የጠ. ሚ መለስ ዜናዊ ዜና ዕረፍት | ኢትዮጵያ | DW | 21.08.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የጠ. ሚ መለስ ዜናዊ ዜና ዕረፍት

አቶ መለስ ለ 1 አመት ያህል ጤናቸው ታውኮ መቆየቱንና ባለፉት 10 ሳምንታትም በውጭ ሃገር የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱን አቶ በረከት ተናግረዋል ። አቶ መለስ ዜናዊ በሐምሌ ወር ለህክምና ቤልጂግ የሚገኝ ሆስፒታል መግባታቸው ሲዘገብ የህመማቸው ምንነት ግን አልተነገረም

የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሞቱትን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ተክተው በቅርቡ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቃለ መሃላ እንደሚፈፅሙ የኢትዮጵያ መንግሥት lዛሬ አስታወቀ ። አቶ ኃይለ ማርያም ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ የተነገረው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ማረፋቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ዛሬ በይፋ ካሳወቀ በኋላ ነው ። የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ በረከት ስምኦን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በህክምና ሲረዱ በቆዩበትና በስም ባልጠቀሱት የውጭ ሃገር ትንንት ማምሻውን ማረፋቸውን ዛሬ ጠዋት አስታውቀዋል ። ፓርላማው እንደተሰበሰበ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ቃለ መሃላ እንደሚፈፅሙም ገልፀዋል ።ላለፉት 21 ዓመታት ኢትዮጵያን በፕሬዝዳትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት አቶ መለስ ዜናዊ የሞቱት ድንገተኛ ኢንፌክሽን ባስከተለባቸው ውስብስብ የጤና ችግር ሰበብ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል ።

አቶ መለስ ለ 1 አመት ያህል ጤናቸው ታውኮ መቆየቱንና ባለፉት 10 ሳምንታትም በውጭ ሃገር የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱን አቶ በረከት ተናግረዋል ። አቶ መለስ ዜናዊ በሐምሌ ወር ለህክምና ቤልጂግ የሚገኝ ሆስፒታል መግባታቸው ሲዘገብ የህመማቸው ምንነት ግን አልተነገረም ። ከ 1 ወር በፊት አቶ መለስ በጠና ታመው ብራስልስ ውስጥ በህክምና ላይ እንደሚገኙ የውጭ ዲፕሎማቶች ባሳወቁበት ወቅት አቶ በረከት ህመማቸው ለህይወታቸው ያሰጋል መባሉን አሰተባብለው በአስተማማኝ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀው ነበር ። አቶ መለስ በሃገራቸው የኢኮኖሚ ስድገት በማስመዝገብና የአፍሪቃ ቀንድን ሠላም ለማስከበር አደረጉት ላሉት ጥረት ምዕራባውያን መንግሥታት ያወድሷቸዋል ። በአንፃሩ በተቃዋሚዎችና በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ሰብአዊ መብቶችን በመርገጥ ተቃዋሚዎችን በመግደልና በማሰር ጋዜጠኞችንም በማዋከብና በማሰር እንዲሁም የፕሬስ ነፃነትን በማፈን በሐይማኖት ተቋማትም ጣልቃ በመግባት የሚወገዙ መሪ ነበሩ ። 20 ዓመት ሳይሞላቸው የህክምና ትምህርታቸውን አቋርጠው የደርግ መንግሥትን ለመውጋት የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ድርጅት ህወሀትን የተቀላቀሉት አቶ መለስ በ1981 ዓም ነበር የድርጅቱን መሪነት የተረከቡት ። ህወሃት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን የመሰረተው ፣ የአሁኑ ገዥ ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ኢህአዲግ ሊቀመንበርም ነበሩ ። አቶ መለስ የቀድሞ የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ታጋይ ከነበሩት ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አዜብ መስፍን ያፈሯቸው የሁለት ሴቶች ና የአንድ ወንድ ልጆች አባት ነበሩ ። ለ 2 ወራት ከህዝብ እይታ ተሰውረው የቆዩት አቶ መለስ ያረፉት በ 57 አመታቸው ነው ። ኢትዮጵያ መሪዋን ለማሰብ ከዛሬ ጀምሮ የሃዘን ቀን ማወጇን አቶ በረከት ተናግረዋል ።

ሒሩት መለስ

ነጋሽ መሐመድ