1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለትግራይ ልሂቃን የተላለፈው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጽሑፍ መልእክት

ማክሰኞ፣ ጥር 27 2017

የትግራይ ሕዝብ ካለፈው ቁስሉ ሳያገግም አሁንም በጦርነት ስጋትና ሽብር ላይ መሆኑን ጠ/ሚኒስትር አብይ አሕመድ ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለትግራይ ሕዝብ በተለይም ደግሞ ለትግራይ ልሂቃን ብለው ትናንት በትግርኛ ባስተላለፉት መልእክት፤ የትግራይ ልሂቃን ልዩነታቸው እንዲፈቱ ቀጥሎም ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር በሕግ አግባብ እንዲነጋገሩ ጥሪ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/4q1Xp
ጠ/ሚኒስትር አብይ አሕመድ
የኢትዮጵያ ጠ/ሚ አብይ አሕመድ ፎቶ ከማኅደርምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጽሑፍ መልእክት

 

ከረዥም ጊዜ በኋላ የኢትዮጵያው  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ትናንት በትግርኛ ለትግራይ ሕዝብ በተለይ ደግሞ ለትግራይ ልሂቃን ብለው ያስተላለፉት መልእክት፥ በርካታ ነጥቦችን ያካተተ ነው። የትግራይ ሕዝብ በታሪክ በኢትዮጵያ የነበረውን ትላልቅ ሚና በዝርዝር የሚጠቅሰው የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሦስት ገፅ ጽሑፍ፥ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ባጋጠሙ ቅሬታዎች ምክንያት የትግራይ መሬት የጦርነት ምድር ሆኖ ቆይቷል ብሏል። 

የትግራይ ሕዝብ ካለፈው ቁስሉ ሳያገግም፥ አሁንም በጦርነት ስጋትእና ሽብር ላይ መሆኑን ያነሳው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር የጽሑፍ መልእክት፥ ከዚህ እንዴት መውጣት ይገባል ለሚል በስክነት መነጋገር ያሻል ነው ያለው። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ልሂቃን መካከል መከፋፈል መኖሩን በማንሳት ልሂቃኑ ልዩነታቸውን በመግባባትና የትግራይ ሕዝብን አንድነት በሚያረጋግጥ መንገድ ሊፈቱ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በመቀጠልም ከፌደራል መንግሥት እና ሌሎች ሐይሎች ጋር ያላችሁን ልዩነት በዴሞክራሲያዊ እና ሕገመንግሥታዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ሁኑ ሲልም ለትግራይ ልሂቃን ጥሪ አቅርቧል።

ይህ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ መልእክት በተለይ በትግራይ ክልል በበርካቶች ዘንድ የመወያያ አጀንዳ ሆኗል። ጉዳዩን አንዳንዶች በአወንታ ሲያነሱት ሌሎች ደግሞ ስጋት የሚፈጥር ብለውታል። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡት ፖለቲከኛው አቶ ዮሴፍ በርሃ  የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልእክት ከጦርነቱ በፊት ከነበረው ጋር ያመሳስሉታል። ሌላው አስተያየት ሰጪ የፅላል ሲቪል ማሕበረሰብ አመራር የሆኑት አቶ ዳንኤል ነጋሽ በበኩላቸው፥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ጥሪ በአንፃራዊነት በአወንታ የሚታይ ይሉታል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ