የጥቅምት 28 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. የስፖርት ጥንቅር | ስፖርት | DW | 07.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የጥቅምት 28 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. የስፖርት ጥንቅር

«የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኾኜ በመመረጤ እጅግ ኩራት ይሰማኛል! ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ታላቅ ስኬትም እሠራለሁ።» አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ነበር ይኽን ያለው። የሚገጥመው ተግዳሮት ግን ከፍተኛ እንደሚኾን የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የኢትዮጵያ ዘጋቢ ጋዜጠኛ ኤልሻዳይ ነጋሽ ገልጧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:36
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:36 ደቂቃ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዲስ ፕሬዚዳንት

የማራቶን እና የረዥም ርቀት ሯጮች ዓለም አቀፍ ማኅበር የሚያበረክትለትን የሕይወት ዘመን ሽልማት ለመቀበል የፊታችን ዐርብ ኅዳር 2 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. ወደ አቴንስ ግሪክ ይበራል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት መኾኑ ከተነገረ ከአንድ ሣምንት ግድም በኋላ ማለት ነው፤ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ። «እንግዲህ አኹን ዐርብ ሽልማቱን ስቀበል፤ ያው እንደ ኃይሌም እንደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ኾኜ ነው» ያለው አትሌት ኃይሌ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ለሚቀጥሉት ለአራት ዓመታት ለመምራት የተመረጠው ቅዳሜ ጥቅምት 26 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. ነበር።  

በዓለም አቀፍ መድረክ ዝነኛ ስም አለህ፤ በዓለም ዙሪያ በከፍተኛ ደረጃ ነው የምትታወቀው እናም አኹን የምትመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በብዙ ችግሮች ይታማል። ሙስና፣ የዝምድና አሠራር፣ ወገንተኝነት የመሳሰሉት ነጎሮች አሉ። ይኽንን ምን ያኽል ልትዋጋው ተዘጋጅተሀል? ስንል ላቀረብንለት ጥያቄ ኃይሌ ሲመስልስ፦ «የዝምድናው፣ የሙስናው፣ የመሳሰሉት በየትም [ቦታ] አሉ፤ ግን ልዩ የሚያደርገው በስፖርቱ የምታየው ሙስና እና የዝምድና የመሳሰሉት ነገር ሜዳ ላይ ቁልጭ ብሎ ለሚሊዮኖች ይታያል። ያ ደግሞ ያጋልጥኻል ማለት ነው። ምንም የፖሊስ ምርመራ ሳያስፈልገው የሚጋለጥ ነገር ነው። እኔ የምጥረው ያ እንዳይኾን ነው» ብሏል። 

እንደ ጋዜጠኛ ኤልሻዳይ ማብራሪያ ግን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃይሌ ከፊቱ ተደቅነው የሚጠብቁት ተግዳሮቶች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ዙሪያ ለዓመታት ተወሳስበው የቆዩ ችግሮችን ኃይሌ በአራት ዓመት ብቻ ሊቀርፋቸው እንደማይችል ጠቅሷል። «በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ሙሉ ለሙሉ ይኽንን ፌዴሬሽን ወደ ጥሩ ተቋም እና ስፖርቱንም ወደ ትልቅ ደረጃ  ለመመለስ ይችላል ብዬ አልገምትም።»

የአትሌቲክስ ስፖርት በኢትዮጵያ መቼ፣ የትና እንዴት እንደተጀመረ የሚገልፁ ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት እንደማይቻል፤ ኾኖም  ከ1890 ዓ. ም. ቀደም ብሎ በትምህርት ቤቶችና በወታደራዊ ካምፖች ይዘወተር እንደነበር ስለመነገሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድረ-ገጽ ላይ ሠፍሯል። 

የአትሌቲክስ ስፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ በተቋም ደረጃ «የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን» በሚል መጠሪያ የተቋቋመው በ1941 ዓ. ም. ስለመኾኑ ድረ-ገጹ ላይ የሰፈረው መረጃ ያመለክታል።

ከስድሳ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ይኽ ተቋም ከመንግሥት በጀት ተጽዕኖ ተላቆ በራሱ በጀት እና ተቋማዊ አሠራር፣ እንዲሁም ፋይናንስ መጠቀም ከጀመረ የዐሥር ዓመት ግድም እድሜ እንዳለው፣ ብዙ ችግሮችም እንደገጠሙት ጋዜጠኛ ኤልሻዳይ ነጋሽ ይገልጣል። «ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ እንዲሁም የተመረጡት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት» አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ተብትበው የያዙት ችግሮችን ለመፍታት «ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ ሥራ የሚያስፈልገው» ይመስለኛል ሲል ተናግሯል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች