የፊናንሱ ቀውስ በቡድን-ሃያ ጉባዔ ዋዜማ | ኤኮኖሚ | DW | 01.04.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የፊናንሱ ቀውስ በቡድን-ሃያ ጉባዔ ዋዜማ

የዓለም የፊናንስ ጉባዔ ነገ ለንደን ላይ ይካሄዳል። የቡድን-ሃያ መሪዎች በዋሺንግተን ተሰብስበው ዓለምን በወጠረው ቀውስ ላይ ከመከሩ ከአራት ወራት በኋላ የሚካሄደው ተከታይ ጉባዔ ጭብጥ ውሣኔዎችን ያስተላልፋል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

የጉባዔው ተቃዋሚዎች በለንደን

የጉባዔው ተቃዋሚዎች በለንደን

የፊናንሱ ቀውስ በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት ቀደምት መንግሥታትና ቻይናን በመሳሰሉት በተፋጠነ ዕድገት ሲራመዱ የቆዩ አገሮች ውስጥ ብርቱ የኤኮኖሚ ፈተናን ሲደቅን አፍሪቃም በጅምሩ ከታሰበው ይልቅ ተጎጂ እየሆነች ነው የሄደችው። በአንድ በኩል የፊናንሱን ስርዓት በመጠገኑ ረገድ በአሜሪካና በአውሮፓ መካከል ያለው ልዩነት፤ በሌላም በዓለም ኤኮኖሚ ስርዓት ላይ መሠረታዊ ተሃድሶ በማድረጉ በኩል ብዙም ዕርምጃ አለመታየቱ የአዲስ ዘመን ተሥፋን የሚያጠናክር አይደለም። ለመሆኑ በዚህ ሁኔታ ከለንደኑ ጉባዔ ምንድነው ሊጠበቅ የሚችለው?

ያለፈው 2008 ዓ.ም. የነዳጅ ዘይትና የምግብ ምርቶች ዋጋ ከዚያ ቀደም ባልታወቀ መጠን መናር የዓለምን ኤኮኖሚ፤ በተለይም ታዳጊውን ዓለም ክፉኛ የፈተነበት ነበር። እንዲያም ሲል ነበር ወደ ዓመቱ መጨረሻ መቃረቢያ በአሜሪካ የቤት ባለቤቶች የዕዳ ችግር የተቀሰቀሰው ቀውስ የዓለምን የፊናንስ ገበዮች ውዥቀት፤ ውዥምብር ላይ የጣለው። ከሰላሣኛዎቹ ዓመታት የዓለም ኤኮኖሚ ውድቀት ወዲህ አቻ ያልታየለት ቀውስ በባንኮች ክስረት ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ወደ አምራቹ የኤኮኖሚ ዘርፍ በመሸጋገር ለአያሌ ኩባንያዎች መክሰርና ለሥራ አጥነት መበራከት ምክንያት ሆኗል። የፊናንሱ ቀውስ መዘዝ በአፍሪቃም የውጭ መዋዕለ ነዋይ ፍሰትንና የልማት ዕርዳታ አቅርቦትን እየቀነሰ በመምጣት ያለፉትን ዓመታት ተከታታይ ዕድገት እየቀጨ ነው።

የችግሩ ገጽታ በአጭሩ ይህን የመሰለ ሲሆን በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት ቀደምት መንግሥታት ባንኮችን ከለየለት ውድቀት ለማዳንና በፊናንሱ ገበዮች ላይ መልሶ ዓመኔታን ለማስፈን፤ በአጠቃላይ ችግር የተጣባውን ኤኮኖሚያቸውን መልሶ ለማነቃቃት በሚሊያርዶች የሚቆጠር ዶላር አፍሰዋል። ቀደምቱን ባለ ኢንዱስትሪ አገሮችና ራመድ ያሉ አገሮችን የጠቀለለው ቡድን-ሃያ ስብስብ ባለፈው ሕዳር ወር ዋሺንግተን ላይ ባካሄደው በመጀመሪያው የዓለም የፊናንስ ጉባዔ አርባ ጭብጥ ዕርምጃዎችን ያቀፈ የተግባር ዕቅድ አውጥቶ ነበር የተበተነው። ከነዚሁም መካከል አንዱ የተሻለ የፊናንስ ገበዮች ቁጥጥርን ማስፈን ሲሆን አብዛኞቹ ነጥቦች አሁን በለንደኑ ጉባዔ ገቢር መሆን እንዲያዙ ነው የታሰበው። የጉባዔው አስተናጋጅ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን ነገም ለጠበቀ ቁጥጥር ባለፈው ሣምንት በአውሮፓ ፓርላማ አድርገውት የነበረውን ጥሪ እንደገና እንደሚያነሱ ነው የሚጠበቀው።

“ለዚህም ነው እያንዳንዱ ክፍለ-ዓለም በባንክ ስርዓቱ ላይ ለጋራ ብልጽግና በር ከፋች የሆነ ለውጥ ማድረጉን የሚያረጋግጥ ቁርጠኛ ዕቅድ ገቢር ይሆን ዘንድ አውሮፓ የመሪነቱን ሚና እንድትይዝ የማሳስበው። እያንዳንዱ ክፍለ-ዓለም የፊናንስ አቀነባበርን የተመለከተ ዓለምአቀፍ ደምብ በማስፈኑ ረገድ እንዲሳተፍና እንዲተባበር፤ የኤኮኖሚ ዕድገትና የሥራ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስፈልገውን ገንዘብ እንዲያቀርብም መደረግ አለበት”

ጥያቄው ይህን መሰሉ ሚና ዕውን ሊሆን መቻሉ ላይ ነው። ጉዳዩ ከዋሺንግተኑ የዓለም የፊናንስ ጉባዔ ወዲህ ዕለታዊ የውይይት ርዕስ ሆኖ፤ በየቦታው የስብሰባ ማራቶን ተይዞበትም ነው የቆየው። የዓለምአቀፉ የፊናንስ ሥርዓት አወቃቀር ወደፊት ምን መልክ ሊይዝ ይገባዋል? በአውሮፓ ሕብረት፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ በደቡብ ምሥራቅ እሢያና በሌሎች ቦታዎችም በየጊዜው’ ምላሽ ለማግኘት መሞከሩ አልቀረም። ሆኖም ሃቁ እስካሁን ጭብጥ መፍትሄ እየተገኘ ወይም እየታየ ነው ለማለት ከሚያስደፍር ደረጃ ላይ አለመደረሱ ነው።

እርግጥ ዓለምን ፋታ ያሳጣው የኤኮኖሚ ቀውስ በገበዮች፣ በመንግሥትና በዓለምአቀፉ ገንዘብ ድርጅቶች ሚና ላይ የተሃድሶን አስፈላጊነት ሃሣብ አጠናክሯል። በነባሩና አሁንም ባለው የዓለም ኤኮኖሚ ስርዓት ላይ ብዙም ዓመኔታ የለም። ጥሪው ስርዓቱ በአዲስ መልክ መቀናጀት ይኖርበታል የሚል ነው። ይህ በተለይ ቻይናና ሕንድን ከመሳሰሉት በተፋጠነ ዕድገት ከሚገኙ አገሮች አኳያ ጠንከር ብሎ ይሰነዘራል። ቻይና ለምሳሌ በዓለም የምንዛሪ ድርጅት ውስጥ የታዳጊ አገሮች የድምጽ ድርሻ ከፍ እንዲልና የሃብታም መንግሥታት ፍጹም የበላይነት ያለፈ ታሪክ እንዲሆን ትሻለች። ሆኖም ይህን መሰሉ ሂደት በቡድን-ሃያ ጉባዔ ሂደት ተገቢውን ክብደት ማግኘቱ ቢቀር በወቅቱ ያጠያይቃል።

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ አፍሪቃንም ክፉኛ እየመታ በመሄድ ላይ ነው። የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ፍሰት ማቆልቆል፣ የልማት ዕርዳታ መገደብና የጥሬ ዕቃ ዋጋ መቀነስ፤ ሌሎች ምክንያቶችም ታክለውበት ለዕድገት መሰናክል ሆነዋል። በነዳጅ ዘይት ዋጋ መጨመር ባለፉት ዓመታት ተጠቃሚ ሆነው የነበሩት አንጎላንና ናይጄሪያን የመሳሰሉ በዚህ ጸጋ የታደሉ አገሮች ዕድገት በሰፊው ነው ያቆለቆለው። በዚህ ዓመት ጨርሶ ዕድገት የሚባል ነገር ላይኖርም እንደሚችልምመነገሩ አልቀረም። በዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎም በውጭ መዋዕለ-ነዋይ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ከአርባ የሚበልጡ የማዕድን ፕሮዤዎች ተዘግተዋል። ሌሎች የአፍሪቃ አገሮችም ከልማት ዕርዳታው ማቆልቆል ባሻገር በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻቸው ወገን ለመደገፍ የሚልኩት ገንዘብ በፊናንሱ ቀውስ ሳቢያ በሰፊው በመቀነሱ እጥፍ ድርብ ፈተና ተደቅኖባቸው ነው የሚገኙት።

በርካታ የአፍሪቃ አገሮች ያለፈትን ዓመታት ተከታታይ የኤኮኖሚ ዕድገት በማሣየት ነበር ያሳለፉት። በአማካይ ከአምሥት እስከ ስድሥት በመቶ ዕድገት ሲያስመዘግቡ ቆይተዋል። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ድርጅት IMF እንደሚገምተው ወደ አፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የዘለቀው የውጭ መዋዕለ-ነዋይና ብድር ከ 2000 ዓ.ም. ወዲህ በአምሥት ዕጅ በመጨመር ወደ 53 ሚሊያርድ ዶላር ከፍ ለማለት የበቃ ነው። ይህም ሆኖ ግን ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ የተፈጥሮ ሃብት ያላቸውንም ሆነ ሌሎቹን አገሮች እኩል ችግር ላይ እንደሚጥል ነበር የአፍሪቃ ልማት ባንክ ፕሬዚደንት ዶናልድ ካቤሩካ በቅርቡ ያስጠነቀቁት።

“የፊናንሱንና የኤኮኖሚውን ቀውስ ለያይተን ማየት ይኖርብናል። እስካሁን በፊናንሱ ቀውስ የተነካ አንድም የአፍሪቃ ባንክ የለም። በኤኮኖሚው ላይ ግን እርግጥ ተጽዕኖ አለ። በመሆኑም በያዝነው 2009 ዓ.ም. በአማካይ ከ 4 እስከ 4,5 በመቶ ዕድገት ነው የምንጠብቀው። ከዚህ በላይ ዕድገት አይኖርም፤ እንዲያውም ዝቅ ሊል ይችላል”

ካቤሩካ ከዚሁ ሃቅ በመነሣት አፍሪቃ ውስጥ የራስን መዋዕለ-ነዋይ ማንቀሳቀሱ እንዲጠናከር ነው የሚያሳስቡት። የአፍሪቃ የልማት ባንክ የክፍለ-ዓለሚቱ የካፒታል ክምችት በጠቅላላው 400 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ እንደሚጠጋ ይገምታል። እርግጥ ይህ ሃሣብ በአጭርና በአማካይ ጊዜ ችግሩ በሚጠይቀው መጠን ገቢር ሊሆን ይችላል ማለቱ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህም የፊናንስ ቀውሱ ተጽዕኖ ተጠናክሮ መቀጠል በታዳጊ አገሮች ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት እጅግ የሚያከብድ ነው የሚሆነው። ችግሩ ባለበት ከቀጠለ እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ ድህነትን በከፊል ለመቀነስ የተያዘውን የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ዕቅድ ከንቱ ተሥፋ እንደሚያደርገው አንድና ሁለት የለውም።

ለነገሩ በጥቅሉ ድህነትን የመታገሉ ጥረት በዓለምአቀፍ ደረጃ ዕርምጃ ታይቶበታል። ግን በአፍሪቃ ፈጣን ከሆነው የሕዝብ ቁጥር መናር ጋር ተያይዞ በመቶ ሲሰላ መጠኑ ከነበረበት ፈቀቅ አላለም። የተባበሩት መንግሥታት የልማት ዕቅድ ባለሥልጣን አድ ሜልከርት እንዳስረዱት ድርሻው አሁንም 50 ከመቶ ገደማ የሚጠጋ ነው።

“እዚህ ላይ በእርግጥ የችግሩን አሳሳቢነት መቀበልና መፍትሄ ለማግኘት አጥብቀን መሥራት ይኖርብናል። በፊናንሱ ቀውስ ቀደም ካሉት ዓመታት ይበልጥ የበለጠ ሕዝብ ነው ወደ ድህነት የሚገፋው። ሂደቱን መቀየር ይኖርብናል ማለት ነው። ከዚህ ሌላ አማራጭ የለም”

እንግዲህ ረሃብና ድህነትን በመታገሉ ረገድ በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉት መንግሥታት የሚጠበቀው ብዙ ነው። ሃሣቡም ሆነ ጥሪው እርግጥ አዲስ አይደለም። ይሁንና የወቅቱ የፊናንስ ቀውስ ያስከተለው መዘዝ ችግሩን ይበልጥ ወቅታዊ ያደርገዋል። የበለጸገው ዓለም ባንኮችን ከክስረት ለማዳን በብዙ ሚሊያርድ የሚቆጠር ገንዘብ አፍስሷል። በሌላ በኩል የልማት ዕርዳታው እያቆለቆለ ሲሄድ ነው የሚታየው። አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት ከዚህ ገንዘብ ጥቂቱ እንኳ ድህነትን ለመታገል በሥራ ላይ ቢውል በዓለም ላይ አንድም ረሃብተኛ ባልተገኘ ነበር። ግን ይህ አልሆነም፤ ብርቱ የሞራል ጥያቄን የሚያስነሣ ነው። የጀርመኗ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ሃይደማሪ-ቪቾሬክ-ሶይል እንዳሉት ለነገሩም ከበለጸገው ዓለም አኳያ አቅሙ ጠፍቶ አይደለም።

“የፊናንሱን ስርዓት ከውድቀት ለማዳን ሶሥትና አራት ሚሊያርድ ዶላር ማንቀሳቀስ የሚቻል ከሆነ በጣም ባነሰ ገንዘብ ዓለምን ከረሃብና ከድሀነት ማትረፉ የሚያዳግት መሆን የለበትም”

በነገው የለንደን ጉባዔ ምናልባት የፊናንሱን ገበያ በማረጋጋት፣ የተሻለ ቁጥጥርን በማስፈንና ስርዓቱን በመጠጋገኑ ላይ ያለሙ አንዳንድ ዕርምጃዎች ሊወሰዱ ይችሉ ይሆናል። በዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ስርዓት ላይ መሠረታዊ ለውጥ እንዲሰፍንና ዘላቂ መፍትሄ እንዲገኝ ጥርጊያ የሚከፍት ጭብጥ ውሣኔን መጠበቁ ግን እስካሁን ከታየው ሂደት አንጻር የሚያዳግት ነው የሚሆነው።

መሥፍን መኮንን, DW