የ«ጸጉር ሽያጭ»፤ «የኛ» ፕሮጀክት እና የኦባማ ስንብት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 13.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የ«ጸጉር ሽያጭ»፤ «የኛ» ፕሮጀክት እና የኦባማ ስንብት

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባደረጉት ንግግር ስለ ጸጉር ሽያጭ ያነሱት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰፊ መነጋገሪያ ኾኖ ቆይቷል። አስተያየቶቹን አሰባስበናል። «የኛ» ለተሰኘው የሴቶች ፕሮጀክት የብሪታንያ መንግሥት የገንዘብ ድጋፉን ማቋረጡ፤ የኦባማ የስንብት ንግግርንና ተተኪያቸው ዶናልድ ትራምፕን የተመለከቱ አስተያየቶችን አካተናል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:55

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

አጠር ያሉ የቪዲዮ ምስሎችን መቀባበል በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅ ከሆኑ ስልቶች አንዱ ነው። 
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ባሳለፍነው ሰኞ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተናገሩበት አጠር ያለ ቪዲዮ ይጠቀሳል።  

ጠቅላይ ሚንስትሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሌሎችም ሃገራት ቀደም ሲል የተከሰተ ስለመሆኑ ካሜራ ፊት ቀርበው ያብራሩበት የቪዲዮ  ምስል በኢንተርኔት በስፋት ተሰራጭቷል። 

«ዛሬ በኢኮኖሚያቸው ውስጥ የተትረፈረፈ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ያላቸው እነ ቻይና፣ እነ ኮሪያ እነ ጃፓን፤ ሁሉም በእኛ እድሜ ላይ በነበሩ ጊዜ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ክፉኛ ተፈታትኗቸዋል። ሌላው ቀርቶ የሴቶቻቸውን ጸጉር ጭምር ቆርጠው ኤክስፖርት እስከማድረግ ተገደው ነበር። ስለዚህ፦ ይኼ በእድገት ደረጃ ማለፍ ያለብን ጉዳይ ነው። ተስፋ የሚያስቆርጥ ጉዳይ አይደለም።»  

የጠቅላይ ሚንስትሩን ንግግር በተመለከተ በትዊተርም በፌስቡክም የተለያዩ አስተያየቶች ተሰራጭተዋል። ሚሊዮን ኃይለሥላሴ በትዊተር ገጹ፦ «የጨነቀው አዲስ አበቤ እንዲህ አለ» በማለት ይጀምራል። ቀጠል አድርጎም፦ «ወይ ጉዴ! ቤቴ ለልማት ተነሳ፤ አሁን ደግሞ የሚስቴ ፀጉር ሊነሳ ነው?» ሲል ጥያቄ አቅርቧል። 
ኤርሚያስ ቶኩማ በበኩሉ በትዊተር ያሰፈረው አጭር ስንኝ እንዲህ ይነበባል፦ «ያደግኩበት ቀዬ ያደግኩበት ሰፈር በመንግሥት ፈራርሷል የእህቴም ፀጉር በልማት ሊነሣ ቀን ተቆርጦለታል።» 

በድርሰቱ ዓለምም ሆነ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ ጥቂት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የሆነው በዕውቀቱ ሥዩም በፌስቡክ ገጹ ያሰፈረው ስላቅ በርካቶች ተቀባብለውታል፤ በስፋትም መነጋገሪያ ኾኗል።

በዕውቀቱ የስላቁ መንደርደሪያ ያደረገው ኮምጨን ነው። «በደርግ ጊዜ ጉዋድ ኮምጨ፤ በደብረማርቆስ አደባባይ ገበሬዎችን ሰብስቦ ይሰረብታል። (በጎጃም አማርኛ ሰረበተ ማለት ፕሮፖጋንዳ አደረገ ማለት ነው)» ሲል በዕወቀቱ ባሰፈረው ጽሑፍ ይንደረደራል። 

ኮምጬ የቻይና ገበሬዎች በአብዮቱ ፈታኝ ዘመን ጫማቸውን እስከመብላት መድረሳቸውን ሲያብራራ ከአንድ ገበሬ ያልጠበቀው ጥያቄ እንደቀረበለትም ይጠቅሳል። ወደ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሰሞኑ ንግግር በመመለስም በዕውቀቱ እንዲህ ይላል፦ «ጠቅላይ ምኒስትሩ 'ቻይናና ኮርያ እኛ በነበርንበት ደረጃ ላይ ፤የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ሲሉ የሴቶቻቸውን ፀጉር ይሸጡ ነበር ' ብለው ተናገሩ ሲባል ብሰማ ይሄ ወግ ትዝ አለኝ:: ባጋጣሚ ይቺን እየፃፍኩ ሳለ፣ምሽቴ ከፀጉር ቤት ተመልሳ ፤በሩን ከፍታ ገባች ፤ መቸም ሁለመናየ ግጥም ነውና እንዲህ የሚል ግጥም አመለጠኝ፤ ፀጉርሽን ተሰርተሽ፤ ጀርባሽ ላይ ነስንሰሽ ተሽሞንሙነሽ፤ መጣሽ ቡዳስ መቸም የለም ፤ ከመንግስት አይን ያውጣሽ። እናቶቻችን የሴት አንበሳን አርአያ በመከተል፤ ፀጉራቸውን ያሳጥሩ ነበር። ወይዛዝርት ሆይ !ፀጉራችሁን በመሸለት የአናቶቻችንን ባህል አስፋፉ። ኢኮኖሚውንም ደግፉ» ይላል የበዕወቁቱ የፌስቡክ ስላቅ። የሀገር ልብስ የለበሰች፣ የተከደነ ሙዳይ በቀኝ እጇ የያዘች፣ አጭር ጸጉር ያላት፤  በጎን ገጿ የሚታይ የቆየ ምስልም ከጽሑፉ ጋር አያይዟል። 

Haarverlängerung

አሚር ቢን ያሲር ትዊተር ላይ፦ «ይሄ መሀል ከተማ የሚታየው ጸጉር የምር መስሎት ነው ለኤክስፖርት የተመኘው?እረ ወዳጆቼ ንገሩት የተገዛ ነው ብላችሁ፤ በኋላ እንደ ባሌስትራው ወርቅ ስማችን እንዳይጠፋ!!» ሲል ጽፏል። አሚር «ባሌስትራው ወርቅ» ሲል የጠቀሰው ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁርጥራጭ ብረቶችን ወርቅ በማስመሰል በማቅረብ ከ95.5 ሚሊዮን ብር በላይ አጭበርብሮ የተሰወረውን ግለሰብ ለማስታወስ ይመስላል። ግለሰቡ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ እና ፖሊስ ኮሚሽን ብሔራዊ ኢንተርፖል ተቋማት በኩል ከ2 ዓመት በፊት ተላልፎ መሰጠቱ፤ የተፈረደበት የ25 ዓመት እስራት ውሳኔ ተሰርዞም ክሱ እንደ አዲስ እንዲጀምር መወሰኑ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ተዘግቦ ነበር።

ተስፋሁን አያሌውም በፌስቡክ ገጹ፦ «ረጅም ፀጉር ያላችሁ ሴቶቻችንን ይመለከታል፤ ገና አይንና ጥርስ እያወለቁ ይሸጣሉ፤ ደግነቱ አብዛኛው ሴት ሁማን ሄር ተጠቃሚ ነው» ብሏል። ሁማን ሄር ማለቱ ተገዝቶ የሚቀጠል ጸጉር መሆኑን ለማመላከት ነው። በዚህ ርእሰ-ጉዳይ ዙሪያ የተወሰኑትን አቀረብንላችሁ እንጂ በፌስቡክ እና በትዊተር ላይ የተሰጡት አስተያየቶች በርካታ ናቸው። 

ብሪታኒያ ከተደጋጋሚ ትችት በኋላ «የኛ» በሚል ስያሜ ለሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሮጀክት የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጧን ማስታወቋ ሌላኛው የሰሞኑ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ጉዳይ  ነበር።  

የብሪታንያ  ዓለም አቀፍ የልማት ጽ/ቤት «የእኛ» የተሰኘው የኢትዮጵያ ፕሮጀክትን ለሚደግፈው «ገርል ኢፌክት» የተያዘ 9 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲቋረጥ መወሰኑን ይፋ  ያደረገው ባሳለፍነው ዐርብ ነበር። 

ለ«የኛ» ፕሮጀክት ድጋፉ እንዲቋረጥ ከ3 ዓመታት በላይ ውትወታ ሲያደርግ የቆየው የብሪታንያው «ዴይሊ ሜይል» የተሰኘ ታብሎይድ ጋዜጣ ነው። ጋዜጣው ከብሪታንያ ቀኝ ፖለቲከኞች ጋር በመተባበር «የኛ» ፕሮጀክት ላይ የተቀናጀ ዘመቻ ሲያደርግ መቆየቱን ኩዋርትስ የተሰኘው ዕለታዊ ዜና በኢሜል የሚልከው ድረ-ገጽ ጠቅሷል። «የኛ» ፕሮጀክት ላይ የደረሰውን የገንዘብ ድጋፍ እገዳ፦ «የወግ አጥባቂዎች እይታ ሰለባ» ነው በሚል ርእስም ኩዋርትስ ጥልቅ ዳሰሳ አድርጎበታል።

 

ትውልደ-ኢትዮጵያዊው ብሪታንያዊ ባለቅኔ ለምን ሲሳይ በትዊተር ገጹ ባሰፈረው የእንግሊዝኛ ጽሑፍ፦ «አዎን፤ የኛ። የበለጠ ሚዛናዊ አቀራረብ ከ ዘ ጋርዲያን» ይላል። ዘ ጋርዲያን የተሰኘው የእንግሊዝ ጋዜጣ «የኛ» ፕሮጀክትን በተመለከተ በድረ-ገጽ ያቀረበውን ጽሑፍ ለምን ሲሳይ ከትዊተር መልእክቱ ጋር አያይዟል። «የኢትዮጵያ የሙዚቃ ፕሮጀክት ከፕሬስ ተደጋጋሚ ነቀፌታ ከደረሰበት በኋላ ከብሪታንያ የሚያገነውን ገንዘብ ድጋፍ አጣ» የሚል ርእስ ይዟል የዘ ጋርዲያን ጽሑፍ። በሙዚቃ እና በሬዲዮ የሴቶች መብቶችን የሚያቀነቅነው «የኛ» የተሰኘው ፕሮጀክት ተደጋጋሚ ሙገሳ ይሰጠው ከነበረው የብሪታንያ  ዓለም አቀፍ የልማት ጽ/ቤት የሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ መቋረጥ ከባድ ራስ ምታት ነው ብሏል። 

የብሪታኒያ ዓለም አቀፍ የልማት ጽ/ቤት ውሳኔ የተላለፈው አምስት ወጣት ሴቶች አባላት ያሉት የሙዚቃ ጓድ በሚያቀርበው የሙዚቃ ሥራዎች እና በራዲዮ ድራማዎች የሚታወቀው «የኛ» የተሰኘ ፕሮጀክት 6.3 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ባገኘ ጥቂት ጊዜያት ውስጥ ነው። 

ዴይሊ ሜይል ትናንት ባወጣው እና በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በተንሸራሸረው የኢንተርኔት ዘገባው ደግሞ የገርል ኢፌክት ሥራ አስኪያጅ ቀድሞ የብሪታኒያ ዓለም አቀፍ የልማት ጽ/ቤት ባልደረባ ነበሩ፦ የድርጅታቸው የአንድ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ዝቅተኛው ደሞዝ 40,000 ፓውንድ ገንዘብ እና ጥቅማጥቅሞችን ያካትታል ሲል አስነብቧል። 

የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን አባል የሆነው አጥናፍ ብርሐኔ በትዊተር ገጹ፦ «'የኛ'የተሰኘው ሴቶች ላይ የሚሠራ ፕሮጀክት ከእንግሊዝ መንግሥት የሚያገኘውን የገንዘብ ድጋፍ ስለተነፈገ የአንድ አንድ ሰዎች እልልታ አብሮን የኖረውን ምቀኝነት የሚያሳይ ነው» ሲል ጽፏል። ለአጥናፍ መልስ ከሰጡ ሰዎች መካከል ኪሩቤል ተሾመ፦ «አጥናፍ ወንድሜ እዛ ፕሮጀክት ላይ የፈሰሰው ብር ሁሌም ይዘገንነኝ ነበር። ወያኔ ካልደገፈህ ፈቅ የማትልበት የቀን ጅቦች ሃገር መሆኑን አንዱ ማሳያ ነው» ብሏል።

«የኛ» ፕሮጀክት  በሙዚቃዎች፣ የራዲዮ መሰናዶዎች እና ድራማዎች ያለ ፍላጎት በሚፈፀም ጋብቻ፤ የቤት ውስጥ ጥቃት፣ ያለ እድሜ እርግዝና እና ትምህርት ማቋረጥን የመሰሉ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ለማሥጨበጥ ይሠራል። 

«የኛ» ፕሮጀክትን ያስጀመረው «ገርል ኢፌክት» የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት «አዳዲስ ሐሳቦች ብዙ ጊዜ ተቃውሞ  እንደሚገጥማቸው ተናግሯል። «ገርል ኢፌክት» በተባባሪዎቹ በኩል «የኛ» ለተሰኘው ፕሮጀክት አሁንም ድጋፍ ለማድረግ እንደሚጥር ገልጧል። 

የዩናይትድ ስቴትስ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ባራክ ዖባማ ማክሰኞ እኩለ-ሌሊት እንዲሁም ተተኪያቸው ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በነጋታው ያደረጓቸው ንግግሮች በደጋፊዎቻቸውም በተቃዋሚዎቻቸውም በኩል አነጋግሯል።

በዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል የፌስቡክ ገጽ ላይ ከቀረቡ አስተያየቶች መካከል ከማል ሙሻ፦ «ዖባማ ምንም የፈየደው ነገር የለም ጥርግ እንኳን አለ» ሲል ጽፏል። መኮንን በየነ ሆኮቴ በበኩሉ፦ «ዖባማ ለአፍሪቃ አንዳችም የፈየደው ነገር የለም» ሲል በእንግሊዝኛ አስተያየት ሰጥቷል። ኢሳያስ ፈንቴ ደግሞ፦ «ትረምፕ ከቀዳሚው» ከዖባማ ማለቱ ነው። «ከቀዳሚው በጋራ ጥቅም ላይ መሰረት ያደረገ ግንኙነት ይከተላል ብዬ እጠብቃለሁ» ብሏል። ዶናልድ ትራምፕ የአፍሪቃ ጉዳይ ላይ እንደ ቻይና ጣልቃ እንደማይገቡ ግምቱን አስፍሯል። ከሰሃራ በስተደቡብ የሚገኙ የአፍሪቃ ሀገራት ከቀረጥና ኮታ ነፃ ሸቀጦች ወደአሜሪካ እንዲያስገቡ የሚፈቅደዉ በ እንግሊዝኛ ምኅፃሩ (AGOA) በመባል የሚታወቀዉ ዉልንም ዶናልድ ትረምፕ ሊሰርዙት እንደሚችሉ ገምቷል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ
 

Audios and videos on the topic