የፀጥታው ምክር ቤት ዳግም ስለ ኢትዮጵያ | አፍሪቃ | DW | 09.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የፀጥታው ምክር ቤት ዳግም ስለ ኢትዮጵያ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ባባረረቻቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች ጉዳይ ላይ ረቡዕ በአስቸኳይ ተሰብስቧል። ዓለም አቀፍ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለመምከር ሲሰሰበሰብ ሁለተኛው ነው። በስብሰባዎቹ የፀጥታው ምክር ቤት የተከፋፈለ ሐሳብ ተንጸባርቆበታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:18

ለዐሥር ጊዜያት በኢትዮጵያ ጉዳይ ተወያይቷል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በትግራይ ክልል ግጭት ከተቀሰቀሰበት ካለፈው ዐሥራ አንድ ወራት ግድም አንስቶ ለዐሥር ጊዜያት በኢትዮጵያ ጉዳይ ሊወያይ ስብሰባ ተቀምጧል። ስብሰባዎቹ አንዴ በዝግ ሌላ ጊዜ ደግሞ በይፋ ቢሆኑም  ዐሥራ አምስቱ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ ጉዳይ አንድ አቋም መያዝ ግን አልቻሉም።  ከ«ታላቁ የሕዳሴ ግድብ» አንስቶ እስከ ትግራይ ክልል ግጭት ጉዳይ ምክር ቤቱ ተደጋጋሚ ውይይት አድርጓል። አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን በሚመለከት ወደ ምክር ቤቱ ሊሄዱ የማይገባቸውን ጉዳዮች ሊወስድ አይገባም ሲሉ ይሞግታሉ። የፀጥታው ምክር ቤት ስለኢትዮጵያ በተደጋጋሚ መወያየቱን ግን ቀጥሎበታል።

ምናልባትም የኢትዮጵያ ጉዳይ ምክር ቤቱን ከተለመደ አሠራሩ ወጣ ያሉ ክስተቶች እንዲንጸባረቁበትም ሳያደርግ አልቀረም።  ረቡዕ ዕለት የፀጥታው ምክር ቤት፦ «ሠላም እና መረጋጋት በአፍሪቃ» በሚል አጀንዳ ቀርጾ ሲወያይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ዐቢይ  ርእሱ ነበር። ኢትዮጵያ «የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጥስ እና ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት የሚሆኑ ድርጊቶችን ፈጽመው በመገኘታቸው» በሚል ከሀገር ስላባረረቻቸው ሰባት የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች ጉዳይ ምክር ቤቱ በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባው ተነጋግሯል።

ለወትሮው በፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ንግግር በሚደረግበት ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ጣልቃ ገብተው ጥያቄ ሲያቀርቡ ታይተው ዐያውቁም። በዚህ ስብሰባ ወቅት ግን የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ በተመድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጥያቄ ጠይቀዋቸዋል። ኢትዮጵያ የመንግሥታቱን ድርጅት ሠራተኞች ላባረረችበት ክስ ማስረጃ ታቅርብም ብለዋል ዋና ጸሐፊው።

«አንድ ነገር ልጠይቆት እፈልጋለሁ ሚስተር አምባሳደር። ከሀገር ስለ ተባረሩት የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች በኢትዮጵያ መንግሥት ለየትኛውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋም የቀረበ ማንኛውም የተጻፈ ሠነድ ካለ የዚያ ቅጂ እንዲደርሰኝ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ስለእነዚያ ምንም የማውቀው ነገር የለም። ሠነድ ለድርጅቱ ቀርቦ እኔ ጋር ካልደረሰ በድርጅቴ ውስጥ ስለሆነው ነገር ምርመራ ማድረግ ይኖርብኛል፤ እናም ሠነዱ ለእኔም ነገሩን ለማወቅ በጣም ይጠቅመኛል።»

አንቶኒዮ ጉተሬሽ የተመድ ሠራተኞች ገለልተኝነት በተመለከተ ከኢትዮጵያ ቀረበ ስላሉት ቅሬታ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ መረጃውን እንዲልኩላቸው ለሁለት ጊዜያት መናገራቸውን አክለው ገልጠዋል። በዋና ጸሐፊው ለቀረበው ጥያቄ አምባሳደር አጽቀ ሥላሴ መልስ ሲሰጡ የሚያገኙትን «ማንኛውንም ሠነድ» እንደሚያቀርቡላቸው ተናግረዋል።

«ሚስተር ዋና ጸሐፊ በሚገባ ተረድቼዎታለሁ። ለሕዝባችን እና ለመንግሥቴ ጭምር የሰጡትን ድጋፍ በሚገባ እረዳለሁ እገነዘባለሁኝ። ልብዎ የት ጋር እንዳለም ዕናውቃለን። ጉዳያችንን በቀናነት ለመመልከት ጥረዋል። ያንንም እጅግ በጣም እናከብራለን። ጥያቄዎን በተመለከተ ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር እነጋገራለሁ። በእርግጥ ያን በፍጥነት ነው የምናደርገው። በመግለጪያዬ ግልጽ እንዳደረግሁት ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ እና በተመድ ነው መታየት ያለበት። እጄ የሚገባውን ማንኛውንም ሠነድ ለጽ/ቤቶ አቀርባለሁ ክቡርነትዎ። አመሠግናለሁ።»

አምባሳደር አጽቀ ሥላሴ፦የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ እና በተባበሩት መንግሥታት መካከል ያለን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ መወያየቱ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል። ሌሎች በርካታ ሃገራት የተመድ ሠራተኞችን ግልጽ ወይንም ግልጽ ባልሆነ መንገድ ከሀገራቸው ሲያባርሩ የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ስብሰባ የጠራበትን አንድም ጊዜ እንደማያስታውሱም አክለዋል። ከኢትዮጵያ የጽሑፍ መረጃዎች አልደረሱኝም መረጃዎቹ ይቅረቡልኝ ያሉት የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ከዚህ ልዩ ስብሰባ ሲወጡ በአንዲት ጋዜጠኛ ድንገተኛ ጥያቄ ቀርቦላቸውም ነበር።

«ዋና ጸሐፊ፦ እስከማስታውሰው ድረስ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ መልስ ሲሰጡ አንድም ጊዜ ታይተው ዐያውቁም ነበር። ይኼ የሚያሳየው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ መንግሥት ደስተኛ ያለመሆኖትን መጠን ይሆን

ዋና ጸሐፊው በአጀብ ከፊት ለፊታቸው ወደሚገኘው ደረጃ ከመውጣታቸው በፊት ላፍታ ቆም ብለው፤ ቆጣ ባለ ገጽታ ቀጣዩን አጠር ያለ መልስ ሰጥተዋል።

«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ክብርን ማስጠበቅ ግዴታዬ ነው።»

ከኢትዮጵያ የተባረሩትን የተመድ ሠራተኞችን አስመልክቶ በፀጥታው ምክር ቤት በተካሄደው አስቸኳይ ስብሰባም በድጋሚ አባል ሃገራት አንድ አቋም መያዝ ሳይችሉ ተለያይተዋል። ሆኖም በስበሰባው የታደሙ በርካታ ሃገራት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚደንት ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ የአፍሪቃ ኅብረት የአፍሪቃ ቀንድ ከፍተኛ ልዑክ መሆናቸውን እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic