1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች የማንነት ጥያቄ

ሰኞ፣ ሰኔ 12 2015

“በጠለምት፣ ማይፀምሪና ዲማ አካባቢዎች አጠቃላይ ህዝቡ ሰልፍ ወጥቷል፣ የሰልፉ ዋና ዓላማ እኛ የጠለምት ነዋሪዎች ማንነታችን ይከበርልን፣ ማንነታችን በአመፅ በጉልበት፣ ተጨቁነን የሰው ባህል፣ የሰው ማንነት ይዘን ለ30 ዓመታት ቆይተናል፣ አሁን ነፃ ወጥተናል፣መንግስት ላለፉት ሁለት ዓመታት ያለበጀት ቆይቷል፣ በጀት እንዲበጅትልን፡፡ ”

https://p.dw.com/p/4Slip
Protest held in areas where the Amhara and Tigray regions are in dispute
ምስል Tsegaye Eshete/DW

የጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ

የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው አካባቢዎች የአማራ የማንነት ጥያቄን በተደጋጋሚ ሲያነሱ የቆዩት የጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን በመያዝ ትናንትናም ወደ አደባባይ ወጥተዋል፡፡
የጠለምት አማራ አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ መምህር ፀጋዬ እሸቴ የሰልፉን ዓላማ በተመለከተ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ገልፀዋል፡፡
“በጠለምት፣ ማይፀምሪና ዲማ አካባቢዎች አጠቃላይ ህዝቡ ሰልፍ ወጥቷል፣ የሰልፉ ዋና ዓላማ እኛ የጠለምት ነዋሪዎች ማንነታችን ይከበርልን፣ ማንነታችን በአመፅ በጉልበት፣ ተጨቁነን የሰው ባህል፣ የሰው ማንነት ይዘን ለ30 ዓመታት ቆይተናል፣ አሁን ነፃ ወጥተናል፣መንግስት ላለፉት ሁለት ዓመታት ያለበጀት ቆይቷል፣ በጀት እንዲበጅትልን፡፡ ” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በወረዳው የሚመለሱ በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩም ማንነታችን እንዲከበር እንጠይቃለን ሲሉ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴው ሰብሳቢ መምህር ፀጋዬ አመልክተዋል፡፡
“ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ሆስፒታሎች  ወድመዋል፣ ሁሉም አገልግሎት እየሰጡ አይደለም፣ በጦርነቱ የተጎዱ ሰዎች አሉ፣ ከአለ አሳዳጊ የቀሩ ህጻናት አሉ፣ አዛውንቶች ያለጧሪ መንገድ ላይ ነው ያሉት፣ የመልሶ ማቋቋም ስራ እንዲሰራ፣ ወንጀል የፈፀሙ እንዲጠየቁ፣ ከሁሉም በላይ ግን አዲስ ማንነት፣ አዲስ አማራ እያልን ሳይሆን፣ ከዚህ በፊት ስሪታችን አማራ ነው፣ አሁንም በአማራነት ነው የምንቀጥል፣ በአማራነት ነው የምንተዳደር ነው ዋናው ጥያቄያችን”
ሰልፈኞች ከያዟቸው መፈክሮች መካከል፣ “ማንነታችን አማራ ነው፣ እኛ ጎንደሬዎች ነን፣  እኛ አማራ ነን እንጂ አማራ እንሁን ብለን አልጠየቅንም፣ ልማታችንንና ሰላማችን መንግስት ያስከብርልን” የሚሉ እንደሚገኙበት አንድ የሰልፉ ተሳታፊ አመልክተዋል፡፡ 
ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ለአካባቢዎቹ ምንም ዓይነት በጀት ከየትኛውም አካል እንደማይደርሳቸው የሚናገሩት ሰልፈኞቹ በየደረጃው ያለው የመንግስት አካል በጀት እንዲመድብላቸው ጠይቀዋል፡፡
“በጀት የለንም፣   የምናገኘው ነገር የለንም፣ የወረዳው  መንገስስት ይሁን፣ የፌደራሉ መንግስት ይሁን የክልል መንግስት በጀት ሊመድብልን ይገባል፣ አገር ሰላም እንዲሆን፣ ከወገንተኝነት ተላቅቀን ራሳችን በራሳችን የምንተዳደርበት እንድንሆን፣ መንግስት ከጎናችን ይሁን፡፡”
የኢፌድሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ  የሀገሪቱ የ2016 ዓም በጀት ሰሞኑን በፀደቀበት ወቅት ለኢፌድሪ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት ከየአካባቢዎቹ የሚነሳው ጥያቄ ተገቢ ቢሆንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዞንና ለወረዳ በጀት የመመደብ ስልጣን የለውም፡፡
ከስምንት ወራት በፊት የፌደራሉ መንግስትና ህዝባዊ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በደረሱበት ስምምነት  “ሁለቱ አካላት የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው አካባቢዎች በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ ህገመንግስት መሰረት ይፈታል” ቢልም እስካሁን በጉዳዩ በይፋ ዙሪያ የተደረሰበት ነገር የለም፡፡   
በቅርቡ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ባሕር ዳር በመጡበት ጊዜ አንድ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የማንነት ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች በሰላም እንዲፈቱ አስተያየት ሰጥተው ነበር፡፡
አስተያየቱን ተከትሎ የአማራና የትግራይ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች  ስለ አወዛጋቢ አካባቢዎች ቀጥተኛ ምላሽ ባይሰጡም “ከህዝቦች ፍላጎት በላይ የሚሆን ችግር ባለመኖሩ ልዩነቶችን በውይይት እንፈታልን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በሰለፎቹ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች  ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለአማራና ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዎች፣ ለአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ የሚመለከተው አካልና ለሌሎችም ኃላፊዎች ብደውል ስልካቸው አይነሳም፣ አሊያም ዝግ ነው፡፡

Protest held in areas where the Amhara and Tigray regions are in dispute
የጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች ጥያቄምስል Tsegaye Eshete/DW
Protest held in areas where the Amhara and Tigray regions are in dispute
የጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች ጥያቄምስል Tsegaye Eshete/DW


ዓለምነው መኮንን


ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ