የጦር ወንጀል ስጋት በየመን | ዓለም | DW | 18.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የጦር ወንጀል ስጋት በየመን

የየመን ተቀናቃኝ ሀይሎች የጦር ወንጀል ሳይፈጽሙ አይቀርም ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰሰ። የሑቲ አማጽያን፤የአብደረቦ መንሱር ሐዲ ታማኞችና ሳዑዲ አረቢያ መራሹ የአየር ጥቃት ንጹሃን ዜጎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ጥቃት ፈጽመዋል የሚክ ክስ ቀርቦባቸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:29
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:29 ደቂቃ

የጦር ወንጀል ስጋት በየመን

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የየመን ተቀናቃኝ ሃይሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል ሲል ከሰሰ። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በሑቲ አማጽያን፤የአብድረቦ መንሱር ሐዲ ታማኞችና የሳዑዲ አረቢያና አጋሮቿf የአየር ጥቃት የተፈጸመው ግድያ የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ ያደረገው ዘገባ ሳዑዲ አረቢያና አጋሮቿ የአየር ጥቃቱን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በመኖሪያ ቤታቸው፤የስራ ቦታቸው አሊያም በትምህርት ቤቶች ሰዎች መገደላቸውን ያትታል። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የየመን ተመራማሪዋ ራሻ መሐመድ የሳዑዲ አረቢያና አጋሮቿ የአየር ድብደባ ንጹሐንን ከጦር ዒላማዎች አለመለየቱን ይናገራሉ።

«በሳዑዲ አረቢያ ከሚመራው ትብብር ስምንት የአየር ድብደባዎችን መርምረናል። እነዚህ የአየር ድብደባዎች በጦርነት ህግጋት ግዴታ የሆነውንና የንጹሐንን ሞት ለመቀነስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አላደረጉም። እንዲህ አይነት የአየር ድብደባዎች በንጹሃን ላይ ሞትና የመቁሰል አደጋ በማስከተላቸው እንደ ጦር ወንጀል ሊወሰዱ ይችላሉ። እነዚህ የአየር ጥቃቶች ትምህርት ቤቶችን ፣መጠለያ ያጡ ሰዎችን፣ገበያዎችን፣ሰዎች የሚጸልዩባቸውን መስጊዶች ኢላማ አድርገዋል። በአካባቢዎቹ የጦር ኢላማ የነበረ ለመሆኑ ማረጋገጫ የለም።»

ሳዑዲ አረቢያ መራሹ የአየር ጥቃት በሆዴይዳ ከተማ የእርዳታ ድርጅቶች እቃ መጫኛዎችንና መጋዘኖችን ማጋየታቸው ተሰምቷል። ትናንት የታዒዝ ከተማን ለመቆጣጠር በተደረገ ከባድ ውጊያ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ80 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል። በሰሜንና ደቡባዊ የመን ቁልፍ ቦታ ላይ የምትገኘውን የታዒዝ ከተማ ለመያዝ የሚደረገው ፍልሚያ አሁንም አልበረደም። የሑቲ አማጽያንና የቀድሞው ፕሬዝዳንት አሊ አብደላ ሳሌህ ታማኞች በከተማዋ የሚገኙ ተዋጊዎቻቸውን ማጠናከራቸው ተነግሯል። ራሻ መሐመድ መሐመድ በየመን የሑቲ አማጽያንና የአብደረቦ መንሱር ሐዲ ታማኞች ንጹሃን ዜጎች ለሞት ለሚያደርስ ጥቃት አጋልጠዋል ይላሉ ።

«በኤደንና ታዒዝ ከተማ የተፈጸሙ 30 ክስተቶችን መርምረናል። የሑቲ አማጽያንና ተቃዋሚዎቻቸው ሞርታርና ከባድ መሳሪያዎችን በመኖሪያ መንደሮች ላይ ተኩሰዋል። በዚህም 68 ንጹሃን ሰዎች ተገድለዋል።ከሆስፒታልና የትምህርት ቤቶች አካባቢዎች ጥቃት ፈጽመዋል። በዚህም ንጹሀን ዜጎችን ለጥቃት አጋልጠዋል።»

የሳዑዲ አረቢያ መራሹ የአየር ጥቃት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 1,950 ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውንና 4,271 ደግሞ መቁሰላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ የጦር ወንጀል መፈጸም አለመፈጸሙን በገለልተኝነት የሚያጣራ ኮሚሽን ሊያቋቁም ይገባል ሲል ጥሪ አቅርቧል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዝምታ «አስደንጋጭ ነው» የሚሉት ራሻ መሐመድ በየመን ካሁኑ የባሰ አሰቃቂ ክስተት ከመግጠሙ በፊት ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ይናገራሉ።

«የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዝምታ በጣም አስደንጋጭ ነው። ጥሪያችን ጀርመንና የአውሮጳ ህብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጦር ወንጀል ሊሆን የሚችለውን ጥሰት አድምጠው እንዲቃወሙ ነው። ይህን ማድረግ ካልተቻለ በየመን ይቅርታ የማያሰጥ ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል።»

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic