የጠቅላይ አቃቤ ሕግ መስፈርቶች ከፖለቲካ ምህዳር አንጻር | ኢትዮጵያ | DW | 15.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የጠቅላይ አቃቤ ሕግ መስፈርቶች ከፖለቲካ ምህዳር አንጻር

ዛሬ ጠዋት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የፍርድ ሂደታቸው በመታየት ላይ የሚገኙ 528 ተጠርጣሪዎች ክስ በመጀመሪያ ዙር እንዲቋረጥ መወሰኑን ገልጿል። ይህን እዉን ለማድረግ ከተቀመጡት መስፈርቶች ዉስጥ ሕገ-መንግሥቱን ወይም ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን  ለመናድ ሚና ያልነበራቸዉ፤ የሰዉ ሕይወትን ያላጠፉ ወይም ጉዳት ያላደረሱና ሌሎችም ይገኙበታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:12

ተፈቺዎች መስፈርቶች ማሟላት አለባቸው ተብሏል

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ  ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የፍርድ ሂደታቸው በመታየት ላይ ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች ውስጥ በፌዴራል ደረጃ የ115፣ የተቀሩት ደግሞ ከደቡብ ክልል ክሳቸው እንደሚቋረጥ ተናግረዋል። ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ከፌዴራልና ከደቡብ ክልል ዉጭ በሌሎች ክልሎች ክሳቸዉ የሚቋረጥ ተጠርጣሪዎች ገና አለመቅረባቸዉን አሳዉቀዋል።     

ይሁን እንጂ ክሳቸዉ የሚቋረጥላቸዉ ተጠሪጣርዎች ሁሉ አራት መስፈርት ማሟላት እንዳለባቸዉ አስገንዝበዋል። መስፈርቶቹ «ሰው ያልገደለ እና ከባድ የአካል ጉዳት ያላደረሱ፣ ንብረት ያላወደሙ፣ሕገ መንግስታዊ ሰርዓቱን ለመናድ ቁልፍ ሚና ያልነበራቸዉ፣ መንግስት መስራት ሲገባው ግን ባልሰራቸው ስራዎች ምክንያት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተነድተው በግጭት እና ሁከት ውስጥ የተሳተፉ» ናቸው።  

ይፋ የተደረጉት መስፈርቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተወሰኑ የፖለቲካ አመራሮችና ግለሰቦች ከእስር ይፈታሉ ሲሉ ከገለፁት ጋር ይጣረሳል ሲሉ የሕግ ባለሙያዎች ይከራከራሉ። መስፈርቶቹ ማኅበረሰቡ ይፈታሉ ብሎ ተስፋ ያደረገባቸዉ እስረኞች እንዳይፈቱ የሚገድብ ነዉ ይላሉ።

«ሕዝቡ ይፈታሉ ብሎ በጉጉት እየተጠባበቀ ያለዉ በአቃብያነ ሕጎች አራቱንም መስፈርቶች ጥሰዋል በሚል የተከሰሱትን እንደሆነ» የሕግ ባለሙያው አቶ ሽብሩ በለጠ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። «የተቀመጡት መስፈርቶችን አሟልቶ ከእስር የሚፈታ ካለ ሰብዓዊ መብቱን ስለጠየቀ መጀመሪያዉኑም መታሰር አልነበረበትም» የሚሉት ደግሞ የሕግ ባለሙያዉ አቶ ተማም አባቡልጉ ናቸዉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፍርድ ቤት የተፈረደባቸዉ ወይም በአቃቤ ሕግ ክስ የተመሰረተባቸዉ የፖለቲካ አመራሮችና ግለሰቦች የተሻለ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሲባል፣ የዴሞክራሲና ፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት አንዳንዶቹ  ክሳቸዉ ተቋርጦ ምሕረት እንደሚደረግላቸዉ በቅርቡ መናገራቸዉ ይታወሳል። የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ያስቀመጣቸዉ መስፈርቶች የአገሪቱን የዴሞክራሲና ፖለቲካ ምኅዳሩን ያሰፋል ወይስ ያጠባል በተለያየ መልክ ሊታይ ይችላል። እንደ ሕግ ባለሙያዉ አቶ ሽብሩ አባባል መስፈርቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከተናገሩት ጋር ይጣረሳል።   

አቶ ጌታቸው አምባዬ በዛሬዉ መግለጫቸው እንደጠቀሱት በፌዴራል ደረጃ ያሉ 115 ተጠርጣሪዎች ዛሬ እና ነገ «የተሃድሶ ስልጠና» ከወሰዱ በኋላ ረቡዕ ይለቀቃሉ። ይሁን እንጂ «የተሃድሶ ስልጠና» የተባለዉ «ሰዉ ያለፍላጎቱ የርዕዮተ-ዓለም ትምህርት እንዲማር ማድረግ ስለሆነ ይህ በራሱ ወንጀል ነዉ» ሲሉ አቶ ተማም ተችተዋል።  

መርጋ ዮናስ 

አዜብ ታደሰ
 

Audios and videos on the topic