1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጸባይ ለውጥ ጉባኤ፣ ለመስኩ ተመራማሪዎች ዕውቅና ተሰጥቷል

ማክሰኞ፣ የካቲት 19 2016

ማህበረሰባዊ የጸባይ ለውጥ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን መልካም ልማዶች እያበረታቱ ጎጂዎችን በሌላ መተካት ነው የሚሉት የጥናትና ምርምር ባለሙያ፤ አሁን አሁን በኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ የጸባይ ለውጥን የመፍጠሩ አስፈላጊነት ጉልህ እንደሆነም ያምናሉ፡

https://p.dw.com/p/4cwXt
አገር አቀፍ የማህበራዊ እና ጸባይ ለውጥ ጉባኤ በኢትዮጵያ ለሶሰርተኛ ጊዜ ሲካሄድ ከተሳተፉት በከፊል
አገር አቀፍ የማህበራዊ እና ጸባይ ለውጥ ጉባኤ በኢትዮጵያ ለሶሰርተኛ ጊዜ ሲካሄድ ከተሳተፉት በከፊልምስል Seyoum Getu/DW

የጸባይ ለውጥ ጉባኤ በአዲስ አበባ

ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የተጀመረውና ለሶስት ቀናት በሚቀጥለው ጉባኤ ከጤና አጋር ድርጅቶች እና ከአገሪቱ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች ታድመውበት የተለያዩ ጥናቶችም እየቀረቡ ይገኛል፡፡

ወጣቱ  ተመራማሪ

እዮብ ከተማ ይባላል፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በስነባህሪ ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ትምህርት እና ፕሮሞሽን የሙያ ማህበር ጋር ባዘጋጁት አገር አቀፍ የማህበራዊ እና የጸባይ ለውጥ ጉባኤ ላይ  ተሸልመዋል፡፡ ከ300 በላይ አገር አቀፍ እና ዓለማቀፍ ተሳታፊዎች በታደሙበት በዚህ መድረክ በዘርፉ ለተጉት በርካታ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የእውቅና ሽልማት ተሰጥቶአቸዋል፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱ የሆነው  ወጣቱ አጥኚ እዮብ ከተማ፤ ከ30 በላይ ጥናቶችን በዘርፉ በማካሄድ አሳትሟል፡፡ 20ዎቹ ደግሞ በመታተም ሂደት ላይ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ “ጥናቶቼ የማህበረሰቡን ባህሪ እንዴት እንቀይረው በሚል ላይ ነው የሚያጠነጥኑት፡፡ በዚህም በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ባህሪ ለውጥ ማዕከል እስከ ማቋቋም ደርሰናል” ነው ያሉት፡፡

ወጣቱ አጥኚ እዮብ ከተማ ስለ ጥናታቸው ግብ ሲያስረዱም፡ “የጥናት ግብ ክፍተቶችን ማሳየት ነው፡፡ የችግሩን መነሻ እና ምንጩ ስታሳይ ቀሪው ስራ የፖሊሲ አውጪዎች ስራ ነው የሚሆነው፡፡ በዚያው ሂደት የባህሪ ለውጥ ቀስ በቀስ እየፈጠረ ይሄዳል” ብለዋል፡፡

የማህበረሰባዊ የጸባይ ለውጥ ውጤት ለምን?

ማህበረሰባዊ የጸባይ ለውጥ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን መልካም ልማዶች እያበረታቱ ጎጂዎችን በሌላ መተካት ነው የሚሉት የጥናትና ምርምር ባለሙያው፤ አሁን አሁን በኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ የጸባይ ለውጥን የመፍጠሩ አስፈላጊነት ጉልህ እንደሆነም ያምናሉ፡፡ በጤና ረገድ ሊመጣ የሚችለው የማህበረሰቡ የባህሪ ለውጥ የበርካታ ለውጦች ድምርም ነው ይላሉ፡፡ “አሁን በፖለቲካ በኩል የምናየው ቀውስ እንኳ ሁሉም ማህበረሰብ ሃይማኖቱን፣ ባህልና ወጉን በሚገባ ቢያከብር ሊከሰት የሚችልበት መንገድ ባልኖረ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል አሁን አሁን ለጋሾች እንኳ በዚህ የባህሪ ለውጥ ላይ አተኩረው እየሰሩ ያሉት፡፡ ከጤና አኳያም አስፈላጊው የባህሪ ለውጥ ካልመጣ ሰውን በማከም ብቻ ማዳን አዳጋች ነው” ብለዋል፡፡

የአገር አቀፍ የማህበራዊ እና የጸባይ ለውጥ ጉባኤ በኢትዮጵያ
የአገር አቀፍ የማህበራዊ እና የጸባይ ለውጥ ጉባኤ በኢትዮጵያ ምስል Seyoum Getu/DW

ቅንጅታዊ አሰራር አስፈላጊነት

ሲስተር አጸደ ከበደ ደግሞ በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ስር በተለያዩ ማህበረሰብ ተኮር ስራዎች ላይ ላለፉት 38 ዓመታት ባበረከቱት የጥናትና ምርምር ስራዎች የህይወት ዘመን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ እንደ እሳቸውም አስተያየት የማህበረሰብ ለውጥ ማምጣት በሁሉም ዘርፍ ውጤት ማስገኘትና በሂደቱም ቅንጅታዊ ስራን የሚሻ ነው ይላሉ፡፡ “የማህበረሰብ ለውጥ የሚመጣው ቅንጅት ሲኖር ነው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ ተመገቡ ከማለት አስቀድሞ የኢኮኖሚ ችግሩን መቅረፍ ይሻል፡፡ የማህበረሰብ ባህሪ ለውጥ የሚመጣውም ከአማራጮች ጋር ሲቀርብ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተውናል፡፡

ኢትዮጵያ ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ ባዘጋጀችው የማህበራዊ ባህሪ ለውጥ አገር አቀፍ ኮንፈረንስ በዘርፉ የሚሰሩ በርካታ አገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ተገነ ረጋሳ እንደሚሉትም ማህበረሰባዊ የባህሪ ለውጥ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል አይነተኛ መሳሪያ ነው፡፡ “ይህ የስራ ዘርፍ ከዚህ በፊት ብዙም ትኩረት ያገኘ አልነበረም፡፡ ግን ደግሞ እጅጉን አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡ በሽታን አስቀድሞ የመከላከል ስራችንን ተግባራዊ ለማድረግ ሁነኛ መሳሪያ ነው” ብለዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ማንተጋፍቶት ስለሺ