የፊናንሱ ቀውስ፤ የመፍትሄው ጥረትና ታዳጊው ዓለም | ኤኮኖሚ | DW | 14.01.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የፊናንሱ ቀውስ፤ የመፍትሄው ጥረትና ታዳጊው ዓለም

የዓለም ኤኮኖሚ ከመቼውም በላይ እየተሳሰረ መሄድ ከጀመረ ሰንበት ያለ ጉዳይ ነው። ግን ዓለም አጽናፋዊ ትስስር በሰፈነበት ወቅት ውስጥ የምትገኝ ቢሆንም ምዕራባውያን መንግሥታት ቀውሱን ለማስወገድ የሚያደርጉት ጥረትና የሚዘይዱት መላ ሁሉ በብሄራዊ ጥቅም ላይ ያተኮረ ሆኖ መታየቱ ነው ሃቁ!

የፊናንስ ውዥቀት

የፊናንስ ውዥቀት

በዚህ በአውሮፓና ከአትላንቲክ ባሽገር በአሜሪካም እያንዳንዱ መንግሥት ቀውሱን ለመጋተር በሚነድፈው ጽንሰ-ሃሣብና በሚያወጣው ዕቅድ የራሱን የቤት ሥራ ለማከናወን ነው የሚጥረው። ለነገሩ የዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ሰለባ ዛሬ የበለጸገው ዓለም ብቻ አይደለም። በተናጠል በብሄራዊ ደረጃ በሚራመድ ዕቅድ ዓለምአቀፍ የሆነ ችግርን ለመፍታት መቻሉም ሲበዛ ያጠያይቃል። ታዲያ በወቅቱ ሂደት ታዳጊ አገሮች እንደገና ተጎጂዎቹ እንዳይሆኑ የሚሰጉት የኤኮኖሚ ጥበብት ጥቂቶች አይደሉም።

ዓለምአቀፉን የፊናንስ ቀውስ ለመታገል ካለፈው ሕዳር ወር ወዲህ እስካሁን በአውሮፓና በአሜሪካ የፈሰሰው ገንዘብ በብዙ ሚሊያርድ ዶላር የሚቆጠር ነው። የፊናንሱ ቀውስ አምራቹን ኤኮኖሚም ችግር ላይ መጣሉ ጎልቶ በተከሰተበት በአዲሱ ዓመትም መንገዳገድ የያዙ ባንኮችንና ኩባንያዎችን ለማዳን ሰፊ በጀት ማፍሰሱ ቀጥሏል። ይሁንና መንገዱ አጠያያቂ ነው። በግብር ቅነሣም ሆነ በመዋቅራዊ ግንባታ ላይ መዋዕለ-ነዋይ ማቅረቡ፤ እንደ ጀርመን የአገሪቱ የኤኮኖሚ ምሶሶ የሆነውን ቁልፍ የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪ መደጎም-ማራመድም ይሁን ወይም የአውሮፓ ሕብረት ባቀረበው ሃሣብ መሠረት ለተፈጥሮ እንክብካቤ የሚበጅ ቴክኖሎጂን ማስፋፋቱ፤ ሁሉም በጠባቡ ለብሄራዊ ፈውስ መወጠኑ ነው ችግሩ!
ማገገሚያው ዕቅድ የዓለምአቀፉን የፊናንስ ገበዮች ችግር ለማሸነፍ በሚበጅ መንገድ ተቀናጅቷል ለማለት አይቻልም። እያንዳንዱ መንግሥት የራሱን መራጮች ፍላጎት በማሟላቱ ጉዳይ የተወሰነ መሆኑን ለምሳሌ የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክል በአገሪቱ በተካሄደው የኤኮኖሚ ማነቃቂቂያ በጀት ክርክር ዋዜማ የተናገሩት ግልጽ ያደርገዋል።

“በአጠቃላይ ግባችን ላይ አንድነት አለን፤ ይህም የሥራ ቦታዎችን ማረጋገጥና መፍጠር፤ ማለት ጀርመንን ለወደፊቱ ጊዜ ማዘጋጀት ነው”

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በጅምሩ የአሜሪካን ታላላቅ የመዋዕለ-ነዋይ ባንኮች ተራ በተራ ሲያናጋና ብርቱ የገበያ ውዥምብርን ሲፈጥር ምታቱ በዚያ መጠን አውሮፓን ያዳርሳል ብሎ ለማመን የፈለገ ብዙ አልነበረም። ይሁንና እያደር የአውሮፓ የፊናንስና የኢንዱስትሪ ዘርፎችም በወቅቱ የችግሩ ተጽዕኖ እየተሰማቸው መሄድ ይዟል። በጀርመን በዓለም ላይ ቀደምቱ የሆነውና የአገሪቱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ሆኖ ትርፍ በትርፍ ሲሆን ያለፉትን አሥር ዓመታት ያሳለፈው የአገሪቱ የውጭ ንግድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰፊ ማቆልቆል ታይቶበታል።
የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪው በፊናንሱ ቀውስ የተነሣ በተከሰተው የፍላጎት መቀነስ ሳቢያ ምርቶቹን እንደቀድሞው ገበያ ላይ ሊያውል አልቻለም። ለዚሁ የኢንዱስትሪ ዘርፍ መለዋወጫ ዕቃ የሚያመርቱ በሺህ የሚቆጠሩ ኩባንያዎችም ሠራተኛ ወይም የምርት ሰዓት እስከመቀነስ ደርሰዋል። በግንቢያው መስክም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ቪስባደን ከተማ ላይ ተቀማጭ የሆነው ፌደራል የሰንጠረዥ ቢሮ ባቀረበው መረጃ መሠረት የጀርመን መንግሥት በቅርቡ በተገባበደው 2008 ዓ.ም. የ 1.59 ሚሊያርድ ኤውሮ የበጀት ኪሣራ ደርሶበታል።
ይህም ከአገሪቱ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት አንጻር 0,1 ከመቶው መሆኑ ነው። የሚቀጥለው 2010 ዓ.ም. የበጀት ኪሣራ እንዲያውም ወደ አራት ከመቶ ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ግምት አለ። ችግሩ ጠንከር ያለ ዕርምጃን የሚጠይቅ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። የአገሪቱ ጥምር መንግሥት ባለፈው ሰኞ የተስማማበትን ሰፊ የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕቅዱን በፍጥነት ገቢር ለማስደረግ ሲጥር መሰንበቱም የጉዳዩን ክብደት የሚያሳይ ነው።

የበርሊኑ ካቢኔ በዛሬው ዕለት በጉዳዩ ከመከረ በኋላ ቻንስለር እንጌላ ሜርክልም ዕቅዳቸውን ለም/ቤት አብራርተዋል። ዕቅዱ በዚሁ በያዝነው ወር በሕግ ይጸናል ተብሎ የሚጠበቅ ነው። ይሄው የታቀደው የ 50 ሚሊያርድ ኤውሮ የኤኮኖሚ ማነቃቂያ በጀት የአገሪቱን ዜጎች የገበያ አቅም ለማዳበርና የመዋዕለ-ነዋይ ፍሰትን ለማጠናከር ብዙ ሳይቆይ በሥራ ላይ እንዲውል የሚፈለግ ነው። መንግሥት በውድቀት አፋፍ ላይ የሚገኙ ኩባንያዎችን ለማዳንም ማቀዱ አልቀረም። በአንዳንድ የኤኮኖሚ ጠበብት ግምት ይሁንና ዕቅዱ ገቢር ቢሆን ሁኔታውን የማሻሻል ተጽዕኖው ከሚቀጥለው 2010 ዓ.ም ቀድሞ የሚከሰት አይደለም። .....

በኢንዲስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት አመለካከትና ፍላጎት በአውሮፓው ሕብረት ውስጥ እንደሚታየው ሁሉ በአሜሪካም የተለየ አይደለም። ተመራጩ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ በሚቀጥለው ሣምንት ሥልጣናቸውን በይፋ ሲረከቡ ግዙፍ የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕቅዳቸውን ገቢር ማድረግ ይጀምራሉ። ችግሩን ለመወጣት ከ 800 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት ለማፍሰስ ያቅዳሉ። ዕቅዳቸው ታዲያ ከሁሉም በላይ በአገራቸው የሥራ ቦታዎችን በመፍጠርና የሕዝቡን የፍጆት አቅም በማጠናከር የአሜሪካን ኤኮኖሚ ከገባበት አዘቅት ማውጣት ነው።

ብርቱ ፈተና የተደቀነበትን ብሄራዊ ኤኮኖሚ መልሶ የማጠናከሩ ጥረት በመሠረቱ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ባልከፋ! ችግሩ ይህን መሰሉ ዕቅድ የራስን ኤኮኖሚ በማደስ ብቻ ሣይወሰን የመራጭን ድምጽ ለማረጋገጥም የተሰላ እንደሆን ነው። ይህ ከሆነ ብሄራዊው የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕቅድ እዚህም ሆነ እዚያ በታዳጊው ዓለም ሕዝብ ትከሻ የሚራመድ እንዳይሆን የሚሰጉት ታዛቢዎች ብዙዎች ናቸው። በመሆኑም ዕቅዱ ዓለምአቀፍ እንዲሆን የሚሹት የጀርመኑን ግብረ-ሰናይ ድርጅት የቴር-ዴስ-ሆምስን ሥራ አስኪያጅ ፔተር ሙከን የመሳሰሉት ተቺዎች ጥቂቶች አይደሉም። እንደርሳቸው አባባል ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ይበልጡን የሚጎዳው ታዳጊዎቹን አገሮች ነው።

“ወደነዚህ ሃገራት የሚፈሰው ካፒታል በጥቂቱ የተወሰነ ነው የሚሆነው። የቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ አቅርቦትና የጥሬ ዕቃ ዋጋም ያቆለቁላል። እና እነዚህ ሃገራት የውጭ ንግዳቸው በኢንዱስትሪው ዓለም ፍላጎት መቀነስ ስለሚነካ ችግር ላይ ይወድቃሉ። በመሆኑም ከሁሉም በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ አገሮች የሚፈለገው ሌላ ዕርምጃ ነው። በተለይ አሁን ነው የልማት ዕርዳታው ማደግ ያለበት። አሁን ነው የሰሜን-ደቡብ የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕቅድ አስፈላጊ የሚሆነው”

ይሁንና በወቅቱ በርካታ ለጋሽ መንግሥታት ዓለምአቀፍ የልማት ዕርዳታቸውን መቀነሳቸው እንጂ መጨመራቸው አይታይም። ጀርመን ለጊዜው በዓለምአቀፍ ንጽጽር በሁለተኛ ቦታ ላይ ትገኛለች። ግን ይህ የሆነው ጀርመን የልማት በጀቷን በመጨመሯ አይደለም። ይልቁንም ብሪታኒያና ጃፓን ዕርዳታቸውን በመቀነሣቸው እንጂ! ፈረንሣይ እንዲያውም ለአፍሪቃ የምታቀርበውን የልማት ዕርዳታ አግዳዋለች። የኢጣሊያም ሁኔታ ለሌሎቹ የተለየ አይደለም። “Global Call for Action Against Poverty” የተሰኘው ዓለምአቀፍ ጸረ-ድህነት የተግባር ዘመቻ አመራር ዓባል ሢልቪያ ቦረንና መሰሎቻቸው ሁኔታውን ሞራላዊነት የጎደለው አድርገው ነው የሚመለከቱት።

“በወቅቱ እስከ 4000 ሚሊያርድ የአሜሪካ ዶላር፤ አራት ትሪሊዮን መሆኑ ነው፤ ባንኮችንና የፊናንሱን ስርዓት ለማዳን እያፈሰስን መሆኑን ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል። የዚህ ግዙፍ ገንዘብ አንድ ወይም ሁለት በመቶዋ እንኳ የድሃ ድሃ በሆኑት አገሮች ቁጥር ስፍር የሌለውን ሕይወት ለማትረፍ በቻለች ነበር። እና የፊናንሱን ስርዓት ለማረጋጋት በአንዴ ሰፊ የግብር ገንዘብ ማውጣት እያቻልን ለድሆቹ መርጃ መጥፋቱ ሊያምኑት ያስቸግራል። ይህ ለኔ ታላቁ የዘመናችን የሞራል ክስረት ነው”

ሢልቪያ ቦረን ቀውሱን የፍጆት አቅምን በማዳበር ለማስወገድ ይቻላል፤ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት ሃገራት ኤኮኖሚ መልሶ መነቃቃት በመጨረሻ ለሶሥተኛው ዓለም የገበያን ዕድል የሚከፍትና ዕድገትንም የሚያስከትል ነው የሚለውን አባባል አይቀበሉትም። የበለጸገው ዓለም የኤኮኖሚ ዕድገት ጥቅም ታች ላሉት እንዳልደረሰ ያለፉት 15 ዓመታት ልምድ አሳይተዋል ባይ ናቸው።

“የኤኮኖሚው ችግሮች ግን እስከታች ይዘልቃሉ። በወቅቱ የፊናንስ ቀውስ የተነሣ ዋነኞቹ የችግሩ ሰለቦች በአብዛኛው ቁዋሚ ሥራ የሌላቸው፤ እዚህም እዚያም እያሉ ለመኖር የሚጥሩት የድሃ ድሃዎቹ ናቸው። ቀውሱ መካከለኛውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ሲያዳርስ በመጀመሪያ የሚያስከትለው ደግሞ በአገልግሎት ሰጪውና ለድሃው የሕብረተሰብ ክፍል የሕልውና መሠረት በሆነው ዘርፍ የጊዜያዊ ሥራዎች መሰረዝን ነው”

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ከቀውስ ለመላቀቅ በያዙት ማነቃቂያ ዕቅድ የልማት ዕርዳታውን ይበልጥ የራሳቸውን ኤኮኖሚ ለማንቀሳቀስ እንዳይጠቀሙ ስጋት መፈጠሩም አልቀረም። እንደተለመደው የልማት ዕርዳታው ከሁሉም በላይ ለለጋሾቹ ሃገራት ኢንዱስትሪዎች ገበዮችን ከመክፈት ቅድመ-ግዴታ ጋር የተሳሰረ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ታዲያ የወቅቱ ዓለምአቀፍ ቀውስ ዋነኛ ተጎጂዎች ታዳጊዎቹ አገሮች መሆናቸው የጀርመኗ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ሃይደማሪ-ቪቾሬክ-ሶይል ጭምር እንዳሉት ከአሁኑ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ነገር ነው።

“ታዳጊዎቹ አገሮች በ 2008 ዓ.ም. ነዳጅ ዘይት ወደ አገር ለማስገባት 50 ሚሊያርድ ዶላር መክፈል ነበረባቸው። ራሳቸው ዋና አምራች ካልሆኑ በስተቀር ምግብ ለማስገባትም ከፍተኛ ዋጋ ነው የሚከፍሉት። በአካባቢ አየር ለውጥ የተፈጠረው ችግርም አለ። አሁን ደግሞ በአሜሪካና በሌሎች ቦታዎች በተከሰተው የኤኮኖሚ ቀውስ የተነሣ የውጩን ንግድ ሊገፉበት አልቻሉም። የብድር ችግርም መኖሩ አልቀረም። ስለዚህም እኔ የማሳስበው የዓለም ሕብረተሰብ ለ 21ኛው ምዕተ-ዓመት የሚሆን አዲስ ዓለምአቀፍ ውልን እንዲያሰፍን ነው”

ጥያቄው ይህን መሰሉ ተሃድሶ ዕውን ሊሆን ይችላል ወይ ነው። ዓለምአቀፉን የኤኮኖሚ ስርዓት ፍትሃዊ አድርጎ መጠገኑ ቀላል ነገር እንዳልሆነ ቢቀር በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ ሲካሄድ የቆየው የዶሃ ድርድር ለዓመታት ሲጎተት ከቆየ በኋላ መሰናከሉ በቂ ምስክር ነው። ስኬት እንዲገኝ ከተፈለገ ዓለም ከብሄራዊ ክልሉ ባሻገር አርቆ ማተኮር መቻል ይኖርበታል።ተዛማጅ ዘገባዎች