የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ምን ይዟል? | ኢትዮጵያ | DW | 16.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ምን ይዟል?

የኢትዮጵያ መንግሥት የጦር መሳሪያ አያያዝ እና ዝውውርን የሚቆጣጠር ጠበቅ ያለ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቷል። በረቂቁ መሠረት የጦር መሳሪያ መታጠቅ የሚችለው ማነው? ቁጥጥሩንስ ማን ያከናውናል?

የኢትዮጵያ መንግሥት የጦር መሳሪያ አያያዝ እና ዝውውርን የሚቆጣጠር ጠበቅ ያለ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቷል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ይኸው ረቂቅ አዋጅ በኢትዮጵያ ሕግ የጦር መሳሪያ መታጠቅ የሚፈቀድበት ሁኔታ፣ የጦር መሳሪያ አያያዝ እና ዝውውርን የሚደነግግ ነው።

ማን ይቆጣጠራል?

ይኸው ረቂቅ አዋጅ የጦር መሳሪያ አስተዳደርን የመቆጣጠር ሥልጣን ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወይም ዉክልና ለሚሰጣቸው የክልል የፖሊስ ኮሚሽኖች ይሰጣል። የመቆጣጠር ኃላፊነት የሚጣልበት ተቋም "በስሩ ብሔራዊ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር የስራ ክፍል አደራጅቶ" አዋጁን የማስፈጸም ግዴታ አለበት።

ተቆጣጣሪው "የጦር መሳሪያ ለመጠቀም ፈቃድ መስጠት እና ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ አጠቃቀምን መቆጣጠር፣ ጉዳት አድራሽ ዕቃዎች ወደ ሀገር ማስገባት፣ ማምረት፣ ማዘዋወር፣ ማከማቸት፣ መሸጥ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ እና ፈቃድ በሚወጣ ደንብ መሰረት መስጠት፣ መቆጣጠር" ይጠበቅበታል። የጦር መሳሪያ ለመታጠቅ የተሰጠ ፈቃድን ማገድ፣ መሰረዝ እንዲሁም "ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት አስጊ ሆኖ የተገኘን ማንኛውንም ፍቃድ ያለውንም ሆነ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ የታጠቀን ሰው የማስፈታትና የመውረስ" ሥልጣንም ተሰጥቶታል።

ማን መታጠቅ ይችላል?

በረቂቅ አዋጁ መሰረት በልማድ የጦር መሳሪያ ለሚታጠቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድ ሰው አንድ የጦር መሳሪያ የመታጠቅ ፈቃድ ይሰጣል። በረቂቅ አዋጁ "በተለምዶ የጦር መሳሪያ የሚያዝባቸው አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ" ግለሰቦች ተቆጣጣሪ ተቋም በየአካባቢያቸው በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በአንድ አመት ውስጥ በአካል ቀርበው የጦር መሳሪያ ለመታጠቅ ፈቃድ መጠየቅ እንደሚኖርባቸው ይደነግጋል። ረቂቅ አዋጁ እንደሚለው ተቆጣጣሪው ተቋም በሚሰጠው የጊዜ ገደብ ፈቃድ ያልወጣበት የጦር መሳሪያ በመንግሥት ይወረሳል።

የጦር መሳሪያ መታጠቅ የፈለገ ግለሰብ በአዋጁ የተቀመጡ መሥፈርቶችን ካሟላ ሥልጣን በተሰጠው ተቋም ፈቃድ ይሰጠዋል። ፈቃዱን ለማግኘት አመልካች ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው አሊያም በኢትዮጵያ የመኖር ፈቃድ የተሰጠው መሆን ይኖርበታል።

ፈቃዱን ለማግኘት "የአደገኛ ዕፅ ወይም የመጠጥ ሱስ የሌለበት፣ ቋሚ አድራሻ እና መተዳደሪያ ገቢ ያለው፣ በሙሉ ወይም በከፊል በፍርድ ወይም በሕግ ችሎታውን ያላጣ፣ የአዕምሮው ሁኔታ የተስተካከለ እና አላስፈላጊ የኃይል አጠቃቀም ባህሪ የሌለው መሆኑ በተቆጣጣሪው ተቋም የታመነበት" ሊሆን ይገባል።

የጦር መሳሪያን አጠቃቀም ስልጠና መሳተፍ፤ ለጦር መሳሪያ ፈቃድና እድሳት አስፈላጊውን ክፍያ መክፈል፣ ከሚኖርበት አካባቢ አስተዳደር መልካም ስነ-ምግባር ያለው ለመሆኑ የትብብር ደብዳቤ ማቅረብ የሚችል እንዲሁም የጦር መሳሪያ ለመያዝ በቂ እና አሳማኝ ምክንያት ያለው መሆን በረቂቅ አዋጁ ከተዘረዘሩ መሥፈርቶች መካከል ይገኙበታል።

በተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የሚሰጠው ፈቃድ የጦር መሳሪያ ለመታጠቅ ፈቃድ የተሰጠው  ሙሉ ስም፣ ፎቶ፣ የትውልድ ቀን፣ አድራሻ፣  የጦር መሳሪያውን አይነት፣ የውግ ቁጥር፣ የጥይት ብዛት፣ ተዛማጅ እቃ፣ ፈቃዱን የሰጠው ባለስልጣን ስም፣ ፊርማ፣ ማህተም፣ ፈቃዱ የተሰጠበት ቀን እና ፈቃዱ የሚያበቃበት ቀን ይሰፍርበታል።  ፈቃድ የሚሰጠው የጦር መሳሪያው መለያ ቁጥር ሊኖረው እንደሚገባ በዚሁ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተገልጿል። ይኸ ፈቃድ ለግለሰቦች በሁለት አመት ለድርጅቶች በአምስት አመት ይታደሳል።

ረቂቁ የጦር መሳሪያ ባለቤትነት ሊሰረዝ የሚችልባቸውን ምክንያቶች ዘርዝሯል። ከእነዚህ መካከል "መሳሪያው ወንጀል የተፈፀመበት መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ" የሚለው ቀዳሚው ነው። በረቂቁ መሰረት "ባለፈቃዱ ሲሞት፣ ያለበት አድራሻ ሳይታወቅ ሲቀር ወይም በፍርድ ወይም በህግ ችሎታውን ሲያጣ" የመሰረዝ ዕድል ይገጥማዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ ፈቃድ የተሰጠው ድርጅት ከፈረሰ ወይም ከተዘጋ፣ ፍርድ ቤት ፈቃዱ እንዲሰረዝ ከወሰነ፣ ባለፈቃዱ በራሱ ፍላጎት ፈቃዱን ከመልሰ፣ ፈቃዱን ለማግኘት ከሚያስፈልጉ መስፈርቶች አንዱ የተጓደለ መሆኑ ከታወቀ ሊሰረዝ ይችላል።

አይቻልም!

ረቂቁ ሲጸድቅ ሰላማዊ ሰልፍ ወይም አድማ በሚደረግባቸው፣በምርጫ ሕግ ወይም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚወሰኑ ፣ በሆቴሎች፣ በሲኒማና ትያትር ቤቶች፣ በሙዚየሞችና ተመሳሳይ በሆኑ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፣በትምህርት ተቋማት፣ በሀይማኖትና እምነት ተቋማት ግቢ ውስጥ፣ እና በሆስፒታልና ክሊኒኮች፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች እና በሌሎች ተመሳሳይ ለህዘብ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ስፍራዎች የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት ይከለከላል።

በረቂቅ ሕጉ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የእምነት ተቋማት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት እንዲሁም የትምህርት ተቋማት ለጥበቃ ከሚያስፈልጋቸው ውጪ የጦር መሳሪያ አይሰጣቸውም።

ረቂቅ አዋጁ ካለፈቃድ "የጦር መሳሪያ፣ የጦር ሜዳ መነፅር፣ በጦር መሳሪያ ላይ ሊገጠም የሚችል ማንኛውም አይነት መነፅር ወይም የጦር መሳሪያ ሲተኮስ ድምፅ ለማስወገድ የሚያገለግል መሳሪያ ወደ ሀገር ማስገባት፣ ከሀገር ማስወጣት፣ መያዝ፣ ማስቀመጥ፣ ማከማቸት፣ መገልገል፣ ማሳየት፣ መደለል፣ መሸጥ፣ መግዛት፣ ማስተላለፍ፣ ማዘዋወር፣ ማጓጓዝ፣ ማምረት፣ ማሰልጠን፣ መጠገን ወይም ማስወገድ" ይከለክላል።

ቅጣት

ረቂቅ አዋጁ ጸድቆ ሥራ ላይ ሲውል አዋጁን "የተላለፈ ከአንድ አመት እስከ ሶስት አመት በሚደርስ ቀላል እስራት እና ከአምስት ሺህ እስከ አስር ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ" ይቀጣል።

ባለፈው ሚያዝያ በረቂቁ ላይ የተወያየው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውጭ ጉዳይ እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ እንዲሁም ለሕግ ፍትኅ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች መርቶታል።

 

ተዛማጅ ዘገባዎች