1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጡት ካንሰር አይድንም?

ሸዋዬ ለገሠ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 19 2017

ሰዎች ስለካንሰር ያላቸው ግንዛቤ መሻሻል እንዳለበት ዛሬም የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ሀኪም ዘንድ የሚሄዱ የካንሰር ታማሚዎች ችግሩ ከጠናና በህክምና ለመርዳትም ፈታኝ ደረጃ ሲደርስ መሆኑ፤ ካንሰር አይድንም ወደሚለው መደምደሚያ እንዳደረሰም ያመለክታሉ።

https://p.dw.com/p/4mMuc
Symbolbild: Weltkrebstag
የዓለም የጡት ካንሰር መለያ ምልክት ፎቶ ከማኅደር ምስል ARUN SANKAR/AFP/Getty Images

የጡት ካንሰር አይድንም?

ካንሰር በጊዜው ከተደረሰበት መታከም እንደሚችልም ያስገነዝባሉ።

ስለካንሰር የኅብረተሰቡ ግንዛቤ

ኢትዮጵያ ውስጥ ቀደም ሲል በውስን ጤና ተቋም ብቻ ሲሰጥ የነበረዉ የካንሰር ሀክምና አሁን የካንሰር ህክምና ማዕከላት አስፈላጊው ግብዓት ተሟልቶላቸዉ ኅብረተሰቡ አገልግሎቱን እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑ ይነገራል። ሰዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት ለካንሰር መጋለጣቸው ሲነገራቸው ሞታቸውን ብቻ ያስቡ ነበር፤ አሁን ግን ጥቂት የማይባሉት የካንሰር ታማሚዎች ፈጥነው ወደ ህክምና በመሄድ ካንሰሩን አሸንፈው፣ ለሌሎችም ተሞክሯቸውን ሲያጋሩ ማየት ተለምዷል። በአብዛኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ሲታመሙ በሽታው ስር እስኪሰድ ወደ ሀኪም ቤት ሳይሄዱ መቆየታቸው በህክምና የመረዳት ዕድሉን እንደሚያጠበው የህክምና ባለሙያዎች በየጊዜው ይገልጻሉ።

በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የህክምና ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የካንሰር ከፍተኛ ሀኪም ዶክተር ቢንያም ተፈራ ሰዎች ለህክምና ለምን ዘግይተው ለመሄዳቸው አንድም ስለካንሰር ህመም ግንዛቤ አለመኖር እና የህክምናው አገልግሎትም በብዛት በከተሞች ላይ ብቻ መገኘቱን በምክንያትነት ያነሳሉ።

የጡት ካንሰር ይድናል?

በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች የጡት ካንሰርን ታክመው ድነው እነሱም በተሞክሯቸው ለሌሎች ተስፋ ለመሆን ሲጥሩ ይታያል። ኢትዮጵያ ውስጥም እንዲሁ፤ ይህ እውን የማይመስላቸው ግን አሉ። የካንሰር ከፍተኛ የህክምና ባለሙያው ዶክተር ቢንያም ለመዳን ያለውን ዕድል ይናገራሉ።

«የጡት ካንሰርን ኢፌክቲቭሊ ለማዳን የሚቻለው በጊዜ ተገኝቶ በጊዜ ህክምናውን ሲወስዱ ነው። በዚህ እረገድ ኢትዮጵያ ውስጥም ቶሎ የሚመጡ ታማሚዎቻችን እውነት ለመናገር በትክክል ታክመው በትክክል ይድናሉ።»

ማሞግራም
የጡት ካንሰር ምርመራ ከሚደረግባቸው የህክምና መሳሪያዎች አንዱ ማሞግራምፎቶ ከማኅደር ምስል Monkey Business Images/Colourbox

ታክመው የዳኑ እማኞች ሚና

በእርግጥም የታማሚዎች ለህክምናው መዘግየት ካለው የህክምና አቅም ጋር ተደማምሮ የካንሰርን ገዳይነት ብቻ ሲያውጅ ኖሯል። በተቃራኒው በጊዜው ተመርምረውና ህክምናውን አድርገው ካንሰሩን ማሸነፋቸውን የሚገልጹ በርክተዋል። ዶክተር ቢንያም በቅርብ የሚከታተሏቸው የካንሰር ታማሚዎችን ያካተቱ የመረጃ መለዋወጫ ስብስቦች ለበርካቶች ግንዛቤ የማግኛ መድረኮች ሆነዋል። የእነዚህ ስብስቦች እንቅስቃሴ ምን ያህል ለውጥ ማምጣት ችሎ ይሆን?

ዶክተር ቢንያም በተለይ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ያሉም ቢሆኑ በቤተሰብ የካንሰር ህመም ታሪክ ካለ ለቅድመ ምርመራው ትኩረት በመስጠት ማሞግራም በተሰኘው የጡት ካንሰር መመርመሪያ መታየት  እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ከምርመራው ጎን ለጎንም ሰዎች የአኗኗር ዘይቤያቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ መክረዋል።

አስቀድሞ በጡት ላይ ወይም በብብት ስር እያለ ከተደረሰበት ወዲያው ህክምና ከተደረገ የመሰራጨት ዕድሉ እንደሚቀንስ፤ በተቃራኒው ያለህክምና ዓመት ሁለት ዓመት ከተቆየ ግን መሠራጨቱ እንደማይቀር፤ ካንሰር አንዴ ከተሰራጨ ደግሞ ህክምናው በጣም አስቸጋሪ እየሆነ እንደሚሄድም አስገንዝበዋል።

በየዓመቱም በመላው ዓለም 2,3 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ለጡት ካንሰርእንደሚጋለጡም የዓለም የጤና ድርጅት ይገልጻል። ድርጅቱ እንደሚለው የጡት ካንሰር በዓለም በብዛት ሰዎችን የሚያጠቃ የካንሰር ዓይነትም ነው። የጡት ካንሰር የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል ቅድመ ምርመራ እና የአኗኗር ዘይቤ ላይ ትኩረት እንድናደርግ ያሳሰቡንን የካንሰር ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ዶክተር ቢንያም ተፈራን ለጊዜያቸውና ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ እናመሰግናለን።

 ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር