የጎዳና ሥነ-ጥበብ በአዲስ አበባ | ባህል | DW | 19.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የጎዳና ሥነ-ጥበብ በአዲስ አበባ

አዲስ አበባችን ድንጋያማ ገፅታ ከሚኖራት «ዲዛይኖቹን በኢትዮጵያ ባህላዊ እቃዎች አምሳል የተለያዩ ታሪካዊና ተፈጥሮዋዊ ነገሮችን በመሳል ነዉ ድንጋያማዉን ገፅታ ለመሸፈን የሞከርነዉ። በሌላ በኩል ከተማም ስለሆነ አረንጓዴ ነገር ያስፈልገዋል በሚል፤ አደይ አበባን ዲዛይን አድርገን የሠራን።» ይላሉ ፤ የስነ-ጥበብ ባለሞያዎቹ!

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:24
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
16:24 ደቂቃ

የአዲስ የጎዳና ሥነ-ጥበብየአፍሪቃ ኅብረት መቀመጫ በሆነችዉ በመዲና አዲስ አበባ ጎዳናዎች ዳር ዳር በቆሙት ሰፋፊ የኮንክሪት ድንጋዮች፤ የመንገድ መክፈያ ኮንክሪቶች እንዲሁም ድልድዮችን የተሸከሙት ግንቦች ላይ ወጣት ሠዓልያንን በመምራት የኢትዮጵያዉያንን ባህል የሚንፀባርቁ ሥዕሎችን በመሳል ለከተማዉ ሌላ የዉበት ገፅታ በመስጠት አስተዋፅኦ ካደረጉት መካከል የኢትዮጵያ ሠዓሊያን እና ቀራፂያን በማኅበር ዋና ጸሐፊ ሠዓሊ ሰይፉ አበበን የተናገረዉ ነዉ።

አዲስ አበባ ዉበትና መናፈሻ ዘላቂ ማረፍያ ኤጀንሲ ለኢትዮጵያ ሠዓልያንና ቀራጽያን ማኅበር በቀረበዉ ጥያቄ መሠረት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ዳር ዳር ላይ በቆሙት ትልልቅ ኮንክሪት ድንጋዮች ላይ የኢትዮጵያን ባህላዊ ነገሮችን የሚያንፀባርቁ ሥዕሎችን ለመሳል ቻልን። ከተማችን ላይ ዘመናዊነት እየታየ ነዉ፤ ዘመናዊነት ግን ሥነ-ዉበትን አካቶ መሆን አለበት የሚልም እምነት ስላለን በቀለም ቡሩሻችን ለዓይን የሚታክተዉን ለአዕምሮ የሚያዳግተዉን ድንጋያ በጥበብ ለመሸፈን ሞክረናል፤ ሥዕሎቻችን ጥበብ በጎዳና የሚል መልክትንም ይዘዋል ሲሉ የገለፁልንን በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ሠዓልያንና ሥራቸዉን ይዘን በዕለቱ መሰናዶ ቀርበናል ።ጥበባዊ ሥራዎች ወደ ጎዳና ሲወጡ ኅብረተሰቡ ሥለ-ጥበብ የተሻለ ግንዛቤ ይኖረዋል፤ ከዚያም አልፎ ለከተማዋ ዉበት ሌላ ገፅታ ነዉ። በመሆኑም የአዲስ አበባን አዳዲስና ድንጋያማ ገፅታ በሥነ-ጥበብ ለመቀየር የነበረን ሕልም ተሳካ ሲሉ፤ የሠዓሊያንና የቀራፂያን ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሠዓሊ ሰይፉ አበበ ገልጸዉልናል።

« እንደሚታወቀዉ አዲስ አበባ የተለያዩ መንገዶች ተሰርታዉላታል። መንገዱ ተሰርተዉ ካለቁ በኋላ መንገዱ ላይ በርካታ ሰፋፊ ኮንክሪቶች ሆኖ ተከቦ ታየ። እነዚህ ሰፋፊ ድንጋዮች ለተመልካች አንዳንዴ መንገዱ ተሰርቶ ያላለቀ ስሜትን ሁሉ ይፈጥራሉ። እና እዚህ ላይ ሥዕል ብንስልበት እያልን እንጓጓ ስለነበርን ህልማችን እዉን ሆንዋል። ከአዲስ አበባ የዉበት መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ልማት ኤጀንሲ ደግሞ አንድ የጥያቄ ደብዳቤም ደረሰን። ጥያቄዉ በጎዳና ላይ የሚሠሩ የጥበብ ሥራዎችን በነዚህ ኮንክሪቶች ላይ እንድንሠራ ነበር። ጥያቄዉን ይዘን ወደ መሥርያ ቤቱ ሄድን በነገሩ ላይ ተነጋግረን ተደስተን ሥራዉን ለመስራት ተስማማን ተመለስን። ሥዕሉን ከመሳላችን በፊት ቦታዎቹን ፎቶ አንስተን በኮንፒዉተር ምን ሊሆን እንደሚችል ቁጭ ብለን ሠራን። እኔ ደግሞ በዲጂታል አርትና ዲዛይን ሞያ ስለምሠራ ማኅበሩ ነገሩን በኃላፊነት ሠጠኝ። በዚህም ወደ ስድስት ሰባት የሚሆኑ ናሙናዎች በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ባህላዊ ነገሮችን የሚንፀባርቁ ነገሮችን አካተን ሠራን። ይህን የሠራነዉን ናሙና ለአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤት፤ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ፤ እንዲሁም ለከተማዋ የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ኃላፊዎች አሳየናቸዉ በጣም ተደሰቱ። ይህን ሥዕል ልንሰራባቸዉ የተዘጋጃናቸዉ መንገዶች በተለይ እሁድ እሁድ የትራፊክ ጭንቅንቅ ስለማይኖር እሁድ እሁድ ተዘግተዉ እንዲሠሩ ተወስኖ እሁድ እሁድ መስራታችንን ቀጠልን።»

ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት በበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ የተቋቋመዉ የኢትዮጵያ ሠዓልያን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ስዩም አያሌዉ በበኩላቸዉ
«ይህች አዲስ አበባ ከተማችን የአፍሪቃ መዲና እየተባለች ነዉ፤ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫም እየሆነች ነዉ። ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መቀመጫም እየሆነች ነዉ። እና ቀለሞችዋ እየበዙ ነዉ የሚል እምነት አለን። እነዚህ ቀለማት ደግሞ አዲስ አበባን የሚወክሉ የአደይ አበባ/ አዲስ የሚመጣ አበባ፤ በሚል የተወሰኑ ሥራዎች ሰርተናል። ከዚህ ዉጭ ግን በጎዳ ና ላይ ከተሳሉት ስዕሎች መካከል፤ ከጥንታዊ ዘመን የዋሻ ስዕሎች ጀምሮ እስከ ዘመናዊ ማለት እስከ 18ኛ ክፍለ ዘመን ድረስ ያሉ ቅርሶችን ነዉ ለማሳየት የሞከርነዉ። ላሊበላ፤ አክሱም፤ በአልባሳት ላይ ያሉ ጌጣጌጦች፤ ጥለትን የመሳሰሉት ለየት ያሉ ስለሆኑ ትልቅ ዉበት ናቸዉ። በቀጣይ የኢትዮጵያዉያን ናቸዉ ብቻ ብለን ልንሰራቸዉ ያሳብናቸዉ ትልቅ ነገሮችም አሉ። በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ማበጠርያዎቻችን የሚያሳይ ሥዕልን ሰርተናል፤ የኮንሶ ኃዉልት ሁሉ የመሳሰሉትን ነገሮች ሰርተናል፤ ወደፊት ሌሎች ሌሎች ነገሮችንም ለመስራት እያሰብን ነዉ። በቀጣይ በሰፋፊዉ ለመሥራት እያሰብን ያለዉ ፤ በጎዳና የዉስጥ መተላለፍያ መንገዶች ዉስጥ ባሉት ሠፋፊ የኮንክሪት ግድግዳዎች ላይ እዉነት የኢትዮጵያዉነትን የሚገልጹ የሥነ-ጥበብ ሥራዎች ይሰራሉ ብለን ትልቅ የፕሮጄ ኃሳብ ለመሥተዳድሩ አቅርበናል። እነዚህን ሥራዎች በቀጣይ እየሰራን ነዉ ብለን ነዉ የምናምነዉ።»


በተለይ ቦሌና ወሎ ሰፈር ጎዳናዎች ላይ የቆሙት የኮንክሪት ድንጋዮች በቀለማት በተለይም ደግሞ ባህላዊ ምስሎችን በሚያንፀባርቁ ምስሎች በአማርኛ ፊደላት በግዕዝ ቁጥሮች በአበሻ ልብስ የጥበብ ዲዛይን ሁሉ መሞላታቸዉና በጎዳናዉ ለሚዘዋወረዉ ሕዝብ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረለት ነዉ የተነገረዉ። የሠዓሊያንና የቀራፂያን ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሠዓሊ ሰይፉ አበበ፤ በዚህ ፕሮጀክት የተሳተፉት ወደ 30 የሚሆኑ ወጣት ሠዓልያን መሆናቸዉን ገልፀዉልናል።
«በሥራዉ ላይ የተሳተፍነዉ ሦስት ሱፐር ቫይዘሮች እና ወደ ሠላሳ የሚሆኑ ወጣት ሰዓሊዎች ናቸዉ። የሥነ- ጥበቡን ሥራ ስንሰራ በደንብ እየተነጋገርን እየታዘዙንና እያስረዳናቸዉ ነበር ። ብዙ ሰዎች በሥራዎቻችን ተደስተዋል፤ በርካታ ሠዎች እንደሚሉት ይህን ኮንክሪት ወደ ሥነ-ጥበብ መድረክ መቀየር አለበት፤ መደፈን አለበት ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዉናል። በዚህም ከተማዋን በቡሩሾቻችን በፍጥነት ዉብ እናደርጋለን ብለን እናስባለን።»
የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ ሃሳብን ከሥዕል መሳያ ሸራና ወረቀት ባለፈ ለማኅብረሰቡ መልክት በተለይ አዲስ አበባ ላይ በተጀመረዉ አይነት የጎዳና ላይ የሥነ-ጥበብ ትርኢት አይነት መሆኑን ገልፀዋል። ይህ በጎዳና ላይ የሥነ-ጥበብ ክህሎትን የማሳየት ባህል በኢትዮጵያ መለመድ እንዳለበትም ሲሉ ነዉ ጥሪያቸዉን ያቀረቡት።


የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች በከተማዋ ይህን ሥራ እንዲሰሩ ሥራ ያቀረበዉ በአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የተቋቋመዉ የዉበት መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ልማትና አስተዳደር ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን፤ ለከተማችን ዉበት ይላሉ


« የከተማ ዉበት በሕንጻ ፤ በአካባቢ አጥሮች ፤ በቀለም የሚገለጽ ነዉ የሚሆነዉ። ሁለተኛ ዉበት በጣም የብዙ ነገሮች ድብልቅ ነዉ። በዉስጡ ባህል፤ ታሪክ፤ አኗኗርን ሁሉ አካቶአል። ዉበት ማንነትን ገላጭ ነዉ። ሃገራችን ቁጥር ስፍር የሌላቸዉ ማንነታችንን ከፍ የሚያደርጉ ባህላዊ እሴቶች አሏት። ስለዚህ ይህን ስናስብ ሰፋፊ ግንብ የሚመስሉ የመንገድ አካፋዮች ካሉ ማስዋብ፤ ለዓይን ጥሩ ገጽታ እንዲኖረዉ ማድረግ አለብን፤ ብለን ተነሳን። አንደኛዉ ይሠራበት ብለን ያሰብነዉ መንገድ አዲስ አበባ ቦሌ አዉሮፕላን ማረፍያ ጀምሮ ወደ ከተማዋ የሚያስገባዉ መንገድ ላይ ነዉ። ይህ መንገድ በርካታ ሰዎች የሚገቡበት በርካታ ሠዎች የሚንቀሳቀሱበት፤ ቱሪስቶች የሚታዩበት ቦታ ስለሆነ በመጀመርያ እዚህ ቦታ ላይ ያለዉን የመንገድ አካፋይ የተዋበ ማድረግ አለብን ብለን አሰብን ። በሌላ በኩል ይህን ቦታ ዉብ እናደርጋለን ስንል ምንን ይዘን ምንን ለማስተዋወቅ ነዉ የተነሳነዉ የሚለዉንም ጥያቄ አሰብንበት። ማንነታችንን የሚገልጽ ነገር አልን፤ በመጀመርያ አዲስ አበባ የሚለዉን ስም ዋና ከተማችን አዲስ አበባ የአበባ ምሳሌ ናት፤ አደይ አበባ ደግሞ በኢትዮጵያ ታዋቂዋ አበባ በመሆንዋ አደይ አበባን ለመሳል ወሰንን። ሌላዉ የኢትዮጵያዉያን የማበጠርያ አይነቶችንንም ስለናል። እነዚህ ማበጠርያ አይነቶዎች ከዘጠኙም ክልሎች የመጡ ናቸዉ፤ የአፋር ፣ የትግራይ፤ የሃረር፤ የጎንደር የደቡብ አካባባ ማበጠርያዎች ሁሉ ናቸዉ የተሳሉት። ሰዉ እነዚህን ማበጠርያዎች ሲያይ ይጠይቃል ይረዳል፤ በሌላ በኩል ሃገሪቱን ይተዋወቃል። ፤ የሙዚቃ መሳርያዎቻችንንም በዚሁ ኮንክሪቶች ላይ ስለናቸዋል፤ በዚህም ባህላችንን እያስተዋወቅንን ነዉ ማለት ነዉ፤ በተጨማሪ ዉበትም ነዉ »በአዲስ አበባ በተለይ ወደ ቦሌ መንገድ በሚወስዱ ጎዳናዎች ላይ የተሳሉት ባህልን ገላጭ የሥነ-ጥበብ ዉጤቶች በሰሞኑ ከፍተኛ ዝናብና ጎርፍ አልተበላሹ ይሆን፤ ሰዓሊ ሰይፉ አበበ እንደሚሉት አልተበላሸም።
« ስዕሎችን ለመሳል የተጠቀምነዉ የብረት ቀለም ነዉ። ይህ ቀለም ጥሩ ወዝም እንዳለዉ እናዉቃለን። ሰዓሊ ስለሆንም ምን ቀለም መጠቀም እንዳለብን። የትኛዉ ነዉ ጥሩ ቀለም ብለን እንመርጣለን። ግን በሚቀጥለዉ ጊዜ ከአንዳንድ የቀለም ፋብሪካዎች የተሻለ ቀለም የሚባለዉን ፤ አስር አስራ አምስት ዓመት መቆየት የሚችለዉን ቀለም ለመጠቀም እንሞክራለን። እስካሁን ግን ምንም የለቀቀ ነገር የለም። እንደዉም የመኪና ጢስ ምናምን ያጠቆረዉን ዝናቡ አጠበዉ ።»
ሰዓሊ ሰይፉ አበበ የቀለሙን ወጪ እንዲሁም የመሳያ ቡሩሽ በአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የተቋቋመዉ የዉበት መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ መሸፈኑን፤ ሰዓልያኑ በነጻ ግልጋሎት ማበርከታቸዉን ገልፀጸዉልናል። ሰዓልያኑ ይህን ሥራ በነጻ የሠሩት በሃገሪቱ የሥነ-ጥበብ ሥራን ማጉላት አለብን ብለን ስለምናምን ነዉ ሲሉ ገልጸዉልናል።


የአፍሪቃዉያንና የተለያዩ ዴፕሎማቶች መኖርያና መዳረሻ የሆነችዉ መዲና አዲስ አበባን በይዝትዋ በዉበትዋ ከሌሎች ታዋቂ የዓለም ከተሞች እኩል ማድረግ አለብን ብለን ተነስተናል ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የተቋቋመዉ የዉበት መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ልማትና ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን
«የአዲስ አበባ ሰዓልያን ማኅበር ትልቅ ተቋም ነዉ ።ያዉ እንደገለጽኩት አዲስ አበባ የአፍሪቃ መዲና፤ የአፍሪቃዉያን መዳረሻና መኖርያ ከተማም ናት። አዲስ አበባ የተለያዩ የዓለም ዲፕሎማቶች የሚኖሩባት ከተማም ናት። ይህን ከተማ ከሌሎች የዓለም ሃገራት መዲናዎች፤ እንድትስተካከልና ደረጃዋን የጠበቀች እንድትሆን፤ ብሎም የአፍሪቃዉያን መዲና የሚለዉን ጠብቃ እንድትዘልቅ ለማድረግ መሥራት ይኖርብናል። አሁን የተሠራዉ የሙከራ ሥራ ነዉ፤ ከዚህ ሥራ በኃላ ነዋሪዉ ምን አለ የከተማዋ ሰዉ ምን አስተያየት ሰጠ ስንል ሃሳብን አሰባሰብን ፤ የተሰጠን አስተያየቶች በሙሉ እጅግ ጥሩ ነዉ የሚል ነዉ። በቀጣይ የሃረር ግንብ የአክሱም ሃዉልቶች ፤ የላሊበላ ዉቅር ቤተክርስትያናት፤ የጥያ ትክል ድንጋዮች ፤ በባሌ የሚገኘዉ ዋሻ አለ፤ ፋሲለደስ የመሳሰሉ ኢትዮጵያን የሚገልፁ በርካታ ታሪካዊ ቦታዎችም አሉን። ከዚህ በተጨማሪ የኛን ማንነት የሚገልጹ አለባበሶች የፀጉር ሥራዎች፤ የአመጋገብ ሥርዓቶች ሁሉ አሉን። እነዚህን ነገሮች ራሳችን መግለፅ በምንችልበት ሁኔታ ቀለማትንም ጭምር በነዚህ ኮንክሪቶች ላይ እንዲያርፉ እንፈልጋለን። በዚህም እንደዚህ አይነት የዉበት ሥራ በከተማችን እንሰራለን ብለን እያሰብን ያለነዉ።


በአዲስ አበባ በመንገድና በቤቶች ግንባታ ተጠምዳ ከተማዋ አረንጓዴ ከመሆን ወደ ድንጋያማነት እየተቀየረች ነዉ የሚባለዉን ትችት ወ/ሮ አልማዝ መኮንን አስተባብለዋል። ይሄን የሚለዉ በቅርቡ አዲስን ያልጎበኘ ነዉ ባይ ናቸዉ።
« ይሄን የሚለዉ በቅርብ አዲስ አበባን ያላየ ነዉ። በርግጥ ቀደም ሲል አጀማመሩ ወደዝያ አጋድሎ ነበር፤ ግን ይህ ነገር ወድያዉ እንዲቆም ተደርጎአል። አሁን እየተከተልን ያለዉ የግንባታ ሥራ ከተማዋን አረንጓዴ የማድረግ መርህንም የተከተለ ነዉ ። 30% ፤ 30% ፤ 40% የሚለዉን መርህ እየተከተልን ነዉ ያለነዉ። ይህ ማለት 30 ከተማዋን አረንጓዴ ለማድረግ 30 ለመንገድ ሥራ 40 ደግሞ ለግንባታ ሥራ ስንል በመረሃግብር ይዘናል። በቅርቡ ካቢኔዉ የሚያፀድቀዉ የከተማዋ ፕላን ከተማዋን 30% አረንጓዴ ለማድረግ ብሎ ወስኖአል። ስለዚህ ከተማዋ ድንጋያማ ሆነች የሚለዉ፤ የመረጃ እጥረት ነዉ የሚመስለኝ።


በአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የተቋቋመዉ የዉበት መናፈሻና ዘላቂ ማረፍያ ልማትና አስተዳደር ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን ፤ ፕሮጀክቱን የመሩት የሠዓሊያንና የቀራፂያን ማኅበር ዋና ፀሐፊ ሰዓሊ ሰይፉ አበበም ያለምንም ክፍያ ለከተማዋ ነዋሪዎችና ጎብኝዎች ይንን ልዩ የጎዳና ላይ ጥበብ ለሰሩትን ሠዓልያንን አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ ሠዓልያና ቀራጽያን ማኅበር አዲስ አበባ ከተማን ለማስዋብ የጀመሩት ሥራ ይበል የሚያሰኝ ይመስለናል። በዝግጅቱ ቃለ ምልልስ በስጠት የተባበሩንን በሙሉ በማመስገን ሙሉ መሰናዶዉን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ


ሸዋዬ ለገሠAudios and videos on the topic