የጠ/ሚ መለስ ህልፈትና ብሄራዊ ሀዘን | ኢትዮጵያ | DW | 22.08.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የጠ/ሚ መለስ ህልፈትና ብሄራዊ ሀዘን

ኢትዮጵያዉያን በጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈት ሀዘናቸዉን በተለያየ መንገድ እገለጡ መሆናቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ከአዲስ አበባ ዘገበ። እንደዘገባዉ ከሆነም እስካሁን የቀብሩ ዕለት እና ስፍራ አልታወቀም።

የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን የሚረከቡት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሁለት ቀናት ዉስጥ ምክር ቤት ቀርበዉ ቃለ መሃላ እንደሚፈፅሙም ተገልጿል። የአቶ ኃይለማርያም የስልጣን ዘመንም እስከ አዉሮጳዉያኑ 2015ዓ,ም ድረስ እንደሚዘልቅ ዘገባዉ አመልክቷል። ሮይተርስ ከናይሮቢ እንደዘገበዉ የ57ዓመቱ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ሞት ሀገሪቱ ዉስጥ የፖለቲካ ክፍተት ሳይፈጥር አልቀረም። የዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር መሐሪ ታደለ በበኩላቸዉ ይህን ይላሉ፤
«ሀገሪቱ የመረጋት ችግር ያላት አትመስልም በአሁኑ ስናየዉ፤ ለወደፊትም ቢሆን ዉስጣዊ የሆነ የፖለቲካ ሽኩቻ ካልተፈጠረና፤ ከተፈጠረም አሁን ወዲያዉ የሚፈጠር አይመስለኝም። ካልተፈጠረ በስተቀር ለወደፊቱ ለሀገሪቱ የሚጠቅም ሁኔታ ላይ የሚሄድ ነዉ። ይህ ከተባለ በኋላ ግን አሁን የስልጣን ክፍተት ባያጋጥምም የብቃት ክፍተት ግን ሊኖር ይችላል በአመራር ደረጃ።»

Äthiopien - Premierminister Haile Mariam Desalegne

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ


የፈረንሳይ የዜና ወኪል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊዉን ከራሳቸዉ ፓርቲ ማለትም ከህወሀት ሊተኩ ይችላሉ ያላቸዉን ፖለቲከኞች ስም ደርድሯል። ከደቡብ ተገኙ ካላቸዉ ከአቶ ኃይለማርያም ሌላ አቶ ብርሃነ ገብረክርስቶስ፤ የጠ/ሚ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን፤ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለዚህ ስፍራ እጩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነዉ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ከአዲስ አበባ የጠቆመዉ። በኢትዮጵያዉ ጠ/ሚ መለስ ሞት የተለያዩ መንግስታት እና ተቋማት ሀዘናቸዉን እየገለፁ ነዉ። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ አቶ መለስ እድሜያቸዉን ሙሉ ለኢትዮጵያ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ሲያወድሱ፤ የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ኪሙን በበኩላቸዉ ለአመራራቸዉና ለአፍሪቃ ጉዳዮች በመሟገት ይታወሳሉ ብለዋል። የአፍሪቃ ኅብረት ሞት የአፍሪቃን ጠንካራ ልጅ ነጠቀ ማለቱም ተዘግቧል። የIMF ዋና ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድም አፍሪቃ ቃል አቀባይዋን ማጣቷን ባወጡት የሀዘን መግለጫ ጠቅሰዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ