የጠ/ሚ መለስ ዕረፍትና ዓ/አቀፍ አስተያየት | ዓለም | DW | 21.08.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የጠ/ሚ መለስ ዕረፍትና ዓ/አቀፍ አስተያየት

የኢትዮጵያ ጠ/ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ህልፈተ -ህይወት ዛሬ ይፋ ከተነገረ ወዲህ ፤ ከዓለም ዙሪያ የተለያዩ መሪዎች፤ ስለ ጠቅላይ ሚንስትሩ ስብእናና ተግባራት የየቡኩላቸውን አስተያየት ሰንዝረዋል። የጎረቤት ኬንያ ጠ/ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ ፣

«መለስ ትልቅ መሪ ነበሩ ፤ በአርሳቸው ሞት ሳቢያ የኢትዮጵያ መረጋጋት መቻል ያሥፈረኛል» ነው ያሉት ። ፕሬዚዳንት ሞይ ኪባኪ፣ፖለቲካን በተግባር የሚተረጉሙና ራእይ ያላቸው መሪ ነበሩ ብለዋል። የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚዳንት ጄኮብ ዙማ፤ ብዙውን ጊዜ በጦርነት ከላሸቁት በዙሪያዋ ከሚገኙ አገሮች ፣«የተረጋጋች ኢትዮጵያ፣ ጠንካራ መሪ ነበሩ» ሲሉ ተናግረዋል።

ዩጋንዳ፤ የመለስ ሞት «አስደንጋጭና አሳዛኝ፤ ለአፍሪቃው ክፍለ ዓለም ትልቅ እጦት » ነው ስትል፤

የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በጠ/ሚንስትር መለስ ሞት «እጅግ ማዘኑን » ገልጿል። ሱዳን ውድ ወዳጅዋን አጥታለች፤ የአፍሪቃው ክፍለ ዓለምም ፤ ታዋቂ፤ አስተዋይ ተመክሮ ያለው መሪ አጥታለች ብሏል።

ከአፍሪቃ ውጭ ፤ የብሪታንሪያው ጠ/ሚንስትር ዴቪድ ኬምረን፤ «መለስ፤ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች፤ ለአፍሪቃ ብሩኅ ተስፋ አሳዳሪ ቃል አቀባይ ነበሩ ሲሉ በውዳሴ አስበዋቸዋል።

የአውሮፓው ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ሆሴ ማኑኤል ባሮሶ፣ በ 20 ዓመት አመራራቸው ፣ አቶ መለስ «የተከበሩ አፍሪቃዊ መሪ ነበሩ» ብለዋል።

ተሰናባቹ የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዣን ፒንግ፣ ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ ያለ ዕድሜአቸው ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው፤ ዜና ዕረፍታቸው ኅብረቱን «ክፉኛ አስደንግጧል ፣ አሳዝኗል » ነው ያሉት።

የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን ፤ የአቶ መለስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ፣ «ለኢትዮጵያ ፈታኝ ጊዜን ይደቅናል » ብለዋል።

የምዕራቡ ዓለም ወዳጅ እየተባሉ ይነገርላቸው የነበሩት ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በተደጋጋሚ ብርቱ ወቀሳ ሲሰነዘርባቸው መቆየቱ የሚታወስ ነው። ዋና ጽ/ቤቱ በለንደን ፤ ብሪታንያ የሚገኘው፤ የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት AI የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ተመራማሪ ክሌር ቤስተን፤ የኢትዮጵያ መንግሥትና ተተኪው ጠ/ሚንስትር ፣ አጋጣሚውን በመጠቀም፤ ለውጥ በማድረግ፤ በሰፊው ሰብአዊ መብት የሚከበርበትን እርምጃ ሊወስድ ይገባል ማለታቸውን AFP ጠቅሷል። ሌላው ዋና ጽ/ቤቱ በኒው ዮርክ ፤ ዩናይትድ እስቴትስ የሚገኘው ታዋቂው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅት HRW ፣ የአፍሪቃ ጉዳዮች ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፤ ሌስሊ ሌፍኮቭ፣

«የኢትዮጵያ አመራር ሰብአዊ መብትን እንደሚያከብር ባስቸኳይ በተሃድሶ የለውጥ እርምጃ ያሳይ አንዳንድ እጅግ ጎጂ ህግጋትን ፤ ጸረ ሽብር ደንብ የተሰኘውን ፣ የሲብሉን ህብረተሰብ መብት የሚገድበውን ያስወግድ ወይም ያሻሽል » ሲሉ አሳስበዋል።

ህገ ወጥ በሆነ እርምጃ የታሰሩ አያሌ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ ሽግግሩ ትርጉም ያለውና የፖለቲካ ምኅዳሩን እንዲከፍትም ሆነ እንዲያሰጋፋ ሲሉም ሌፍኮቭ አስገንዝበዋል።

የጠ/ሚንስትር መለስን ዜና ዕረፍትና መጪውን ጊዜ በተመለከተ የሁለት ዓለም አቀፍ ተቋማት ተማራማሪዎች በበኩላቸው አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። በመጀመሪያ በለንደን የስምጥ ሸለቆው ተቋም የተሰኘው የሰብአዊ መብት ተመራማሪ ድርጅት ባልደረባ ሳሊ ሂሊ የመለስ ሞት በኢትዮጵያ የሚያስከትለው ችግር ይኖር እንደሁ ተጠይቀው ሲመልሱ--

« መታወቅ ያለበት ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥታዊ ተቋማት ያሏት ሀገር መሆኗ ነው። ስለዚህ የጠ/ሚንስትሩ ሞት የአስተዳደር መናድ ያስከትላል ብለን መገመት የለብንም። በመጪው ጊዜ ምላሽ ማግኘት ያለበት ጥያቄ እነዚህን መንግሥታዊ ተቋማት የሚቆጣጠራቸው ማን ይሆናል? የሚለው ነው። ይህ ደግሞ ባስቸኳይ እልባት የሚያገኝ አይመስለኝም።

ምንም እንኳ በተለይ ከተቃዋሚው ወገን ዘወትር መለስ ብቸኛ አምባገነን ነበሩ የሚል አመለካከት ቢኖርም በበኩሌ መለስ እንዴት ይመሩ እንደነበረ ፣ በትክክል የሚገልጽ አባባል አይመስለኝም። ነገር ግን፣ የሥርዓቱ ዘዋሪ ነበሩ ማለት ይቻላል። እናም ፤ የእርሳቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየት በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። ቅጽበታዊ የሥርዓት መፈራረስ ያጋጥማል ማለት ሳይሆን ፣ በእርግጥ ለሀገሪቱ የአንድ አዲስ ምዕራፍ ጅምር ነው የሚሆነው።»

(------------------)

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 21.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15tu2
 • ቀን 21.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15tu2