የጥር 3 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 11.01.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የጥር 3 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

የተከላካይ ክፍተቱን መሸፈን የተሳነው መሪው ባየር ሙይንሽን ላይፕትሲሽን የሚበልጠው በሁለት ነጥብ ብቻ ነው። በፕሬሚየር ሊጉ መሪው ሊቨርፑል አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ምናልባትም የመሪነት ደረጃውን አስረክቦ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ሊያሽቆለቊልም ይችላል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:40

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የተከላካይ ክፍተቱን መሸፈን የተሳነው መሪው ባየር ሙይንሽን ላይፕትሲሽን የሚበልጠው በሁለት ነጥብ ብቻ ነው። አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ባየር ሙይንሽን የሚበልጠው በአምስስት ነጥብ ብቻ ነው። በፕሬሚየር ሊጉ መሪው ሊቨርፑል አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ምናልባትም የመሪነት ደረጃውን አስረክቦ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ሊያሽቆለቊልም ይችላል።

ፕሬሚየር ሊግ

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኘው ሼፊልድ ዩናይትድ ከኒውካስትል ጋር በሚያደርገው ፍልሚያ ከነገ ጀምሮ ይቀጥላል። ነገ ከኒውካስትል ግጥሚያ በኋላ በተመሳሳይ ሰአት ሁለት ጨዋታዎች አሉ። በደረጃ ሰንጠረዡ ከመሪው ሊቨርፑል በአንድ ነጥብ ብቻ የሚበለጠው ማንቸስተር ዩናይትድ በርንሌይን ይገጥማል። ማንቸስተር ዩናይትድ በተስተካካይ ጨዋታው 16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው በርንሌይን ካሸነፈ ነጥቡን 36 በማድረስ ሊቨርፑልን በ3 ነጥብ ይበልጣል። ይህ ግጥሚያ ለማንቸስተር ዩናይትድም ሆነ ታች ካሽቆለቆለበት ለመውጣት ለሚታገለው በርንሌይ ወሳኝ ግጥሚያ ነው። ጨዋታውን የሊቨርፑል ደጋፊዎችም የሚመለከቱት ለበርንሌይ ወግነው ነው ቢባል ስህተት አይሆንም።

ኤቨርተን ከዎልቨርሀምፕተን ጋር ነገ በሚያደርገው ሌላ ተስተካካይ ግጥሚያ አራተኛ ደረጃን የማግኘት ተስፋ ሰንቋል። በእርግጥ ተመሳሳይ 29 ነጥብ ያላቸው ቶትንሀም፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ሳውዝሀምፕተን ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ተደርድረዋል። ማንቸስተር ሲቲ ሁለት ከሳውዝሀምፕተን ውጪ ሌሎቹ አንድ ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀራቸዋል። ቶትንሀም ሆትስፐር ረቡዕ ማታ ከአስቶን ቪላ ጋር ገጥሞ ካሸነፈ የላይስተር ሲቲን የሦስተኛ ደረጃ ይረከባል። አስቶን ቪላም ቢሆን ቀሪ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎቹን ማሸነፍ ከቻለ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ የማለት ዕድል አለው።

ማንቸስተር ሲቲ ረቡዕ ምሽት ከብራይተን እንዲሁም እሁድ ማታ ከክሪስታል ፓላስ ጋር የሚያደርጋቸውን ተስተካካይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ከቻለ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ መሪ የመሆን ዕድል አለው። ማንቸስተር ዩናይትድ የነገውን ግጥሚያ ካሸነፈ ግን ማንቸስተር ሲቲ ዕድሉ የሁለተኛ ደረጃ ብቻ ይሆናል። ከሁለት አንዱን ተስተካካይ ጨዋታ ብቻ አሸንፎ ግን የሦስተኛ ደረጃን ማግኘት ይችላል።  እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ በሚኖሩ ግጥሚያዎች የደረጃ ሰንጠረዡን በ33 ነጥብ የሚመራው ሊቨርፑል ወደ ሁለተኛ እንዲሁም ወደ ሦስተኛ ደረጃም ሊንሸራተት ይችላል። ምናልባት ግን ማንቸስተር ዩናይትድ ነጥብ ከጣለ እሁድ ከሊቨርፑል ጋር የሚኖራቸው ግጥሚያ መሪውን የሚለይ ይሆናል። በአጠቃላይ የሊቨርፑል የመሪነት ዕድል የተንጠለጠለው በቀጣይ ጨዋታዎች ውጤት ላይ ነው። ላይስተር ሲቲ ከሊቨርፑል በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

 

ኤፍ ኤ ካፕ

የእንግሊዝ የኤፍ ኤ ካፕ ሦስተኛ ዙር ግጥሚያ ቀጥሎ ዛሬ ማታ  ዌስትሀም ስቶክፖርትን ይገጥማል። በትናንት ግጥሚያዎች፦ ቶትንሀም ሆትስፐር ማሪነን 5 ለ0 ሲያንኮታኩት፤ ቸልሲ ሞርካምቤን 4 ለ0 ሸኝቷል። ማንቸስተር ሲቲ ቢርሚንግሃምን 3 ለ0 አሸንፏል። ዋትፎርድ በማንቸስተር ዩናይትድ ቅዳሜ ዕለት 1 ለ0 ተሸንፏል። አርሰናል ኒውካስልን 2 ለ0 ድል አድርጓል። ቅዳሜ ዕለት በኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያዎች በርካታ ግቦች ተቆጥረዋል።  ላይስተር ሲቲ ስቶክን 4 ለ0 እንዲሁም ቦርመስ ኦልሃምን 4 ለ1 አሸንፈዋል። ኤቨርተን ሮተርሀምን ያሸነፈው 2 ለ1 ነበር። ዐርብ ማታ ሊቨርፑል ቪላ ፓርክ ስታዲየም ውስጥ አስቶን ቪላን 4 ለ1 ድል አድርጓል።

ቡንደስሊጋ

ከቡንደስሊጋው አጠቃላይ 34 ግጥሚያዎች 15ኛው ዙር ግጥሚያ በሳምንቱ መጨረሻ ተከናውኗል። መሪው ባየርን ሙይንሽን 33 ነጥብ ይዞ ላይፕትሲሽን የሚበልጠው በ2 ነጥብ ብቻ ነው። ትናንት በቦሩስያ ዶርትሙንድ የ3 ለ1 ሽንፈት ባይገጥመው ኖሮ ላይፕትሲሽ የመሪነት ስፍራውን ከባየር ሙይንሽን መረከብ ይችል ነበር። ቦሩስያ ዶርትሙንድ 28 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ባየር ሌቨርኩሰን በ4 ነጥብ ብቻ ተበልጦ ሦስተኛ ደረጃ ይዟል። 

ዑኒየን ቤርሊን እና ቮልፍስቡርግ 25 ነጥብ ይዘው 5ኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በ24 ነጥቡ 7ኛ ነው። 8ኛ እና 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፍራይቡርግ እና ፍራንክፉርት ከመሪው ባየር ሙይንሽን የነጥብ ልዩነታቸው የ10 ብቻ ነው።

 

ትናንት በተከናወኑ የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች ከታችኛው ዲቪዚዮን ዘንድሮ ወደላይ ከፍ ያለው አርሜኒያ ቢሌፌልድ ሔርታ ቤርሊንን 1 ለ0 አሸንፏል። ኾኖም አርሜኒያ 13 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ 15ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ሽቱትጋርት 76ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ተጨዋቹን በቀይ ያጣው አውግስቡርግን 4 ለ1 ረትቶ ደረጃውን በአንድ ወደ 10ኛ አሻሽሏል። ቅዳሜ ዕለት በተከናወኑ ጨዋታዎች፦ ኮሎኝ በሰፋ የግብ ልዩነት በፍራይቡርግ 5 ለ0 ተሸንፏል። ከቬርደር ብሬመን ጋር አንድ እኩል የተለያየው ባየር ሌቨርኩሰን ነጥብ በመጣሉ ሁለተኛ ደረጃ የመያዝ ዕድሉን አምክኗል። ሻልከ የበርካታ ጊዜያት የሽንፈት ሰንሰለቱን በጥሶ ሆፈንሃይምን በሰፋ የግብ ልዩነት 4 ለ0 ድል አድርጓል።

መሪው ባየርን ሙይንሽን ዐርብ ዕለት በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ የ3 ለ2 ሽንፈት ገጥሞታል። ባየርን ዘንድሮ በታሪኩ የተከላካይ ክፍሉ እጅግ ደካማ የሆነበት የጨዋታ ዘመን ነበር የ2020። በመጀመሪያዎቹ 15 የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች 24 ግቦች ሲቆጠሩበት ከ39 ዓመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በ1981/82 የጨዋታ ዘመን ነበር እንዲህ ሰፊ ግብ የተቆጠረበት። በወቅቱ ባየርን ሙይንሽን በ15 ዙር ግጥሚያዎች 25 ግቦችን ለማስተናገድ ተገዶ ነበር። ባየርን ሙይንሽን በዚህ የጨዋታ ዘመን ግብ ያልተቆጠረበት ለሁለት ጊዜያት ብቻ ነው። ሻልከን 8 ለ0 ድባቅ በመታበት የመክፈቻ ጨዋታ እና ፍራንክፉርትን 5 ለ0 ባሸነፈበት 5ኛው ዙር ግጥሚያ ብቻ ነበር ባየርን ሙይንሽን መረቡን ያላስደፈረው። 

ባየርን ሙይንሽን ላይ ከታች ያደገው ቢሌፌልድ እንኳን አስቆጥሮበታል። በ4ኛው ዙር ግጥሚያ ባየርን አርሜኒያ ቢሌፌልድ ላይ 4 ግቦችን ሲያስቆጥር፤ ቢሌፌልድ የባየርን መረብ ላይ 1 ግብ ማሳረፍ ችሏል። በተከላካይ በኩል ከፍተኛ ክፍተት የሚታይበት ባየርን ሙይንሽን ከተቆጠሩበት 24 ግቦች መካከል 14ቱ ከመጀመሪያው አጋማሽ በፊት ነው የተመዘገቡት። ብዙዎቹ ግቦች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 15 ደቂቃ ሲቀረው ነው የተቆጠሩት። በዚህ መልኩ 7 ግቦች ተቆጥረውበታል።

 

ባየርን ሙይንሽን ዐርብ እለት መሸነፉ የዓለማችን ምርጥ ግብ ጠባቂ ላይም ተጽኖውን አሳርፏል። የዐርቡ ሽንፈት ተደምሮ ማኑዌል ኖየር ባለፉት ዐሥር ጨዋታዎች ቢያንስ አንድ ግብ እንዲቆጠርበት ግድ ብሏል። ከዚህ ቀደም የሻልከ ግብ ጠባቂ በነበረበት ጊዜ እንኳን ማኑዌል ኖየር ላይ እንዲህ ግብ አልተቆጠረበትም። ባየር ሙይንሽን የተከላካይ ክፍሉ ተደጋጋሚ ክፍተት እና ድክመት ታይቶበታል።

በዐርቡ ግጥሚያ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባህ ከ2 ለ0 ተነስቶ ነው ያሸነፈው። ላይፕትሲሽ ቦሩስያ ዶርትሙንድን ቅዳሜ ዕለት ቢያሸንፍ ኖሮ የደረጃ ሰንጠረዡን ይመራ ነበር። ግን ኧርሊንግ ሃላንድ በገነነበት ምሽት በዶርትሙንድ 3 ለ1 ሽንፈት ቀምሷል። ሃላንድ ሁለት ግቦች፤ ጄደን ሳንቾ አንድ ግብ አስቆጥረዋል።

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያ፦ ጌታፌ ዛሬ ማታ ኤልሼን ሲገጥም ቤቲስ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 20ኛ የሚገኘው ሆዬስካን ሊገጥም ወደ ኤል አልኮራዝ ስታዲየም ያቀናል። ቤቲስ 20 ነጥብ ይዞ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ጌታፌ እና ኤልሼ 17 እና 16 ነጥብ ይዘው 17ኛ እና 18ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት፤ በእርግጥ ኤልሼ ሁለት ጌታፌ አንድ ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀራቸዋል።  

በላሊጋው ሦስት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት አትሌቲኮ ማድሪድ በ38 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ሪያል ማድሪድ በ37 ነጥብ ይከተላል።  ባርሴሎና 34 ነጥብ አለው። ሦስተኛ ደረጃን ይዟል። 32 ነጥብ ያለው ቪላሪያል የአራተኛ ደረጃን ተቆናጧል። 30 ነጥብ ይዞ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሴቪያ የባርሴሎናን የሦስተኛ ደረጃ የመረከብ ዕድል አለው። አንዱን ተስተካካይ ጨዋታውን ነገ ማታ ከመሪው አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ያከናውናል። ሁለተኛውን ቀሪ ጨዋታውን የሚያከናውነው ደግሞ የነገ ሳምንት ከአላቬስ ጋር ነው።

አላቬስ እንደ ቫላዶሊድ 18 ነጥብ ይዞ ግን በግብ ክፍያ በልጦ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ ከሜዳ በተሰናበተበት ግጥሚያ ትናንት ከካዲዝ ጋር ገጥሞ 3 ለ1 ተረትቷል። ካዲዝ በግብ ክፍያ ብቻ ተበልጦ በ23 ነጥቡ  ደረጃው 9ኛ ነው። ነገ ማታ ግራናዳ ከኦሳሱና ጋር የሚያደርጉትም ጨዋታ የሚጠበቅ ነው። 19ኛ ደረጃ ላይ በ15 ነጥብ የተወሰነው ኦሳሱና ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት፤ ግራናዳ ደግሞ ከ7ኛ ደረጃ ወደ ላይ ጠጋ ለማለት ርብርብ የሚያደርጉበት ግጥሚያ።

አትሌቲክስ

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ትናንት ጥር 2 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ለ20ኛ ጊዜ ተከናውኗል። በውድድሩ ታዋቂ አትሌቶች እና ኅብረተሰቡ የተካፈለ ሲሆን ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር ተያያዥ የሆኑ መፈክሮችም በተሳታፊዎች ሲስተጋቡ ተደምጠዋል። በ10 ኪሜ የሴቶች ሩጫ ውድድር ፅጌ ገ/ሰላማ እንዲሁም በወንዶች ፉክክር አቤ ጋሻሁን አሸናፊ በመሆን ለእያንዳንዳቸው የተዘጋጀላቸውን የብር 100,000.00 ሽልማት መረከባቸው ተዘግቧል።

በሌላ የአትሌቲክስ ዜና፦ «1ኛ ደረጃ የዓለም አትሌቲክስ አሰልጣኝነት ሥልጠና» ትናንት መጀመሩን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዐስታውቋል። ሥልጠናውን የሚከታተሉት በሀገር ውስጥ የ2ኛ ደረጃ የአትሌቲክስ ስልጠናን በብቃት አጠናቀው የጨረሱና በሞያው ስልጠና እየሰጡ የሚገኙ ሰልጣኞች እንደኾኑ ተገልጧል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic