የፆታ ዉዝግብ በዛምቢያ | የጋዜጦች አምድ | DW | 06.01.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የፆታ ዉዝግብ በዛምቢያ

ዛምቢያ ዉስጥ በወንዶችና ሴቶች መካከል ሊኖር ስለሚገባዉ የፆታ እኩልነት የሚደረገዉ ፍልሚያ በያቅጣጫዉ እየተካሄደዉ ይገኛል። ዛሬ ጊዜ ዛምቢያ ዉስጥ ለመኖርና ተገቢዉን ፍትህ ለማግኘት ወንድ ሆኖ መፈጠር ሳይሻል አይቀርም የሚል ቅሬታ እየተሰማ ነዉ።

የዚህ ቅሬታ መነሻ የሆነዉ የአገሪቱ ፍርድ ቤት ክሪስታል ዴን በተባለችዉ ሴት ላይ በቅርቡ የበየነዉ የእድሜ ልክ እስራት ቅጣት ነዉ።
በአገሪቱ ታዋቂ ከሆነዉ የእግር ኳስ ተጫዋች ባሏ ጋር በነበራት የአምስት አመት የጋብቻ ህይወት ዴን በትዳር አጋሯ ይደርስባት በነበረዉ በደል ስትሰቃይ እንደኖረች ተገልጿል።
ባለቤቷ በየጊዜዉ ቤት ዉስጥም ሆነ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ይደበድባት ነበር።
ራሷን ለመግደል ሞክራ ሳይሳካላት ቢቀርም በመጨረሻ በተለመደዉ አለመግባባታቸዉ ባለቤቷን እ.ኤ.አ. 1999 አ.ም. ላይ ገደለችዉ።
ይህን ተከትሎ በተመሰረተባት ክስም ዳኛ የእድሜ ልክ እስራት ፈረደባት።
የሴቶች መብት ተሟጋቾች ወዲያዉኑ ይህ ዉሳኔ እንደተሰማ የዴንን ድርጊት ቢኮንኑም ብያኔዉ በአግባቡ ፆታ ሳይለይ በዛምቢያ በተግባር ላይ ስለማይዉል ተቃዉሞ ጀመሩ።
በደቡባዊ የአፍሪካ አገራት ሚስቶቻቸዉን የገደሉ ወንዶች ክሳቸዉ የነፍስ ማጥፋት ከመባል የዘለለ ከባድ የግድያ ወንጀል ተብሎ አይወሰድም።
በመሆኑም አብዛኛዎቹ ነፍሰ ገዳይ ወንዶች ጉዳያቸዉ በይደር እንዲቆይ ይበየናል ወይም ግፋ ቢል የሶስት አመት እስር ይወሰንባቸዋል።
በዚያ አካባቢ ሚስቱን በመግደሉ የእድሜ ልክ እስራት የተበየነበት ወንድ የለም ይላሉ የሴቶች መብት ተሟጋቾቹ።
የደቡብ አፍሪካ አገራት የህግ ባለሙያ ሴቶች ቅንጅት የዛምቢያዉ ፅህፈት ቤት አስተባባሪ ማርቲን ቹሉ የሚሉት ይህን ሚዛን የለሽ የፍትህ ሁኔታ የማስተካከያ ጊዜዉ አሁን ነዉ።
ቹሉ ህጉ በሁሉም ላይ በእኩል በተግባር ሲዉል የምናይበት ጊዜ አሁን መሆን አለበት ይላሉ።
የቅንጅቱ ልሳን በሆነዉ ፍትህ ለሁሉም በተሰኘዉ የዜና መፅሄታቸዉ የቅርብ ጊዜ ዕትም ላይ የህግ ባለሙያዎቹ ህብረት ሴቶችና ወንዶች በእኩል ያልተዳኙባቸዉን በርካታ ህግ ነክ ጉዳዮችን ለማሳያ አዉጥተዋል።
ቴዲ ካሱባ የተባለ ሰዉ ከ10 አመት በፊት ከስራ የምትመለስ ሚስቱን በሚያደርሳት መኪና ላይ ተኩስ በመክፈት ሚስቱን ገደለ።
ፍርድ ቤት ሲቀርብ ካሱባ ድርጊቱን የፈፀመዉ በወቅቱ ግራ ተጋብቶ እንደነበር በመናገሩ ፍርድ ቤቱ ወንጀሉ የሚያሳየዉ ማንኛዉም ምክኒያታዊ ወንድ ሊያደርገዉ የሚችል ነዉ በማለት በነፍስ ማጥፋት ቀጥቶት ፋይሉን በይደር ዘጋ።
በሌላ ጊዜ ደግሞ ከስድስት አመት መሆኑ ነዉ በፊት ኖሳል ናታ የተባለችዉን ሴት ባለቤቷ ደብድቦ ይገድላታል። ሆኖም ፍርድ ቤት 18 ወራት ብቻ ካሰረዉ በኋላ በድጋሚ ሲያገባ እንዳሁኑ አስቸጋሪ ሰዉ እንዳይሆን መክሩን ሰጥቶ ከእስር ፈቶታል።
ይህ ዉሳኔ በተለይ እ.ኤ.አ. 1984 ዓ.ም. እሷንና ልጆቿን ለመግደል ሲያስፈራራት የፈላ ዘይት ላዩ ላይ ደፍታ ባሏን ከገደለችዉ ኤስተር ሚዊምቤ ጉዳይ ጋር በእጅጉ ይቃረናል።
ኤስተር ያደረገችዉ ያልሞት ባይ ተጋዳይ ድርጊት መሆኑ በግልፅ እየታየና አቤቱታዋን ለፍርድ ቤቱ አቅርባ እያለ ይግባኙን ወደጎን በመተዉ የሞት ቅጣት ተፈረደባት።
ኤስተር እንደ እድል ሆኖ ከሰባት አመታት የእስር ዘመን በኋላ በስልጣን ላይ በነበሩት በቀድሞዉ የዛምቢያ ፕሬዝዳንት ኬኔት ካዉንዳ ምህረት ተደርጎላታል።
የህግ ባለሙያዋ ቹሉ የሚሉት የዛምቢያ ፍርድ ቤት በሴቶች ላይ በቤት ዉስጥ የሚፈፀሙ ጥቃቶችንና ጥቃቱ የደረሰባቸዉን ሴቶች የስነልቦና ሁኔታ የሚያገናዝብበት አቅም የለዉም።
ፍርድ ቤቶቹ ምግብ ለምን አላዘጋጀሽም ከሚለዉ ተራ የግጭት መንስኤ አንስቶ እስከ ቀዝቃዛ ምግብ ለምን አቀረብሽ ባሉት ተልካሻ ምክንያቶች በሴቶች ላይ የሚፈፀሙትን ግድያዎች ወደ ነፍስ ማጥፋት ዝቅ በማድረግ ነፍሰ ገዳዩን ባል የ12 ወራት የእስር ቅጣት ብቻ ይበይኑበታል።
ይህ አይነቱ የፍርድ ቤቶቹ የብያኔ ልማድ ኤስተር ለፍርድ በቀረበችበት ጊዜ በግልፅ ታይቷል ይላሉ ቹሉ።
ባሏ ከፍተኛ የደህነት ሰራተኛ ከሚባሉት መካከል ነበር። ልክ ሌሎች ሰዎችን ለምርመራ በሚያሰቃይበት ስልት ነበር ኤስተርንም የሚያሰቃያት።
ኤስተር በተደጋጋሚ ለፓሊስ እንዴት እንደሚያሰቃያት አመልክታ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤት በቀረበችበት ወቅት ግን ፓሊስ ጋ የነበረዉ መረጃ አስቀድሞ እንዲሰወር በመደረጉ በፍርድ ቤቱ ፊት አረመኔ ነፍሰ ገዳይ ተደርጋ እንደታየች ትናገራለች።
ከዚህ በመነሳትም የህግ ባለሙያዎቹና የሴቶች መብት ተሟጋቾቹ አንድ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ዳኞቹ ወንዶች ናቸዉ በመሆኑም የወንዶች ተረት የሆነዉን ከማንፀባረቅ ወደኋላ አይሉም።
እናም ዛምቢያ ዉስጥ ፍት ለማግኘት የግድ ወንድ ሆኖ መፈጠር ሳያስፈልግ አይቀርም።
በእነሱ እምነት ይህ ሴቶችን እንደሸቀጥ የሚያስቆጥረዉ የባህል ጉዳይ ነዉ ያዉም ጎጂ ባህል ያስከተለዉ መዘዝ። በትዳር ዉስጥ ባለጥቃት ጉዳይ ዙሪያ ማንም ምንም ለማለት አይፈልግም።
የዴንን ጉዳይ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ትዳሯ ሰላም እንዳልነበረዉ ቢቀበልም ባሏ ስላደረሰባት ጥቃት ስምንት ጊዜ ያቀረበችዉን አቤቱታ ተመልክቶ የእሷን እንክብካቤ ለሚፈልጉት ህፃናት ልጆቿ ሲል ዉሳኔዉን ለማስተካከል ፈቃደኛ አልሆነም።
የህግ ባለሙያዎቹ የሚሉት ፍርድ ቤቱ ነገሮችን የሚያየዉ ከምክንያታዊ ወንድ አንፃር እንጂ ድብደባና ስቃይ ከተፈፀመባት ተጠቂ ሴት አንፃር አይደለም።
አሁንም ባለፈዉ የፈረንጆቹ አመት በእንጥልጥል ያለ የሁለት ባሎቻቸዉን የገደሉ ሴቶች ጉዳይ በፍርድ ቤት ተይዟል።
በዚህ የመብት ትግል መሃልም የክሪስታል ዴን የእድሜ ልክ እስራት ወደ 15 አመት የተለወጠላት ሲሆን ጨርሶም ነፃ ልትወጣ ትችል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ለዚህም የመጨረሻ ተስፋዋ የአገሪቱ ህገመንግስት አንቀፅ 59 ሲሆን ይህም በአገሪቱ መሪ ምህረት ሊደረግላት ወይም የእስራት ዘመኗን እንዲያጥርላት ማድረግ የሚያስችል የህግ ክፍል ነዉ።
ይህን አስመልክቶም የህግ ባለሙያዎቹ ቅንጅት በዴን ብያኔ የተቃዉሞ ፊርማ በማሰባሰብ ላይ ሲሆን ፕሬዝዳንቱም ጠይቆ ምላሻቸዉን እየጠበቀ መሆኑ ታዉቋል።