የጠ/ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ማስጠንቀቂያ እና የኦፌኮ አስተያየት | ኢትዮጵያ | DW | 17.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የጠ/ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ማስጠንቀቂያ እና የኦፌኮ አስተያየት

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አሸባሪ ባሏቸው ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ ። በአማራ ክልል ብጥብጥ አስነስተዋል ባሏቸው ላይም እንዲሁ መንግሥት ምህረት የለሽ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 02:39
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
02:39 ደቂቃ

የጠ/ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ማስጠንቀቂያ


የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን የአዲስ አበባና የኦሮምያ ልዩ ዞን የተቀናጀ እቅድን በመቃወም በተፈጠረው ብጥብጥ እጃቸው አለበት ባሏቸውና በስም ሳይጠቀሱ አሸባሪ ባሏቸው ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ ። በአማራ ክልል በቅማንትና በአማራ ብሄር መካከል ብጥብጥ አስነስተዋል ባሏቸው ላይም እንዲሁ መንግሥት ምህረት የለሽ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል ።የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ አባል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በምህፃሩ ኦፌኮ ግን መፍትሄው ውይይት እንጂ እርምጃ መውሰድ አይደለም ብሏል ።

የመብት ተሟጋች ቡድኖችም ኢትዮጵያ ባለፉት ሳምንታት ባንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተካሄዱትን እና መንግሥት የሽብርተኞች ስራ ናቸው ሲል የፈረጃቸውን ተቃውሞዎች በኃይል አፍነዋል ያሉዋቸውን የፀጥታ ኃይሎችዋን ከዚሁ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎች መንግሥት ተቃውሞዎችን ለማፈን በሚጠቀምባቸው ጥጥር ፀረ ሽብር ርምጃዎች ተገድለዋል በማለት ርምጃዉን እና መንግሥት ተቃዋሚዎቹን ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ያገናኘበትን ድርጊት በጥብቅ ነቅፎዋል።

መንግሥት ግን የሞቱት ሰዎች አምስት ብቻ እንደሆኑ ማስታወቁን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ያወጣው ዘገባ አሳይቶዋል። ዜና ወኪሉ በኬንያ የሚገኘው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሙቶኒ ዋንዬኬን ጠቅሶ እንዳመለከተው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይላቱ የፈፀሙትን ሕገ ወጥ ግድያ በማውገዝ ፈንታ፣ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ተጨማሪ የኃይል ርምጃ እንዲወሰድ አዞዋል። ሌላው የመብት ተሟጋች ድርጅት «ሂውመን ራይትስ ዎች»ም ኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎችዋ ከኃይሉ ተግባራቸው እንዲያስቆም እና የሰብዓዊ መብት እንድታከብር ጥሪ አቅርቦዋል። ባለፈው ወር የተጀመሩት ሰላማዊ ተቃውሞዎች ኃይል ወደታከለበት ሁከት መባባሳቸውን እና ተቃዋሚዎች ሲቭሉን ሕዝብ ማሸበራቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሚውኒኬሽን ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ለአዲስ አበባ ከተማ የነደፈዉ የማስፋፊያ ዕቅድ የኦሮሞ ሕዝብን ካካባቢው የሚያፈናቅል ነው በሚል በሀረማያ፣ ወሊሶ እና ሮቤ ከተሞች ተቃዉሞ መካሄዱን ዘገባዉ ጠቅሶዋል።

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
አርያም ተክሌ

ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic