የጎዳና ላይ አደጋን ለመግታት የሚደረገው ሥነ-ቴክኒካዊ ጥረት፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 14.12.2011
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የጎዳና ላይ አደጋን ለመግታት የሚደረገው ሥነ-ቴክኒካዊ ጥረት፣

በትራፊክ መጨናነቅ ሳቢያ ፤ የዔሊ ዓይነት ጎዞ መጓዝም ሆነ መንፉዋቀቅ፣ ብዙዎች አሽከርካሪዎችን የሚያናድድ፤ የሚያበሳጭ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል። በኢንዱስትሪ በበለጸጉት ሃገራት ጎዳናዎች፣ የኢንዱስትሪው ነርቮች ናቸው ማለት ይቻላል።

default

6D

 ሥፍር- ቁጥር የሌላቸው የጭነት ተሽከርካሪዎች፤ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ከቦታ ቦታ ባያንቀሳቅሱ፣ ጥሬ ሃብቶችን ለኢንዱስትሪዎች ባያደርሱ ኖሮ ፤ ኤኮኖሚው ቀጥ! ነበረ የሚለው። በየታላላቅ መደብሮች ፣ የዕቃ መደርደሪያዎች ጢም ብለው የሚሞሉትም ፣ ተሽከርካሪዎች አዘውትረው   ስለሚያቀርቡ ነው። ከዚህ ሌላ፤ ህዝቡ ፣ ምቾቱ እንደተጠበቀ፣ ከሞላ ጎደል ፣ የትም ቦታ በሚያደርሱት ፣ በግል መኪናዎቹ መገልገሉን ለማቆም አይፈልግም።

ይሁንና፤ ፤ ለሥራ ፤ ለንግድ፤ ለኢንዱስትሪ  የሚበጅ ዕለታዊ እንቅሥቃሤ ብቻ አይደለም በጎዳናዎች የሚከሠተው። አደጋም ያጋጥማል። በኢንዱስትሪ በበለጸገችው ጀርመን፤ በጎዳናዎቿ፣ በትራፊክ  አደጋ ሳቢያ አምና ብቻ ከ 3,600 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ፣ 370,000 ቆስለዋል። አሳዛኝ ሁኔታ ነው ። የህንድ ደግሞ ከዚህ እጅግ የከፋ ነው። በዓለም ውስጥ በትራፊክ አደጋ እጅግ በዛ ያለ ህዝብ የሚያልቅባት ሀገር ህንድ ናት። በህንድ ሀገር፤ ከሞላ ጎደል በየደቂቃው የትራፊክ አደጋ የሚያጋጥም ሲሆን ፣ በ የ 4ቱ ደቂቃ ደግሞ አንድ ሰው በትራፊክ አደጋ ሳቢያ ህይወቱ ያልፋል። የህንድ መንግሥት የሰጠው መግለጫ እንደሚያስረዳውከ 2 ዓመት በፊት እ ጎ አ በ 2009 ዓ ም ፤ በአንድ ዓመት ብቻ ባጋጠመ ግማሽ ሚሊዮን ያህል የትራፊክ አደጋ ፤ 125,000 ሰዎች ናቸው ህይወታቸውን ያጡት። ጀርመን ውስጥ፤  በዚያው ዓመት ፤ በጎዳናዎች በደረሰ  አደጋ ፣ 4,152 ሰዎች ናቸው በአጭር የተቀጩት ። ጀርመን 82 ሚሊዮን፤ ህንድ ደግሞ 1,2 ቢሊዮን ኑዋሪዎች አሏት። የ 2006 የዓለም ባንክ መዘርዝር ጥናት እንደሚያስረዳው፣ በጀርመን ለየአንድ ሺው ኑዋሪ 600 አውሞቢሎች ፣ በህንድ ደግሞ ለ የአንድ ሺው 15 አውቶሞቢሎች ይደርሷቸዋል። በህንድ አሁንም በተሽከርካሪዎች ሳቢያ የሚደርሰው አደጋ እየጨመረ ሲሄድ፤  በብዙዎቹ የበለጸጉ ሃገራት እየቀነሰ በመሄድ ላይ ነው፤ ከህንድ የበለጠ የህዝብ ቁጥር ባላት ቻይና ጭምር!

አፍሪቃ ውስጥ በተሽከርካሪዎች ሳቢያ ጎዳና ላይ የብዙ  ሰው ህይወት ከሚጠፋባቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት ። እንዲያውም በዚህ ረገድ የመሪነቱን ሥፍራ ሳትይዝ እንዳልቀረች ነው የሚነገረው። እ ጎ አ በ 2008 ዓ ም፣ «ንውስዊክ» መጽሔት ባቀረበው ዘገባ ላይ የተሽከርካሪዎችን መጠንና የሚደርሰውን አደጋ  በስሌት በማሰብ በዓለም ውስጥ አደጋው ክፉኛ  የሚጎንጣት፤  በ የ 10,000  አውቶሞቢል፣  190 ሰው በአደጋ የሚሞትባት ሀገር አድርጎ  ነው ያቀረባት። ከግማሽ በላይ የትራፊኩ አደጋ እግረኞችን ያጠቃልላል፤ ከእነዚህም 20 ከመቶው ዕድሜአቸው ከ 18 ዓመታ በታች የሆነ፣  ልጆችና ወጣቶች ናቸው የአደጋው ሰለባዎች የሚሆኑት። የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ባቀረበው ዘገባ መሠረት ፣ ኢትዮጵያ  ውስጥ በተሽከርካሪ አደጋ ሳቢያ እስካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ድረስ ህይወታቸውን ያጡት ሰዎች ቁጥር  22,786 ደርሶ ነበር። ታይላንድ ፣ ማሌሺያ፤ ዩናይትድ እስቴትስም በብዛት የትራፊክ አደጋ የሚያጋጥማቸው አገሮች ናቸው። በአጠቃላይ ፤ ኢትዮጵያ ፣ በዚህ ረገድ ፤ ከዓለም  12 ኛውን ደረጃ ሳትይዝ አልቀረችም።

በዓለም ዙሪያ፣ በያመቱ ከ 1,2 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በተሽከርካሪዎች አደጋ ሳቢያ ህይወቱ  ያልፋል። ጠበቅ ያለ የመከላከያ እርምጃ ካልተወሰደ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት እንደሚያስጠነቅቀው እ ጎ አ በ 2020 ፣ በዓመት ውስጥ ከ 2 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በዚህ ሰው-ሠራሽ መቅሠፍት ህይወቱ ሊቀጠፍ ይችላል። በአሁኑ ጊዜ በአውቶሞቢል አደጋ ሳቢያ እንደተጠቀሰው ከሚሊዮን በላይ ህዝብ ብቻ አይደለም የሚሞተው። ቀላልና ከባድ የመቁሰል አደጋ የሚያጋጥመውም፤ አኀዝ  በ 20 እና  50 ሚሊዮን መካከል ሊሆን እንደሚችል   ነው የሚገመተው።

«በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ፣ እንደሚባለው በድርቅና ረሃብ ፤ በወባና በተለያዩ ተዛማች በሽታዎች ብዙ ሰዎች በሚሞቱበት በአፍሪቃው ክፍለ ዓለም ፤ በጎዳናዎች በሚያጋጥም የተሽከርካሪዎች አደጋ የሚያልቀው ሰው ቁጥር እየጨመረ መምጣት በጣሙን ማሳሰቡ አልቀረም። እንዲያውም፤ በ 5 እና 44 ዓመት የዕድሜ ዕርከን ላይ ለሚገኙ አፍሪቃውያን ፣ በሁለተኛ ደረጃ ለኅልፈተ ህይወት የሚዳርገው ፤ ይኸው በጎዳናዎች የሚያጋጥመው የትራፊክ አደጋ መሆኑን መዘርዝር ጥናቶች ይጠቅሳሉ። በአጠቃላይ ፤ 70 ከመቶ የትራፊክ አደጋ ሰለባዎች የአዳጊ  አገሮች ዜጎች ናቸው። ገሚሱ፤ ማለትም 50 ከመቶው  ህዝብ፤ በዕድሜ ከ 16 ዓመት በታች በሆነበት የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም፤ ይኸው ዘመናዊ ሰው-ሠራሽ መቅሠፍት ፣   የ 10 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እያስከተለ መሆኑም ተነግሯል።

 ለትራፊክ አደጋ  ዋና- ዋና መንስዔዎቹ፤  በተለያዩ ሃገራት፣ እንደ መንግሥታቱ ጥብቅ ደንብና መመሪያ፣ እንደ አሽከርካሪዎቹ  የትራፊክ ህግ አክባሪነት ፣ እንደ ህዝቡ ተባባሪነት ፤ እንደ አውቶሞቢሎች የተሟላ ቴክኒካዊ ይዞታ፤ ይለያያል።

ባለፈው ዓመት በግንቦት ወር ፤ የታወጀው እ ጎ አ ከ 2011-2020 ጎዳናዎችን አስተማማኝ የማድረግ፤   ዓለም አቀፍ እንቅሥቃሤ ፤ በመንግሥታትና በህዝብ ትብብር ፣ ይበጃሉ በሚባሉ አዳዲስ ደንቦችና የሥነ ቴክኒክ እገዛዎች፤ የትራፊክ አደጋ እጅግ ሊቀነስ እንደሚችል ተስፋ ይደረጋል።

አደጋን ለመግታት፣ አዲስ የአውቶሞቢል ሥነ-ቴክኒክ በጀርመን፤

ለአውቶሞቢል አሽከርካሪዎች፤ ለተሳፋሪዎች  ደኅንነት ጭምር  ታስቦ የተሠራው የመኪና ቀበቶ ፤ ድንገተኛ አደጋ ሲያጋጥም በቀጥታ ተስፈንጥሮ ለፊትና ደረት ተከላካይ የሚሆነው አየር የተመላ ፊኛ (Airbag) የተሽከርካሪ መግቻ ሥርዓት፤ እና አስተካካይ የኤሌክትሮኒክ መርኀ-ግብር ፤ በአነዚህ እገዛ ሳቢያ ባለፉት 20 ዓመታት የትራፊክ አደጋ ሰለባዎችን ቁጥር ግማሽ -በግማሽ ለመቀነስ ቢቻልም የአንድ ሰው ህይወት እንrk4 ማለፍም ሆነ በአደጋው ሳቢያ አላ,ካለ-ሥንኩልነት መደረግ ኅሊናን የሚያረጋጋ አይደለም።  በመሆኑም በጀርመን ሀገር በአውቶሞቢል ኢንዱስትሪዎች የሚሠሩ ተማራማሪዎች ፣ የአውቶሞቢል አሽከርካሪዎችንና ተሳፋሪዎችን ደኅንነት ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ ከመጣር የቦዘኑበት ጊዜ የለም። ታዲያ በዓለም ውስጥ አውቶሞቢል ለመጀመሪያ ጊዜ ከ126 ዓመት ገደማ በፊት በተሠራበት ሀገር ፣ በጀርመን፣ ከታወቁት የአውቶሞቢል ፋብሪካዎች መካከል የዳይምለር አክሲዮን ማኅበር አዲስ ግኝት አስተዋውቋል። የአሽከርካሪ  ረዳትም ተብሏል፣ግኝቱ። የታራፊክ አደጋን እጅግ ይቀንሳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ይኸው ግኝት፣ በመሠረቱ የዐይንና የአንጎልን አሠራር ተመርኩዞ ነው ተግባሩን የሚያከናውነው። (6 ማዕዘናዊ ርዑይነት(6 D Vision) ይኸው የሥነ-ቴክኒክ ፈጠራ ፣ ከሰው ልጅ የማስተዋል ሁኔታ ፈጥኖ ሊከሠት የሚችል አደገኛ ሁኔታን በመገንዘብ ከሌላ መኪና ጋርም ሆነ፤ ድንገት ወደ መንገድ ሮጦ የሚገባ ልጅ እንዳይገጭ ፣አሽከርካሪውን አስጠንቅቆ አደጋው እንዲገታ የሚያስችል ነው።

እንበል ከተማ ውስጥ፤ በሰዓት 50 ኪሎሜትር ፍጥነት የሚነዳ አሽከርካሪ፤ ድንገት አንድ ልጅ ሮጦ ከፊቱ ቢደቀን ፣ እርምጃ ለመውሰድ የአንዲት ሴኮንድ ጊዜ ነው ያለው። አውቶሞቢሉን ለማቆም ፣ መግቻውን ፤ በእግሩ ጠንከር አድርጎ ቢረግጥውም እንኳ 15 ሜትር  ከተንሸራተተ በኋላ ነው መኪናው መቆም የሚችለው። ይህ ደግሞ፤ የሚገጭ  ሰውን ህይወት ማትረፍ የማይቻል ሊሆን ይችላል። ግማሽ ሴኮንድ ቀደም አድርጎ እርምጃ መውሰድ ቢቻል ፤ ርቀቱን በ 7 ሜትር ነው ማሣጠር የሚቻለው።

የዳይምለር የምርምር ቡድን መሪ፣ ዑቨ ፍራንከ፣ ስለአደጋ መከላከያው መሣሪያ እንዲህ ይላሉ።

«ዋናው ጠቃሚ ጉዳይ፤ ተሽከርካሪው ልክ እንደ ሰው ሁለት ዐይን ኖሮት፤ ጋራ-ቀኙን፣ የሩቅ-የቅርቡን ርቀት እንዲያገናዝብ ነው ያደረግነው።»

ይሁንና 3 የካሜራ ዕይኖች ቢኖሩትም ተሽከርካሪው በ 3 ባቻ ሳይሆን፤ በ 6 ማዕዘናዊ አቅጣጫ ሁሉን እንዲከታተል ነው የተሠራው። ይኸው መኪና ውስጥ ሆኖ ዙሪያውን  ግራ ቀኙን ከቅርብና ሩቅ የሚቆጣጠረው ስድስት ዐይናው ኮምፒዩተር በተንቀሳቀሽ ስዕል በመመልከት አደጋ የሚደርስ መሆኑን  ሲገነዘብ ላ,ውቶሞቢሉ መሪና መግቻ (ፍሬን) ቅብበታዊ ትእዛዝ ያስተላልፋል ማለት ነው። ከዚህ ቀደም በዚህ ክፍለ ጊዜ እንዳወሳነው ያለአሽከርካሪ ጎዳና ላይ በኮምፒዩተር ርዳታ የሚሽከረከር አውቶሞቢል መፈተሹና ጎዳና ላይ ሊሠማራ እንደሚችል  የተመሠከረለት መሆኑ የሚታወስ ነው።

ግራም ነፈሰ ቀኝ ፤ በጎዳናዎች ላይ የተሽከርካሪ አደጋ እንዳያጋጥም፤ ከሰው, ዐይን በላቀ ሁኔታ በማገናዘብ የሚያስጠነቅቀው የአውቶሞቢል ባለ 6 ማዕዘናዊ ካሜራም ሆነ «ዐይን»

በዘንድሮው የጀርመን መጻዔ-ዕድል ሽልማት(ሱኩንፍትስፕራይስ) ለተሰኘው የ 250,000 ዩውሮ ሽልማት ከ 3 እጩዎች አንዲዱ ሆኖ መቅረቡ ፣ የዚህን የፈጠራ ውጤት ሰፊ ጠቀሜታ ጠቋሚ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 14.12.2011
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13Smg
 • ቀን 14.12.2011
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13Smg