«የጡት ልጅ» በፊልም ሥራ ባለሞያዉ | ባህል | DW | 25.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

«የጡት ልጅ» በፊልም ሥራ ባለሞያዉ

«የጡት ልጅ» በሚል በኃይሌ ገሪማ ሊሰራ የታቀደዉ ፊልም በ1960ዎቹ ከጣልያን ወረራ ከ 20 ዓመታት በኃላ በማደጎ የተሰጠች አንዲት ታዳጊ ህጻን ሕይወት ላይ እንደሚያተኩር ነዉ የተነገረዉ። ግን ለዚህ ፊልም ሥራ ማስኬጂያ ገንዘብ አልተሟላም። በአዉሮጳ ሕብረት ስር የሚገኘዉ ተቋም ለፊልሙ ሥራ ማስኬጃ የሚሆን 500 ሺህ ዩሮ እሰጣለሁ ብሎ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:54
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
15:54 ደቂቃ

«የጡት ልጅ» በፊልም ሥራ ባለሞያዉ

ግን ገንዘቡ ይሰጠዉ እተባለበት እጅ ሳይደርስ ቀርቶአል። ችግሩ ምን ይሆን ? ዛሬ ፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ መልስ ይሰጡናል። በዩኤስ አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን በበኩላቸዉ ታሪኩ የራሳችን የኢትዮጵያዉያን በመሆኑ፤ ታሪካችን በራሳችን ብዕር፤ በራሳችን ጉልበት፤ በራሳችን ወጭ፤ ልንሥራ ይገባል ሲሉ፤ በየፊናቸዉ ለፊልሙ ማሰርያ የገንዘብ ማሰባሰብያ ዘመቻ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

Regisseur Haile Gerima

ፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ

በዓለምአቀፉ የፊልም መድረክ በተለይ ጤዛ፤ ሳንኮፋ፤ ዓድዋ ፤ቡሽ ማማ ፤ በተሰኙት ፊልሞቻቸዉ ሽልማትና እዉቅናን ያገኙት ኢትዮጵያዊዉ የፊልም ሥራ ባለሞያ ፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ፤ «የጡት ልጅ » ለተሰኘዉ አዲስ ፊልም መስሪያ « ኢንዲጎጎ» የተሰኘ የገንዘብ ማሰባሰብያ ድረ-ገጽ ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ እስከ ሰኔ 23 ድረስ የሚዘልቅ የማሰባሰብያ ዘመቻን ጀምሮአል። ለፊልሙ ማሰሪያ ሊሰበሰብ የታቀደው 500 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ነዉ። ግን ገንዘብ በማሰባሰብ ፊልምን መሥራት ይቻላልን? ስንል ላቀረብነዉ የመጀመርያ ጥያቄ ለፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ ፤ «መጀመርያ «ኤ ሲ ፒ» የሚባል ለአፍሪቃ፤ ካሪቢክ እንዲሁም ለእስያ ሃገራት ፊልም ሠሪዎች ድጎማ የሚሰጠዉ የበጎ አድራጎት ገንዘብ ነበር። ይህ ገንዘብ በጀርመን የፊልም ሥራ አጋሪ በኩል ደርሶኝ ለፊልሙ ስራ ወጭ ሆኖ ባለፈዉ ዓመት ነበር ኢትዮጵያ ገብቼ የፊልም ሥራዉን መተኮስ የነበረብኝ። ጤዛ የሚባለዉ ፊልሜ ሳንኮፋ የሚባለዉ ፊልሜ ሁሉ በዚህ ድርጅት ገንዘብ ድጋፍ ነዉ የተሰራዉ»
ግን ይህ የአዉሮጳ ሕብረት ዉስጥ ያለ ተቋም ሊሰጥ ያሰበዉ ገንዘብ አይበቃም ታድያ?፤ ለሚለዉ ጥያቄ ፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ « ጀርመኑ የሥራ አጋሪ በመታመሙ ገንዘቡ ወጭ ሳይሆን ቀረ። በአዉሮጳ ሕብረት ዉስጥ ያለዉ «ኤ ሲ ፒ» የሚባለዉ ተቋም ገንዘቡን መልሶ ወሰደዉ ። እሱማ የአዉሮጳ ሕብረት ተቋሙ፤ ገንዘቡ የሚሰጠዉ ለፊልም ሰራተኛዉ ለኃይሌ ገሪማ « የጡት ልጅ » ለተሰኘዉ የፊልም ማሳረያ ነዉ፤ ተፈቀዶለታል ብሎ በጋዜጣ ለዓለም ነበር የነሰነሰዉ። እነሱ ይህን ገንዘብ መልሰዉ ሲወስዱት ነዉ እዳዉ የመጣዉ፤ ገንዘቡን ባገኝ ኖሮ እንደዉም ፊልሙን እስካሁን በማቀናበር እጨርሰዉ ነበር።» ታድያ ገንዘብ ማሰባሰቡ ምን ያህል አመርቂ ነዉ።« ብዙም የማዉቀዉ ነገር የለኝም እዉነቱን ለመናገር ይህን ሁሉ የሚሰሩልኝ ወጣት ኢትዮጵያዉያን አሜሪካዉያን በገዛ ፈቃዳቸዉ ተሰብስበዉ ነዉ። ገንዘብ እንደማላገኝ የሚገልፀዉ ዜና ከአዉሮጳዉ ሕብረት ሲመጣ ወጣቶቹ ተሰብስበዉ መላ ፈልገዉ ነዉ፤ የገንዘብ ማሰባሰብያዉን ዘመቻ የጀመሩት። ይህን አይነት ሥራ ሰርቼ ስለማላዉቅ የማዉቀዉ ብዙ ነገር የለም። እኔ እንደዉም ከተጠየኩ ላይቀር ብዙ ጊዜዬን ለማጠፋዉ « Children of Adwa: 40 Years Later ወይም የዓድዋ ልጆች ከ 40 ዓመት በኃላ» ለተሰኘዉ ፊልም ነዉ። ፊልሙን ለመሥራት በፊልም ያሰባሰብኩዋቸዉን መረጃዎች በመቁረጥ ነዉ አብዛኛዉን ጊዜዬን የማጠፋዉ።

30.08.2008 kultrur 21 haile gerima

ፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ


የፊልም ሥራ ባለሞያዉ ኃይሌ ገሪማ እንዳሉት ከሆነ «የጡት ልጅ » የተሰኘዉ ፊልም ጽሑፉ ከተጠናቀቀ ዓመታቶች አልፈዉታል፤ ግን ከዝያ በፊት በኢትዮጵያ የጣልያን ወረራን በተመለከተ ለመሥራት ያሰቡት ሌላ ታሪካዊ ፊልም አላቸዉ። ስለዓድዋ ጦርነት የሚተርከዉ ፊልማቸዉ። በአገራችን የጣልያኑ የሞሶሎኒ ጦርነት እንደሳቸዉ እንደ ፕሮፊሰር ኃይሌም ሆነ እንደአባታቸዉ የሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት የጀመረበት ነዉ። « አባቴ አርበኛ ስለነበር፤ ለአባቴ ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት የጀመረዉ ኢትዮጵያ በጣሊያን ጦርነት በሞሶሎኒ ፋሽስት ስትወረር ነዉ። በዚህም የሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት የሚጀምረዉ በኢትዮጵያ ነዉ ። እኛም እንደሱ ብለን ካላየነዉ ነገሩ ይበላሻል። ምክንያቱም በዝያን ጊዜ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብዙ የጦር ኃይል የመጣባት፤ ኢትዮጵያ «በሊግ ኦፍ ኔሽን» ማኅበርተኛ የነበረች፤ ግን በዝያን ጊዜ የተካደች፤ የመርዝ ጋዝ የተጣለባት፤የሞቱት ሰዎች ቁጥር ስፍር እጅግ ብዙና የማይታወቅ፤ በዚያን ጊዜ ጣልያኖች እዝያዉ የማጎርያ ጣብያ ሰርተዉ ብዜ ሰዎችን የጨረሱበት ነዉ። ግርያዝያኒን ለመግደል ሙከራ ከተደረገ በኃላ በመጣዉ መአት እጅግ ብዜ ኢትዮጵያዉያኖችም አልቀዋል። ጣልያኖችም ቢሆኑ አሁን በዝያን ጊዜ ያለቀዉን ህዝብ ቁጥር ለማወቅ ብዙ ጥናን ጀምረዋል፤ ነገሩ አዲስ ነገር አይደለም። አዉሮጳዉያን ሂትለር ኦስትርያና ፖላንድን ሲወር ነዉ ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ተጀመረ ብለዉ ታሪክን ያስቀመጡት። ለኃያላኑ አገራትም የሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት በዚህ ጊዜ ተጀመረ ብለዉ ነዉ የሚሉት። ኢትዮጵያ ግን በዝያን ጊዜ በነበሩት ኃያላን ሃገራት ተክዳ፤ ያን ያህል ወርዶባት፤ የሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት ታስቦ ሲዉል የኢትዮጵያ የዚያን ጊዜዉ ችግር የዓድዋዉ ትግል እንብዛም አይነሳም። ስለዚህ ቢያንስ እኛ የራሳችንን ታሪክ ማንፀባረቅ አለብን ነዉ።» ለፊልሙ ትረካዉን ጽፊ ጨርሻለሁ ያሉን ፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ፤ ይህን በፊልም መልክ በማቀናበር ከ20 ዓመታት በላይ እንደሰሩ ተናግረዋል። « የዚህን ታሪክ በፊልም ለማስቀመጥ ካቀድኩ ቆየሁ፤ ስራዉን ከጀመርኩ ከ20 ዓመታ በላይ ሆነኝ። አርበኞችን ባገኘሁ ቁጥር በፊልም መልክ እየቀዳሁ ስብስቤ አስቀምጥ ነበር። እናም አርበኞችን በፊል የቀርፅኩ ታሪኩን የሚዉቁ የታሪክ ሰዎችን እየጠየኩ እስካሁን ፊልሙን ስሠራ ነበር። ጤዛ የተሰኘዉንም ፊልሜን ስሠራ ወጣ ገባ እያልኩ በጎን «የዓድዋ ልጆች ከ 40 ዓመት በኃላ» የሚሰኘዉን ፊልሜን ሳቀነባብር ስሠራ ነበር። እስከ ፊታችን መስከረም ወር ያልቃል የሚል ተስፋ አለኝ፤ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ወደ አዉሮጳ ይዤዉ ሳልመጣ አልቀርም።

Äthiopien D 2008 Haile Gerima Aaron Arefe Aby Tedla

ጤዛ ፊልም


የፊልም ባለሞያው የኃይሌ ገሪማ ወዳጆችና አድናቂዎች በዋሽንግተን ዲሲ ለፊልሙ መስሪያ የሚውል የገንዘብ ማሰባሰብያ ምሽት አዘጋጅተዋል። በዝግጅቱ ላይ የኃይሌ ፊልም ይቀርባል ፤ ዉይይትም እንደሚኖር ከዝግጅቱ አስተባባሪዎች አንዱ የሆነዉ፤ ጋዜጠኛና ደራሲ ታምራት ነገራ ገልፆአል። « በዲሲ የምንገኝ አብዛኛዎቻችን ኢትዮጵያዉያን ፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማን ፤ ጋሼ ኃይሌ ነዉ የምንለዉ። ጋሽ ኃይሌ በአሜሪካ ዉስጥ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ካደረጉ ሰዎች መካከል አንዱ ነዉ። በተለይ በፊልሞግራፊ ላይ። በአጠቃላይ በፊልም ኢንዱስትሪ ሁለት ነገር አለ የቴክኒክ እጥረት፤ ሁለተኛዉ ጥቁርን በመልካም ነገር የመግለፅ ችግር ነዉ። ሆን ተብሎ ተቋማዊ ዘረኝነት ከሚገለፅባቸዉ መድረክ አንደኛዉ ፊልሞች ናቸዉ። ጋሽ ኃይሌ ትልቅ ተፅኖ አድራጊ ነዉ። ጋሽ ኃይሌ ሃዋርድ ዩንቨርስቲ ማስተማር ከጀመረ ጀምሮ የጥንታዊ ኢትዮጵያዉያንን ስዕል በመጠቀም፤ ጥቁር አሜሪካዉያን ጥቁር ተማሪዎቹ፤ ከተለያየ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ተማሪዎቹን ፤ ራሳቸዉን እንዴት ማየት እንዳለባቸዉ መቀየር የቻለ ሰዉ ነዉ። ይህ ደግሞ በጣም ትልቅ ስኬት ነዉ። እኔ ደግሞ የፊልም አድናቂ ነኝ። ፊልም እወዳለሁ። ጠጋ ብዬ ጋሽ ኃይሌን ስከታተለዉ በጣም የሚገርም ስራዎችን ነዉ እየሰራ ያለዉ። እዚህ ዲሲ መኖር ከጀመርኩ ጀምሮ ሳንኮፋ በተሰኘዉ መገናኛ ቤቱ እናገኘዋለን፤ እንጫወታለን በጣም ጋሽ ኃይሌ ለሰዉ ቅቡል ሰዉ ነዉ። ከወጣት ጋር መሆን ፤መወያየት፤ መጨቃጨቅ ይወዳል ።ስቱድዮ አስገብቶ እንዴት እንደሚሰራ ምን ምን ፕሮጀክት እንዳለዉ የሚያካፍል ሰዉ ነዉ። እና ይህ « የጡት ልጅ» የተሰኘዉን ፕሮጀክቱን ስንሰማ አንድ አርቲስት ወይም የፊልም ሥራ ባለሞያ ለፊልም ሥራ ማስኬጃዉ አድናቂዎቹ ገንዘብ የሚያሰባስቡለት መንገድ እዳለ ነገርነዉ ፤ ፕሮጀክቱንም ጀመርንለት። የፊታችን ቅዳሜም ትንሽ የመግብያ ብር አድርገን የሱን ፊልም በጋራ ለማየት ቡና ሻይ በጋራ ለመጠጣት ለመወያየት እቅድ ይዘናል» ፊልም ማሰርያ የታቀደዉ ገንዘብ 500 ሺህ ዶላር ነዉ። ታድያ ገንዘብ ይሟላ ይሆን? ለተሰኘዉ ጥያቄ፤ ጋዜጠኛና ደራሲ ታምራት ነገራ « አንድ ሰዉ በዚህ አይነት ፕሮጀክት ላይ የሚሳተፈዉ የተፈለገዉ ብር ይሟላል ብሎ አይደለም። ይህ ገንዘብ በትልልቅ ካንፓኒዎች ወይም በሃገር ደረጃ ድጋፍ ካላገኘ ይህን ያህል ብር መሰብሰብ ላይሆን ይችላል። ግን በዚህ ምክንያት ብቻ የሚፈጠረዉ ማህበረሰብ በራሱ ትልቅ ነገር ነዉ። ሃያ፤ ሰላሳ እስከ አንድ ሽ ዶላር የሚያዋጡ አሉ። በሌላ በኩል በዚህ መድረክ የጡት ልጅ የተባለዉ የፊልም ስራ እቅድ ላይ መሆኑ መታወቁ፤ በራሱ ትልቅ ጉዳይ ነዉ። ይህ ፕሮጀክት ባይሟላም ሌላዉ ይከተላል። ስለዚህ ግቡ የግዴታ ብር ማምጣትና ግቡን መምታት አይደለም። ግን የራሳችንን ሥራ የራሳችንን ባህል የራሳችንን ታሪክ ራሳችን በጀት መመደብ እንዲህ ነዉ የምንለማመደዉ። የግዴታ ሆሊዉድ ብር እንዲሰጠን መጠበቅ አይደለም። የግዴታ የእገሌ መንግሥት ብር እንዲሰጠን መጠበቅ አይደለም። ስለዚህ ልምምዱ ነዉ ዋናዉ፤ የግድ ገንዘቡ ይሟላ አይደለም።»

Äthiopien Regisseur Haile Gerima

ፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ


ዩኤስ አሜሪካና ኢትዮጵያ የተመዘገበዉ የፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ የፊልም ድርጅት«ነጎድጓድ ፕሮዳክሽን» ይባላል። የፊልም ባለሞያዉ ዋሽንግተን ላይ ሳንኮፋ የሚል የመገናኛ መደብርም እንዳለቸዉ ነዉ የገለፁት፤ እንደ አንዱ የፊልማቸዉ ስያሜ። ኃይሌ ገሪማ «ኢንዲጎጎ» የርዳታ ማሰባሰብያ በእኛም ሃገር ለሚገኙት ጥሩ ጥሩ ወጣት ፊልም ሰራተኛ ወጣቶች መደገፍያ መለመድ እንዳለበት ሳይገልፁ አላለፉም። «በርግጥ ይህ አይነቱ የገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላሉት የፊልም ሰራተኞች ሊታሰብ የሚገባ ነዉ። ግዜ ሳያመልጠን የዓይን ምስካሪዎች ከጃችን ሳይሾልኩ በፊልም ሰራተኞች እገዛ ታሪካችንን ጽፈን ለተቀሪዉ ትዉልድ ልናስተላልፍ ይገባል ብለዋል።
ጋዜጠኛና ደራሲ ታምራት ነገራ በመጨረሻ መልክት አለኝ ይላል «በዚህ አጋጣሚ የትኛዉም በዉጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ በተለይ በአዉሮጳ፤ በአሜሪካ፤ በአዉስትራልያ የምንኖር የራሳችንን ታሪክ የመናገር ግዴታ አለብን። ገና የራሳችንን ብዙ ብዙ ፊልም የመስራት ግዴታ አለብን። የራሳችንን ፊልሞች የራሳችንን ትያትሮች የራሳችንን መፅሐፎች በራሳችን ቋንቋ መስራት መቻል አለብን እላለሁ። ለምሳሌ ጤዛ የተሰኘዉ የጋሽ ኃይሌ ፊልም በጀርመኖች ርዳታ ነዉ የተሰራዉ ይኸዉ ፊልም የተለያዩ ዓለማቀፍ ሽልማትችን አግኝቶአል። ከዚህ በኃላ ግን እኛም ራሳችን መስራት መቻል አለብን፤ ራሳችን መጀመር አለብን። የራሳችንን የፊልም ሥራ ባለሞያዎች የራሳችን ደራሲዎች የራሳችን ከያኒዎች፤ እኛ መሸከም መጀመር አለብን ። ይህ ፕሮጀክት የኛ ኃላፊነት ነዉ ። ማንም የኛን ታሪክ አይናገርልንም። እስካሁን ብዙ አይነት የሁለተኛ አይነት የጦርነት ፊልሞችን አይተናል። እስካሁን ግን የአድዋ ድል በተሳካ መልኩ ተሰርቶ በርካታ ህዝብ ሲያየዉ አላየንም። ይህ የኛ ኃላፊነት ነዉ። እናም የራሱን ታሪክ ማየት የሚሻ ሰዉ ይህን ፕሮጀክት እንዲረዳ እጋብዛለሁ። ለፊልም ሥራዉ የሚያስፈልገው ገንዘብ ተሟልቶ «የጡት ልጅ» ፊልም ከፍጻሜ ደርሶ ለተመልካች እንዲቀርብ እንመኛለን። ሙሉ መሰናዶዉን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ
ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic