የፀጥታዉ ምክር ቤት ዉሳኔና ሱዳን | የጋዜጦች አምድ | DW | 20.09.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የፀጥታዉ ምክር ቤት ዉሳኔና ሱዳን

ፕሬዝዳንት ዑመር አል-በሽር የፀጥታዉ ምክር ቤት ዉሳኔን አንፈራም ሲሉ እንደ ዲፕሎማቶቻቸዉ ዉሳኔዉን የመቃወም-ለዉሳኔዉ የመገዛትም ድብልቅ መልዕክት ማስተላለፋቸዉ ይሁን ወይም እደ አፈጉባኤዉ ዉሳኔዉን እንደ ወረራ ዝግጅት መተርጎማቸዉ በዉል አልታወቀም።አል-በሽር ዉሳኔዉ ማምሻ ከመተላለፉ በፊት ቅዳሜዉኑ ቀን ላይ እንዳሉት ግን መንግስታቸዉ ለዳርፉር ጥያቄ ሰላማዊ መፍትሔ ለማግኘት አበክሮ ከመጣር አይቦዝንም።


የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ዑመር ሐሰን አል-በሽር ሐገራቸዉ የተባባሩት መንግስታት የፀጥታዉ ምክር ቤት ያሳለፈዉ ዉሳኔ እንደማያስፈራት አስታወቁ። የፀጥታዉ ምክር ቤት ባለፈዉ ቅዳሜ ያሳለፈዉ ዉሳኔ የምዕራባዊ ሱዳን ግዛት ዳርፉርን ቀዉስ ለማስወገድ የሱዳን መንግስትና የአፍሪቃ ሕብረት የሚያደርጉትን ጥራት ከማወሳሰብ ሌላ የሚተክረዉ እንደሌለ የሱዳን ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እያስታወቁ ነዉ።የሱዳን መንግስት ዳርፉርን የሚያዉከዉን ቀዉስ ካላስቆም አለም-አቀፍ ማዕቀብ እንደሚጣልበት የፀጥታዉ ምክር ባለፈዉ ቅዳሜ ወስኗል።የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የበላይ ወይዘር ሊዊስ አርቦር ደግሞ የዳርፉርን ሠብአዊ ይዞታ ለመጎብኘት ካርቱም ናቸዉ።


ፕሬዝዳንት ዑመር ሐሰን አልበሽር ትናንት ለሱዳን ክፍለ-ግዛት ባለሥልጣናት እንደነገሩት ሱዳን የተባበሩት መንግስታትን ዉሳኔዉንም አትፈራም።አል-በሽር ብዙም ማብራሪያ ያልሰጡበትን የመንግስታቸዉን አቋም ከመግለጣቸዉ በፊት በተለያየ ደረጃ ያሉ የሐገሪቱ ባለሥልጣናት ለቅዳሜዉን ዉሳኔ የሰጡት ምላሽ ዛቻን-ከይሁንታ፣ ዉግዘትን-ከአወንታ ጋር የቀየጠ ነዉ። ትናንት ካርቱም የገቡትን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የበላይ ወይዘሮ ሊዊስ አርቦርን ያነጋገሩት የሐገሪቱ የፍትሕ ሚንስትር ዓሊ ዑስማን መሐመድ ያሲን እንዳሉት የአርቦር ተልዕኮ እንዲሳካ መንግስታቸዉ ይተባበራል።

ይሁንና ሚንስትሩ አክለዉ እንዳሉት ዳርፉር ዉስጥ የዘር-ማጥፋት አልተፈጸመም።ሴቶችም አልተደፈሩም።ባለፈዉ ቅዳሜ ድምፅ በድምፅ የመሻር ሥልጣን ካላቸዉ የፀጥታዉ ምክር ቤት አባላት ቻይናና ሩሲያ፣ ከተለዋጮቹ ደግሞ አል-ጀሪያና ፓኪስታን ድምፃቸዉን አቅበዉ በ-አስራ-አንድ ለ0 ድምፅ የፀደቀዉን ዉሳኔ ለምክር ቤቱ ያቀረበችዉ ዩናይትድ ስቴትስ የሱዳን መንግስትና መንግስት የሚደግፋቸዉ የጃንጃዊድ ሚሊሻዎች ዳርፉር ዉስጥ ዘር እያጠፉ ነዉ በማለት ትወንጀላቸዋለች።የዋሽንግተንን አቋም እስካሁን የተቀበለዉ ሐገር የለም።አንዳድ የምዕራብ ሐገራት መንግስታትና የርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት ግን የጃንጃዊድ ሚሊሺያዎች የዳርፉር ጥቁር ሕዝብ ቤቶችን እያጋዩ ነዉ።ሴቶቹን መድፈራቸዉን።ሌላዉን መግደላቸዉንም አላቆሙም።

ዛሬ ዳርፉርን የሚገበኙት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የበላይ ተልዕኮም በዳርፉር ሕዝብ ላይ ይፈፀማል የሚባለዉን የሰብአዊ መብት ረገጣ ማጣራት ነዉ።የፀጥታዉ ምክር ቤት ባሳላፈዉ ዉሳኔ መሠረት አለም አቀፉ ድርጅት ዳርፉር ዉስጥ ተፈፀመ የተባለዉን የዘር-ማጥፋት ወንጀል የሚያጣራ ልዩ ኮሚቴ ይሰይማል።ዳርፉር የሰፈረዉ የአፍሪቃ ሕብረት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ቁጥርም እንዲጨምር ዉሳኔዉ ይጠይቃል።የሱዳን መንግስት የተባለዉን ከላደረገ ወይም የዳርፉርን ቀዉስ ካለስወገደ በምክር ቤቱ ዉሳኔ መሠረት የነዳጅ ዘይት ሽያጭን ጨምሮ በአለም አቀፍ ማዕቀብ ይቀጣል።

የሱዳን ባለሥልጣናት የቅዳሜዉ ዉሳኔ ከመተላለፉ በፊትም ዩናይትድ ስቴትስ ሥለዳርፉር የያዘችዉ አቋም፣ ለዳርፉር አማፂዎች ተዘዋዋሪ ድጋፍ እየሆነ ነዉ።በአፍሪቃ ሕብረት ሸምጋይነት አቡጃ- ናይጄሪያ ዉስጥ የተያዘዉ ድርድር ወዴት እንደሚጓዝ ሳይታወቅ-የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሱዳን መንግስትንና የጃንጃዊድ ሚሊሺያዎችን በዘር-አጥፊነት መወንጀላቸዉ የሱዳን መንግስት ባለሥልጣናት እንደሚሉት አማፂያኑ አክራሪ አቋም እንዲይዙ ዋና ምክንያት ሆኗል።የአማፂያኑ አቋም በፋንታዉ ድርድሩ አጉሎታል።

የቅዳሜዉ ዉሳኔ ደግሞ የሱዳን ምክትል የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሙጠሪፍ ሲዲቅ እንዳሉት የአፍሪቃ ሕብረት ሽምግልናን የመንግስታቸዉንም ጥረት ከማደናቀፍ ሌላ ለዳርፉር ችግር መፍትሔ አይሆንም።ያም ሆኖ ምክትል ሚንስትሩ እንዳሉት በሱዳን መንግስት ላይ ግፊት ተደረገበትም አልተደረገበት የዳርፉርን ችግር በሰላም ለማስወገድ መንግስታቸዉ እንደመንግስት የሚያደርገዉን ጥረት ይቀጥላል።

የሱዳኑ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ኢብራሒም አሕመድ አል-ጣሒር ግን የፀጥታዉ ምክር ቤትን ዉሳኔን ከዉግዘትም በላይ እንደ ድፍረት ነዉ-የቆጠሩት።አፈ-ጉባኤዉ ለዳርፉር ጎሳ ተጠሪዎች «ኢራቅ ለምዕራቦች አንድ የሲዓል በር ከከፈተች፣ እኛ ደግሞ ሰባት የሲዖል በሮች እንከፍትላቸዋለን»--አሏቸዉ።ፕሬዝዳንት ዑመር አል-በሽር የፀጥታዉ ምክር ቤት ዉሳኔን አንፈራም ሲሉ እንደ ዲፕሎማቶቻቸዉ ዉሳኔዉን የመቃወም-ለዉሳኔዉ የመገዛትም ድብልቅ መልዕክት ማስተላለፋቸዉ ይሁን ወይም እደ አፈጉባኤዉ ዉሳኔዉን እንደ ወረራ ዝግጅት መተርጎማቸዉ በዉል አልታወቀም።አል-በሽር ዉሳኔዉ ማምሻ ከመተላለፉ በፊት ቅዳሜዉኑ ቀን ላይ እንዳሉት ግን መንግስታቸዉ ለዳርፉር ጥያቄ ሰላማዊ መፍትሔ ለማግኘት አበክሮ ከመጣር አይቦዝንም።