የጥቅምት 29 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ  | ስፖርት | DW | 08.11.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የጥቅምት 29 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ ሃገራት ከ20 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ውድድር የቡሩንዲ አቻውን በማሸነፍ ለፍጻሜ በቅቷል። መውደቁን ከወዲሁ ያረጋገጠው የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹን ለማከናወን ወደ ደቡብ አፍሪቃ ያቀናል። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የጀርመን ቡንደስሊጋ ግጥሚያዎችን ዳሰናል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:03

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ ሃገራት ከ20 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ውድድር የቡሩንዲ አቻውን በማሸነፍ ለፍጻሜ በቅቷል። መውደቁን ከወዲሁ ያረጋገጠው የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹን ለማከናወን ወደ ደቡብ አፍሪቃ ያቀናል። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የጀርመን ቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች ላይ ዳሰሳ አድርገናል። የመኪና ሽቅድምድም እና ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተሳተፉባቸውን የአትሌቲክስ ውጤቶችን አካተናል። 

አትሌቲክስ
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተደረጉ በርካታ ውድድሮች በተለይ ኢትዮጵያውያቱ አስደሳች ውጤቶችን አስመዝግበዋል። ፈረረንሳይ ሊል ከተማ ውስጥ ቅዳሜ ዕለት በተከናወነው የ5 ኪሎ ሜትር ድብልቅ የጎዳና ላይ የሩጫ ፉክክር (mixed race) ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዳዊት ሥዩም ክብረወሰን በመስበር ለድል በቅታለች። ዳዊት ሥዩም ውድድሩን በ2 ሰከንዶች ልዩነት አሻሽላ በአንደኛነት ያጠናቀቀችበት ሰአት 14 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ ነው።  በዚሁ ውድድር ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መስከረም ማሞ በ14:55 በሆነ ሰዓት በመግባት 3ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች። ኬኒያዊቷ አትሌት ኖራህ ጄሩቶ ደግሞ ባለፈው የካቲት ወር ፈረንሳይ ሞናኮ ውስጥ በኬኒያዊቷ አትሌት ቢያትሪስ ቼፕኮዬች በክብረወሰንነት ተይዞ በነበረው ልክ የ14 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ በማጠናቀቅ የሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።  በወንዶቹ ውድድር አትሌት በሪሁ አረጋዊ በ12:52 በሆነ ሰዓት ሲያሸንፍ ሌላው ኢትዮጵያዊ አትሌት ያሲን ሃጂ በ13:29 በሆነ ሰዓት 3ኛ ወጥቷል።

በአሜሪካው የኒውዮርክ ማራቶችን የሩጫ ፉክክር አትሌት አባብል የሻነህ 2 ሰአት ከ22 ደቂቃ ከ52 ሰከንዶች በመሮጥ የ3ኛ ደረጃን አግኝታለች። ኬኒያዊቷ አትሌት ፔሬዝ ጄፕቺርቺር 2:22:39 በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች። አትሌት አባብል የሻነህ የሦስተኛ ደረጃን ያገኘችው ከሌላኛዋ ኬኒያዊት አትሌት ቪዮላ ቼፕቱ በስምንት ሰከንዶች ልዩነት ብቻ ተበልጣ ነው። አትሌት ቪዮላ ቼፕቱ ሁለተኛ ደረጃን ያገኘችው 2:22:44 በመሮጥ ነው።

ለሦስት ጊዜያት በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎችን የሰበሰበው፤ ለሁለት ጊዜያትም የቤርሊን ማራቶን ባለድል የነበረው ኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በዚህ የኒውዮርክ ማራቶን ሩጫ ፉክክር በስድስተኛነት አጠናቋል። የኒውዮርክ ማራቶን ለቀነኒሳ ብቻ ሳይሆን ለሌላኛው ለዓለም ክብረወሰን ባለቤቱ ኬኒያዊ አትሌትም እጅግ አበሳጭ ሆኖ አልፏል። በዓለም የግማሽ ማራቶን ሩጫ ክብረ-ወሰን ባለቤት ኪቢዎት ካንዲ በትናንቱ የኒውዮርክ ማራቶን ፉክክር በዘጠነኛነት ነው ያጠናቀቀው። በኒውዮርክ ማራቶን 2:08:22 በመሮጥ የአንደኛ ደረጃን ያገኘው ኬኒያዊው አትሌት አልበርት ኮሪር ነው። የሞሮኮው አትሌት ሞሐመድ ኤል አራቢ 1ኛ ከወጣው ኬኒያዊ አትሌት 44 ሰከንዶች በኋላ ተከትሎት በመግባት ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። 

ስፔን በተካሄደ የባርሴሎና ማራቶን ውድድር፡-በሴቶች ከአምስተኛ በስተቀር ኢትዮጵያውያቱ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያለውን ቦታ ተቆጣጥረዋል።  በዚህም መሠረት፦ ታዱ ተሾመ 2:23:53 በመሮጥ 1ኛ ወጥታለች። 2ኛ ደረጃ ያገኘችው መሰረት ጎላ የገባችበት ሰአት 2:24:09 ነው። መሰረት በለጠ 2:24:25 ሮጣ በመግባት 3ኛ በመሆን አጠናቃለች።  በቀለች ጉደታ በ2:24:51 እንዲሁም ትንቢት ግደይ በ2:29:28 4ኛ እና 6ኛ ሆነው አጠናቀዋል። በዚሁ የወንዶች ውድድር ክብሮም ደስታ እና የማነ ፀጋዬ 7ኛ እና 8ኛ ሆነዋል። እዛው ስፔን በተደረገ የሳን ሰባስቲያን 7600 ሜትር አገር አቋራጭ ውድድር ደግሞ በሴቶች ዘነቡ ፍቃዱ በ25:28 1ኛ ደረጃን ይዛ አሸንፋለች። ዘርፌ ወንድማገኝ በ25:39 በሆነ ሰዓት 2ኛ ደረጃን በማግኘት አጠናቃለች፡፡

ቱርክ ውስጥ በተደረገው የኢስታንቡል ማራቶን ውድድር ደግሞ በሴቶች አያንቱ አብዲ 2:24:45 በመሮጥ 3ኛ ደረጃን ይዛለች። በፖርቹጋል የፖርቶ ማራቶን ውድድር በወንዶች አስናቀ ዱብሪ2:10:14 በመሮጥ 3ኛ ደረጃን ይዟል። በሴቶች 1ኛ ቅድሳን አለማ በ2:28:01፤ 2ኛ ሸዋረግ አለነ በ2:28:16 እንዲሁም 3ኛ ሞቱ መገርሳ በ2:28:56፤ 4ኛ ፈይኔ ገመዳ በ2:29:32፤ 5ኛ መሰለች ፀጋዬ በ2:29:38 ወጥተዋል። ጣሊያን በተካሄደ ሳን ቢያጆ ግማሽ ማራቶን ውድድር በወንዶች ዳምጤ ኳሹ በ1:06:55 1ኛ ደረጃን ይዞ አሸንፏል። በሴቶችም መሰረት እንግዱ 1:15:42 በመሮጥ አሸንፋለች። አስመራወርቅ በቀለ 1:17:35 በመሮጥ 2ኛ ወጥታለች። ስዊዘርላንድ በተካሄደ የጄኔቭ 20 ኪሎ ሜትር ውድድር ደግሞ በወንዶች ታደሰ አብርሃም 59:28 በመሮጥ 2ኛ እንዲሁም በሴቶች ሄለን በቀለ በ1:07:05 በመግባት 1ኛ ኾነዋል። 

በፈረንሳይ የሊል አርባን ትሪያል 10 ኪሎ ሜትር ውድድር፡- በወንዶች 1ኛ ጭምዴሳ ደበሌ በ27:16፤ 3ኛ ማሞ አደላድለው በ27:27 ወጥተዋል።  በሴቶች በላይ አበራሽ በ31:00 4ኛ ደረጃን አግኝታለች። በፈረንሳይ የሊል አርባን ትሪያል 5 ኪሎ ሜትር ድብልቅ ውድድር በወንዶች በሪሁ አረጋዊ በ12:52 ሮጦ 1ኛ ወጥቷል። በ3ኛነት የተከተለው ያሲን ሃጂ የገባበት ሰአት13:29 ነው። መረጃውን ያገኘነው ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው።

እግር ኳስ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ ሃገራት ከ20 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ፉክክር ለፍጻሜ ደረሰ። ተጋጣሚዎቹን እጅግ በሰፋ የግብ ልዩነት በተደጋጋሚ ያሸነፈው የኢትዮጵያ ቡድን ቅዳሜ ዕለት በተደረገው ግጥሚያ ቡሩንዲን 1ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ቅዳሜ ጥቅምት 27 ቀን፣ 2014 ዓ.ም በተደረገው ጨዋታ በ59ኛው ደቂቃ ላይ ለኢትዮጵያ የማሸነፊያዋን ግብ ያስቆጠረችው አሪያት ኦዶንግ ናት። 

ቡድኑ እስካሁን ባካሄደው ጨዋታዎች 12 ነጥቦችን በመሰብሰብ ተመሳሳይ ነጥብ ካለው የዩጋንዳ ቡድን ጋር ለዋንጫው ጨዋታ ተፎካካሪ መሆን ችሏል። 20 የግብ ክፍያ ያላት ዩጋንዳ ኢትዮጵያን የምትበልጠው በ6 የግብ ክፍያ ላዩነት ብቻ ነው። በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ጥቅምት 20 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የጀመረው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ ሀገራት ውድድር ጥቅምት 30 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል። በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ጥቅምት 20 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የጀመረው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ ሀገራት ውድድር ነገ ጥቅምት 30 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

በአለም ዋንጫ ማጣሪያ እንደ ዚምባብዌ ሁሉ ከምድቡ መውደቁን አስቀድሞ ያወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ደግሞ  ለቀሪ ጨዋታዎቹ የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ አከናውኗል። ቡድኑ በነገው ዕለት ወደ ደቡብ አፍሪቃ በመጓዝ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹን ከጋና እና ከዚምባቡዌ ጋር ያከናውናል። 

ቡንደስሊጋ 
በጀርመን ቡንደስሊጋ ቅዳሜ ዕለት ፍራይቡርግን 2 ለ1 ያሸነፈው ባየርን ሙይንሽን በ28 ነጥብ ይመራል። በተመሳሳይ ቀን ግጥሚያ በላይፕትሲሽ የ2 ለ1 ሽንፈት የገጠመው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ24 ነጥብ ይከተላል። ፍራይቡርግ 22 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። አውግስቡርግ፣ አርሜኒያ ቢሌፌልድ እና ግሮይተር ፊዩርትስ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ግርጌ ላይ ተደርድረዋል።

ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ቸልሲ ቅዳሜ ዕለት ባልተጠበቀ መልኩ ከበርንሌ ጋር አንድ እኩል በመለያየት ነጥብ ጥሏል። እንዲያም ሆኖ በ26 ነጥብ 1ኛነቱን አስጠብቋል። ማንቸስተር ሲቲ ማንቸስተር ዩናይትድን 2 ለ0 በማሸነፍ 23 ነጥብ ሰብስቧል፤ የሁለተኛ ደረጃም ይዟል። ተመሳሳይ ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ የሚበለጠው ዌስትሀም ዩናይትድ ትናንት ሊቨርፑልን 3 ለ2 ድል አድርጓል። ደረጃውንም ከሊቨርፑል ነጥቆ ሦስተኛ መሆን ችሏል። ሊቨርፑል በ22 ነጥቡ ተወስኖ ወደ 4ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። አጀማመሩ ላይ ነጥብ በመጣል አሽቆልቁሎ የነበረው አርሰናል ትናንት ዋትፎርድን 1 ለ0 በማሸነፍ 20 ነጥብ ይዞ ሊቨርፑልን ተጠግቷል። በደረጃ ሰንጠረዡም 5ኛ ላይ ተቆናጧል። የቸልሲ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል ክርስቲያን ፑሊሲች በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም አቀፍ ውድድር በቆየበት ወቅት ከተገቢው በላይ መሰለፉ አሳስቦኛል አሉ። ክርስቲኢን ፑሊሲች ባለፈው መስከረም ወር ከዩናይትድስ ስቴትስ ቡድን ጋር በቆየበት ወቅት ከገጠመው የቁርጭምጭሚት ጉዳት ቢያገግምም ለሁለት ጊዜያት ብቻ ነው መቀየር የቻለው። የ23 ዓመቱ አማካይ አጥቂ ባለፈው ከማልሞ ጋር በነበራቸው የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ የተሰለፈው ለ16 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። ከዚያ ውጪ ባሳለፍነው ቅዳሜ በፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ ከበርንሌይ ጋር አንድ እኩል በተለያየበት ግጥሚያ በመጨረሻዎቹ አምስት ደቂቃዎች ብቻ መሰለፍ ችሏል። 

ክርስቲያን ፑሊሲሲች ከደረሰበት የቁርጭምጭሚት አደጋ ሙሉ ለሙሉ አገግሞ በደንብ ለመሰለፍ ቢያንስ ከአራት ውድድሮች ማረፍ እንደሚገባው ጀርመናዊው የቸልሲ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል ተናግረዋል። ክርስቲያን ፑሊሲች ከጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ያለፈው የጨዋታ ዘመን በፊት ወደ ቸልሲ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ለ81 ጊዜያት ለቡድኑ ተሰልፏል። ቸልሲ ከመጣበት ጊዜ አንስቶም ለቡድኑ 18 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ እና 18 ግብ የሆኑ ኳሶችን ማመቻቸትም የቻለ አጥቂ ነው።  ከሁለት ዓመት በፊት በ64 ሚሊዮን ዩሮ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ወደ ለንደን ያቀናው ክርስቲያን ፑሊሲች ከቸልሲ ቡድን ጋር የገባው ውል የሚጠናቀቀው ከሁለት ዓመት በኋላ ነው። 

ፎርሙላ አንድ 
በሜክሲኮ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን ዳግም ድል ተቀዳጅቷል። የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ዳግም ሽንፈት ገጥሞታል። ትናንት በውድድሩ አሸናፊ የኾነው ማክስ በዚህም አለ በዚያ በስተመጨረሻ ለማሸነፍ ቆርጦ እንደነበር ተናግሯል።

«በተቻለ መጠን በስተመጨረሻ ላይ ሾልኮ የመውጣት ጉዳይ ነበር» ብሏል ከሦስተኛነት እንዴት አድርጎ አፈትልኮ እንደወጣ ሲናገር። «ከሦስተኛ ወደ ፊት አንደኛ በመምጣቴ ውድድሩን የራሴ ማድረግ ችያለሁ። ምክንያቱም ትኩረቴ በአጠቃላይ ስለራሴ ነበር» ሲልም አክሏል።

ለስድስት ጊዜያት የፎርሙላ አንድ የዓለም ባለለድል የኾነው ብሪታኒያዊው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን በዚህ ውድድር የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። ሌላኛው የሬድ ቡል አሽከርካሪ ሠርጂዮ ፔሬዝ በሦስተኛነት አጠናቋል። እስካሁን በተደረጉ ሽቅድምድሞች ማክስ ፈርሽታፐን 312.5 ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል። ሌዊስ ሐሚልተን 293.5 ነጥቦች ይከተላል። ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ቫለሪ ቦታስ በ185 ነጥቡ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች