የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና የላይፕዚሽ ትብብር | ጤና እና አካባቢ | DW | 08.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና የላይፕዚሽ ትብብር

ከዓመታት በፊትበ ኢትዮጵያ ትምህርቱንም ሆነ ዘመናዊ ህክምናን የሚሰጡ ሃኪሞች ቁጥር ትንሽ በነበረበት ጊዜ የያኔው የጎንደር የጤና ኮሌጅ ከጀርመኑ የላፕዚሽ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትብብር መጀመሩ ብዙ በሙያው የተካኑ ሀኪሞችን ማፍራት እንዳስቻለው ነው የሚነገረው። ጀርመንን ከፍሎ የነበረው ግንብ ከፈረሰ 30ኛ ዓመት ይደፍናል። ትብብሩ 40 ዓመት ተሻግሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:26

«ከጤና ኮሌጁ ጋር የተጀመረው ትብብር 40 ዓመት ሞላው»

የዛሬው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአራት አስርት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የህክምና ትምህርት መስጠት እንዲችል የተመቻቸ ተቋም መሆኑን ታሪኩን የሚያውቁ ይናገራሉ።  በጎርጎሪዮሳዊው 1954 ዓ ም የተቋቋመው የያኔው የጎንደር ጤና ኮሌጅ በዘመነ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በጤናው ዘርፍ ለሀገር የሚያስፈልገውን እውቀት እና ክህሎት ለማስፋት በኢትዮጵያ መንግሥት፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በዓለም የጤና ድርጅት እና በተመ የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ አማካኝነት ለህክምና ትምህርቤትነት የተመቻቸው  ከጀርመን ጋር በተደረገ ትብብር ጀርመናውያን ባለሙያዎች ወደዚያ በመሄድ እንዲሠሩ ማድረግ ጀመረ። በወቅቱ ከጎንደር የጤና ኮሌጅ ጋር ሙያዊ ትብብር ያደረገው የምሥራቅ ጀርመን አካል በሆነችው ላይፕዚሽ ከተማ የሚገኘው የካርል ማርክስ ዩኒቨርሲቲ ነው። በማስተማርና በህክምና ትብብር የተጀመረው ግንኙነት አድጎም የጤና ኮሌጁ ተማሪዎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወደ ላይፕዚሽ በመሄድ ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ መንገድ ተከፈተ። ዛሬ ራሱን ችሎ በኢትዮጵያውያን ምሁራን እና ባለሙያዎች የሚንቀሳቀሰው አንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ ሀኪም ብርቅ በነበረባት ኢትዮጵያ በርካቶችን በህክምናው ዘርፍ እያሰለጠነ ማቅረቡን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገሩለታል።

ያኔ ምሥራቅ ጀርመን ተብሎ ይታወቅ ነበረው የላይፕዚሽ ከተማ ዩኒቨርሲቲ እና የጎንደር ጤና ኮሌጅ ከአንድ ሳምንት በፊት የትብብራቸውን 40ኛ ዓመት ላይፕዚሽ ላይ አክብረዋል። ዘመናትን የተሻገረው የሁለቱ ዩኒቨርቲዎች ትብብር በሁለት ጉዳዮች ላይ ማተኮሩን በዚህ ክብረ በዓል ላይ ከተገኙት እና የጎንደር ጤና ኮሌጅ ተማሪ ከነበሩት አንዱ ፕሮፌሰር ያሬድ ወንድምኩን ገንፀውልናል።

ላይፕዚሽ ዩኒቨርሲቲ

ላይፕዚሽ ዩኒቨርሲቲ

ድምጽ 1 «ከ40 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የህክምና ትምህርት ቤት ብቻ ነበር የነበረው። በጥቁር አንበሳ ሀኪም ቤት ውስጥ የሚገኘው ሜዲካል ፋኩልቲ፣ እናም የሚፈጠሩት ሀኪሞች ቁጥራቸው ትንሽ ነው። በዚያን ወቅት ሁለተኛ የህክምና ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፈት ሲታሰብ ትልቁ ችግር የነበረው መምህራን ከየት ይገኛሉ የሚለው ነበር። »

ያኔ ይላሉ ፕሮፌሰር ያሬድ፤ ያኔ ወደጤና ኮሌጁ የሚገቡ ተማሪዎችን ከሁለተኛ ዓመት በኋላ የሚሰጡትን ሙያዊ የህክምና ትምህርቶች ሊያስተምሩ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ስለነበር፤ የታሰበው የህክምና ባለሙያዎችን የማፍራቱ ተግባር እንዲሳካ ጀርመናውያን ምሁራን ነበሩ የሚያስተምሩት። ከትምህርቱ ጎንለጎንም አስፈላፊውን የህክምና አገልግሎት ቀዶ ህክምናን ጨምሮ ጀርመናውያኑ ሀኪሞች በመስጠት ያገለግሉ እንደነበርም አንስተዋል።

ወደጀርመን ሀገር ለከፍተኛ ትምህርት ከተላኩ የያኔው የጎንደር የጤና ኮሌጅ ተማሪዎች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ያሬድ የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሃኪም ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ በሰሜን አሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ሜሪዋሽንግተን ሆስፒታል በመሥራት ላይ ይገኛሉ። የዛሬ አርባ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የነበረውን የህክምና ሁኔታ መነሻ በማድረግ በላይፕዚሽ እና በጎንደር ዩኒቨርቲዎች መካከል የተደረገው ትብብር ያስገኘውን አዎንታዊ ውጤት እንዲህ ይገልጻሉ።

ለተጨማሪ ትምህርት እና የሙያ ስልጠና ወደ ጀርመን የመሄድ ዕድሉን ያገኙ ኢትዮጵያዉያን ሃኪሞች ከሚቀስሙት እውቀት በተጨማሪ የአሠራር  እና የማስተማር ዘይቤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ውስጥም አስተዋፅኦ ማድረጉንም አንስተዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደተማሩበት እና ወዳገለገሉበት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብቅ ባሉበት ጊዜም ለዓመታት የዘለቀው ትብብር ያፈራውን ውጤት አስተውለዋል። አሁንም ታዲያ የሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ግንኙነት ቀጥሏል።

በላይፕዚሽ ዩኒቨርሲቲ እና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መካከል ዓመታትን የዘለቀው ትብብር በርካታ የህክምና ባለሙያዎችን ለኢትዮጵያ ማትረፉ ነው ከባለሙያው የተረዳነው። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በፌስቡክ ገፁ ላይም ትብብሩ ያስገኘለትን የሚያመለክት መረጃ ይፋ አድርጓል። እንዲህ ያለው ትብብር ሌሎቹም ዩኒቨርቲዎች እና ተቋማት ቢያገኙ በተለይ በጤናው ዘርፍ ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን ይታመናል። ፕሮፌሰር ያሬድ ከእንግዲህ የሚደረጉ ትብብሮች በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚፈሱ መሆን እንደማይኖባቸው ነው ያመላከቱት። በተጓዳኝነት ለመሥራት የሚፈልጉ ሁሉ ከኢትዮጵያ በኩል ሊያገኙ የሚፈልጉት ጠንካራ ነገር ለምሳሌ ለምርምር መመቸት፣ በርካታ ወጣት ባለሙያዎች መኖር እንዲሁም የበሽታ አይነቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ ያንን ተቋማት አጥንተው ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚኖርባቸውን ይመልክራሉ።

የኢትዮጵያ በርካታ የህክምና ባለሙያዎቿ ከሀገር ውጭ እንደሚገኙ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለዚህ በመንስኤነት የሚያነሱት በያዙት የህክምና ሙያ ተጨማሪ ክህሎት ለማሳደግ ማለምን ቢሆንም፤ ተመልሰው ወደሀገራቸው በመሄድ እንዳያገለግሉ ግን ለሥራው አስፈላጊ መሣሪያዎችም ሆኑ መድኃኒት አቅርቦት አለመኖር አለመገኘት፣ ለአገልግሎታቸውም ተመጣጣኝ ክፍያ አለማግኘትን ነው። ይህ ችግር የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የአፍሪቃ ሃገራትም ዋና ችግር መሆኑን ያረጋፈጡት ፕሮፌሰር ያሬድ በየህክምናው ዘርፍ ሀኪሞች አስፈላጊና ተቸማሪ ክህሎቶችን እሚያሳድጉባቸው የስልጠና መስኮች በሀገር ውስጥ እንዲያገኙ ማመቻቸቱን እንደ አንድ መፍትሄ አንስተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ከሀገር ውጭ የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች ለሀገራቸው አስተዋፅኦ እንደማያደርጉ አድርጎ ማሰብ ተገቢ እንዳልሆነም ያመለክታሉ።

ውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች ካሉበት እየተመላለሱ ከሚሰጡት የሙያ አገልግሎት ባሻገር  እሳቸውን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉት ወደ ሀገራቸው ጠቅልለው በመመለስ የመሥራት ፍላጎት እንዳላቸውም ነው የገለፁልን የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሀኪሙ። ሊያከናውኑ የሚችሉትን ከማስላት በተጨማሪ የሁኔታዎችን መስተካከል የሚጠብቁም ይመስላል። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና በላይፕዚሽ ዩኒቨርሲቲ መካከል ዘመናት የተሻገረው ትብብር ያስገኘውን አስመልክቶ እንደአንድ እማኝ ጊዜ ወስደው ላካፈሉን መረጃ ፕሮፌሰር ያሬድን በማመስገን ለዕለቱ ያልነውን በዚሁ እናብቃ።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic