የጥቅምት 1 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ  | ስፖርት | DW | 11.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የጥቅምት 1 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ 

በቺካጎ ማራቶን ኢትዮጵያዊው አትሌት ሠይፉ ቱራ ድል ቀንቶታል። በሜዳው የ3 ለ1 ሽንፈት የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የመልስ ጨዋታውን ጆሐንስበርግ ከተማ ውስጥ በነገው ዕለት ያከናውናል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን በሬድ ቡሉ አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን በነጥብ ተበልጧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:30

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በቺካጎ ማራቶን በወንዶች የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሠይፉ ቱራ ድል ቀንቶታል። ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ «እኔ ለባሕር ዳር ሰላም እሮጣለሁ» በሚል መሪ ቃል የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ተከናውኗል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በሜዳው የ3 ለ1 ሽንፈት የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የመልስ ጨዋታውን ጆሐንስበርግ ከተማ ውስጥ በነገው ዕለት ያከናውናል። ምድቡን ደቡብ አፍሪቃ ይመራል። ዚምባብዌ የመጨረሻውን ደረጃ ይዟል። ለዚሁ ለዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ማጣሪያ በዛሬው ዕለትም በመላው ዓለም በርካታ ጨዋታዎች ይኖራሉ። ብራዚሊያዊው ኮከብ ኔይማር ከካታሩ የዓለም ዋንጫ በኋላ ጫማውን እንደሚሰቅል ይፋ አድርጓል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን በሬድ ቡሉ አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን ተቀድሟል።

አትሌቲክስ

ትናት በተከናወነ የቺካጎ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሠይፉ ቱራ አሸናፎ ሆነ። በሴቶች ተመመሳይ የሩጫ ውድድር ከዚህ ቀደም በግማሽ ማራቶን አሸናፊ የነበረችው ኬኒያዊቷ ሯጭ ሩት ቼፕንጌቲች አንደኛ ወጥታለች። ሠይፉ 42,195 ኪሎ ሜትር ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት 2:06:12 ነው። ሩት ቼፕንጌቲች 2:22:31 በመሮጥ ነው ለድል የበቃችው። አሜሪካውያቱ አትሌቶች ኤማ ባቴስ እና ሣራ ሐል ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል። በወንዶች ፉክክር አሜሪካዊው ሩፕ ጋሌን ሁለተኛ፤ የኬንያው አትሌት ኤሪክ ኪፕታኑይ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። ዛሬ በተከናወነው የቦስተን ማራቶን ኬንያዊው አትሌት ቤንሶን ኪፕሮቶ 2 ሰዓት ከ09 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ በመሮጥ አሸናፊ ኾኗል። ኢትዮጵያውያኑ ለሚ ብርሃኑ እና ጀማል ይመር ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሆነው አጠናቀዋል። ባይልኝ ተሻገር እና ደጀኔ ደበላ ጎንፋ አራተኛ ስምንተኛ ሆነው ውድድሩን ጨርሰዋል።  

እግር ኳስ

ለካታር የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያ ለማለፍ የሚደረገው ፉክክር ተጧጡፎ ቀጥሏል። ቅዳሜ ዕለት ባሕር ከተማ ውስጥ በደቡብ አፍሪቃ ቡድን 3 ለ1 የተሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው ዕለት የመልስ ጨዋታውን ጆሐንስበርግ ከተማ ውስጥ ያከናውናል። ቅዳሜ በተደረገው ጨዋታ ጋና ዚምባብዌን 3 ለ1 አሸንፋለች። ሁለቱ ቡድኖች ለመልስ ጨዋታቸው በነገው ዕለት ከሰዓት ተቀጣጥረዋል።

ደቡብ አፍሪቃ በደረጃ ሰንጠረዡ አንደኛ መኾን ችሏል። በቅዳሜው ግጥሚያ ለደቡብ አፍሪቃ፦ ቴቦሆ ሞኮይና የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመረው 1 ደቂቃ ላይ ከርቀት የለጋት የቅጣት ምት ኳስ ከግብ ጠባቂው እጅ አፈትልካ ከመረብ አርፋለች። የግብ ጠባቂ ድክመት የታየበት ግብ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ሆነ የሚመለከታቸው የስፖርት አካላት የጠንካራ ግብ ጠባቂዎች እጥረት ለምን በቡድኑ እንደተከሰተ ጥናት አድርገው መፍትኄ ሊያበጁለት የሚገባ ጉዳይ ነው እንላለን።

ለደቡብ አፍሪቃ፦ በ71ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ምቶቢ ምቫላ ሁለተኛውን ሲያስቆጥር፤ ሁለተኛው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪው አንድ ደቂቃ ላይ ኢቪደንስ ማክጎፓ ሦስተኛዋን የማሳረጊያ ግብ ከመረብ አሳርፏል። ሦስተኛዋ ግብ ሙሉ ለሙሉ የተከላካዮች ድክመት የታየበት ነው። ግብ ያስቆጠረው ተጨዋች ኳስ ሲሻማ ነጻ ሆኖ መቆሙን አንድም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ያስተዋለው አልነበረም። ለኢትዮጵያ ብቸኛዋን ግብ ጌታነህ ከበደ በ67ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ከአንድም ሁለት ጊዜ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝተው ማስቆጠር ተስኗቸዋል። የባፋና ባፋናዎቹ ግብ ጠባቂ ተደጋጋሚ አደገኛ ሙከራዎችን ግብ ከመሆን ማጨናገፍ ችሏል።

በምድቡ ደቡብ አፍሪቃ በ7 ነጥብ እና 3 የግብ ክፍያ የመሪነቱን ደረጃ ይዛለች። ጋና በ6 ነጥብ እና በ2 የግብ ክፍያ የሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ በ3 ነጥብ እና 3 የግብ እዳ የሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። 1 ነጥብ ብቻ ያለው የዚምባብዌ ቡድን ከ3የግብ እዳ ጋር የመጨረሻውን ደረጃ ይዟል። የሁለተኛውን ደረጃ ከጋና ለመረከብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደቡብ አፍሪቃን በሰፋ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ያም ብቻ አይደለም ዚምባብዌ በሜዳዋ የጋና ቡድንን በሰፋ የግብ ልዩነት ልታሸፍ ይገባል። ከጋና ጥንካሬ እና ደቡብ አፍሪቃ በሜዳው የሚጫወት ከመሆኑ አንጻር የኢትዮጵያ ቡድን ለማለፍ በሚደረገው ፉክክር ብርቱ ፈተና ይጠብቀዋል። ይህንኑም ዋና አሰልጣኙ ውበቱ አባተ የቅዳሜው ጨዋታ እንደተጠናቀቀ ተናግረዋል። ከምንም በላይ ቡድኑ ልምድ የሚቀስምበት ሁኔታ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉም ገልጠዋል።  

ከዚሁ የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ማጣሪያ ሳንወጣ፦ ዛሬ ማታ ከሚከናወኑ ጨዋታዎች መካከል ቤላሩስ ከቼክ ሪፐብሊክ፤ ኤስቶኒያ ከዌልስ፤ ላቲቪያ ከቱርክ፣ ሆላንድ ከጂብራልታር፤ኖርዌይ ከሞንቴኔግሮ ፤ ሲፕረስ ከማልታ፤ ክሮሺያ ከስሎቫኪያ፤ ስሎቫንያ ከሩስያ፤ አይስላንድ ከሌሽተንሽታይን፣ ሰሜን መቄዶንያ ከጀርመን እንዲሁም ሩማንያ ከአርሜኒያ ጋር የሚያደርጓቸው ይገኙባቸዋል። ሁሉም ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰአት ምሽት ለአራት ሩብ ጉዳይ ላይ ይከናወናሉ።

ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አፍሪቃ ውስጥ ዛሬ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ደግሞ፦ቡርኪናፋሶ ከጅቡቲ፤ አይቮሪኮስት ከማላዊ፤ ሊቢያ ከግብፅ ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይገኙበታል። በዛሬው ዕለት ቀደም ሲል በተደረጉ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ሞዛምቢክ በካሜሩን የ1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። እንዲሁም ጋቦን አንጎላን 2 ለ0 አሸንፏል።

በነገው ዕለት ደግሞ፦ ዚምባብዌ ከጋና እንዲሁም ናሚቢያ ከሴኒጋል ጋር በተመሳሳይ ከሰአት በኋላ 10 ሰአት ላይ ይጋጠማሉ።  ሦስት ሰአት ዘግየት ብሎ ደግሞ በተመሳሳይ ሰአት ሦስት ጨዋታዎች ይኖራሉ።  ደቡብ አፍሪቃ ከኢትዮጵያ፤ ኒጀር ከአልጄሪያ እንዲሁም ኮንጎ ከቶጎ ጋር ከምሽቱ አንድ ሰአት ላይ ይፋለማሉ። ከዚያም ምሽት አራት ሰአት ላይ ጊኒ እና ሞሮኮ የሚያደርጉት ጨዋታም ይኖራል።

ለዚሁ የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ማጣሪያ በነገው ዕለት በአውሮጳ 13 ጨዋታዎች ይኖራሉ። ፖርቹጋል ከሉግዘምበርግ፤ ስዊድን ከግሪክ፤ ቡልጋሪያ ከሰሜን አየርላንድ፤ ዴንማርክ ከኦስትሪያ፤ እንዲሁም እንግሊዝ ከሐንጋሪ ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በብዙዎች ዘንድ የሚጠበቁ ናቸው።

በኔሽን ሊግ የአውሮጳ የእግር ኳስ የፍጻሜ ግጥሚያ ፈረንሳይ የስፔን ቡድንን 2 ለ1 በሆነ ውጤት ትናንት አሸንፏል። ለፈረንሳይ የማሸነፊያዎቹን ሁለት ግቦች ካሪም ቤንዜማ እና ኪሊያን እምባፔ አስቆጥረዋል። ለስፔን ብቸኛዋን ግብ ከመረብ ያሳረፈው ሚኬል ኦያርዛባል ነው። የባለፈውን የዓለም ዋንጫ የወሰደው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ድልን በማስታወስ የፈረንሳይ ጋዜጦች «ዳግም ዋንጫ ወደ ፈረንሳይ መጣ» ሲሉ በደስታ ጽፈዋል። ለሦስተኛ ደረጃ በተደረገው ግጥሚያ፦ ጣልያን ቤልጂየምን 2 ለ1 አሸንፋለች። የቤልጂየም ቡድን ወሳኝ ተጨዋቾች ሮሜሉ ሉካኩ እና ኤደን ሐዛርድ በጉዳት አልተሰለፉም።

ባሕር ዳር ሩጫ

«እኔ ለባሕር ዳር ሰላም እሮጣለሁ» በሚል መሪ ቃል ትናንትና በባሕር ዳር የ10 ኪሎ ሜትር ሕዝባዊ ሩጫ ተካሂዷል። በሩጫው ያሸነፉ ሯጮችም የገንዘብ ሽልማትና የተሳትፎ የምስክር ወረቀቶችን ከባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ድረስ ሳህሉ ተቀብለዋል።

ሩጫው የተካሄደው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ «ዌክ አፕ አፍሪካ» ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው። የዌክ አፕ አፍሪካ የባህር ዳር አስተባባሪ ወጣት ታዬ ልይህ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገረው የሩጫው ዓላማ እየተቀዛቀዘ የመጣውን አካል ብቃት ለማነሳሳትና ወጣቱ ከወንጀል እንዲርቅ፣ ለከተማዋ ሰላም እንዲሰራ ለማሳሰብ ጭምር ነው። በሩጫው ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተውታታ እስከ 3000 የሚደርስ ሯጭ መሳተፉንም ወጣት ታዬ አመልክቷል።

በሩጫው አንደኛ የወጣው የአማራ ክልል ፖሊስ አትሌት በረከት ዘለቀ ሩጫው ትንሽ ከበድ ያለ እንደነበር ተናግሯል፣ ቢሆንም በሩጫው ደስተኛ ነበር። ሌላዋ የከአማራ ክልል ፖሊስ አትሌት ዘሪቱ አደራ ከሴቶች 3ኛ የወጣች ሲሆን አስተያየቷን ጠይቀናታል እንደአትሌቷ ነፋስና ሙቀት ቢኖርም ሩጫው አስደሳች እንደነበር ገልፃለች።

በሩጫው ከተሳተፉ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች መካከል አንዱ አቶ ፀጋው ወለላው ሲሆን እንደዚህ ዓይነት ሩጫዎች ለጤናም ከፍተኛ ጥቅም አላቸው ነው ያሉት። በወንዶች በረከት ዘለቀ፣ መለሰ ብርሀንና ድንቃለም አየለ 3ቱም ከአማራ ክልል ፖሊስ ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት እንደየቅደም ተከተላቸው የምስክር ወረቀትና የ10፣ የ7እና የ5ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።

በሴቶች ደግሞ ዓለም አዲስ አያና፣ ከደባርቅ ዋሊያ አትሌቲክስ፣ አሳየች አይቸው ከአዊ ልማት ማህበር፣ ዘውዲቱ አደራ ከአማራ ፖሊስ በቅደም ተከተል ሩጫቸውን አጠናቅቀው የምስክር ወረቀትና የ10፣ የ7እና የ5ሺህ ብር ከባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ እጅ ተቀብለዋል። የባህር ዳሩን ዘገባ ያጠናቀረው ዓለምነው መኮንን ነው። 

ፎርሙላ አንድ

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን በሬድ ቡሉ አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን በነጥብ ተበልጧል። ማክስ ፈርሽታፐን ትናንት ሁለተኛ ሆኖ ባጠናቀቀበት የቱርክ ግራንድ ፕሪ ሽቅድምድም ብሪታንያዊው የዓለማችን ድንቅ አሽከርካሪ በአምስተኛ ደረጃ ለማጠናቀቅ ተገዷል።  ኢስታንቡል ፓርክ መወዳደሪያ ሥፍራ በተከናወነው የትናንቱ ፉክክር ላይ አንደኛ ደረጃን ያገኘው ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ቫለሪ ቦታስ ነው። እስካሁን በተደረጉ ውድድሮች በአጠቃላይ ማክስ ፈርሽታፐን በጠበበ የ6 ነጥብ የበላይነትን ተቆናጧል። ሌዊስ ሐሚልተን በ256,5 ነጥቡ የሁለተኛ ደረጃን ለመያዝ ተገዷል።

ዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ

የቀድሞው የክሮሺያ ፕሬዚደንት ኮሊንዳ ግራባር-ኪታሮቪች የቀጣይ ኦሎምፒክ አስተናጋጅ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ። ኮሊንዳ ኃላፊነቱን የተረከቡት ክሪስቲን ክሎስተር አሴን የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ (IOC) የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ሆነው በመረጣቸው ነው። በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ደምብ መሰረት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል የቀጣይ ኦሎምፒክ አስተናጋጅ ኮሚሽን ውስጥ መሥራት አይችልም። ያም በመሆኑ ክሪስቲን ኃላፊነታቸውን ለቀድሞው የክሮሺያ ፕሬዚደንት ኮሊንዳ አስረክበዋል። የቀጣይ ኦሎምፒክ አስተናጋጅ ኮሚሽን ወደፊት ኦሎምፒክ ማዘጋጀት ከሚፈልጉ ሃገራት እና ከተሞች ጋር ተቀራርቦ ይሠራል።

የብራዚሉ ኮከብ ተጨዋች ኔይማር የካታሩ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻው መሆኑን ዐስታወቀ። የፓሪስ ሳንጃርሞ አጥቂው የ29 ዓመቱ ኔይማር የልጅነቱ ሕልም የሆነው የዓለም ዋንጫ ለብራዚል ለማስገኘት እንደሚጥርም ገልጧል። ብራዚል በአሁኑ ወቅት በደቡብ አሜሪካ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከምድቧ አንደኛ ናት።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች