያደረገው ነገር ሕጋዊ ነው ወይም አይደለም ለማለት አስቸጋሪ ነው» ይላሉ፡፡ «ብዙ ጊዜ የፌስቡክ ገጽ ያለን መምረጥ የምችለው ለማን ነው? ለማን ማጋራት እችላለሁ? ፌስቡክ የእኔን መረጃ ወስዶ ምን ማድረግ ይችላል? የሚለው መምረጥ የምችለው በጣም ብዙ ነገር ስለሆነ ለአብዛኛው ሰው ትክክለኛውን መምረጥ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡

ለምሳሌ አንድ ነገር በምለጥፍበት ሰዓት ጓደኞቼ ብቻ ናቸው የሚያዩት ወይስ የጓደኞቼ ጓደኞች የሚለውን መምረጥ አለብኝ፡፡ ግማሹ ሰው በእርግጥ መምረጥ ያለበትን ነገር ሊያውቅ ይችላል፡፡ ግማሹ ሰው ደግሞ ላያውቅ ይችላል፡፡ አሁን አስቸጋሪነቱ የተፈጠረው ምንድነው፡፡ እኔ ስለጓደኞቼ ስም ዝርዝር መስጠት እፈልጋለሁ ብዬ ልፈቅድ እችላለሁ፡፡ ጓደኞቼ ግን ላይፈልጉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በህጉ መሰረት የትኛው ነው ትክክለኛ ሊሆን  የሚችለው? እና በህግም ደረጃ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ይመስለኛል እዚህ ደረጃ ላይ የደረስነው፡፡»

የአዲስ አበባው አብዱራዛቅ እንደ ፌስቡክ ያሉ ማኅበራዊ ድረገጾች እና መተግበሪያዎችን በሚጠቀሙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የግል መረጃን የመጠበቅ (privacy) ጉዳይ ያን ያህል የሚያስጨንቅ ነገር አይደለም ይላል፡፡ “አብዛኛው ሰው ከprivacy ጋር አይጨነቀም፡፡ ምኑ ነው የሚያሳስበው? የሚጠቀምበት መተግበሪያ ምን ያህል ህይወቴን ያቀለልኛል ወይም ደግሞ ምን ያህል ያዝናናኛል የሚለው ነው እንጂ መረጃዬ ለሌላ ሰው ተሰጠ፣ አልተሰጠ የሚለው ነገር አብዛኛው ሰው ያን ያህል አያሳስበውም፡፡ ስለዚህ አሁን ህዝቡ ላይ ትልቁ ነገር መሰራት ያለበት የግል መረጃዬ ለሌላ ሰው መስጠቴ አስፈላጊ ነው ወይስ ጎጂ ነው? የሚለውን ነገር እውቀት መፍጠሩ እርሱ ወሳኝ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡”  

አብዱራዛቅ ኢትዮጵያውያን ፌስቡክን መሰል የማኅበራዊ መገናኛዎችም ሆኑ የመተግበሪያ ተጠቃሚዎች ለሚያጋሯቸው መረጃዎች ቁጥብ መሆን እንዳለባቸው ይመክራል፡፡ ሙሉ ለሙሉ መረጃን ማቀብ ግን «ጫካ ውስጥ መኖር እንደማለት ነው» ሲል ከባድነቱን ያስረዳል፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ
 

Audios and videos on the topic