የጥላቻ ንግግር ከትችት እንዴት ይለያል? | ወጣቶች | DW | 12.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

የጥላቻ ንግግር ከትችት እንዴት ይለያል?

በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ያለው የጥላቻ ንግግር እና የሀሰት ወሬን አስመልክቶ ሀገሪቱ የፀረ ጥላቻ ንግግር ህግ አርቅቃለች። ባለፈው ሳምንት ይፋ የሆነው ረቂቅ  ከፀደቀ ህጉ በነፃነት የመናገር መብታችንን ሊነፍግ ይችላል የሚሉ አንዳንድ ወጣቶች ስጋታቸውን አካፍለውናል። በርግጥ ስጋታቸው ከፀረ ጥላቻ ህግ ጋር ይገናኛል? ወይስ ህጉን አልተረዱትም?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:16

የፀረ ጥላቻ ንግግር

ረቂቅ ህጉ  ፀድቆ ተግባራዊ እስከሚሆን ረዥም ሂደት አለው።ረቂቁ ላይ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ  ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይቀርባል። ይህም ምክር ቤት ካጸደቀው ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይተላለፋል። ከዛ በኋላ ነው ፀድቆ ተግባራዊ መሆን የሚችለው።  
በአሁኑ ወቅት በተለይ በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በብሔር ላይ የተመረኮዙ የጥላቻ መልዕክቶች መነበባቸው ቀጥሏል። ከዛም አልፎ ምስሎችን በመቀያየር የተሳሳተ መረጃዎች ይሰራጫሉ። አብዮት ግን ስለ ጥላቻ ንግግር ረቂቅ ህጉ ብዙ መረጃ ባይኖረውም በደፈናው ይቃወመዋል። « የግድ ቃላትን መምረጥ ያስፈልጋል። መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ያኔ ደግሞ ላለመናገር ወደመፈለግ ያመራል» ይላል።

የፀረ ጥላቻ ንግግር ህግ የመናገር መብትን እንዳልገደበ የሌሎች ህጉን ተግባራዊ ያደረጉ ሀገሮች ተሞክሮ ያመላክታል። ይልቁንስ ሰዎች የሚያሰራጭቱን መልዕክት ሁለት ጊዜ እንዲያጤኑት ነው ያበረታታው። የጥላቻ ቃል ምንድን ነው? እዚህ ጀርመን  ከጥላቻ ንግግር ጋር በተያያዘ የተሰጡ ፍርዶችን በምሳሌነት እንጥቀስ፣ አንድ የ 28 ዓመት ጀርመናዊ መራሄ መንግሥት ሜርክል « በአደባባይ በድንጋይ መደብደብ አለባቸው » የሚል መልዕክት በማህበራዊ መገናኛ በማሰራጨቱ 2000 ዩሮ እንዲቀጣ ተፈርዶበታል። መልዕክቱ ሌሎችን ለአመፅ ይጠራል በሚል ነው። 
አንድ የ 34 ዓመት በርሊናዊ ደግሞ የጥላቻ ንግግሩን በማን ላይ እንደነበር ግልፅ ሳያደርግ በጥቅሉ « የጋዝ ክፍሎች መከፈት አለባቸው» በማለቱ 4800 ዩሮ ተቀጥቷል። በእነዚህ ክፍሎች በናዚ አገዛዝ ጊዜ የብዙ አይሁዳውያን ህይወት በጋዝ ታፍነው የተገደሉበት በመሆኑ ነው።


ሌላው ደግሞ ሶስት ዓመት ከአራት ወር እስራት የተፈረደበት የአልቃይዳ ቡድን የሰዎችን ሲገድል የሚያሳይ ቪዲዮ ሌሎች እንዲያዩት በማሰራጨቱ ወይም በግል ገፁ ላይ ሼር በማድረጉ ነው። 
አንድን ፖለቲከኛ  «ህፃናት ደፍሯል» ሲል የሀሰት ወሬ ያሰራጨ ጎልማሳ ደግሞ በስም ማጥፋት ወንጀል  1 ዓመት ከ 9 ወር እስራት ተፈርዶበታል። 
ወደ አልጸደቀው የኢትዮጵያ የፀረ ጥላቻ ህግ ረቂቅ እንመለስ፤ እዛ ላይ ሶስት አይነት ቅጣቶች ተቀምጠዋል።ቅጣቱ እንደ ጥፋቱ ክብደት  ይለያያል። የፌደራል ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ለDW እንደገለፁት ቅጣቱ  የማህበረሰብ አገልግሎች ከማበርከት እስከ ገንዘብ እና እስራት ቅጣት ሊደርስ ይችላል። ይህም ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ነው። የረቂቅ ህጉን የተከታተለው ወጣት ቅጣቱ ከፍ ማለት እና ህጉም በፍጥነት ተግባራዊ ቢሆን ይመርጣል። « ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ይሄ ትንሽ ነው ባይ ነኝ። ህጉ ቢሆር ደስተኛ ነኝ። መንግስት ይህንን በፍችነት ቢያደርገው እና ሀገሪቱን ማረጋጋት ቢቻል ጥሩ ነው ይላል።

እዮብም የውሹት ና የጥላቻ ንግግርን የሚያስተላልፉትን ማስቆሙ ጥሩ ነው ይላል። እንደ እሱ ከሆነ ግን ለዚህ የግድ ህግ መውጣት የለበትም። « ውሸትን ለማጥፋት አስር ጊዜ ህግ ማውጣት ሳይሆን መንግሥት እውነትን እና ፈጣን ርምጃ ሲዘረጋ ነው። ችግር ሲደርስም ቶሎ አለሁ ሲል ነው።» እዮብ የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን አጠቃቀሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደተቀየረ እና ስሜታዊ እየሆነ መምጣቱንም ነግሮናል። « ሰው ነኝ እና የሆነ የሚያናድድ ነገር ስሰማ ለዛ ምላሽ እሰጣለሁ። አንዳንዴ ከተናገርኩት በኋላ ይጸፅተኛል።»ወጣት አህመድ ሀገሪቱ ያለችበት ቀውስ ነው ለጥላቻና ለሀሰት ወሬዎች ምክንያት የሆኑት ይላል። መረጃዎቹን የሚያገኘው ከመገናኛ ብዙኃን ይሁን ከግለሰቦች ሳይገልፅ የሚያነባቸው ብዙው መረጃዎች ግን ትክክል ናቸው ይላል። « በርግጥ የተጋነነ ቢሆንም እውነታ አላቸው።» ይላል። አብዛኛውን ጊዜ የጥላቻ ንግግሮች ወይም የሀሰት መረጃዎች ተስፋፍተው የሚታዩት ወይም የሚነበበቡት እንደ ፌስቡክ ባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ነው። ከመልዕክቱ በስተጀርባ ያለው ሰው የግድ ግልፅ አይደለም። ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን የኢንተርኔት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ወንጀሎችን የሚፈፅሙ ሰዎች ማንነታቸው እንዳይታወቅ አድርገው ስለሆነ ወንጀል የሚሰሩት የጥላቻ ንግግር የሚያሰራጩትን ሰዎች ለይቶ ማግኘትን የስራው ሂደት አድርገው ይመለከቱታል። ወንጀሉን የሰራውን መርምሮ ማግኘት እና ማጣራት ደግሞ የፖሊስ ስራ ስለሆነ በተመሳሳይ አግባብ እንደሚስተናገድ ገልፀውልናል። ግለሰቦቹ ከሀገር ውጪ ከሆነስ የሚገኙት? ዶክተር ጌዲዮን ቃል በቃል ያሉን እንደሚከተለው ይነበባል።« ከተለያዩ ሀገራት ጋር አብሮ ለመስራት በህግ ጉዳዮች ላይ ትብብር የማድረግ ስምምነት የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያየ ጊዜ ተፈራርሟል። እየተፈራረመም ይሄዳል። በተለይ የሰብዓዊ መብት አያያዛችን እየተሻሻለ በሄደ ቁጥር ፣ ተቋሞቻችን እና ህጎቻችን ላይ የምናደርገው ማሻሻያ ፍሬ እያፈራ በሄደ ቁጥር ብዙ ሀገሮች አብሮ ለመስራት ፍቃደኛ ይሆናሉ። » ይላሉ የህጉ ባለሙያ። 


የፀረ ጥላቻ ንግግር ህጉ ተግባራዊ እስኪሆን መጣቶች እንዴት መረጃ መሰብሰብ ይጠበቅባቸዋል? ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ «ህጉ ሳይወጣም ሆነ ከወጣም በኋላ ከዜጎች የሚጠበቀው የሚያሰራጩትን፣ የሚያነቡትን የሚቀበሉትን ማንኛውንም መረጃ እና ዜና ከተአማኒ ምንጭ ነው የመጣው አይደለም ፤ መረጃውን እያሰራጨ ያለው ሰው ማነው ብለው ማጤን ይገባቸዋል።» ብለዋል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ


 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች