1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀጥታ ችግር የሠቆጣ የምርምር ተቋም ላይ እክል ፈጥሯል

ዓለምነው መኮንን
ማክሰኞ፣ ኅዳር 17 2017

ቀደም ሲል በሰሜኑ ጦርነት አሁን ደግሞ አማራ ክልል ውስጥ በቀጠለው ጦርነት እና የሰላም እጦት የተነሳ የሠቆጣ ማዕከል የግብርና የምርምር ሥራዎችን በተሟላ መልኩ መስራት እንዳልቻለ ተገለጠ ። ዕከሉ ምርምሮችን በማከናወን ለአርሶ አደሮች ድጋፍ ያደርግ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/4nRX0
አማራ ክልል በጦርነቱ የተነሳ የግብርና ምርምር ማዕከላትም እክል እንደገጠማቸው ተገልጧል
አማራ ክልል በጦርነቱ የተነሳ የግብርና ምርምር ማዕከላትም እክል እንደገጠማቸው ተገልጧልምስል Alemenew Mekonnen/DW

አማራ ክልል የፀጥታ ችግር የግብርና ምርምር ላይ መሰናከል ፈጥሯል

ቀደም ሲል በሰሜኑ ጦርነት አሁን ደግሞ አማራ ክልል ውስጥ በቀጠለው ጦርነት እና የሰላም እጦት የተነሳ የሠቆጣ ማዕከል የግብርና የምርምር ሥራዎችን በተሟላ መልኩ መስራት እንዳልቻለ ተገለጠ ። ጦርነቱ አማራ ክልል እስከተቀሰቀሰበት እስካለፈው ዓመት ድረስ ማዕከሉ ምርምሮችን በማከናወን ለአርሶ አደሮች ድጋፍ ያደርግ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል ።  የሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርምር ማዕከል በችግርም ውስጥ ሆኖ የተውስኑ ሥራዎችን ማከናውኑን የማዕከሉ ዳይሬክተር አመልክተዋል ። ዓለምነው መኮንን ተጨማሪ ዘገባ አጠናቅሯል ።

ማዕከሉ ባለፉት 4 ዓመታት  በሰሜኑ ጦርነት የወደሙ  የምርምር እቃዎች ወደነበሩበት ባለመመለሳቸው በማዕከሉ ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሆን የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር አዳነ ባሕሩ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። እንደዳይሬክተሩ አካባቢው ከዚህ በፊት በሕወሓትና በመንግሥት ጦርነት ወቅት፣ የምርምር ቁሳቁሶች ወድመዋል፣ አሁንም ማዕከሉ ያላገገመ በመሆኑ በሥራቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ነው ያስረዱት፡፡

ማዕከሉ በ4 ወረዳዎች የሚያደርጋቸው ምርምሮች የተሟሉ አይደሉም

ከአለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ በአማራ ክልል ከተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ ጋር ተያይዞ በተለይም ማዕከሉ ተንቀሳቀሶ ይሠራባቸው በነበሩ የሰሜን ወሎ ዞን አራት ወረዳዎች እንደልብ ተንቀሳቅሶ ምርምሮችን ማካሄድ እንዳልተቻል ነው ዳይሬክተሩ ያስረዱት፡፡

ምርምሮችን በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳድር ውስጥ የተሻለ የምርምር ሥራ ማከናወን ቢሞክርም  በሰሜን ወሎ ዞን  ላስታ፣ ቡግና፣ ግዳንና ላሊበላ ወረዳዎች ተንቀሳቅሶ የምርምር ስራ መስራት አዳጋች ሆኗል፣ አርሶአደሩን ሰብስቦ ማነጋግር አልተቻለም፣ በዚህም በወረዳዎቹ ይካሄዱ የነበሩ የምርምር ሥራዎች እክል ገጥሟቸዋል ብለዋል፡፡

የሠቆጣ ከተማ ከፊል ገጽታ ። ፎቶ፦ ከማኅደር
የሠቆጣ ከተማ ከፊል ገጽታ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Alemnew Mekonnen/DW

ምንም እንኳ ማዕከሉ ባጋጠሙት ችግሮች የተፈለገውን ያክል ውጤት ማስመዝገብ ባይችልም፣  በችግርም ውስጥ ሆኖ የተወሰኑ የምርምር ሥራዎች እንዲከናወኑ ማድረጉን ዶ/ር አዳነ ተናግረዋል።

የምርምር ማዕከሉ 3 አዳዲስ የቦቆሎ ዝርያዎችን አስመዝግቧል

"... በአጭር የዝናብ ስርጭትና ከፍተኛ ሙቀት ባለበት አካባቢ ላይ የተሻለ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ 3 የቦቆሎ ዝርያዎችን ማስመዝገብ ችለናል” ብለዋል፡፡ ሌሎች ሁለት ዝርያዎችንም ለአገር አቀፍ ዘር አፅዳቂ ኮሚቴ ልከው ውጤት እየተጠበቁ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የላስታ ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይትባረክ መርሻ ማዕከሉ ቀደም ባሉት ጊዜዎች  የምርምር ሥራዎችን  ሲያከናውን እንደቆየ አስታውሰው አሁን በፀጥታ ችግር ምክንያት ተግባሩ የተቀዛቀዘ ቢሆንም ሥራው እንዳይቋረጥ ጥረት እየተደረገ እንደሆን አመልክተዋል፡፡

ወጣት ገበሬ በበሬ ሲያርስ
የምርምር ማዕከላት የግብርና ውጤቶችን ለማጎልበት አስተዋጾአቸው ከፍ ያለ ነውምስል Alemnew Mekonnen/DW

"ተቋሙ ቀደም ሲል አርሶ አደሩን በምርምር ያግዝ ነበር” የላስታ ወረዳ አርሶአደር አቶ ጥላሁን ደባሽ የተባሉ በሰሜን ወሎ ዞን የላስታ ወረዳ አርሶአደር የምርምር ማዕከሉ ለአርሶአደሩ ደጋፍ ሲያደርግ መቆይቱን አመልክተው፣ በፀጥታ ምክንያት አሁን ሥራዎች እንደበፊቱ አይደለም ነው ያሉት፡፡

ምርምር ማዕከሉ የራሱ የሆነ የምርምር ቦታ ገዝቶ ምርምር ሲያካሂድ እንደነበርና አርሶአደሩንም ሲደግፉ እንደነብር አቶ ጥላሁን ተናግረዋል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን ከፀጥታው ጋር ተያይዞ  ሠራተኞቹ ወደ አካባቢው መምጣት ማቆማቸውን አመልክተዋል፡፡

የሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርምር ማዕከል በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስር የሚገኝ ሲሆን፣ ዝናብ አጠር በሆነው በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ይገኛል፣ ማዕከሉ በአፈር ለምነት፣ በአዝርዕት፣ በአበርገሌ የፍየል ዝርያዎች ማሻሻልና በሌሎችም መስኮች ላይ ምርምሮችን የሚያካሂድ ማዕከል ነው።

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ