የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ዉለታ | ባህል | DW | 27.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ዉለታ

«እኛ ሃገር ባህላዊ ሆነዉ እየተከበሩ ያሉት በዓላት የሐይማኖት በዓላት ናቸዉ። የሐይማኖት በዓላት እድሜ ለአባቶቻችን እና ለእናቶቻችን ከባህላችን ጋር በደንብ አድርገዉ እንደ ጥሩ ስፊት እንደ ጥሩ ስንደዶ ማንም በማያላቅቀዉ ሁኔታ ሰፍተዋቸዋል። የካቲት 12 እኮ ዳቦ አይቆረስለት፤ ቡና አይፈላለት፤ በግ አይታደርለት ጠላ፤ አይጠመቅለት።

ጉዝጓዝ አይጎዘጎዝለት እንዴት አድርጎ ከባህላችን ጋር ሊዋሐድ ይችላል? የአዋሃደዉም ሰዉ የለ» ሲሉ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የዛሬይቱ ኢትዮጵያን ስላቆዩን ስለ ጥንት አባቶቻችን እና እናቶቻችን የድል ቀናት አከባበርና ታሪክ እየተረሳ መምጣት በተመለከተ አስተያየታቸዉን ሰጥተዉናል።

78 ተኛው የሰማዕታት ቀን ለሰማዕታቱ መታሰቢያ በቆመበት በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ሃውልትና በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በፀሎተ-ፍትሃት ሥነ-ሥርዓት ተዘክሯል። በተለያዩ ዓለም ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንም ባለፈዉ እሁድ ቀኑን በተለያዩ ዝግጅቶች አስበዉት ነዉ የዋሉት። በዘመኑ የነበሩ ኢትዮጵያዉያን የጣልያንን ቅኝ ግዛት ሙከራን ዋጋ ከፍለዉ ማቆማቸዉ በዚህ ዘመን ላለችዉ ኢትዮጵያ ምን አይነት ፋይዳ ማብርከቱን ስንቶቻችን እንረዳ ይሆን? ይህንን ቀን ማሰቡ ታሪክን ማወቁ ምን ጠቀሜታ ይኖረዉስ ይሆን ? በለቱ ዝግጅታችን የአባት አርበኞች ለኢትዮጵያ ያበረከቱት አስተዋፅዖ በታሪክ ብቻ ተፅፎ የሚቀመጥ ሳይሆን፤ ህያዉ ሆኖ እንዲኖር ታሪካችንን ማስተማር ለትዉልድ ማስተላለፍ አለብን፤ የሚሉንን እንግዶች አስተያየት አቀናብረን ይዘናል።

የአባቶች ቆራጥ የጀግንነት ቅርስ መረሳት የለበትም ሲሉ የገለፁት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ጆቴ መስፍን 78 ተኛው የሰማዕታት ቀን ለሰማዕታቱ መታሰቢያ በቆመበት በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ሃውልትና በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲሁም በአንዋር መስጊድ በፀሎት ሥነ-ስርዓት መዘከሩን ገልፀዋል።

ግን በዘንድሮዉ የአከባበር ሥነ- ስርዓት ላይ እጅግ ጥቂት ሰዎችናና የአባት አርበኞች ብቻ መገኘታቸዉ ነዉ የተገለፀዉ ይህ እዉነት ነዉ ምክንያቱስ ምን ይሆን? እንደኛ በደማቅ መከበሩን ነዉ ያሉት አቶ ዳንኤል እንዲያም ሆኖ አዲሱ ትዉልድ እንደ ቀድሞ ግዜ ስለታሪኩ በትምህርት ቤት የሚያገኘዉ እዉቀት እየቀዘቀዘ ነዉ ብለዋል። ቢሆንም ቢሆንም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ድርጅት በየትምህርት ቤቱ የታሪክ ትምህርት እንዲሰጥ ጥረት ለማድረግ ዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

የአባት አርበኞች ሥራ ታሪክ ሆኖ ብቻ እንዲቆይ ሳይሆን ህያዉ ሆኖ እንዲቆም አዲሱ ትዉልድ የጀግኖችን ታሪክ በትምህርቱ በሙዚቃዉ በሥነ-ፅሑፉ ሁሉ ማንሳቱ ትልቅ ጥቅም አለዉም ሲሉ አክለዋል።

በሌላ በኩል ጀግኖች አባቶቻችን ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ መኖር አባት እናቶቻችን የከፈሉትን መስዋትነት በጋራና በአንድነት ለማስታወስና ለመዘከር እንዲያስችለን ከእለት ኑሮአችን እና ህይወታችን ጋር የምናያይዝበትን መንገድ አልፈጠርንም፤ ይህን ቀን በዓመት አንድ ግዜ ብቻ ነዉ የምናስበዉ ስለዚህም ልናስታዉሰዉ አልቻልንም፤ ከዚህ ይልቅ ስለእንጊሊዝ የእግር ኳስ ብዙ እናዉቃለን ሲሉ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ያላቸዉን አስተያየት ገልጸዋል።

ታድያ ይህን የጀግኖቻችን ታሪክ የምንዘክርበትን በዓል ማክበሩ ምን ይጠቅም ይሆን? የካቲት 12 የኢትዮጵያዉያን ሰማዕታት ቀን ለኢትዮጵያዉያንስ ምን ትርጉም ይሰጥ ይሆን ለሚለዉ ጥያቄ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሁለት ነገር ይጠቅማል ብለዋል። ይህ አስከፊ ታሪክ እንዳይደገም እናደርጋለን፤ ታሪክን በደንብ የማያዉቅ ሰዉ በታሪክ የተፈፀሙ ስህተቶችን እንደገና ለመድገም የተረገመ ነዉ። ሁለት፤ ለነዚህ ጀግኖች ዋጋ ካልሰጠናቸዉ እኛም ነገ ለምንሰራዉ ሥራ ዋጋ የሚሰጥ ትዉልድ አናገኝም። ምክንያቱም አሉ ዲያቆን ዳንኤል ማንም በሰፈረበት ቁና ነዉ የሚሰፈረዉ።

በጀርመን በተለይም በኮለኝ ከተማ ከተቋቋመ 30 ዓመት በላይ በሆነዉ በደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስትያን 78ኛዉን የሰማዕታት ቀን በማስመልከት በርካታ ኢትዮጵያዉያን በተገኙበት ፀሎተ-ፍትሃት ተካኢዶአል። የቀድሞ የተመድ ሠራተኛ አቶ ኪዳኔ አለማየሁ የግራዚያኒ ሐውልት እንዲፈርስ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ የሚያስተባብረው ግብረ ሀይል ቦርድ ም/ሰብሳቢ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ ቀኑ በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ መዋሉን ገልፀዉልናል።

በጣልያን አፊሌ በተባለ ከተማ ኢትዮጵያዉያንን ለጨፈጨፈዉ የጦር ወንጀለኛ መታሰብያ መሰራቱን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃዉሞ በማድረግ እና ኢትዮጵያዉያንን በማሰባሰብ የሚታወቁት አቶ ኪዳኔ አለማየሁ እንደገለፁት በጣልያን መንግሥት ላይ እየተደረገ ያለዉ ግፊት ዉጤት እያስገኘ ነዉ፤

የግራዚያኒ ሐውልት እንዲፈርስ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ የሚያስተባብረው ግብረ ሀይል ቦርድ ም/ሰብሳቢና የቀድሞ የተመድ ሰራተኛ አቶ ኪዳኔ አለማየሁበኢትዮጵያ ላይ የደረሰዉ ግፍ እጅግ ከፈተኛ ነዉ ። ጣልያኖች በሌሎች ሃገራት ላይ ላደረሱት ከፍተኛ ግፍ ከፍተኛ ካሳን ከፍለዋል፤ ለምሳሌ አሉ አቶ አለማየሁ በቅርቡ ለሊቢያ አምስት ቢሊዮን ዶላር ካሳን ለመክፈል ተስማምተዋል። ቀደም ሲል ለዮጎዝላቪያ መቶ ሃያ አምስት ሚሊዮን ካሳ ከፍለዋል። ለግሪክ ሃገር መቶ አምስት ሚሊዮን ካሳ ለቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት መቶ ሚሊዮን ዶላር ካሳን ከፍለዋል። ለኢትዮጵያ ግን የቆቃ ግድብን ነዉ የገነቡበት ሃያ አምስት ሚሊዮን ዶላር ነዉ የሰጡት። በይፋም ይቅርታን አልጠየቁም። ይባስ ብሎ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ኢትዮጵያዉያንን ለጨፈጨፈ ፤ በሶስት ቀን ዉስጥ ሰላሳ ሺ ህዝህብ ለጨረሰ የጦር ወንጀለኛ የማስታወሻ ቦታ

ተገንብቶለታል።

ቫቲካን ኢትዮጵያዊ ካርዲናልን መሾምዋ ለኛ ትልቅ ክብር ነዉ ያሉት አቶ ኪዳኔ አለማየሁ ማሕበራቸዉ ለካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ደብዳቤ መፃፉንና ከካርዲናሉ በትህትና የመልስ ደብዳቤ ማግኘቱንን በዝርዝር ገልፀዋል።

የአባቶቻችንና የእናቶቻችን የጀግንነት ታሪክ ለነፃነት መስዋዕት የተከፈለበት የኛነታችን የማዕዘን ድንጋይ በመሆኑ ልናዉቀዉ ልንማርበት ልዩ ክብርም ልንሰጠዉ ይገባል ያሉንን የለቱን እንግዶቼን ለሰጡን ቃለ-ምልልስ አመሰግናለሁ። አድማጮች የአድዋን ድል በምን ሁኔታ ለማክበር ለማሰብ ተዘጋጅታችኋል? አስተያየታችሁን ላኩልን በዚሁ ርዕስ ስር በዝግጅታችን ለመሳተፍ የምትሹም ስልክ ቁጥራችሁን ላኩልን በማለት የለቱን ሙሉ ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን ተጭናችሁ እንድታደምጡ እንጋብዛለን ።

አዜብ ታደሰ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic