የጦር መሣሪያ ንግድ፤ የጥሬ ዕቃዎች ዋጋ መናር | ኤኮኖሚ | DW | 17.03.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጦር መሣሪያ ንግድ፤ የጥሬ ዕቃዎች ዋጋ መናር

ለነገሩ ሶሻል ዴሞክራቶችና አረንጓዴዎች የተጣመሩበት የበርሊን መንግሥት የጦር መሣሪያ የውጭ ንግድን በተመለከተ ቁጥብ ፖሊሲ እንደሚከተል ሲያስታውቅ ነው የቆየው። ግን ጉዳዩ ሲበዛ አሻሚ መሆኑ አልቀረም። በአሕጽሮት BITS በመባል የሚታወቀው በርሊን ላይ ተቀማጭ የሆነ የትራንስ አትላንቲክ ጸጥታ መረጃ ማዕከል ባለፈው ሣምንት ባካሄደው የጠበብት ጉባዔ በዚሁ ሲበዛ ሽፍንፍን በሆነው የንግድ ዘርፍ ላይ አተኩሮ ነበር።

ቢትስ በጸጥታና ወታደራዊ ፖሊሲዎች አኳያ ነጻ ሆኖ ምርምር የሚያካሂድና መሠረታዊ መረጃዎችን የሚያቀርብ ምንጭ አድርጎ ነው ራሱን የሚመለከተው። ለተግባሩ አስፈላጊ የሆነውን በጀት የሚያገኘውም ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ዓለምአቀፍ ተቋማት ነው። ከነዚሁ መካከል የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት፣ ዓለምአቀፉ የተፈጥሮ ጥበቃ ቡድን ግሪንፒስ፣ የፎርድ ፋውንዴሺንና ለጀርመኑ አረንጓዴ ፓርቲ ቀረብ ያለው በጎ አድራጎት ማሕበር ሃይንሪሽ በል ሽቲፍቱን ይገኙበታል።

የጀርመን ጥምር መንግሥት የጦር መሣሪያ የውጭ ንግዱን በተመለከተ ባለፈው ታሕሳስ ወር ያወጣው የ 2003 ዓመታዊ ዘገባ የተነሳበትን የቁጥብነት ዓላማ የሚጻረር ወይም ገደቡን ያላከበረ ነው። የጦር መሣሪያ ንግዱ ውጥረት በበዛበት በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ የሚገኙ አገሮችንም ይጠቀልላል። ይህ ደግሞ የጥምሩን መንግሥት አረንጓዴ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ክላውዲያ ሮትን ጨምሮ ብዙዎች የንግዱን ተቃዋሚዎች ነው ያስቆጣው።

በዘገባው መሠረት የመንግሥቱን ፈቃድ አግኝቶ ለውጭ ንግድ የቀረበው የትጥቅ ምርት በ 4.9 ሚሊያርድ ኤውሮ ይገመታል። ይህም ቀደም ካለው 2002 ዓ.ም. ሽያጭ ሲነጻጸር በግማሽ፤ ማለት 50 በመቶ ከፍ ያለ መሆኑ ነው። የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር መሥሪያ ቤት የንግዱ ዋጋ ሲበዛ ለጨመረበት ሁኔታ ምክንያቱ አንዳንድ ተናጠል ሽያጮች፤ ለምሳሌ ከደቡብ አፍሪቃና ከማሌዚያ በከፍተኛ ደረጃ በመከናወናቸው ነው ይላል።

ሆኖም ይህን መሰሉ ምክንያት አረንጓዴዋን ፖለቲከኛ ክላውዲያ ሮትንም ሆነ የበርሊኑን የትራንስ አትላንቲክ ጸጥታ መረጃ ማዕከል አዋቂዎች የሚያረካ ሆኖ አይገኝም። የማዕከሉ ባልደረባ ክሪስቶፈር ሽታይንሜትስ እንዲያውም የጀርመን መንግሥት በዓለምአቀፍ ደረጃ እንዲካሄድ በሚያደርገው የትጥቅ ዕቃዎች ንግዱ በማይገባው ቦታ በጦር መሣሪያ አካልነት ተግባር ላይ እንዲውሉ አብቅቷል በማለት ይወቅሳሉ።

“የጀርመን ምርቶች ያለተባበሩት መንግሥታት ፈቃድ በተካሄደው በኢራቅ ጦርነት እንደታየው ሁሉ በየፍልሚያው ቦታ ይገኛሉ። የብሪታኒያና የአሜሪካ የጦር መሣሪያ ዘዴ አካላት ናቸው። መካከለኛውን ምሥራቅ በመሰለው የቀውስ አካባቢ በሰፊው የተሰራጩ ሲሆን የእሥራኤል፣ ግብጽ፣ ሳውዲት አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤሚሮች ግዛት ታንኮች በጀርመን መሣሪያ ጥበብ ነው የሚንቀሳቀሱት። መሣሪያዎቹ በሰብዓዊ መብት ረገጣ በተወነጀሉ ወይም የእርስበርስ ጦርነት ወደሚያካሂዱ ሕንድን፣ ኢንዶኔዚያንና ቤላሩስን ወደመሳሰሉ ሃገራትም ይላካሉ።”

ክሪስቶፈር ሽታይንሜትስ እንደሚያሳስቡት የጀርመን ፌደራል መንግሥት በዚህ መስክ የሚከተለውን የውጭ ንግድ መርሁን ከአጠቃላዩ ጦር መሣሪያ ቁጥጥር ሕግ መስፈርት ጋር ማጣጣም ይኖርበታል። ለምሳሌ የባሕር ውስጥ ጀልባ U-Boot ሞተሮች በተሟላ መልካቸው ያላንዳች ሕጋዊ ችግር ማዕቀብ ለተጫነባት ለቻይና የሚሸጡ ከሆነ ፌደራላዊው መንግሥት መስፈርቱ ተዛብቶበታል ማለት ነው። ምርቶቾ ለሲቪል ግልጋሎት ነው ሥራ ላይ የሚውሉት የሚለው ቃልም ያን ያህል የረባ ትርጉም አይኖረውም።

የበርሊኑ የጸጥታ ጠበብት ጉባዔ ያመለከተው በጦር መሣሪያው የውጭ ንግድ ዘርፍ ከተሟሉ መሣሪያዎች ይልቅ ተናጠል አካላቱን በመሸጡ አኳያ የተቀባዮቹን ሃገራት ባሕርይ በሚገባ መመርመር እንደሚገባ ነው።

“ስጋት የሚፈጥሩት ቦትሱዋናን፣ ማላዊን፣ ላኦስን ወይም ኡዝቤኪስታንን የመሳሰሉት አገሮች አይደሉም። ይልቁንም የጸጥታ ፖሊሲ አጋሮቻችን ፈረንሣይ፣ ብሪታኒያና አሜሪካ እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ በጦር መሣሪያው ምርት ዘርፍ ነብር ግዛቶች እያልን የምንጠራቸው የአዳጊ አዳጊ አገሮች ናቸው። እነዚሁ ለምሳሌ ብራዚል፣ እሥራኤል፣ ደቡብ አፍሪቃና ኮሪያ የራሳቸው የሆነ የጦር መሣሪያ አመራረር ብቃት አላቸው። በመሆኑም የጀርመንን ቴክኖሎጂ ከራሳቸው የጦር መሣሪያ ዘዴ ጋር የማጣጣም ብቃት ያላቸውና ዘግየት ብሎም ይህንኑ ወደ ውጭ ለመሸጥ የሚችሉ ናቸው።”

እንግዲህ በዚህ መንገድ የጦር መሣሪያዎቹ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የቀውስና የጦርነት አካባቢዎች ብቅ ሊሉ ይችላሉ። ከመንግሥት ነጻ የሆኑት የበርሊኑ መረጃ ማዕከልና ኦክስፋም-ጀርመን ደግሞ ይህን አዙሪት ለመግታት ነው የሚፈልጉት። እርግጥ የኦክስፋም መሪ ፓውል ቤንዲክስ እንደሚሉት የድርጅታቸው አቋም በጠቅላላው ጸረ-ጦርነት አይደለም። “የጦር መሣሪያዎች ሕግና ሥርዓትን፣ እንዱሁም ጸጥታን ለማስከበርና ተገቢ ለሆነ የመከላከል ዓላማ ጥቅም ላይ መዋላቸውን እናከብራለን።” ሆኖም ለጦር መሣሪያ ከሚፈሰው በብዙ ሚሊያርድ የሚተመን ወጪ ሰፊ ድርሻ ድህነትን ለመታገል ሥራ ላይ መዋል እንዲችል ገደብ መበጀት ይኖርበታል። በመሠረቱ ኦክስፋም ክብደት የሚሰጠውም ለዚሁ ለኋለኛው ጉዳይ ነው።

ወደ ሁለተኛው የፕሮግራማችን ርዕስ እንሻገርና በዓለም ገበያ ላይ የነዳጅ ዘይት፣ ከሰል፣ ብረታ-ብረት፣ አሉሚኒዬምና መዳብ እንዲሁም ሌሎች ጥሬ ዕቃዎች ዋጋ እንደዛሬው ከመጠን በላይ የናረበትና አምራቾችን ከባድ ፈተና ላይ የጣለበት ጊዜ የለም። ሁኔታው ከአሥር ዓመታት በፊት እንዲህ አልነበረም። የጀርመን ኢንዱስትሪዎች ፌደሬሺን ችግሩን መንስዔ በማድረግ የጥሬ ዕቃ ዋስትና በሚረጋገጥበት ሁኔታ የመከረ ጉባዔ ባለፈው ሣምንት አካሂዶ ነበር። በበርሊኑ የኤኮኖሚ አዳራሽ በርከት ያሉ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ተጠሪዎች ተሳትፈዋል። የጀርመን ኢንዱስትሪ ፌደሬሺን ፕሬዚደንት ዩርገን ትሁማን ስለ ጥሬው ዕቃ ዋስትና ሁኔታ እንደተናገሩት -

“ብዙዎች ኩባንያዎች በወቅቱ ከባድ ትግል ገጥሟቸው ነው የሚገኙት። የጥሬ ዕቃዎች ዋጋ በዓለም ገበያ የዶላርን ምንዛሪ መሠረት አድርገን ከተመለከትን እንኳ ከ 2003 ወዲህ 30 በመቶ ጨምሯል። ዛሬ በጥንካሬው አመቺ ሁኔታ ላይ ከሚገኘው ከኤውሮ አንጻርም 18.5 በመቶ ዕድገት መሆኑ ነው። ችግሩ ከብረታ-ብረት አንስቶ እስከ ንጥረ-ነገርና ፕላስቲክ መላውን አምራች ኢንዱስትሪ ያዳርሳል።”

በጥሬ ዕቃዎች አኳያ ለተፈጠረው እጥረት አንዱ ምክንያት በመካከለኛ የልማት ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች በተለይ የቻይና ኤኮኖሚ በፍጥነት እያደገ መምጣቱ ነው። እርግጥ ቻይና በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ታላቋ ብረት አምራች አገር ናት። ቢሆንም ምርቱን ወደ አገር በማስገባትም የመጀመሪያውን ቦታ ይዛ ነው የምትገኘው። በዓለም ላይ የሚመረተውን ከ 25 በመቶ የሚበልጠውን ብረታ-ብረት የምትፈጀውም ይህችው ግዙፍ አገር ናት። ይህ ሰፊ ፍጆታ ደግሞ የብረታ-ብረት ዋጋ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከ 40 እስከ 60 በመቶ እንዲንር ነው ያደረገው።

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ይህን ሁኔታ በቁጣ ዓይን ነው የሚመለከቱት። ኢንዱስትሪዎቻቸው በተለይ የቻይና፣ የሕንድና የሩሢያ መንግሥታት ጥሬ ሃብታቸውን በሰፊው በአገር በማከማቸት የሚፈጽሙት ድርጊት አልተዋጠላቸውም። የፉክክር እኩልነትን ማስፈን ያለበት የዓለም ንግድ ድርጅትም በበኩሉ በጉዳዩ ዕርምጃ ለመውሰድ ከአንዴም ብዙ ጊዜ ሲሳነው ነው የታየው። ድርጅቱ ለነገሩ አንድ አገር ውሱን የሆነ ጥሬ ዕቃውን ለውጭ ገበያ አላቀርብም ካለ ማድረግ የሚችለው ብዙም ነገር የለም። ሌላው ችግር ጥሬ ሃብት ባላቸው ሃገራት በሚፈጠር አለመረጋጋት የውጭ አቅርቦቱ የሚቋረጥበት ሁኔታ ነው።
ይህ እርግጥ የፖለቲካ ጥያቄ ነው። ለዚህም ነው በጉባዔው ተገኝተው ንግግር ያሰሙት የጀርመን መራሄ-መንግሥት ጌርሃርድ ሽሮደር አደጋው ባለባቸው አካባቢ እርጋታን ለማስፈን መጣሩ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ያስገነዘቡት። የሆነው ሆኖ የጥሬ ዕቃዎች በአጠቃላይና የኤነርጂ ምንጮች ችግር በተለይ አማራጭ መፍትሄዎችን ማስፈኑን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። በዚህ በጀርመን ጸሐይንና ነፋስን የመሳሰሉትን ታዳሽ የኤነርጂ ምንጮች ቴክኖሊጂ በፍጥነት በማዳበር ለችግሩ ምላሽ እንዲሰጥ የሚያሳስቡት ጠበብት ብዙዎች ናቸው። ቢሆንም በጉዳዩ በመንግሥትና በኢንዱስትሪው ተጠሪዎች መካከል ያለው የሃሣብ ልዩነት ገና መፍትሄን የሚሻ ነው። ለጊዜው፤ ማለትም ከሚቀጥሉት ዓመታት ሂደት አንጻር ቁጠባ አንዱ አማራጭ ይሆናል። ግን ይህም የአቶም ኤነርጂን እንደገና ለማነሳሳት የሚፈልገው የኢንዱስትሪው ዘርፍ የማይቀበለው ነገር ነው።