የፀሀይ ግርዶሽና የኢትዮጵያ ጥንታዊ የሥነ-ፈለግ ምርምር | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 24.06.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የፀሀይ ግርዶሽና የኢትዮጵያ ጥንታዊ የሥነ-ፈለግ ምርምር

«በእርግጥ ኢትዮጵያ በዚህ ሳይንስ ቀዳሚ ነበረች።ሆን ተብሎ የራሳችን ነገር እንዲጣል በመደረጉ እንጅ።ሜርኩሪ አጣልድ ትባል ነበር።ቬኑስን ዝሁራ ይሏት ነበር።ማርስን አይህ ይሉት ነበር።ጁፒተርን መሽተል ይሉት ነበር።ሳተርንን ዝኋል ይሉት ነበር።እነዚህ ከክርስቶስ ልደት በፊት የታወቁ ናቸው።»መጋቢ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:14

የፀሀይ ግርዶሽና የኢትዮጵያ ጥንታዊ የሥነ-ፈለግ ምርምር

ከሥነ-ፈለጋዊ ክስተቶች አንዱ የሆነው የፀሀይ ግርዶሽ በዓለም ላይ  በተለያዩ ጊዜዎችና ቦታዎች  ሲታይ ቆይቷል።በኢትዮጵያም ያለፈው ሳምንት መጨረሻ በተለያዩ አካባቢዎች  ተከስቷል።
የሥነ-ፈለግ ምርምር ከጥንታዊ የሳይንስ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ሲሆን ግርዶሽ ደግሞ የዚህ ዘርፍ  አንዱ ክስተት ነው። የዘርፉ ባለሙያዎች  እንደሚሉት  ግርዶሽ  ፤ የጨረቃና የፀሀይ ግርዶሽ ተብሎ በሁለት ይከፈላል። የጨረቃ ግርዶሽም  ጨረቃ  በፀሀይና በመሬት መካከል ስታልፍ  የመሬት ጥላ  ጨረቃ ላይ ሲያርፍ የሚከሰት ሲሆን፤የፀሐይ ግርዶሽ ደግሞ ጨረቃ በምድር እና በፀሐይ  መካከል ስታልፍ የፀሐይን እይታ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በምትጋርድበት ጊዜ የሚከሰት ነው። ይህ የፀሀይ ግርዶሽ  ሙሉ ፣ከፊል ፣ቀለበታማ እንዲሁም ደግሞ አልፎ አልፎ የሚከሰት ድብልቅ ወይም አጥር ግርዶሽ በመባል  ይታወቃል ይላሉ የስነ ፈለግ ባለሙያው መጋቤ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ።
እነዚህ ሥነ-ፈለጋዊ ክስተቶች በዓለም ላይ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ  በተለያዩ ጊዜዎችና ቦታዎች  ሲታዩ መቆየታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።ከክርስቶስ ልደት በኃላም በጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 29 ቀን 1504 ዓ/ም ክርስቶፈር ኮሎምቦስ ማዕከላዊ አሜሪካን ለማሰስ በተጓዘበት ወቅት መርከቡ እክል ገጥሟት ጀማይካ ባረፈበት ወቅት የፀሀይ ግርዶሽ ማየቱን መዛግብት ይጠቁማሉ።በኢትዮጵያም ያለፈው ዕሁድ ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ/ም ከአራቱ የፀሀይ ግርዶሾች መካከል  ቀለበታማ የእሳት ግርዶሽ በተለያዩ አካባቢዎች  ተከስቷል።ይህ የፀሀይ ግርዶሽ  ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በፓኪስታን፣ በህንድ ፣በማዕከላዊ አፍሪካም የታዬ ሲሆን ለኢትዮጵያ ከብዙ ዓመታት በኃላ የታዬ  ለየት ያለ ክስተት መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ሶሎሞን በላይ ይገልፃሉ።
 ከምዕራብ ወለጋ ተነስቶ ወደ ሰሜን  ምስራቅ ኢትዮጵያ  አካባቢዎች የተጓዘው ይህ የፀሀይ ግርዶሽ  በአፋር በአለማጣ በላሊበላ በእንጅባራ፣ በባህርዳር ጭስ አባይና በሌሎች  አካባቢዎች በጉልህ ታይቷል።በተለይ በላሊበላ 98 በመቶ ጨለማ እንደነበር በወቅቱ ሂደቱን የተከታተሉት መጋቢ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ገለፀዋል።እንደ ሥነ-ፈለግ ባለሙያው  ክስተቱ ሌላም የተለዬ ነገር ነበረው ።
«በማንኛዉም ግርዶሽ ፀሀይ ጨረቃ መሬት መስመር መስራታቸው የታወቀ ነው።አሁን ግን የአሁኑ ግርዶሽ ለየት የሚያደርገው»ካሉ በኃላ በሰሜኑ ንፍቀክበብ ረጅሙ የበጋ ወቅት

ከሚጀምርበት ቀን ጋር የፀሀይ ግርዶሹ መገጣጠሙን አመልክተዋል። አያይዘዉም «የተለያዩ መስመሮች በሰማይ ላይ ተገጣጥመዋል» ይሉና «በዕለቱ ብዙ ፕላኔቶች ነበር የወጡት። ሜርኩሪና ቬኑስ ከፀሀይ ጋር በምስራቅ በኩል ወጥተዋል።በስተ ምዕራብ አቅጣጫ ደግሞ ሳተርን፣ጁፒተርና ማርስም ነበሩ።እና እነዚህ ነገሮች ግጥምጥሞሹ ለየት ያለ ነገር አሳይቶናል ብዬ አስባለሁ።» ብለዋል።
እንደ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ተቋም ይህ ክስተት ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሚታወቅ ሲሆን በርካታ ጎብኝዎችን በመሳብ ይገኛል። ዘንድሮ የተከሰተውን የፀሀይ ግርዶሽ ለማየትም በርካታ ሳይንቲስቶችና ጎብኝዎች ቀጠሮ ይዘው የነበረ ቢሆንም በኮሮና ወረርሽን ሳቢያ ሳይሳካ ቀርቷል።የተቋሙ ዳይሬክተር  ዶ/ር ሰለሞን በላይ እንደሚሉት ኮቪድ -19 ሀገሪቱ ከጎብኝዎች ታገኝ የነበረውን  ገቢ ቢያሳጣትም ክስተቱ በዘርፉ ለሚደረገው ሳይንሳዊ ምርምር  ግን አጠቀሜታው የጎላ ነው።
በአጠቃላይ የፀሐይ እና የጨረቃ ግርዶሾች መሬት፣ፀሐይና ጨረቃ በአንድ መስመር ላይ በሚገጣጠሙበት  ጊዜ የሚከሰቱ ሥነ-ፈለጋዊ ክስተቶች ናቸው።እነዚህ ክስተቶች ብዙውን ጌዜ ከተፈጥሮ በላይ ከሆነ አንዳች መለኮታዊ ሀይል ጋር ሲያያዙ የነበረ ቢሆንም፤ የቀን መቁጠሪያዎችን ለመቀመር  መንገድ ከፋች በመሆን በሰው ልጆች የስልጣኔ ታሪክ ውስጥ  ጎላ ያለ  ስፍራ ይዘው ቆይተዋል ፡፡ከዚህ በተጨማሪም  አሪስጣጣሊስ  መሬት ክብ ነች  የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ ለማሳመን ፣ አሪስጣቅሊስ ለተባለው ሌላዉ የግሪክ የሥነ-ፈለግ ተመራማሪ ደግሞ ፀሀይና ጨረቃ ከመሬት ምን ያህል እንደሚርቁ  ለመገመት፣ እንዲሁም አልበርት አንስታይን የአንፃራዊነት ፅንሰ-ሀሳቡን/ሬሌቲቭ ቲዮሪን/ ለማረጋግጥ ረድቶታል።እንደ መጋቢ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ  ሥነ-ፈለግ በኢትዮጵያም ጥንታዊ መሰረት አለው።
«በእርግጥ ኢትዮጵያ በዚህ ሳይንስ ቀዳሚ ነበረች።ሆን ተብሎ የራሳችን ነገር እንዲጣል በመደረጉ እንጅ።ሜርኩሪ አጣልድ ትባል ነበር።ቬኑስን ዝሁራ ይሏት ነበር።ማርስን አይህ ይሉት ነበር።ጁፒተርን መሽተል ይሉት ነበር።ሳተርንን ዝኋል ይሉት ነበር።እነዚህ ከክርስቶስ ልደት በፊት የታወቁ ናቸው።»በማለት አብራርተዋል።
እንደ ባለሙያው በአሁኑ ወቅትም በአለም አቀፉ የሥነ-ፈለግ ህብረትም በዘርፉ  ሶስት የኢትዮጵያ ስራዎች ተመዝግበው ይገኛሉ።
«አሁን ያለው ሳይንስ በ1930ዎቹ ዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ህብረት 88 ህብራተ ክዋክብት «ኮንስታሌሽኖች»ን መዝግቧል።«ኦፊሻል ኮንስታሌሽኖች» ናቸው።ከነዚህ ውስጥ ሶስቱ ከኢትዮጵያ ናቸው።»
ያም ቢሆን ይህ ሀገር በቀል ሀብት ጥቅም ላይ እያዋለ አለመሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።  ዶክተር ሶሎሞን በላይ ችግሩን  እንደሚጋሩ ጠቅሰው እሳቸው የሚመሩት  የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ተቋም ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ሀገር በቀል እዉቀቶችን ከዘመናዊው ሳይንስ ጋር በማጣመር ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ጥናት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
«አንድሮ ሜዳ» በሚል ርዕስ  በኢትዮጵያ ጥንታዊ የሥነ-ፈለግ ምርምር ላይ የሚያተኩረውን መፅሐፍ ጨምሮ የበርካታ መጻህፍት ደራሲ የሆኑት መጋቢ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ፤ በበኩላቸው ትውልዱ ሀገር በቀል እዉቀቶችን እንዲቀስም የሀገሪቱ ስርዓተ-ትምህርትም በኢትዮጵያዊ የሳይንስ መንፈስ እንዲቃኝ መክረዋል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

ኂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic