የጥሬ ሀብት ንግድ ማሽቆልቆል እና አፍሪቃ | ኤኮኖሚ | DW | 11.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የጥሬ ሀብት ንግድ ማሽቆልቆል እና አፍሪቃ

በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያ የጥሬ ሀብት ዋጋ እጅግ አሽቆልቁሎአል። በጥሬ ሀብቱ ዋጋ መቀነስ የተጎዳዉ ደግሞ ደሃዉ የአፍሪቃ ኅብረተሰብ ነዉ።


ዛክ ሊሱኩ በናይጄርያ ሪቨርስ አዉራጃ ዉስጥ በሚገኘዉ አንድ የዘይት ኤንዱስትሪ ማዕከል በኃይል ምንጭ ዘርፍ ባለሞያነት ያገለግላሉ። ዛክ ሊሱኩ ከወራቶች ጀምሮ በሀገራቸዉ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ማሽቆልቆል መጀመሩን እየታዘቡ ነዉ። ባለፈዉ ሰኔ ወር አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ማለትም የ«159» ሊትር የነዳጅ ዘይት፤ 105 ዶላር ያወጣ ነበር። አሁን በያዝነዉ ጥቅምት ወር ማለቂያ ላይ ደግሞ የአንድ በርሜል ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ዋጋ 80 ዶላር ገብቶአል። የነዳጅ ዘይት ዋጋ በማሽቆልቆሉ ግን ምንም ሥጋት እንደሌላቸዉ ነዉ ዛክ ሊሱኩ የሚገልፁት። በአፍሪቃ በነዳጅ ዘይት ንግድ ኤኮኖሚያቸዉ ካደገ ሃገሮች መካከል ናይጀርያ ትጠቀሳለች። የሀገሪቱ 80 በመቶ ገቢ የሚገኘዉ ከዚሁ ከነዳጅ ዘይት ንግድ መሆኑን የኃይል ምንጭ ዘርፍ ምሁሩ ዛክ ሊሱኩ ይናገራሉ፤


እንዲያም ሆኖ በናይጀርያ የነዳጅ ዘይት ንግድ ሽያጭ ማሽቆልቆል እስከመቼ ይሆን? በሀገሬቱ የሚገኙ የዘርፉ ባለሞያዎች ግን እስከ ዛሬ መተንበይ አልቻሉም። ባለፉት ዓመታት ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት ነዉ የታየዉ ። በነዚህ ሃገራት 70 በመቶ የሚሆነዉ ገቢ የተገኘዉም ጥሬ እቃን ለዉጭ ገበያ በማቅረብ ነዉ ። ይህን ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት እንደ ጥሬ እቃዉ ዋጋ ዉድቀት ሊገታ ሊቀንስ ይችላል። ይህን የሚከላከሉበት ምንም አማራጭ ስልት የላቸዉም።»
ሲሉ በሀንቡርግ «ጊጋ » በተሰኘዉ የአፍሪቃ ጥናት ተቋም ፕሬዚዳንትና በአፍሪቃ ኤኮኖሚ ላይ ጥናት የሚያደርጉት ፕሮፊሰር ሮበርት ካፕል ተናግረዋል። ካፕል እንደሚሉት በዓለም ገበያ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ማሽቆልቆል የናይጄያን ኤኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የጎዳዉ የአፍሪቃ ሃገራት ኤኮኖሚንም አንቆ ይዞአል።
ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ጠበብቶችም ጥሬ እቃን ለዉጭ ገበያ በማቅረብ ላይ የተመሰረተዉ የብዙ አፍሪቃ ሀገሮች ኤኮኖሚ ፤ ዘርፋቸዉን በማስፋት ሌላ የኤኮኖሚ ዘርፍን መያዝ መጀመር አለባቸዉ ሲሉ ፕሮፊሰር ሮበርት ካፕል ያሳስባሉ። ተለዋጭ የኤኮኖሚ ገቢ ዘርፍ መጀመር የነበረበት ደግሞ የነዳጅ ዘይት ገብያቸዉ በሰመረበት ግዝያት እንደነበርም አመልክተዋል። ምንም እንኳ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዘይትና የሌሎች የተፈጥሮ ጥሬ ሃብቶች ዋጋ ከፍተኛ ዉዥቀት እንዳለበት ቢታወቅም ኤኮኖሚ ገብያቸዉ ተመጣጣኝ እና የተስተካከለ እንዲሆን ለወደፊቱ ተዘጋጅተዉ የጠበቁ ጥቂት ሀገሮች ብቻ ናቸዉ። ለዚህም በምሳሌነት የባሕረ ሰላጤዉ አረብ ሀገሮች ተጠቃሽ ናቸዉ ። ናይጀርያ ለዉጭ ገበያ ከምታቀርበዉ የነዳጅ ንግድ ተቀማጭ ሃብት የላትም፤ ባገኘችዉ ገቢም ሌሎች የኤኮኖሚ ዘርፎችንም አላቋቋመችም። በዚህም ይላሉ ፕሮፊሰር ሮበርት ካፕል ሀገሮች በነዳጅ ዘይት ዋጋ መዋዠቅ የሚገጥማቸዉ የገቢ ምንጭ ማነስ ችግር ማኅበረሰቡ ላይ ተፅኖ ያሳድራል። ለምሳሌ በመንግሥት መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ የሚፈሰዉ መዋለ ንዋይ ሲቀንስ ተጎጅዉ ማኅበረሰቡ ነዉ።
« አንጎላ ከሠራችዉ ትልቅ ቁም ነገር ገንዘብ አጠራቅማ ወደ ሰላሳ ቢሊዮን ዶላር ተቀማጭ እንዲኖራት ማድረጓ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ አንጎላ ሌላዉን የኤኮኖሚ ዘርፍ ከነዳጅ ዘይት ባገኘችዉ ገቢ በማስፋፋት ወደ 60 በመቶ የሚሆነዉን የሀገሪቱን ገቢ ከአዲስ የኤኮኖሚ ምንጭዋ ማግኘት ችላለች። መንግሥት ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነዉን የሀገሪቱን የነዳጅ ዘይት ገቢ የሚጠራቀምበትን ስልት ቀይሷል።»
ይህ ተቀማጭ ገንዘቧ የኤኮኖሚ ቀዉስ በሚከሰትበት ወቅት ያገለግላታል። አንጎላ በጎርጎረሳዉያኑ 2008 እስከ 2009 ዓ,ም በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤኮኖሚ ቀዉስ ካስከተለዉ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ማሽቆልቆል አደጋ ትምህርትን አግታለች ሲሉ በጀርመኑ ዶቼ ባንክ የዘርፉ ተንታኝ የሆኑት ክሌር ሻፍኒት ቻተርጂ ገልፀዋል።


እንደ ጋቦን እና ኢኳቶርያል ጊኒ የመሳሰሉ ትናንሽ የአፍሪቃ ሀገሮች መሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ማፍሰሳቸዉን በጀርመን የዉጭ ንግድ እና ኢንቬስትመንት የምዕራብ አፍሪቃ ተወካይ ካርስተን ኤለርስ ይገልፃሉ። « በአሁኑ ወቅት የሀገራቱ ዋና ከተሞች አንጻራዊ ዘመናዊነት ይታይባቸዋል። ቢሆንም ቅሉ መሠረተ ልማቱ በበቂ ሥራ ላይ አልዋለም። መዋለ ንዋይ የፈሰሰባቸዉ ግዙፍ ፕሮዤዎች ልክ እንደ ዱባይ ባለሃብትን ወደ ሃገራቸዉ ለመሳብ ታስቦ የተገነባ ቢሆንም አልተሳካላቸዉም።»
የነዳጅ ዘይት ዋጋ ማሽቆልቆል ከቀጠለ የሠሯቸዉን መሠረተ ልማቶች በዘላቂነት ሊጠቀሙባቸዉ አይችሉም። ጋና ዉስጥ በማሽቆልቆል ላይ ያለዉ የጥሬ ሃብት ዋጋ ተፅዕኖ በጣም ጉልህ በሆነ ሁኔታ ይታያል። ይህች ምዕራባዊት የአፍሪቃ ሀገር ከሌላዉ ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ ነዳጅ ዘይትን በማምረት ለዉጭ ገበያ ማቅረብ ጀምራለች። ባለፉት ግዜያት በጋና ለማኅበረሰቡ የሥራ ቦታ ያስገኙ የነበሩ የወርቅ ማዕድን ማዉጫና የካካዎ ምርቶች ነበሩ።
እንደ ኤለርስ የነዚህ ሁለት ጥሬ ሃብቶች ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ ከመጠን በላይ ዝቅ ብሏል።
የወርቅ ማዕድን መቆፈርያ ቦታዎች ትርፍ የማያስገኙ ከሆነ ቶሎ ይዘጋሉ። በነዚህ የማዕድን ማዉጫ ቦታዎች ይሠሩ የነበሩ በርካታ ጋናዉያን ከሥራ ተባረዋል። ችግሩ በጣም ጉልህ ሆኖ የሚታየዉ ትናንሽ የካካዎ ምርት አቅራቢዎች በካካዎ ዋጋ መዉደቅ የሚደርስባቸዉ ኪሳራ ነዉ።
በዓለም ገበያ የካካዎ ምርት በሚወድቅበት ጊዜ የነዚህ ሀገር መንግሥታት ከገበሬዉ የካካዎ ምርቱን የሚሸምቱት በድሮዉ ዋጋ ብቻ ነዉ። እንደ ኤለርስ አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሀገሮች በአብዛኛዉ የሥራ ቦታ ያለዉ እርሻ ላይ ነዉ። ስለዚህም የጥሬ ሃብት ንግድ ማቆልቆል ቀዉስ በሚከሰትበት ወቅት አብዛኛዉ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ችግር ይደርስበታል።


እንደ ኤለርስ ገለፃ በነዳጅ ዘይት ዘርፍ በሚደርሰዉ የዋጋ ዉዥቀት ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችና ትላልቅ ባለሃብቶች ላይ የሚደረሰዉ ቀዉስ በጣም ከፍተኛ የሚባል አይደለም። እነዚህ ባለሃብቶች ሥራ ላይ ያዋሉት ገንዘብ በቢሊዮን የሚቆጠር ቢሆንም ለ 20 ዓመት ታስቦ የተደረገ ነዉ። ስለዚህ ለረጅም ግዜ መዋለ ንዋይ የፈሰሰበት የልማት ዘርፍ በአጭር ጊዜዉ የዋጋ ዉዥቀት ጉዳት አይደርስበትም።
እንደ አብዛኞች ምሁራን አስተያየት ፤ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ በቅርቡ ይንኮታኮታል የሚል እምነት የለም። በጀርመን ባንክ ጥናት ላይ የሚገኙት ቻርተርጂ እንደሚሉት ከሳሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት በከፍተኛ ፍጥነት እድገት እየታየባቸዉ ነዉ። በነዚህ ሃገራት በመጭዉ የጎርጎረሳዊ 2015 ዓ,ም 5 በመቶ እድገት ይታያል ተብሎ ይጠበቃል። በሌላ በኩል የጥሪ ሃብት ዋጋ ማሽቆልቆል በአብዛኛዉ ነዋሪ ላይ ተፅኖ ያሳድራል ሲሉ ፕሮፊሰር ሮበርት ካፕል ይናገራሉ።

ክስ ቦሮዞቭስኪ / አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic