የጨረቃ መንደርና የሳተላይቶቹ መጻኤ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 25.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የጨረቃ መንደርና የሳተላይቶቹ መጻኤ

በኅዋው ሳይንስ ከፍተኛ እመርታ ካስመዘገቡ የለማችን ተቋማት መካከል ግንባር ቀደሙ የአውሮጳ የኅዋ ምርምር ማዕከል የጨረቃ መንደር ምስረታ እና ሳተላይቶች ላይ የተጋረጡ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል መክሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:15

ፍለጋው አያልቅም

የአውሮጳ የኅዋ ምርምር ማዕከል ረቡዕ፤ ጥር 10 ቀን 2009 ዓ ም ዓመታዊ ፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ውስጥ ዓመታዊ ጋዜጣዊ መግለጫውን ሰጥቶ ነበር።  በኅዋው ሳይንስ ዘርፍ የማዕከሉ ያለፉ ሥራዎች እና የወደፊት ዕቅዶችን የዳሰሰ ነበር መግለጫው። የተቋሙ የወደፊት ዕቅዶቹንም አስቃኝቷል። የጨረቃ መንደር ምስረታ እና ሳተላይቶች ላይ የተጋረጡ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻልም የምርምር ማዕከሉ መክሯል። ከኅዋ ላይ ሆኖ ከርሰ ምድርን በሺህ ኪሎ ሜትሮች ጥልቀት ግሉ ብረቷን ከሚዳስሰው ሳተላይት አንስቶ በጥልቊ ኅዋ ድምጽ አጥፍቶ እስከሚከንፈው ሳተላይት ድረስ ብዙ ተብሏል። ከሳተላይቶች የወደፊት ዕጣ አንስቶም ጣሊያንን የመታው ብርቱ ርእደ-መሬትን እስከተነተነው ሳተላይት ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ነሐሴ 18 ቀን 2008 ዓም ጣሊያን ውስጥ የተከሰተው ብርቱ የመሬት መንቀጥቀጥ የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፏል። ከጣሊያን እንብርት የአፔኒነስ ተራሮች የተነሳው በሬክተር ስኬል 6,2 የተመዘገበው ርእደ-መሬት የ293 ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ይታወሳል። ርእደ-መሬቱ በትክክል የተቀሰቀሰበት ቦታ እና ያደረሰውን ጥፋት ሴንቲኔል አንድ ኤ (Sentinele 1A) በተሰኘችው ሳተላይ በመታገዝ የአውሮጳ የኅዋ ማዕከል ዝርዝር መረጃዎችን ሰጥቷል።

 

ሴንቲኔል አንድ ኤ ወደ ኅዋ የተወነጨፈችው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 ነው። ሳተላይቷ ኅዋ ላይ የምትንቀሳቀስበት ኃይል ከፀሐይ እንድታገኝ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ሳህን ተዘርግቶላታል። ይህ የኃይል ማመንጫ ሳህን ግን ከሁለት ዓመት በኋላ የሚያመነጨው ኃይል መቀነሱን ሳይንቲስቱ ደርሰውበታል። ምንም እንኳን የኃይል ማመንጫው ከፊል ብልሽት ሳተላይቱ ሥራውን ባያስተጓጉለውም ኅዋ ላይ በሚወረወሩ በርካታ ስብርባሪዎች ዳግም ጉዳት እንዳያደርስበት ሊጤን እንደሚገባም በመግለጫው ወቅት ተገልጧል። 

67ፒ ቹሪዩሞቭ ጌራሲሜንኮ የተሰኘው የኮከብ ስባሪ ግዛትን ለማሰስ ከ12 ዓመታት በፊት ወደ ኅዋ የተወነጨፈችው የሮዜታ ተልዕኮም መስከረም 20 ቀን 2009 ዓመት ከረፋዱ 11 ሰአት ከ19 ደቂቃ ላይ ተግባሯ አክትሟል። ኮከብ ስባሪ ላይ ተወርውራ በመላተምም እዛው ከስማለች።

ሮዜታ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ጥር 2014 ላይ እንድትነቃ ከመደረጉ አስቀድሞ በጥልቊ ኅዋ ውስጥ ለ31 ወራት ሁሉ ነገሯን አጥፍታ ከተግባር ውጪ ኾና ነበር። ሮዜታ የከዋክብት ስባሪዎች ምኅዋርን ቀርባ በማጥናት የመጀመሪያዋ ሳተላይት ናት። 

ሳተላይቶች የመጨረሻ ግባቸውን ሲመቱ እዛው ኅዋ ላይ እንዲከስሙ ነው የሚደረገው። ሮዜታ ሳተላይት ተላትማ ራሷን በራሷ ከማክሰሟ በፊት የነበረውን ምስል መስከረም 30ቀን 2016 ዓ.ም ማለዳ ላይ ልካለች። ይህም በመግለጫው ተጠቅሷል። የአውሮጳ ኅዋ ተቋም በዋና ኃላፊው ያን ቮርነር በኩል ስለ ጨረቃ መንደር ምሥረታ ምን እየተደረገ እንደሆነም ይፋ አድርጓል።

«የጨረቃ መንደር በጽንሠ-ሐሳብ ደረጃ ያለ ነው። ያ ማለት እኛ እንደ አውሮጳ የኅዋ ተቋም ጥሪ ያስተላለፍነው በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች አካላት ወደ ጨረቃ ተጉዘው እዚያ ከእኛ ጋር በጋራ እንዲሠሩ ነው። ያን ስንል እያንዳንዱ ነገር በዝርዝር አለን ማለት አይደለም። ግን ጨረቃን እንደ ማዕድን ቁፋሮ፣ ቱሪዝም፣ ሣይንስ እና የጨረቃ ሣይንስ ላሉ ለተለያዩ እንቅስቃሴዎች ለመጠቀም ነው። ከዚያም ባሻገር ወደ እኛ ሥርዓተ-ፀሐይ ዘልቆ ለመግባት እንደመንደርደሪያም ለመጠቀም ነው።»

ኤክሶማርስ ሳተላይትን በተመለከተም መግለጫ ተሰጥቷል። ኤክሶማርስ ወደ ኅዋ የተወነጨፈች እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠርበ2016 ዓመት ነው። በ2020 ግን ኤክሶማርስ ተሸክማው የምትዘው በሮቦት እገዛ ማርስ ላይ ቁፋሮ የሚያከናው ሮቨር በዝግታ እና በተረጋጋ መልኩ እዛው ማርስ ላይ ማረፍ ይጠበቅበታል። 

ኤክሶማርስ የማርስ ንፍቀ ክበብ ውስጥ ስትገባ የጫነችው ሳተላይት እውስጡ የተገጠመው ኮምፒውተር ሞተሩ ለሦስት ሰከንድ ብቻ ከሠራ በኋላ እንዲጠፋ በማድረጉ ሳተላይቱ የማርስ ንጣፍን የረገጠችው በከባድ ምት ነበር። 

እንደ ዕቅዱ ቢሆን ኖሮ ሳተላይቱን የጫነችው መንኲራኲር መጀመሪያ  የማርስ ንፍቀ-ክበብ ውስጥ እየከነፈች ጥሳ ትገባለች። በከፍተኛ ፍጥነት ስትከንፍም ነበልባላዊ ግለት ይፈጠራል። ግለቱን መከላከያውም ከሳተላይቱ ተነጥሎ ይወድቃል። ሳተላይቱ ፍጥነቱን ለማረጋጋት ግዙፍ ዣንጥላ ትዘረጋለች። ከዚያም ፍጥነቱ መቀነስ ሲጀምር እና የተፈለገው ርቀት ላይ ሲደረስ የተገጠመለት ሞተር ተነስቶ ሥራ ይጀምራል። ሞተሩ መነሳት እስኪጀምር ድረስ ሁሉም ነገር በታቀደለት መሠረት ነበር የተከናወነው።

ከ3 ሰከንድ በኋላ ሞተር መጥፋቱ የተከሰተው ሳተላይቱ ላይ የተገጠመው ኮምፒውተር የማርስ ዝቅተኛው ከባቢ አየር ውስጥ የገባ ስለመሰለው ነበር ተብሏል። ከሦስት ዓመት በኋላ ማርስ ላይ ቁፋሮ የሚያከናውነው ሮቨር መሰል ችግር እንዳይገጥመው ሳይንቲስቶች ከወዲሁ ጥልቅ ምርምር እያከናወኑ ነው። ከ3 ሰከንድ በኋላ ሞተር መጥፋቱ በዓለም የኅዋ ጠቢባን በጥልቀት ጥናት ይከናወንበታል ተብሏል። ሆኖም በኤክሶማርስ ተጭና የሄደችው የማርስ ከባቢ አየር ቃኚ ሳተላይት ግን በታቀደላት መሰረት ሜታን እና ሌሎች ጋዞችን የማሠሥ ተግባሯን እየፈጸመች መኾኗ ተገልጧል። ጋዞቹን ማጥናቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በአውሮጳ የኅዋ ምርምር ማዕከል የ«ኤክሶማርስ» ተልዕኮ ሣይንቲስት ዮርጌ ቫጎ ቀደም ሲል እንዲህ ብለው ነበር።

«ከማርስ ኤክስፕረስ እና ከሌሎች ተልዕኮዎች ባገኘነው መረጃ መሠረት ሜቴይን ዋነኛ መነጋገሪያ ነጥብ ሆኗል። ስለዚህ የሜቴይን ምንጭን በማርስ የትኛው ክፍል መቼ እንደተመረተ እንዲሁም እንዴትስ ሊጠፋ እንደሚችል ለመረዳት መሞከር እጅግ በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው።»

የኤክሶማርስ ተልዕኮ ምድር ላይ ቅራኔ የገቡ ሃገራትን ጭምር በአንድ ላይ ያሰባሰበ ነው። ለአብነት ያህል፦ምንም እንኳን የአውሮጳ ኅብረት በዩክሬን ቀውስ ከሩስያ ጋር እሰጥ አገባ ቢገጥምም፤ በኤክሶማርስ ተልዕኮ ግን ሩስያውያን ከአውሮጳ ኅብረት ጋር ተባብረው ሠርተዋል። በአውሮጳ የኅዋ ምርምር ማዕከል የኤክሶማርስ ተልዕኮ የጀርመን፣ የፈረንሳይ፣ የጣሊያን፣ የሩስያ እና የታላቋ ብሪታንያ የኅዋ ማዕከላት ተሳታፊ ናቸው። ሃገራቱ በጋራ የላኳቸው ሳተላይቶች የሰአት ችግር እንደገጠማቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል። 

ሳተላይቶች ወደ ኅዋ ሲወነጨፉ ከምድር ውጪ ጊዜን የሚቆጥሩበት ልዩ ሰአት ተገጥሞላቸው ነው። የሰአት ችግር የተፈጠረባቸው የጋሊሊዮ ሳተላይቶች እንደሆኑም ተገልጧል። ሆኖም  የአውሮጳ የኅዋ ምርምር ማዕከል ዋና ኃላፊ ያን ቮርነር ሰአቶቹ ብልሽት ቢገጥማቸውም ሳተላይቶቹን ከመሥራት አላገዱም ብለዋል።

«የሳተላይት አሠሣ በዋናነት እላዩ ላይ በተገጠሙለት ሰአቶች ጥገኛ ነው። ይኽን ሁሉም ሊረዳው ይገባል። እናም በበርካታ ሳተላይቶቻችን ላይ የሰአት ችግር መፈጠሩን አሳውቄያለሁ። በእያንዳንዱ ሳተላይት አራት ሰአቶችን ገጥመናል። የዕድል ጉዳይ ሆኖ ሳተላይቶቹ ላይ የተገጠሙት አንዳንዶቹ ሰአቶች መሥራት አቁመዋል። ግን ጨዋታው እዚህ ጋር ነው። ማለቴ፤ በእያንዳንዱ ሳተላይት አራት ሰአቶችን የገጠምነው ለዚሁ ነው። አንዱ ሲበላሽ በሌላኛው ለመጠቀም። ስለዚህ ዛሬ መግለጥ የምሻው አንድም ሥራ ያቆመ ሳተላይት እንደሌለ ነው። ሁሉም ይሠራሉ።»

ሳተላይቶቹ ላይ የተገጠሙት ሰአቶች ሩቢዲዩም እና ሀይድሮጂን ሜዘር ይሰኛሉ። ሁለቱም የሰአት አይነቶች ብልሽት ስለገጠማቸው ለወደፊቱ ችግሩን ለመፍታት የምርምር  ማዕከል ጥረት እንደሚያደርግ ገልጧል። ሰአቶቹ በድጋሚ እንዲሠሩ ማድረግ ይቻል አይቻል ግን ለጊዜው የሚታወቅ ነገር የለም። የሰአት ችግር በመፈጠሩ እስካሁን ሥራ ያቆመ አንድም ሳተላይት አለመኖሩ ግን እርግጥ ነው። 3 የሩቢዲዩም እና 7 የሀይድሮጂን ሜዘር ሰአቶች ሥራ ማቆማቸውን የአውሮጳ የኅዋ ተቋም ይፋ አድርጓል።

«የሚሠሩ ሰአቶች በቁጥር ከሁለት በታች ያላቸው ሳተላይቶች የሉም። ሌሎቹም እንዲሠሩ ለማድረግ መላ እየሻትን ነው። ጋሊሊዮ በእርግጥም ለረዥም ጊዜ ያለእንከን መሥራት የምትችልበትን ዘዴ እያፈላለግን ነው።»

እስካሁን የአውሮጳ የኅዋ ምርምር ማዕከል ንብረት የሆኑ 15 ጋሊሊዮ ሳተላይቶች ኅዋው ላይ ይሳንፈፋሉ። አንዳቸውም ተግባራቸው አልተቋረጠም። የአውሮጳ የኅዋ ምርምር ማዕከል አሠሣም በጥልቀት ሳይቋረጥ መቀጠሉ አይቀርም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ
 

Audios and videos on the topic