የጥቅም መሳፍንት | ባህል | DW | 30.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የጥቅም መሳፍንት

የጥቅም መሳፍንት የኢትዮጵያዉያን የዴሞክራሲና የነጻነት ጥያቄ ታሪክ ነዉ ማለት እንችላለን። የታሪክ መሳፍንት የሚተርከዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት እንዳያገኝ በሕዝቡ ላይ የተጫኑ አምባገነን መንግሥታት እና ከነሱ ጋር ሆነዉ የሚሰሩ የምዕራባዉያን መንግሥታት እንዴት አድርገዉ የሕዝቡን ነጻነት ፍላጎት ሲያጓትቱት እንደቆዩ የሚያሳይ ታሪክ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:19

«መንግስታቱን የጥቅም ትስስርና ተግዳሮቱን ይዳስሳል»

 

«በትያትሩ አራቱ ገፀ-ባህርያት የሚያቀርቡት ኢትዮጵያ ታሪክን የሚያሳየዉ ትያትር ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ አሳዛኝ እንዳይሆንና በመጠቃለያዉ አስደሳች ለማድረግ እንዴት እናድርግ እያሉ ሲመካከሩ ነዉ፤ ትያትሩን የምንመርቅበት እለት እነ እስክንድር ነጋ የተፈቱት።  በዝያን ወቅት ኢትዮጵያ ዉስጥ ከፍተኛ ተቃዉሞ ተቀስቅሶአል።  ከዝያም ነዉ ትያትሩን በአሳዛኝ ታሪክ ከመዝጋት ምናልባትም የደስታ ታሪኩ የሚጀምረዉ አሁን ነዉ በሚል የትያትራችንን  አንዳንድ ይዘት ለመቀየር የተገደድነዉ።  ትያትሩን በመጀመርያ እለት ወደ መድረክ ከማቅረባችን ከአንድ ሰዓት በፊት ተዉኔቱ  በመድረክ ሲቀርብ ከተዋናዮቹ ጀርባ ከሚታየዉ ዘጋቢ ፊልሞች እና ፎቶግራፎች ስር የሚታየዉን የፅሁፍ ትረካ እየለወጥን ነበር። ትያትሩ በሚታይበት በሁለተኛዉ ቀን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደስአለኝ ስልጣናቸዉን ለቀቁ ።

ስለዚህ ትያትሩ ለሁለተኛ ጊዜ በመድረክ ሲቀርብ ይህንኑ ሁኔታ አስገብተን  ምናልባትም ኢትዮጵያ በለዉጥ መንገድ ላይ ትትገኛለች ብለን  ትያትሩን የደስታ ስሜትን አስይዘን በእንጥልጥል የደመደምነዉ።»    

በስዊዘርላንድ የተለያዩ ከተማ ትያትር ቤቶች በመታየት ላይ ያለዉ « የጥቅም መሳፍንት » አልያም «Kings of Interest» ትያትር ደራሲና አዘጋጅ አሮን የሺጥላ የተናገረዉ ነዉ። ወጣት አሮን « የጥቅም መሳፍንት » በሚል የደረሰዉ ያዘጋጀዉና የሚተዉንበት ይህ ትያትር፤ በኢትዮጵያ የታዩት የአምባገነን ሥርዓቶች ከምዕራባዉያን መንግሥታት ጋር ሆነዉ የሕዝቡን የዴሞክራሲ፤ የነጻነት ጥያቄ ሲያጓትቱና ሲያፍኑ እንደቆዩ በወፍ በረር የሚያስቃኝ ነዉ። በአራት የኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥታት ያለዉን ጨቋኝ አካሄድን የሚተርከዉ ይህ ትያትር፤ ለመጀመርያ ጊዜ የካቲት ወር ላይ ስዊዘርላንድ ላይ  ተመርቆ ለሕዝብ እይታ በመድረክ ሊቀርብ ከሰዓታት በፊት ታዋቂዉን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ፖለቲከኞችና አምደኞች ከዓመታት እስር በኋላ በመለቀቃቸዉ ከቀናት በኋላ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደስአለኝ ስልጣናቸዉን ሲለቁም ዳግም ሌላ ትዕይንት በትያትሩ እንዲያካትቱና ትያትሩ በመደምደምያዉ በሃገሪቱ የለዉጥ ተስፋ እየታየ ይሆን ሲል አጠይቆ በእንጥልጥል ይደመደማል።  

በ1996 ዓም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የትያትር ስራ ሞያ  ምሩቅ ነዉ። ከምረቃዉ በኋላ በጋዜጠኝነት በተለያዩ ጋዜጦችም ላይ ሰርቶአል። አሮን በጋዜጠኝነቱ ላይ ሳለ ለፊልም ድርሰትን ጽፎ «ሚዚዎቹ» የሚል ስምን ሰጥቶ በፊልም ለእይታ ካበቃ በኋላ ዳግም ወደ ኪነ-ጥበቡ ዓለም ሙሉ በሙሉ መለመለሱን ተናግሮአል። «ሚዚዎቹ» የተሰኘዉ ፊልም በጀርመንዋ መዲና በርሊን የአፍሪቃ ፊልም እይታ ሳምንት ላይ ተጋብዞም ታይቶለታል። ከዝያም ነዉ አሮን ኑሮዉን ስዊዘርላንድ አድርጎ፤ የፊልም እና የትያትር ሥራዉን አጠናክሮ መስራት የጀመረዉ።  

 

«እዚህ ከመጣሁ በኋላ መጀመርያ የሠራሁት ዘጋቢ ፊልም ነዉ «In the Face of God and gun» ይሰኛል። ፊልሙ የሚያዉጠነጥነዉ በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ከተለያዩ ሃገራት የመጡና የተለያየ ሃይማኖት ያላቸዉ ሰዎች ሕይወት ታሪክ ላይ ነዉ። ፊልሙ ለእይታ የቀረበዉ በአዉሮጳዉያኑ በ 2012 ነዉ። ከዝያ በኋላ ያመራሁት በትያትር ጥበብ ዉስጥ ወስጥ ነዉ። በመጀመርያ እንደ አማካሪ ሆኜ ሰራሁ፤ ከዝያ በኋላ «ሰሚራ ሚስ» በሚል ትያትር ላይ እንዲሁ አብሬ ሰርቻለሁ። ይህንኑ ትያትር በተለያዩ የስዊዘርላንድ ከተሞች ከባልደረባዬ ጋር አብረን አቅርበናል። እንዲሁም ዋጋዱጉ በነበረዉ ፊትሞ የፊልም ፊስቲቫል ላይ ፊልሙ ተጋብዞ ነበር። ከዝያ በኋላ ደግሞ « የጥቅም መሳፍንት » «Kings of Interest» ትን አራዉ ስዊዘርላንድ ከተማ ከሚገኘዉ ቶህላዉ ትያትር ቤት ጋር በጋራ ሆነን ለሕዝብ በማሳየት ላይ እንገኛለን። ፊልሙን በመፃፍ በማቀናበር በመተወን ሁሉ እሳተፋለሁ።»      

የጥቅም መሳፍንት፤ በሁለት ኢትዮጵያዉያን እና በሁለት የስዊዘርላንድ ዜጎች በጀርመንኛ ቋንቋ የተተወነ ሲሆን ተዋንያኑ የሚናገሩት በአማርኛና በእንጊሊዘኛ ከጀርባ መድረክ ላይ ከተለያዩ ፊልሞች እንዲሁም የፎቶግራፍ መራጃዎች ጋር የተደገፈ ነዉ። የትያትሩ ደራሲና አዘጋጅ አሮን የሺጥላ የጥቅም መሳፍንት ትያትርን ጭብጥ ይናገራል።

«ከርዕሱ እንደምንረዳዉ የጥቅም መሳፍንት ጥቅምን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ አካላትን ነዉ። የኢትዮጵያዉያንን  የዴሞክራሲና የነጻነት ጥያቄ ታሪክን ነዉ ማለት እንችላለን። ስለዚህ የታሪክ መሳፍንት ማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት እንዳያገኝ በሕዝቡ ላይ የተጫኑ አምባገነን መንግሥታት እና ከነሱ ጋር ሆነዉ የሚሰሩ የምዕራባዉያን መንግሥታት እንዴት አድርገዉ የሕዝቡን ነጻነት ፍላጎት ሲያጓትቱት እንደቆዩ የሚያሳይ ታሪክ ነዉ። የጥቅም መሳፍንት የሚያሳየን እነዚህን የጥቅም ትስስሮች ነዉ። ታሪኩ የሚጀምረዉን እና ከምኒልክ ዘመነ መንግሥት ከሚኒልክ ወዳጅ ከአልፍሪድ ኢልግ ጋር ነዉ።

በ 1880ዎቹ ከስዊዘርላንድ ወደ ኢትዮጵያ የመጣዉ አልፍሬድ ኢልግ ፤ የአፄ ምኒሊክ ታማኝ ሆኖ አገልግሎአል። ለአፄ ምኒሊክ በመታመኑም በኢትዮጵያ እስከ ዉጭ ጉዳይ ምኒስትር እስከመሆን የደረሰ ነዉ። ስለዚህ በዝያ በቅኝ ግዛት ዘመን የሚታመን አንድ የአዉሮጳ ዜጋ ባልተገኘበት ጊዜ፤ ከአፄ ምኒሊክ ጋር የነበረዉ ጥሩ ግንኙነት፤ በኋላም ኢትዮጵያ ከቅኝ ግዛት ለመከላከል ባደካሄደችዉ ጦርነት ከኢትዮጵያ ጎን ቆሞ ብዙ አስተዋጽኦ ያደረገ ሰዉ ነዉ። የሁለቱ ግንኙነት በሰብዓዊነት የተመሰረተ ግንኙነት ነዉ። ከዝያ በኋላ የተመሰረቱት ግንኙነቶች ግን በጥቅም ላይ የተመሰረቱ ናቸዉ። ይህን ነዉ ትያትሩ ከሌላዉ የኢትዮጵያ ታሪክ ጋር በማሳየት የሚነጻጽረዉ።»      

ትያትሩ በመቀጠል ወደ አፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት በተለይም የተመድ ከመመስረቱ በፊት በነበረዉ በሊግ ኦፍ ኔሽን፤ ንጉሱ ያደረጉትን ንግግር አያያዞ ይተርካል። ትያትሩ በዓለም ላይ የካፒታሊስት ስርዓት አይሎ በወጣበት ወቅት በደርግ ዘመነ ስልጣን የነበረዉን የጥቅም ትስስር ፤ የሃገሪቱ ነዋሪ የደረሰበት ግፍ ብሎም የፖለቲካ አቅጣጫዉ መቀየሩንም ይዳስሳል። ከደርግም በኋላ ዛሬ ካፒታልስት መሰል ሥርዓትን በምታራምደዋ  ኢትዮጵያ ያለዉ አሮን የሺጥላ በትያትሩ መቀመጥዋን ተናግሮአል።

አንድ ሰዓት ከአስር የሚዘልቀዉ ይህ ትያትር በከምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ድረስ ያለዉን የጥቅም ትስስርን ይዳስሳል።  

በምዕራቡ ዓለም የኢትዮጵያን ታሪክ በትያትር መልክ ጽፎ ከዉጭ ዜጎች ጋር ትያትርን በመድረክ ማቅረብ አይከብድም? ለትያትር እና ፊልም ሥራ ባለሞያዉ ለአሮን የሺጥላ በመጨረሻ የቀረበለት ጥያቄ ነበር።

በኢትዮጵያ ታሪክ ከምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስካሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ የነበረዉ የመንግሥታት የጥቅም ትስስር እንዲሁም የሕዝቡን የዴሞክራሲ የነጻነት ጥያቄን የሚዳስሰዉ ትያትር በስዊዘርላን ጋዜጦች መጽሔቶች ላይ ሳይቀር አድናቆትን ተቸርዋል። በቀጣይ ወደ ጀርመንና ወዴሌሎች አዉሮጳ ሃገራት መድረኮች ለመቅረብ በዝግጅትም ላይ ነዉ። ትያትሩ ወደ ኢትዮጵያ መድረኮችም ይደርሳል የሚል ተስፋ ተጥሎአል። የትያትሩን ደራሲ ጨምሮ ሁለት ኢትዮጵያዉያን ሁለት የስዊዘርላንድ ዜጎች የሚተዉኑበት ትያትር ደራሲ አሮን የሽጥላ ለሰጠን ቃለ ምልልስ በዶይቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉዉን ስርጭት የድምፅ ማድመጫዉን በመንካት ሙሉዉን መሰናዶ እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።   

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ   

Audios and videos on the topic