የጣሊያን ሰርከስ ቡድን በኢትዮጵያ | ባህል | DW | 26.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የጣሊያን ሰርከስ ቡድን በኢትዮጵያ

ከአንድ ወር በፊት ሰርከስ ለማሳየት ከጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘው ቡድን ቺርኮ ኢንዚር ይባላል። ቡድኑ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች እየተዘዋወረ ሰርከስ ሲያሳይ ቆይቶ የመጨረሻውን የመድረክ ዝግጅት በዚህ ሳምንት መጨረሻ አዲስ አበባ ውስጥ ያካሂዳል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:27
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:27 ደቂቃ

ቺርኮ ኢንዚር እና ፍካት ሰርከስ

ከወጣት እና ጎልማሳ ቡድን የተውጣጣው እና ከጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘው የቺርኮ ኢንዚር የሰርከስ ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ወር ሆነው። ለሰርከሱ የሚያስፈልጉትን መገልገያዎች በአይዙሱዙ መኪና ጭኖ ከክፍለ ሀገር ወደ ክፍለ ሀገር እየተዘዋወረ ዝግጅቱን ሲያሳይ ቆይቷል። ቡድኑን ባነጋገርንበት ወቅት ከዝዋይ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ በዝግጅት ላይ ነበር። «ቺርኮ ኢንዚር ከ10-20 ያሉ ሰዎች ስብስብ ነው። የጉዞ ወጫችንን ለመሸፈን ጣሊያን ውስጥ የተለያዩ የሰርከስ ዝግጅቶች እናሳያለን። ከዛ እየተዘዋወርን ዝግጅታችንን እናሳያለን። ቡድኑ ቺርኮ ኢንዚር የተባለበት ምክንያት በሰሜን ምስራቅ ጣሊያን አጠራር በየቦታው የሚዟዟር ሰርከስ እንደማለት ነው።ምክንያቱም የቡድናችን አብዛኞቹ አባላት ከሰሜን ምስራቅ ጣሊያን ከቦሎኒያ አካባቢ ነው የመጡት።»
ትላለች የሰርከስ ቡድኑ ባልደረባ ሊንዳ። እሷም እንደበርካታ የሰርከሱ አባላት የሰርከስ ተማሪ ነበረች። ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘው ከ 12 ባልደረቦቹ ጋር ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ሁለቱ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።« ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው ከፍካት ሰርከስ ጋር ግንኙነት ስላለን ነው። ደረጀን በደንብ እናውቀዋለን። ምክንያቱም ወደ ቦሎኒያ መጥቶ ከአንድ ድርጅት ጋር ይሰራ ነበር። እና ወደ ኢትዮጵያ የመሄዱን ሀሳብ አቀረበልን። በከተማ አካባቢ ሰርከስ እያደገ ቢሆንም በገጠሩ አካባቢ ብዙም አልተስፋፋም እና ስራችሁን እዛ ማስተዋወቅ ትችላላችሁ አለን። የእኛም ፍላጎት ያ ነበር።» ደረጀ ዳኜ ፤ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው የፍካት ሰርከስ መስራች አባል እና ፕሬዚዳንት ነው።ሰሞኑን ከጣሊያን ወደ አዲስ አበባ መመለሱ ነው። ስለ ፍካት ሰርከስ አመሰራረት እና አላማ ገልጾልናል።
Circo Inzir

የቺርኮ ኢንዚር ባልደረቦች

የቺርኮ ኢንዚር ሁለት አይነት ዝግጅቶች አሉት።« አንደኛው በተተከሉ ብረቶች እና እንጨቶች ላይ የሚሰራ የሰርከስ እንቅስቃሴ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ዝምብሎ ጎዳና ላይ የሚደረግ ዝግጅት ነው።» ቺርኮ ኢንዚር ለወህኒ ቤት ታራሚዎች፣ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ሁሉንም ተመልካች ያሳተፈ ሰርከስ እየተዟዟረ እንዳሳየ ሊንዳ ገልፃልናለች። ይህም ያለ ምንም ክፍያ ነው። «ምናልባት በፍካት የሰርከስ ማሳያ በምናቀርበው ዝግጅት ፍካትን ለመተባበር ስለምንፈልግ ክፍያ እንጠይቅ ይሆናል። መጠኑን እኔ ለጊዜው አላውቀውም። ነገር ግን ገጠር ውስጥ ሁሉም ነገር በነፃ ነበር።»
የሰርከስ ቡድኑ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ የተለጠፉ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች እንደሚያመላክቱት፤ ዝግጅቱ ተመልካችንም አሳትፏል። የሰዎቹን አመለካከት ሊንዳ እንዲህ ትገልጸዋለች።« የተመልካቾቹ አቀባበል እጅግ እንግዳ ነበር። ምክንያቱም ሰርከሱን ሀገራችንም አካሂደን እናውቃለን። ይህ ግን ከዛ በጣም የተለየ ነበር። ስንጀምር ህጻናቱ በጣም ይፈራሉ፣ ይጠራጠራሉ። ለነሱም እንግዳ የሆነ ነገር ነው። ነጮች ነን። ነጮች ብዙም አይተው የሚያውቁ አይመስለኝም። በዛ ላይ እንግዳ የሆነ ነገር ነው የምናደርገው። ፀጉራችን፣ የተቀባባነው ፤ የለበስነው ሁሉ ነገር እንግዳ ነው። እና ትንሽ ፍርሃት ይታይባቸው ነበር። እና አንድ ትርኢት የምታሳይ ባልደረባችን ወደ ተመልካች ተጠግታ አብሯት እንዲደንስ አንድ ልጅን ስትጠራ፤ ሰው ሁላ መጮች ጀመረ። ኃላም ብዙ ሲስቁ ነበር። እና ይህን ማየት ትንሽ ይገርም ነበር።»
«በአጠቃላይ ተመልካቾችን ወደ መድረኩ መጋበዛችን የሰዎችን ፍርሃት እና ጥርጣሬ የገፈፍነው ይመስለኛል» ምክንያቱም ስንጨርስ ወደእኛ ተጠግተው ስማችንን እና አድራሻችንን ይጠይቁን ነበርና ትላለች ሊንዳ። ኢትዮጵያውያኑ ለትርዕይቱ እንግዳ ሲሆኑ ጣሊያውያኑ ደግሞ ለኢትዮጵያ እንግዳ ነበሩ። ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን የጎበኙት ጣሊያናውያን ዕይታ ምን ይመስል ነበር?« ትልቅ ሀገር ነው፣ በርካታ የመሬት አቀማመጦች አሉት። አንድ ወር ተጉዘን በርካታ ቦታዎችን ባየንበት ጊዜ የተለያዩ ገፅታዎች፤ ሰዎች አይተናል። እና እኛም ልክ ሰርከሳችንን እንደተመለከቱት ልጆች ሆነን ነበር። ጥርጣሬ፣ ፍርሃት ነበረን። ሰዎች በየሄድንበት ገንዘብ ይጠይቁን ነበር። እኛ ደግሞ ገንዘብ ለመጠየቅም ሆነ ለመስጠት አልነበረም የመጣነው። እና ከትናንሽ ነገሮች አንስቶ የተለየ ነበር። ምግቡ፤ ከሰዎች ጋር ማውራቱ የመሳሰሉት፤አሁን ግን ሁሉንም ነገር ለምደንዋል። ፈታኝ ነገር ለማየት ነው እኛም እዚህ ያለነው።»
ስለ የጣሊያኑ ቺርኮ ኢንዚር ቡድን እና ይህንን ጉዞ ስላመቻቸለት ፍካት ሰርከስ የነበረንን የወጣቶች ዓለም ሙሉ ዝግጅት በድምፅ ያገኙታል።
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic