የጠቅላይ ሚንሥትሩ መልቀቂያ እና የእስረኞች መፈታት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 16.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የጠቅላይ ሚንሥትሩ መልቀቂያ እና የእስረኞች መፈታት

ባለፉት ጥቂት ቀናት በብዙዎች ዘንድ እንዲህ በፍጥነት ሊኾኑ ይችላሉ ተብለው ያልተጠበቁ ነገሮች ተከስተዋል። ጠቅላይ ሚንሥትሩ ሥልጣን መልቀቂያ አስገብተዋል፤ ታዋቂው ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከእስር ቤት ወጥተዋል፤የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ከእስር ወጡ። ብዙዎች በደስታ ሰከሩ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:35

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ባለፉት ጥቂት ቀናት በብዙዎች ዘንድ እንዲህ በፍጥነት ሊኾኑ ይችላሉ ተብለው ያልተጠበቁ ነገሮች ተከስተዋል። የፖለቲካ እስረኞችን መፈታት አስታከው በርካቶች በቀልድ መልክ ቢኾንም «አኹን ደግሞ ተራው የጠቅላይ ሚንሥትሩ ነው» ሲሉ ተደምጠዋል። እንደተባለውም አልቀረ ውሎም ሳይዳር ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ። ትናንት ከሰአት። በርካቶች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተቀባበሉት። ረቡእ እለት ታዋቂው ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከእስር ቤት ወጡ።  ብዙዎች በደስታ ሰከሩ። ማክሰኞ ለበርካቶች ሌላ ቀን ነበር። አያሌ ደጋፊዎች አደባባይ የተመሙላቸው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ  ከእስር የተለቀቁበት ቀን ነበር። ለሁሉም የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።

ብዙዎች የተቀባበሉት፤  በሰበር ዜና የቀረበው የኢትዮጵያ ብርድካስት ኮርፖሬሽን አጭር የቪዲዮ መልእክት እንዲህ ይንደረደራል፦  «ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከድርጅት ሊቀመንበርነት እና ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንሥትርነት በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ።» 

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ሰሞኑን ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላ ቀደም ያሉ ዓመታትን የቃኘ ሰው «ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከቁም እስር ይፈቱ» የሚል ሐረግ በተደጋጋሚ መመልከቱ አይቀርም። ብዙዎች ጠቅላይ ሚንሥትሩ «የይስሙላ እንጂ እውነተኛ ሥልጣን የላቸውም» ሲሉ መስማትም የተለመደ ነው። «አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ካሰራቸው የመለስ ዜናዊ መንፈስ መፈታት የሚችሉት እርሳቸው ነጻ መሆን ከፈለጉ ነው» ለትውስታ ያህል ግርማ ካሳ የዛሬ አራት ዓመት ያቀረቡት የፌስቡክ ጽሑፍ መንደርደሪያ ነው።

ዛሬም ከአራት ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ስላቅ እና ትችት ይስማል። ከጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች «እስረኞች ተለቀቁ አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚንሥትሩ ይፈቱ» የሚሉ መልእክቶችን ያሰራጩ ነበር። ፍስሐ ጌትነት በትዊተር «ጠቅላይ ሚኒስትር ይለ ማርያም ደሳለኝ የራ መልቀቂያ አስገቡ የሚለው ‹ጠቅላይ ሚኒስትር ይለ ማርያም ደሳለኝ እኔንም ከእስር ልቀቁኝ› አሉ በሚል ይተካ!» ብሏል።

አህመድ ትኩ ፌስቡክ ላይ የሰጠው አስተያየት፦ «ለውጥ የለውም፤ ሮም መሪዎቹ እኮ ሌሎች ናቸው ሳምፕል መሆን ሰለቸው!!» በሚል ይነበባል። «ኃይለማርያም ደሳለኝ ታሪክ አፅፈዋል ማለት ይቻላል» ያለው ደግሞ ሚክያስ አዳነ ነው በዛው በፌስቡክ ላይ። ሣሮን ሚልኪያስ፦ «እኛ  ወያኔ  ልጣን ይልቀቅ  አልን እንጂ  መቼ  ኃይለ ማርያም  ይልቀቅ  አልን» ስትል ጠይቃለች በትዊተር።  «ሁሉም ኢህአዴግ ሥልጣን ማስረከብ አለበት» የብሌን የናቷ ልጅ የፌስቡክ አጭር አስተያየት ነው። ጋዜጠኛ አርጋው አሽኔ በትዊተር  ባሰፈረው የእንግሊዝኛ ጽሑፉ ከታኅሣሥ ወር መጨረሻ አንስቶ ጠቅላይ ሚንሥትሩ ሊለቁ ነው የሚል ጭምጭምታ ይሰማ እንደነበር ገልጧል። «እያየለ ከመጣው ሕዝባዊ ተቃውሞ ባሻገር በደካማ አስተዳደር የተነሳ ሥልጣን እንዲለቁ በፓርቲያቸው ግፊት ተደርጎባቸዋል» ሲልም አርጋው ጽፏል። «ጉልቻ ቢለወጥ ወጥ አያጣፍጥም!  ገበየሁ ለማ ... አድሀኖም ገዱ ስልቻ ቀልቀሎ ... ቀልቀሎ ስልቻ !» ያለችው ደግሞ ሊያና ቢ ተፈሪ ናት በዛው በትዊተር ላይ።

ትናንት በጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ የተደመመው የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚ ረቡዕ ዕለትም ሌላ አስደማሚ ነገር ገጥሞታል። የአንድነት ለፍትኅና ዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) አመራር አካል የነበረው አንዷለም አራጌ እና ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ከ700 በላይ እስረኞች መፈታታቸው የተሰማበት ቀን ነበር።  በዕለቱ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች የእስረኞቹን መፈታት ከስፍራው እየተከታተሉ በፎቶግራፍ እንዲሁም በአጫጭር የቪዲዮ ምስሎች እያገዙ በማቅረብ ተጠምደው ነበር የዋሉት። 

የአንዷለም አራጌ ቤተሰቦች እስር ቤት ደጃፍ ኾነው ሲጠባበቁ የለበሱት ቢጫ ካናቴራ ላይ አንዷለም እጁን አገጩ ላይ አስደግፎ ወደጎን ሩቅ የሚመለከትበት ፎቶግራፍ ይታያል። ከትከሻ በላይ የሚታየው ፎቶግራፍ ከስሩ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ተዘርግቶበታል። ገዘፍ  ያለ «እንወድሃለን» የሚል ቃል ይነበባል።  በፈገግታ ተውጠው እየተጠባበቁ ነው። እስክንድርን ለመቀበልም ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከሌላ ሰው ጋር ኾኖ ትልቅ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ የተሽከርካሪው የፊት አካል ላይ ሲዘረጋ ይታያል በፎቶግራፍ። የሙስሊም አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን የሚጠብቁም በርካታ ሰዎችንም ያሳያሉ ፎቶግራፎቹ።

አቶ አህመዲን ጀበልን ጨምሮ አራት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)፣ አቶ ብርሃኑ ተክለ ያሬድ፣ በግንቦት ሰባት አባልነት ተከሰው በእስር ላይ የነበሩት ወ/ሮ  እማዋይሽ ዓለሙ እና የሽብር ክስ የቀረበባት ወጣት ሴና ሰለሞን፤ ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ፤ የቀድሞው የጋንቤላ ክልል ፕሬዝዳንት ኦኬሎ አኳይ እንዲሁም ሌሎች እስረኞች ተራ በተራ መለቀቃቸው በተደጋጋሚ ተሰማ፤ ፎቶግራፎችም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መሰራጨታቸውን ቀጠሉ። የአንዷለም እና የእስክንድር መለቀቅ ግን ዘግየት ብሏል። አንዳንዶች «ልብ አንጠልጣይ» ሲሉ በአጭር ቃል ገልጠውታል ኹኔታውን። በስተመጨረሻ ግን እነ አንዷለም እና እስክንድርም መፈታታቸው ተሰማ።

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተንሸራሸረው አጭር ቪዲዮ አንዷለም አራጌ ቀጣዩን መልእክት አስተላለፈ፦ «እኔ እንደተፈታው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፈታል።»  እስክንድር በበኩሉ ከእስር ቤት እንደወጡ ከአንዷለም ጋር በጋራ ከሚጓዙበት ተሽከርካሪ መስኮት ሁለት እጆቹን ዘርግቶ በማውጣት ቡጢውን ጨብጦ «ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ» ሲል ተናገረ።

ለማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ማክሰኞም ልዩ ቀን ኾኖ አልፏል። በዕለቱ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ እስረኞች ተፈትተዋል። አቶ በቀለ ከእስር እንደተለቀቁ በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በስታዲየም አቀባበል አድርገውላቸዋል። አቶ በቀለ ዶይቸ ቬለን ጨምሮ ከተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ጋር ያደረጉት ቃለ-መጠይቅ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተሰራጭቷል። አቶ በአቶ በቀለ ገርባ ሌሎች እስረኞች እስልካተፈቱ ድረስ ደስታቸው ምሉዕ እንደማይሆን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

ፖለቲከኞች፤ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች እስረኞች እንዲፈቱ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጥሪው ተበራክቷል። እስክንድር መስፍን ፌስቡክ ላይ ባሰፈረው አጭር ጽሑፍ፦ «የዋልድባ ገዳም መነኮሳት ይፈቱ !ገዳማችንን አሳልፈን ለስኳር ፕሮጀክት አንሰጥም በማለታቸው ግንቦት ሰባት ናችሁ ተብለው ከፍተኛ ስቃይ እና እንግልት ተፈጽሞባቸዋል» ብሏል። ሙሉዓለም መንግሥቱ በበኩሉ ጥቁር ቆብ እና ቢጫ አልባሳት ያደረጉ መነኮሳት ፎቶግራፍን አያይዞ ቀጣዩን መልእክት አስፍሯል። «እኒህ የዋልድባ ገዳም መነኮሣትስ? ሃይማኖት ተደፈረ፤ ደንበር ተጣሰ ብለው ነው የታሰሩት ስለምን እነሱስ አልተፈቱም? ስለናንተ የሚጮህ ባይኖርም አይዞአችሁ እግዚአብሔር ያስፈታችኋል» ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ለሦስት ቀናት የተጠራው የንግድ እና የመጓጓዣ እቀባ አድማ የተጠናቀቀው እነ አቶ በቀለ ገርባ በተፈቱበት ዕለት ነበር። ተቃውሞው ግን በተለያዩ አካባቢዎች ቀጥሏል።

በዚሁ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጎልተው ከወጡ ርእሰ ጉዳዮች መካከል የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ሥራ አስኪያጅ ጃዋር መሐመድ የፌስቡክ ገጽ ለሰአታት መዘጋቱ ይገኝበታል። የጀዋር ፌስቡክን ዳግም ለማስለቀቅ በድረገጽ (change.org) የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ተደርጓል። ቆየት ብሎም ዳግም ጃዋር ፌስቡኩ ዳግም መሥራቱን ገልጧል።

የዞን ዘጠኝ ጦማሪ አባላት ክስ መቋረጥም ሌላኛው የዚህ ሳምንት መነጋገሪያ ነበር።  በፍቃዱ ኃይሉ በፌስቡክ ገጹ፦ «ያለመሰልቸት ለደገፋችሁን ወዳጆቻችን በሙሉ፣ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እናመሰግናለን። የእኔ፣ የአጥናፍ እና የናቲ የፍርድ ቤት ጉዳይ ዛሬ ተቋርጧል» ሲል ጽፏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic