የ″ፊፋ″ ውዝግብና የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን መልቀቅ | ስፖርት | DW | 03.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የ"ፊፋ" ውዝግብና የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን መልቀቅ

ከጉቦ ጋር በተያያዘ ብርቱ ጥርጣሬ፤ 7 የ FIFA ሠራተኞች ዙሪኽ ውስጥ ለምርመራ ተይዘው ሲታሠሩ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ ፣ በ FIFA ውስጥ ሳይፈጸም እንዳልቀረ በሚወራለት ሙስና ሳቢያ የተጠረጠሩ 14 ሰዎች እንዲያዙ ማዘዣ ማውጣቷ የሚታወስ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:33

የ FIFA ውዝግብና የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን መልቀቅ

ያ ሁሉ ትርምስ በማነጋገር ላይ እንዳለም ነበረ የ FIFA ኮንግረስ ባለፈው ሐሙስና ዓርብ የተካሄደው። የ 79 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ዜፕ ብላተርም፤ ራሳቸውን ለእጩነት አቅርበው 133-73 በሆነ ከፍተኛ ድምፅ ብልጫ ተመረጡ። ትናንት ሥልጣናቸውን ለቀቁ። ለምን እጩ ሆነው ለመቅረብ ፣ በትጋት ታገሉ? ለምን ከተመረጡ በኋላ ሥልጣን ለቀቁ? የእስፖርቱን ብቻ ሳይሆን የፖለቲካውን ዓለም አስደምሟል።

17 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆዩትና ባለፈው ዓርብ እንደገና ለ 4 ዓመት አገልግሎት በተመረጡ በ 4ኛው ቀን ሥልጣን የለቀቁት ዜፕ ብላተር፣ ይሁንታ ያገኙት «ከእግር ኳሱ ዓለም፤ ከኳስ አፍቃሪዎች፤ ከተጫዎቾች፤ ከክለቦች፤ ልባቸው በእግር ኳስ ፍቅር ከተነደፈ ወገኖች» መሆኑን ነበረ የተናገሩት።

አያይዘውም፤ የዩናይትድ ስቴትስን ባለሥልጣናትና የብሪታንያን የሕዝብ መገናኛ አገልግሎቶች፤ ጸረ-FIFA አጀንዳ አካሄዱ በማለት ነቅፈው ነበር። The New York Times እና ABC News ራሳቸው ብላተር በዩናይትድ ስቴትስ የወንጀል ምርመራ መሥሪያ ቤት በኩል ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ነው የገለጡት። ከዋሽንግተን DC ፣ Ed Wilsonየተባሉት ከድንበር ባሻገር የገንዘብ ዝውውርን ጉዳይ የሚከታተሉ ጠበቃ፤ FIFA ከእግር ጥፍሩ እስከ አናቱ በሙስና የተዘፈቀ ማህበር ነው ባይ ናቸው።

ግን ብላተር ለምን ሥልጣናቸውን ለቀቁ ። ተከታዩን ምክንያት አቅርበዋል።

«የተሰጠኝ ሥልጣን ፤ በእግር ኳሱ ዓለም፤ በእግር ኳስ ደጋፊዎች ፤ በክለቦች፤ በተጫዋቾች በተለይ ለእግር ኳስ ላይ የሕይወት እስትንፋስ በሚሰጡ ሁሉ የተደገፈ መስሎ አልታየም። ለዚህም ነው ልዩ ጉባዔ እንዲጠራና ኀላፊነቴ፤ ተግባሬ እንዲመረመር የማደርገው። ይህ በተቻለ ፍጥነት የሚካሄድ ሲሆን፤ እኔን የሚከተል አዲስ ፕሬዚዳንትም ይመረጣል። አዲስ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ በ FIFA ፕሬዚዳንትነቴ ሥራዬን እቀጥላለሁ»።

ምርጫው መቼ ይካሄዳል? የ FIFA የሂሳብ ምርመራ ክፍል ሊቀመንበር ዶሜኒኮ ስካላ እንዳሉት ከሚመጣው ዓመት ታሕሳስ ወር አንስቶ እስከ መጋቢት 2008 ዓ ም ባለው ጊዜ ውስጥ በልዩ ዐቢይ ጉባዔ መከናወኑ የማይቀር ነው። ባለፈው ዓርብ እጩ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ ያልፈለገው ፣ የ 59 ዓመቱ የቀድሞው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አምበልና አሁን የአውሮፓ የእግር ኳስ ማሕበር ፕሬዚዳንት ሚሸል ፕላቲኒ ፤ ያኔ በእጩነት ይቀርባል፤ የ 39 ዓመቱ ጎልማሣ ዮርዳኖሳዊው ልዑል ዓሊም እንደገና የመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል። በብላተር ሥልጣን የመልቀቅ ውሳኔ አንዳንዶች የመደሰታቸውን ያህል ብዙዎች ያልጠበቁት ነበርና አዝነዋል፤ አድናቆታቸውንም ገልጸውላቸዋል። ለስለስ ያለ ሒስ የሰነዘሩም አልታጡም። ከአፍሪቃ የቀድሞው እውቅ የእግር ኳስ ተጫዋች ሮጀር ሚላ---

«ያዳምጡኛል?፣ ስለ እውነት ነው የምናገረው፤ በእንዲህ ሁኔታ ከሥልጣን መነሣታቸው አሳዝኖኛል። ይነገሩ የነበሩ ተጫባጭ ሁኔታዎችን በትክክል ቢያዳምጡ ኖሮ አሁን እተደረሰበት ደረጃ ላይ አንገኝም ነበር። ብላተር በአንዲህ ሁኔታ መሰናበታቸው ቅር ያሰኛል ፤ ግን ፤ አሁን በቦታው የሉምና ሌላ ከአርሳቸው የተሻለ ችሎታ ያለው ሰው መፈለግ ይኖርብናል። ሁሉንም በጥሞና የሚያዳምጥ፤ በአፍሪቃ የአግር ኳስ ክለቦች የሚፈጸሙ ስሕተቶችን ተመልክቶ ችግሩን የሚያስወግድ ያስፈልገናል። »

የቀድሞው የዓለም የእግር ኳስ ፌደሬሽን (FIFA ) ፕሬዚዳንት ዛዎ ሓቫላንጅና ተከታያቸው ጆሴፍ ብላተር፤ እ ጎ አ ከ 1974 ዓ ም አንስቶ ለብሔራዊ ፌደሬሽኖችና ለአካባቢያዊ የእግር ኳስ ባለሥልጣናት ሥልጣን በመስጠት ታማኝ ደጋፊዎችን ለማፍራት መቻላቸው ይነገርላቸዋል። በሚመጡት ወራት ሁኔታዎች ሊለወጡ እንደሚችሉ ይታሰባል። ዜፕ ብላተር ራሳቸው፤ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ሲያሰላስሉ፤ ማሕበሩ ከሚመራበት አሠራር አንስቶ፤ ከተያዥ ድርጅቶች ፤ ፕሮግራም አሠራጪዎች፤ ፌደሬሽኖች፤ ክለቦች፤ ተጫዋቾችና ደላሎች ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት እንዲመከርበትና ገንቢ ውሳኔ እንዲተላለፍ የሚሹ መሆናቸውን ሳይጠቁሙ አልቀሩም።

የጀርመን ብሄራዊ የእግር ኳስ ማሕበር (DFB) በማሕበራዊ መስክና በፖለቲካውም ያለውን ተሰሚነት በአግባቡ አልተጠቀመበትም የሚል ነቀፌታ በሕዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት (ቡንደስታኽ ) የሶሺያል ዴሞካራቱ ፓርቲ አባላኅት የሆኑ እንደራሴዎች ተጠሪ ቶማስ ዖፐርማን ነቅፈዋል። የሆነው ሆኖ አሁን በተፈጠረው ሁኔታ፤ የተሃድሶ ለውጥ ተካሂዶ አዲስ አሠራር በማስተዋወቁ ረገድ የጀርመን የእግር ኳስ ማሕበር መሪ ድርሻ ሊወጣ ይችላል ሲሉም ዖፐርማን ተናግረዋል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic