1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

የ«ፀሐይ»አውሮፕላን ቴክኒካዊ ይዘት እና የዚያን ዘመኑ የአቬሽን ቴክኖሎጅ

ረቡዕ፣ የካቲት 20 2016

።ፀሐይ በኢትዮጵያ የተሰራች የመጀመሪያዋ አውሮፕላን ስትሆን፤ የተገጣጠመችው በጎርጎሪያኑ 1935 ዓ/ም የፀደይ ወቅት በጀርመናዊው አብራሪ ሉድቪሽ ቬበር እና በወቅቱ በነበሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችች ነበር። ለመሆኑ የነበራት ቴክኒካዊ ይዘት እና የዚያን ዘመኑ የአቬሽን ቴክኖሎጅ ምን ይመስል ነበር?

https://p.dw.com/p/4czUk
የኢትዮጵያን ወረራ ተከትሎ  በቤኒቶ ሞሶሎኒ ወደ ጣሊያን የተወሰደችው ይህች አውሮፕላን እስከ 1941 ዓ/ም ድረስ በካሴርታ አቪዬሽን ቤተመዘክር ከ1941 ጀምሮ ደግሞ በጣሊያን የአየር ሀይል ቤተመዘክር ውስጥ ቆይታለች
የኢትዮጵያን ወረራ ተከትሎ በቤኒቶ ሞሶሎኒ ወደ ጣሊያን የተወሰደችው ይህች አውሮፕላን እስከ 1941 ዓ/ም ድረስ በካሴርታ አቪዬሽን ቤተመዘክር ከ1941 ጀምሮ ደግሞ በጣሊያን የአየር ሀይል ቤተመዘክር ውስጥ ቆይታለችምስል Office of the Prime Minster Ethiopia

ፀሐይ፤ በኢትዮጵያ የተሰራችው የመጀመሪያ አውሮፕላን እውነታዎች

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገጣጠመችው«ፀሀይ» አውሮፕላን፤ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ባለፈው የካቲት 8 ቀን 2016 ዓ/ም  ከጣሊያን ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳለች። የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በአዉሮፕላኗ ቴክኒካዊ ይዘት እና በዚያን ዘመኑ  የአቬሽን ቴክኖሎጅ ላይ ያተኮረ ነው።
በኢትዮጵያ በየዘመኑ የመጡ ቴክኖሎጂዎችን  ከሌሎች ሀገራት ገዝቶ ለመጠቀም ከሚደረገው ጥረት ባሻገር፤ በሀገር ውስጥ ለመስራት እና የቴክኖሎጅ እድገት ተቋዳሽ ለመሆን  በተለያዩ ጊዚያት ሙከራዎች ተደርገዋል። ለአብነትም አፄ ቴዎድሮስ  በኢትዮጵያ ምድር መድፍ ለማሰራት ያደረጉትን ሙከራ መጥቀስ ይቻላል።
በቅርቡ ከጣሊያን ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው እና «ፀሀይ» የተሰኘችው አውሮፕላንም ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ባሻገር ዘመኑ የፈቀደውን ቴክኖሎጅ በሀገር ውስጥ ለማምረት ያለውን ፍላጎት ማሳያ ልትሆን ትችላለች።በጀርመን ሀገር የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ፣ ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አስራተ ካሳ እንደሚሉት «ፀሀይ»አውሮፕላን  ኢትዮጵያ ውስጥ ከመገጣጠሟ በፊት «ንስረ ተፈሪ» የሚባል የመጀመሪያ አውሮፕላን መግባቱን ያስታውሳሉ።

 ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አስራተ ካሳ በጀርመን ሀገር የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ፣ ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ
ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አስራተ ካሳ በጀርመን ሀገር የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ፣ ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝምስል Uwe Zucchi/dpa/picture alliance

ፀሐይ በኢትዮጵያ የተሰራች የመጀመሪያዋ አውሮፕላን ስትሆን፤ የተገጣጠመችው በጎርጎሪያኑ 1935 ዓ/ም የፀደይ ወቅት በጀርመናዊው አብራሪ ሉድቪሽ ቬበር እና በወቅቱ በነበሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችች ነበር። አውሮፕላኗ ኢትዮጵያ 1 እንዲሁም  የንጉስ አይሮፕላን ተብላ ትጠራ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ፀሐይ የሚለውን ስያሜ አግኝታለች። አውሮፕላኗ «ፀሐይ» የሚለውን ስያሜ ያገኘችውም የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ሴት ልጅ ልዕልት ፀሐይን ለማሰብ እንደነበር ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አስራተ ካሳ  ይገልፃሉ።

 የሉድቪሽ ቬበር ወደ ኢትዮጵያ መምጣት
ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ጋር በመሆን ፀሀይን የገጣጠመው ሉዊድቪሽ ዌበር በጀርመን ባደን ቩተንበርግ ግዛት  ፋርይቡርግ ከተማ፤  በጎርጎሪያኑ ጥቅምት 1895 የተወለደ ሲሆን፤ በጀርመኑ ዩንከርስ ኩባንያ መሀንዲስ እና የአውሮፕላን አብራሪ ሆኖ ሰርቷል።ዌበር ከአብራሪነቱ በተጨማሪ የሞተር ሳይክል፣ የመኪና እና የአውሮፕላን ንድፍ ሰሪም ነበር።በጎርጎሪያኑ 1991 ዓ/ም ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስም በዚሁ ሙያው በተለያዩ ሀገሮች ሰርቷል።
ጀርመናዊው መሀንዲስ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በጎርጎሪያኑ መጋቢት 1932 ዓ/ም ዩንከርስ በተባለው የጀርመን ኩባንያ ትዕዛዝ መሰረት ሲሆን፤ ዓላማውም «W 33 C» የተባለ የኩባንያውን አውሮፕላን እንዲጠግን እና የንጉሱ የቀዳማዊ ሀይለስላሴ የግል  አብራሪ ሆኖ እንዲያገለግል ነበር።
ከዩንከር ኩባንያ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረትም በመጋቢት 1932 ዓ/ም ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ የንጉሱ የቀዳማዊ ሀይለስላሴ የግል አብራሪ ሆነ።
ቆይቶም በ1933 ዓም አካባቢ በኢትዮጵያ የተከሰከሰውን የዩንከርስ «W 33 C»አውሮፕላን ሙሉ በሙሉ ከጠገነ በኋላ ሉድቪሽ ቬበር ለኢትዮጵያ አየር ሃይል አውሮፕላን የመስራት ሀሳብ አደረበት።
የሀሳቡ መነሻም በወቅቱ ለመስራት  እና ለመጠገን ቀላል የነበረው «A. VII» በመባል የሚታወቀው የጀርመን  ሞኖ/ባለአንድ ዋና ቋሚ ክንፍ /  አውሮፕላን ሳይሆን እንዳልቀረ መረጃዎች ያሳያሉ።
ንጉሠ ነገሥቱም ለልዊድቪሽ  ሃሳብ ይሁንታ  በመስጠታቸው  በ«A. VII» /ኤ ሰባት/ አውሮፕላንን አምሳል ንድፍ በመስራት በኢትዮጵያ ለመገጣጠም ስምምነት ላይ ተደረሰ። ለዚህም ልዑል አስራተ ካሳ እንደሚገልፁት ቀደም ሲል ንጉሰ ነገስቱ ከጀርመን ጋር  የነበራቸው ጥሩ ግንኙነት ነው። 

የ«ፀሐይ» ቴክኒካዊ ሁኔታዎች
አውሮፕላኑ በወቅቱ የተፈለገው ለአየር ሀይሉ እንደ ማሰልጠኛ ሆኖ እንዲያገለግል  እንዲሁም መገናኛ ሆኖ እንዲሰራ ሲሆን፤ ቬበር አውሮፕላኗን የነደፈው፣«ሞኖ»በሚባለው  ባለ አንድ ቋሚ ክንፍ  የአውሮፕላን ንድፍ ነበር።የንድፍ ስራው በ 1934 መጨረሻ ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ዕቅዱም ሶስት አውሮፕላኖችን ለመገጣጠም ነበር። ያም ሆኖ በ1935 በስኬት የተጠናቀቀችው ፀሀይ  አውሮፕላን ብቻ ነበረች።

መጀመሪያው በረራ  በታህሳስ 1935 የተካሄደ ሲሆን፤ በረራውም  በሉድቪግ ዌበር በግል የተካሄደ ነበር።ይህ በረራ ከአዲስ አበባ 50 ኪሎሜትር ርቀት ከባህር ጠለል በላይ በ1000 ሜትር ከፍታ ሰባት ደቂቃ የፈጄ ነበር።
የ«ፀሀይ» መጀመሪያው በረራ በታህሳስ 1935 የተካሄደ ሲሆን፤ በረራውም በሉድቪግ ዌበር በግል የተካሄደ ነበር።ይህ በረራ ከአዲስ አበባ 50 ኪሎሜትር ርቀት ከባህር ጠለል በላይ በ1000 ሜትር ከፍታ ሰባት ደቂቃ የፈጄ ነበር።ምስል Office of the Prime Minster Ethiopia

የአውሮፕላኗ ሞተርም  የ115 የፈረስ ጉልበት ያለው ባለሰባት ሲሊንደር ዋልተር ቪነስ እና የውሃ ማቀዝቀዣ ስርዓት ያለው ነው።
 ከፍተኛ ኃይል ካለው ሞተሯ በተጨማሪ «ፀሐይ»፤ ባለሁለት መቀመጫ እና መቆጣጠሪያ እንዲኖራት ተደርጋ የተሰራች አውሮፕላን ነች።
 ከመጀመሪያው ባለ ሶስት መቀመጫ «A. VII» ጋር አውሮፕላኗ  ተመሳሳይነት ያላት  ቢሆንም፤ ርዝመቷን ወደ 7.32 ሜትር ዝቅ በማድረግ የአንድ ተሳፋሪ ቦታ በመቀነስ ባለ ሁለት መቀመጫ ሆና ነበር የተሰራችው።
በተጨማሪም አውሮፕላኗ ፤ ኮምፓስ/ የአብራሪዎች የአቅጣጫ መቆጣጠሪያዎች/፣ ሁለት ያለ ፍሬን ማቆሚያ የተገጠሙ የማረፊያ ሽክርክሪቶችም ነበራት ።
ክፈፏ የጨርቅ ሽፋን ያለው ብረት ሲሆን፤የአውሮፕላኗ ክንፍ በአብዛኛው ከእንጨት የተሠራ እና የንፋስ መከላከያዎቹ ደግሞ ከፕላስቲክ የተሠሩ ነበሩ።
ቀለሟም አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ  እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። በወቅቱ ሶስት አውሮፕላኖችን በተከታታይ ለመስራት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረሯ  መስራት  የተቻለው «ፀሐይ»ን  ብቻ ነበር።

የመጀመሪያው በረራ
የመጀመሪያው በረራ  በታህሳስ 1935 የተካሄደ ሲሆን፤ በረራውም  በሉድቪግ ዌበር በግል የተካሄደ ነበር።ይህ በረራ ከአዲስ አበባ 50 ኪሎሜትር ርቀት ከባህር ጠለል በላይ በ1000 ሜትር ከፍታ ሰባት ደቂቃ የፈጄ ነበር። አውሮፕላኑ ሞቃትና ስስ አየር ካለው ማኮብኮቢያ 150 ሜትር ርቆ በአየር ላይ የተጓዘ ሲሆን፤ በመሬትም ሆነ በአየር ላይ ለመቆጣጠር  ቀላል እና ዛቢያዎቹም ላይም ጥሩ መረጋጋት ነበረው።መቆጣጠሪያዎቹ ቢሆን ለማንቀሳቀስ ከሚያስፈልገው አነስተኛ ሀይል ጋር በጥሩ ሁኔታ የተጣጠሙ ናቸው።
በሰባት ደቂቃ ውስጥ አውሮፕላኗ ከ2,500 ወደ 3,500 ሜትር ከፍታ የወጣች ሲሆን፤ ወደ 6,000 ሜትር  ባለው ጣሪያ ወደ 150 ኪ.ሜ. በስዓት ተጉዟል። ከፍተኛው ፍጥነት ደግሞ  ወደ 185 ኪ.ሜ በሰዓት ሲሆን፤ የማረፊያው ፍጥነት ደግሞ 50 ኪ.ሜ በሰዓት ነበር።
በዚህ ሁኔታ  አይሮፕላኗ በአጠቃላይ የበረረችው 30  ሰዓት ብቻ ሲሆን ከዚያም የጣሊያን ወረራ ዌበርን እና ሰራተኞቹን በግንቦት ወር 1936 ዓ/ም ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።
ምንም እንኳ ሄር ቬበር በአውሮፕላኗን በጃን ሜዳ የባህር ዛፍ ጫካ ትተዋት ከሄዱ ወዲህ  ምን እንደተፈጠረ ባይታወቅም፤በአንዳንድ መረጃዎች ግን ጣሊያኖች ተጠቅመውበታል የሚል ግምት አለ።
አውሮፕላኑ በወቅቱ የተፈለገው ለአየር ሀይሉ እንደ ማሰልጠኛ ሆኖ እንዲያገለግል  እንዲሁም መገናኛ ሆኖ እንዲሰራ ነበር። 
«ፀሐይ» በውስን ሃብት እና ስፍራ በጊዜው በነበሩ  አናፂዎች እውቀት እና የእጅ ጥበብ  የተሰራች አውሮፕላን ስትሆን ፤ መዛግብት እንደሚያመለክቱት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት የነበረው የ1930ዎቹ የአቪየሽን ጥረት ማሳያም ጭምር ነች።
ያም ሆኖ ከ89 ዓመት በኋላም ቢሆን በኢትዮጵያ ሌላ አውሮፕላን ስለመገንባቱ መረጃ የለም። ልዑል ዶክተር አስፋወሰን ለዚህ ላለፉት 50 ዓመታት ሀገሪቱ የተጓዘችበትን የፖለቲካ አካሄድ ይተቻሉ።

የፀሐይ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ 
የኢትዮጵያን ወረራ ተከትሎ  በቤኒቶ ሞሶሎኒ ወደ ጣሊያን የተወሰደችው ይህች አውሮፕላን እስከ 1941 ዓ/ም ድረስ በካሴርታ አቪዬሽን ቤተመዘክር ከ1941 ጀምሮ ደግሞ በጣሊያን የአየር ሀይል ቤተመዘክር ውስጥ ቆይታለች።

የአውሮፕላኗ መመለስ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ  «ቀኑ ለኢትዮጵያውያን ታላቅ ኩራት ነው።»ሲሉ በወቅቱ  ገልፀዋል
የአውሮፕላኗ መመለስ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ «ቀኑ ለኢትዮጵያውያን ታላቅ ኩራት ነው።»ሲሉ በወቅቱ ገልፀዋልምስል Office of the Prime Minster Ethiopia

ያም ሆኖ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በጣሊያኑ  ቤተመዘክር የንጉስ አውሮፕላን በሚል ስም ከመቀመጥ ውጭ ስለ አውሮፕላኗ ታሪክ ምንም አይነት ዝርዝር ማብራሪያ ሳይሰፍርበት ቆይቷል።
በዚህ ሁኔታ ላለፉት 89 ዓመታት በጣሊያን ሀገር የቆየችው በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገጣጠመችው«ፀሀይ» አውሮፕላን፤ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ባለፈው የካቲት 8 ቀን 2016 ዓ/ም  ከጣሊያን ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳለች። የአውሮፕላኗ መመለስ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ  «ቀኑ ለኢትዮጵያውያን ታላቅ ኩራት ነው።»ሲሉ በወቅቱ  ገልፀዋል። 
ለልዑል አስፋ ወሰን ግን የአውሮፕላኗን መመለስ አወንታዊ ቢሆንም፤ከዚህ  ይልቅ፤ በኢትዮጵያ በሚታየው የሰላም ዕጦት የበለጠ ያሳስባቸዋል።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ