የፈረንሳይ እና የአፍሪቃ ጉባዔ | አፍሪቃ | DW | 14.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የፈረንሳይ እና የአፍሪቃ ጉባዔ

27ኛው የአፍሪቃ እና የፈረንሳይ ጉባዔ ዛሬ በማሊ መዲና ባማኮ ተጠናቀቀ። እጎአ ከ1973 ዓም ወዲህ በየሁለት ዓመቱ የሚደረገው የዘንድሮው ጉባዔ «ሰላም እና ፀጥታ» በሚል ርዕስ ስር  ነበር የተካሄደው።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:36

የፈረንሳይ እና አፍሪቃውያት ሃገራት ምክክር

 
በዚሁ ጉባዔ ላይ ከ30 የሚበልጡ አፍሪቃውያን መንግሥታት መሪዎች ከፈረንሳይ ፕሬዚደንት ጋር ከፀጥታው ጎን በበርካታ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ምክክር አድርገዋል። በጠቅላላ ወደ 3,000 ተሳታፊዎች የተካፈሉበት የዘንድሮው የአፍሪቃ እና የፈረንሳይ ጉባዔ የመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው የፊታችን ሚያዝያ ለሚያበቃው እና ለሁለተኛ ጊዜ ለማይወዳደሩት የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ኦሎንድ የመጨረሻቸው ነበር።  የፍራንስዋ ኦሎንድ መንግሥት የተከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ 27ኛው የአፍሪቃ እና የፈረንሳይ ጉባዔ በተካሄደባት ማሊ ውስጥ ወሳኝ ሚና ተጫውቶዋል። በስልጣን ዘመናቸው ከአፍሪቃ ጋር ስለነበረው ግንኙነት መለስ ብለው እንዲመለከቱ ጉባዔው መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ያመለከቱት ፈረንሳዊው ርዕሰ ብሔር ኦሎንድ የአፍሪቃ ፖሊሲያቸው በፖለቲካ ሕይወታቸው ትልቅ ትርጓሜ መያዙን ገልጸዋል። « እጎአ ጥር፣ 2013 ዓም  ፈረንሳይ በሰሜናዊ ማሊ ይንቀሳቀሱ በነበሩ ፅንፈኞቹ ሙስሊሞች አንፃር የሚታገል «ሰርቫል» የሚል መጠሪያ የያዘ አንድ ወታደራዊ ግብር ኃይል በማሊ አሰማራች።

 ከዚያም በመፈንቅለ መንግሥት ሰበብ በእርስ በርስ ጦርነት አፋፍ ላይ ትገኝ በነበረችው የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ እጎአ ታህሳስ 2013 ሳንጋሪ የተባለውን የጦር ቡድን ማሰማራቷ  ይታወሳል። አፍሪቃን በተመለከተ ጎርጎሪዮሳዊው 2013 ዓም ለኦሎንድ ወሳኝ መሆኑን የጋቦ ተወላጅ የሆኑት የፖለቲካ ተንታኝ ጆናታን ንዱቱሜ አረጋግጠዋል።
« ፍሯንስዋ ኦሎንድ ማሊን ፅንፈኞቹ ሙስሊሞች ከደቀኑት አደጋ ብቻ ሳይሆን የተከላከሉት፣ ሃገሪቱ እንዳትፈራርስም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክም  የሙስሊሞቹ የሴሌካ  ዓማፅያን፣  በአንጻራቸው የሚዋጉት ፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች እና ሌሎች ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ቡድኖች በሰፊው ይንቀሳቀሱ በነበረበት ጊዜ ፣ ፈረንሳይ ወታደሮቿን በማሰማራት ሃገሪቱ  ከሞላ ጎደል እንድትረጋጋ አስተዋፅዖ  አድርገዋል። »
መንበሩን ፓሪስ ያደረገው የፈረንሳይ ብሔራዊ የፖለቲካ ጥናት ምርምር ተቋም ተንታኝ ሮሎን ማርሻልን የመሳሰሉ  ግን ይህንኑ የጆናታን ንዱቱሜ አስተያየት  አይጋሩትም። ማርሻል የፈረንሳይ ፖሊሲ  ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን በተለይ የተጠቀመበት አሰራር አሳሳቢ ብለውታል።
« የፈረንሳይ ፖለቲካ ለፀረ ሽብርተኝነት ትግሉ ፣ በተለይ በወታደራዊው ጣልቃ ገብነት ርምጃ ላይ ነበር ያተኮረው። ይህ ፖሊሲው ትክክለኛ ስለመሆን አለመሆኑ ባሁኑ ጊዜ ማንም የሚጠይቅ የለም። ግን፣ ማሊን ስንመለከት ይህ ፖሊሲ አለመስራቱን እናያለን። »
የማሊ መንግሥት መልካም አስተዳደር እንደማይከተል እና የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ኢብራሂም ቡባከር ኬይታም በሙስና ቅሌት እንደተዘፈቁ ማርሻል አክለው አመልክተዋል።
 
ጀርመናውያን የፖለቲካ ተንታኞችም የፈረንሳይን የአፍሪቃ ፖሊስ በጥርጣሬ ዓይን ነው የተመለከቱት። በበርሊን ለሚገኘው የጀርመናውያን የውጭ ፖለቲካ ማህበረሰብ በፈረንሳይ የአፍሪቃ ፖሊሲ ላይ ጥናት የሚያካሂዱት ስቴፋን ብሩነም ቢሆኑ የማሊ ፖለቲካዊ ችግር ገና መፍትሔ አላገኘም ይላሉ።
« እርግጥ ነው ፈረንሳውያኑ በአንድ በኩል ከቻድ ልዩ የጦር ኃይላት  ጋር  በማሊ ላጭር ጊዜ  ባደረጉት ትብብር ፍቱን ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። በሌላ በኩል ግን፣ ማሊን በዘላቂነት የሚጠቅም፣ ማለትም፣  ፖለቲካዋን እና  ባህሏ ያገናዘበ ስልት ሳይከተሉ ነው የቀሩት። »


ፍራንስዋ ኦሎንድ ስልጣናቸውን  በተረከቡበት ጊዜ በቅኝ አገዛዙ ዘመን በፈረንሳይ እና በአፍሪቃ በነበሩት ቅኝ  ግዛቶችዋ መካከል የነበረውን ዓይነት ግንኙነት እንደሚያበቁ ስርዓተ ዴሞክራሲን እንደሚያበረታቱ ቃል ገብተው ነበር። ኦሎንድ ይህንኑ የገቡትን ቃል መጠበቃቸውን  የፖለቲካ ተንታኙ ጆናታን ንዱቱሜ ዛሬ ከአምስት ዓመት በኋላ   አጠያ ይቀዋል።
« በብዙዎቹ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሃገራት ዜጎች አስተሳሰብ መሰረት፣ ፈረንሳይ አምባገነን በሚባሉ አፍeሪቃውያት ሃገራት አንፃር፣ በዲፕሎማቲካዊውም ሆነ በፖለቲካዊው ደረጃ ፣ አንድም ርምጃ አልወሰደችም። ይህም ፣ ፍሯንስዋ ኦሎንድ በሃገራቸው እና በአፍሪቃ መካከል ያለውን፣ ከቅኝ  አገዛዝ ዘመን ወዲህ የቀጠለውን ዓይነቱን ግንኙነት ለማብቃት የገቡትን ቃል አለመጠበቃቸውን ነው ያመላከተው።  »   
ብሩነም ቢሆኑ የፈረንሳይን የአፍሪቃ ፖሊሲ ተፃራሪ ሆኖ ነው  ያገኙት። በቻድ ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዚደንት ኢድሪስ ዴቢ ባለፈው ነሀሴ ድጋሚ መመረጣቸውን በመቃወም አደባባይ በወጡ የቻድ ዜጎች አንፃር የኃይል ርምጃ በወሰዱ ጊዜ  ከፈረንሳይ አንድም ጠንካራ አስተያየት አልተሰማም። ፈረንሳይ በናይጀሪያ ዓማፂ ቡድን ቦኮ ሃራም እና በምዕራብ አፍሪቃ በሚንቀሳቀሱት ፅንፈኞች አንፃር ለተጀመረው ትግል በቻድ ጦር ላይ በጣም ጥገኛ ናት። በቀድሞዋ ቅኝ ግዛት ጋቦንም እጎአ በ2016 ዓም ፕሬዚደንት አሊ ቦንጎ ኦንዲምባ ድጋሚ በተመረጡበት እና የተቃዋሚው ወገንም ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ወቀሳ ባቀረበበትም ጊዜ ቢሆን ፈረንሳይ ጉዳዩን እንዳላየ በማየት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች። ምክንያቱም፣ ይላሉ ብሩነ፣
« ጉዳዩ በቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ሻርል ደ ጎል ዘመነ ስልጣን ጀምሮ ካለው የሃገሪቱ ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው። ይኸው ፖለቲካ ፈረንሳይ በማንም ላይ ጥገኛ ያልሆነች የኑክልየር ኃያል መንግሥት ናት የሚሰኘውን ሀሳብ ያጎላ ነው። ይህንንም ለማስቀጠል፣ ማዕድኑን ዩሬንየምን ጨምሮ ሌሎች ጥሬ አላባም ያስፈልጓታል።  ስለዚህ፣   ዩሬንየም ካላቸው ሃገራት ጋር መልካሙን ግንኙነት መፍጠር ይገባል ባይ ናት። »

አርያም ተክሌ/ኤሪክ ቶፖና

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች