የጥቅምት 08 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ  | ስፖርት | DW | 18.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የጥቅምት 08 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ 

አምስተኛ፣ ሰባተኛ እና ዐሥረኛ ከመሀል ኬንያውያቱ ተዘነቁ እንጂ የፓሪስ ማራቶን ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያውያቱ ነበር ማለት ይቻላል። ትናንት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ በተከታታይ የገቡት ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ናቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:07

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

አምስተኛ፣ ሰባተኛ እና ዐሥረኛ ከመሀል ኬንያውያቱ ተዘነቁ እንጂ የፓሪስ ማራቶን ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያውያቱ ነበር ማለት ይቻላል። ትናንት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ በተከታታይ የገቡት ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ናቸው። በወንዶች ብርቱ ፉክክርም ኢትዮጵያ የሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። ለድል ከበቁት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ሁለቱን አነጋግረናል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እጅግ ውብ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ቸልሲ ብሬንትፎርድን 1 ለ0 በማሸነፍ የመሪነቱን ሥፍራ አስጠብቋል። ባየርን ሙይንሽን ባየርን ሌቨርኩሰንን በሰፋ የግብ ልዩነት ድል አድርጓል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ትናንት ዌስትሀም ዩናይትድ ኤቨርተንን 1 ለ0 አሸንፏል። ኒውካስትል ዩናይትድ በቶትንሀም ሆትስፐር የ3 ለ2 ሽንፈት ገጥሞታል። ቅዳሜ ዕለት በነበሩ ግጥሚያዎች ደግሞ፦ እጅግ ብርቱ ፉክክር በታየበት ግጥሚያ ቸልሲ ከታች ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ዘንድሮ ያደገው ብሬንትፎርድን 1 ለ0 ማሸነፍ ችሏል። ቤን ቺልቬል ከግቡ ፊት ለፊት 15 ሜትር ርቀት ላይ ወደ ጎን ተዘምዝዞ በግራ እግሩ በመለጋት ከመረብ ያሳረፈው ኳስ ግሩም የሚባል ነው። በእለቱ የቸልሲው ግብ ጠባቂ ኤዱዋርድ ሜንዲ ቢያንስ ሁለት ያለቀላቸውን ኳሶች ግብ ከመሆን ታድጎ ቡድኑን ከሽንፈት አትርፏል። የሴኔጋል እና ፈረንሳይ ጥምር ዜግነት ያለው ይህ ግብ ጠባቂ የዕለቱ ምርጥ ተጨዋች ነበር ማለት ይቻላል። ማንቸስተር ዩናይትድ በላይስተር ሲቲ የተሸነፈበት የ4 ለ2 ውጤት በርካታ ደጋፊዎቹን ያበሳጨ ነበር።

በአንጻሩ ሊቨርፑል ዋትፎርድን እጅግ በሰፋ የግብ ልዩነት 5 ለ0 አንኮታኩቷል። ሞሀመድ ሳላህ ከተከላካዮች ፊት ወደ ጎን ጨርፎ የላካት ኳስ እየተጥመዘመዘች ሳዲዮ ማኔ ጋር የመድረሷ ልኬት የ ሞ ሳላህ እጅግ ልዩ ጥበብ የታየበት ነበር። ሳዲዮ ማኔም ከኳሷ ፍጥነት ጋር በመሮጥ ተከላካዮች ሳይደርሱበት ከመረብ ያሳረፈበት እንቅስቃሴው የሚደነቅ ነበር። በዕለቱ አራተኛዋን ግብ ሞሀመድ ሳላህ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ሮቤርቶ ፊርሚኖ ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ ሠርቷል።

ዎልቭስ አስቶን ቪላን 3 ለ2 አሸንፏል። ሳውዝሐምፕተን ሊድስ ዩናይትድን 1 ለ0፤ እንዲሁም ማንቸስተር ሲቲ በርንሌይን 2 ለ0 አሸንፈዋል። ኖርዊች ከብራይተን ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። በዚህም መሠረት የደረጃ ሰንዘረዡን ቸልሲ በ19 ነጥብ ይመራል። ሊቨርፑል በ18 ነጥብ ይከተላል። ማንቸስተር ሲቲ 17 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ነው። ብራይተን እና ቶትንሀም 15 ነጥብ ይዘው 4ኛ እና 5ኛ ናቸው። ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ዌስትሀም ዩናይትድ እና ኤቨርተን በ14 ነጥብ ከ6ኛ እስከ 8ኛ ተደርድረዋል።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች፦ ትናንት ባየርን ሙይንሽን በሰፋ የግብ ልዩነት ባየርን ሌቨርኩሰንን 5 ለ1 ጉድ አድርጓል። አርሚኒያ ቢሌፌልድ ከአውግስቡርግ ጋር አንድ እኩል ተለያይተዋል። በቅዳሜ ጨዋታዎችም ፍራይቡርግ ከላይፕትሲሽ፤ እንዲሁም ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ ከሽቱትጋርት ጋር አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ማይንትስን 3 ለ1፣ ሔርታ ቤርሊን ፍራንክፉርትን 2 ለ1፣ ዑኒዮን ቤርሊን ቮልፍስቡርግን 2 ለ0 እንዲሁም ቦሁም ግሮይተር ፊዩርትን 1 ለ0 አሸንፈዋል። ባየርን ሙይንሽን በ19 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡ መሪ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ18 ይከተላል። ባየር ሌቨርኩሰን እና ፍራይቡርግ በ16 ነጥብ 3ኛ እና 4ኛ ናቸው።

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ፦ ትናንት ባርሴሎና ቫለንሺያን 3 ለ1 አሸንፏል። ቪላሪያል በኦሳሱና የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። ሴቪያ ሴልታቪጎን 1 ለ0 ድል ሲያደርግ፤ ኤልሼ በራዮ 2 ለ1 ተሸንፏል። የሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ቢልባዎ፤ እንዲሁም የአትሌቲኮ ማድሪድ እና ግራናዳ ጨዋታዎች ተሰርዘዋል። ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ወደ ደቡብ አሜሪካ ያቀኑ ተጨዋቾች ባለመመለሳቸው እንዲሁም ነገ በሚኖሩ የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች የተነሳ ጨዋታዎቹ ለሌላ ቀን መተላለፋቸው ተገልጧል።  ከትናንት በስትያ በነበሩ የላሊጋ ጨዋታዎች፦ ሳን ሰባስቲያን ማዮካን 1 ለ0 ሲያሸንፍ፤ የሌቫንቴ እና ጌታፌ ጨዋታ ያለምንም ግብ ተጠናቋል።

ሻምፒዮንስ ሊግ

ነገ እና ከነገ በስትያ በሚኖሩ የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች አራት የጀርመን ቡድኖች ይሳተፋሉ። በዚህም መሠረት በነገው እለት ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከሆላንዱ አያክስ አምስተርዳም፤

ላይፕትሲሽ ከፈረንሳዩ ፓሪስ ሳንጃርሞ ጋር ይጋጠማሉ። ረቡዕ ዕለት ደግሞ ባየርን ሙንይሽን ከፖርቹጋሉ ቤኔፊካ እንዲሁም ቮልፍስቡርግ ከኦስትሪያው ኤር ቢ ዛልትስቡርግ ጋር ይጫወታሉ።

ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች፦ ሊዛቦን ከቤሽክታስ፤ ማንቸስተር ሲቲ ከክሉብ ብሩጅ፤ ኤስ ሚላን ከፖርቶ፤ ኢንተር ሚላን ከሸሪፍ፤ እንዲሁም ሊቨርፑል ከአትሌቲኮ ማድሪድ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ። ረቡዕ በሚኖሩ ግጥሚያዎች ደግሞ፦ ባርሴሎና ከዲናሞ ኪዬቭ፤ ቸልሲ ከማልሞይ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ከቤርጋሞ፤ ቪላሪያል ከያንግ ቦይስ፤ እንዲሁም ጁቬንቱስ ከዜኒት ጋር የሚያደርጓቸው ይገኙበታል።

አትሌቲክስ

በፓሪስ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን በትናንትናው ዕለት እጅግ አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል። በተለይ በሴቶች ውድድር ኢትዮጵያውያቱ ሙሉ ለሙሉ መድረኩን ተቆጣጥረውት ነበር። በዚሁ ውድድር ትእግስት ማሙዬ 2:26:12 በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች። የኔነሽ ዲንቄሳ በሦስት ሰከንዶች ልዪዩነት ብቻ የሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። ፋንቱ ጂማ ሦስተኛ፣ እንዲሁም ዋጋነሽ መካሻ አራተኛ ደረጃን አግኝተዋል። የፓሪስ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ የትናንቱን ውድድር ከማለዳው ጀምሮ በቦታው በመገኘት ተከታተትላዋለች። በውድድሩ ወቅት ስለነበረው ድባብ በመግለጥ ትጀምራለች።

በውድድሩ ማጠናቀቂያ ላይ አትሌቶች ችላ መባላቸውን ሃይማኖት ገልጣለች። አንደኛ የወጣችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት ማሙዬ ውድድሩን እንዳጠናቀቀች ያስመልሳት እንደነበረ እና ወኃ ለመጠጣት ፈልጋ የሚሰጣት እንዳልነበረም ተመልክታለች። የመገናኛ አውታሮችም በወንዶች አንደኛ የወጣው ኬንያዊ አትሌት ላይ ሲረባረቡ ኢትዮጵያዊቷ አንደኛ የወጣችውን አትሌት በአስተርጓሚ እንኳን ለማነጋገር አለመሞከራቸው ግራ እንዳጋባት ጠቁማለች።

የቦስተን ማራቶን በተጠናቀቀ በአምስተኛው ቀን የኤርትራዋ ሯጭ ወይኒ ኬላቲ በ10 ሺህ ኪሎ ሜትር ሩጫ ታሪክ መሥራቷ ተዘግቧል። ወይኒ በአሜሪካዊቷ ሞሊይ ሐድል ተይዞ የነበረውን የአሜሪካ ክብረወሰን ቦስተን ውስጥ ቅዳሜ ዕለት በ3 ሰከንድ ልዩነት መስበር ችላለች። ሞሌይ ከ6 ዓመታት በፊት ቦስተን ውስጥ ውድድሩን ያጠናቀቀችው 31 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ በመሮጥ ነበር። ወይኒ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት 31 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ ነው። የ24 ዓመቷ ወይኒ በኒው ሜክሲኮ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ብሔራዊ ድሎችን ካስመዘገበች ወዲህ የቦስተኑ ድሏ የመጀመሪያዋ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

 

Audios and videos on the topic