የፅንፈኝነት ስጋት በሴኔጋል | አፍሪቃ | DW | 06.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የፅንፈኝነት ስጋት በሴኔጋል

የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነችው ሴኔጋል ሕዝብዋ በሰላም እና ተቻችሎ የሚኖርባት ሀገር ናት።ይሁን እንጂ፣ ባለፈው አውሮጳዊ ዓመት መጨረሻ ገደማ በማሊና በአዲሱ ዓመት ጥር አጋማሽ በቡርኪና ፋሶ መዲናዎች ባማኮ እና ዋጋዱጉ ከተጣሉት የአሸባሪዎች ጥቃቶች ወዲህ ፅንፈኞች በዚችው ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር ስር መስደድ እንዳይጀምሩ መስጋቷ አልቀረም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 06:39
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
06:39 ደቂቃ

ሴኔጋል

ይህን ተከትሎም የሴኔጋል ፀጥታ ኃይላት፣ ሀገራቸውን አስግቷል ባሉት የሽብርተኝነትን ተግባር አንፃር ባነቃቁት ጥንቃቄ፣ ፖሊስ ባለፈው የሳምንት መጨረሻ ብቻ ከ900 የሚበልጡ ሰዎችን ማንነት አጣርቷል።. በመላ ምዕራብ አፍሪቃ የፀጥታ ጥበቃው ደንብ መጠናክርን ተከትሎ፣ የሰላም እና የመቻቻል ተምሳሌት በመሆን የምትታወቀው የሴኔጋል ፖሊስም በፀረ ሽብሩ ትግልም ላይ ሊሰማሩ የሚችሎ ከ1000 የሚበልጡ አዳዲስ ሰራተኞችን ማሰልጠን ጀምራለች።

በሴኔጋላዊቷ የሳን ልዊ ከተማ የሚገኘው የጋስቶ ቤርዤ ዩኒቨርሲቲ መምህር ቡካሪ ሳምቤ ከብዙ ጊዜ አንስትው ሀገራቸው ሴኔጋልን ባካባቢው ካሉት ሀገራት ሁሉ የተለየች አድርገው ተመልክተዋት እንደነበር ገልጸዋል።

« ሴኔጋል ያለመረጋጋት በሰፈነበት በምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ ባለፉት ዓመታት የመረጋጋት ደሴት ሆና ቆይታለች። ለዚህም ሁኔታ ሰላምን ማራመድ የተሳካላቸው የሱፊ እስልምና መስመር ተከታዮች የሆኑት መንፈሳውያን መሪዎች ተፅዕኖ ሰፊ አስተዋፅዖ አበርክቶዋል። ይሁን እንጂ፣ ከጥቂት ጊዜ በፊት በዋጋዱጉ የተጣለው ጥቃት ሴኔጋል በምዕራብ አፍሪቃ እንደተምሳሌት ትታይበት የነበረውን ጊዜ ያበቃው ይመስለኛል።»

ሴኔጋል ውስጥ እጎአ ከ1950ኛዎቹ ዓመታት ወዲህ ፅንፈኛ ቡድኖች አስተሳሰባቸውን ለማስፋፋት መሞከራቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። እንዲያም ሆኖ ግ፣ በሳውዲ ዐረቢያ ተፅዕኖ ያረፈባቸው የዋሃቢ እና የሳላፊስት ቡድኖች ከሴኔጋል የሱፊ መስመር ተከታዮች ጋር ጎን ለጎን በሰላም ይኖሩ ነበር፣ አሁን ግን የፅንፈኝነት የሚስፋፋበት ስጋት መጠናከሩ ነው የሚሰማው።

በሴኔጋል ካለፉት ጥቂት ዓመታt ወዲህ በድሆች eና በሀብታሞች መካከል የሚታየው ልዩነት እየሰፋ መሄዱን መታዘባቸውን በመዲናይቱ ዳካር የሚገኘው የጀርመናውያኑ የኮንራድ አድናወር የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ኡት ጊርቺንስኪ ቦካንዴ አስታውቀዋል። የትምህርቱ ስርዓትም እየተበላሸ መጥቶዋል። ብዙ የሴኔጋል ወጣቶችም ወደ ቆርዓን ትምህርት ቤቶች ወይም ዐረባውያን ዩኒቨርሲቲዎች መሄዱን ሲመርጡ ታይተዋል። ይኸው ምርጫቸውም የፈረንሳይኛ ቋንቋ እውቀት አዘውትሮ በሚጠየቅበት የስራው ዓለም ውስጥ የመቀላቀል እድላቸውን ዝቅተኛ አድርጎታል።

«ይኸው ሁኔታም በድሆቹ ዘንድ ብቻ ሳይሆን፣ በተማረው ቡድንም ዘንድ ቀሬታ ፈጥሮዋል። በዚሁ አደገኛ ሁኔታ የተነሳም የሀገሪቱ ባህላዊ የሱፊ እስልምና መስመርን ለመከተል የማይፈልጉት ወጣቶች ቁጥር ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ እየጨመረ በመምጣቱ፣ እነዚህ ወጣቶች ቀላል የፅንፈኛ ድርጅቶች ተፅዕኖ ሰለባ የሚሆኑበት ስጋት ተደቅኖባቸዋል።»

ይኸው ስጋት በተለይ በዳካር መሀይምነት፣ የጎርፍ አደጋ፣ የሕዝብ ቁጥር ፈጥኖ መጨመር ሰበብ ግዙፍ ችግር ባለበት የፒክኔ ሰፈር ጎልቶ እንደሚታይ የራድዮ ኦክሲዠን ኃላፊ ዳውድ ጌይ አመልክቶዋል። በዚሁ ከመዲናይቱ ወጣ ብሎ በሚገኘው ሰፈር ውስጥ ከሁለት ሚልዮን የሚበልጥ ሕዝብ፣ በብዛትም ወጣቶች የሚኖሩ ሲሆን፣ እንደ ጌይ አባባል፣ የነዚሁ ወጣቶች ሀይማኖታዊ ፅንፈኝነት ዝንባሌ ከፍ እያለ መጥቶዋል።

«ሴኔጋል ውስጥ አሁንም በሰፊው የተስፋፋው መቻቻልን የሚያስቀድመው የሱፊ እስልምና መስመር ነው። ይሁን እንጂ፣ በፒክኔ ሰፈር የሚገኙት ወጣቶች የሳላፊስቶቹን አስተምህሮ ለመቀበል የሚያሳዩት ዝግጁነት ከፍ እያለ መምጣቱን ተገንዝበናል። ይህ፣ በርግጥ፣ ወጣቶቹን አክራሪ አድርጓቸዋል እያልኩ አይደለም፣ ግን፣ በዳካር መጋቢያዎች እና በመዲናይቱ ያሉት ወጣቶቹ በአስተምህሮቱ እየተሳቡ መሆናቸውን ነው መግለጽ የፈለግሁት። ይህንኑ መዘዙ አሳሳቢ ሊሆን ይችላል የሚሉትን ስጋት ለማስወገድ ይቻልም ዘንድ ጌይበ«ራድዮ ኦክሲዠን»

በሚያስተላልፉዋቸው ዝግጅቶች የሴኔጋል መንግሥት በፒክኔ ሰፈር የሚገኙትን ትምህርት ቤቶች እና የትምህርቱን ስርዓት በጉልህ እንዲያሻሽል ግፊት ለማሳረፍ ጥረት ጀምረዋል። በሴኔጋል በእምነቶች መካከል አለመቻቻል ባለመኖሩ ሽብርተኝነት እንደማያስፈራቸው የሚናገሩት የ«ራድዮ ኦክሲዘን» ኃላፊ ዳውድ ጌይ ሙስሊም ፅንፈኝነትን ለመታገል ወጣቱን በትምህርት ማነጽ ጥሩ መሳሪያ መሆኑን ያምናሉ።

«ወጣቶቻችን የተረጋጉ እና ከኃይል ተግባር የራቁ ናቸው፣ ለዚህም እስካሁን ሴኔጋል ውስጥ ጥቃት አለመጣሉ ሁነኛ ማስረጃ ነው።»

በጌይ አንፃር የፖለቲካ ተንታኙ ባካሪ ሳምቤ ሴኔጋል ውስጥ ሽብርተኝነትን ለመታገል ባስቸኳይ ርምጃ መወሰድ ይገባዋል ባይ ናቸው።

«በአሁኑ ጊዜ ፅንፈኝነትን ለማስወገድ የማከላከል ርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎንም፣ የሲቭሉን ማህበረ ሰብ ጥቅም ማስጠበቅ የግድ ይላል። እንደኔ አስተሳሰብ፣ ሽብርተኝነት በተለይ፣ በአፍሪቃ ለሚያንሰራራበት ድርጊት እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት መካከል ዋነኛ የሚባሉትን ሁለቱን፣ ማለትም፣ የተበላሸ የመንግሥት አስተዳደርን እና ማህበራዊ እኩልነት የተጓደለበትን አሰራር ማስወገድም ተገቢ ይሆናል።»

ክሪስቲና ሀሪየሷ/አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic