የጎቤ እና ሽኖዬ ባህላዊ የወጣቶች ጭፈራ  | ባህል | DW | 30.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የጎቤ እና ሽኖዬ ባህላዊ የወጣቶች ጭፈራ 

በኦሮሞው የገዳ ስርዓት ከባድና የጥሞና ወቅት ተደርጎ ከሚወሰደው ወርሃ ክረምት ወደ የተስፋ እና ልምላሜ ምልክት የፀደይ ወራት ሲታለፍ የተለያዩ መልእክት ያላቸው የምስጋና እና ባህላዊ የጫወታ ስርዓቶች አሉ፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:00

ከክረምት ወደ ፀደይ ወር ሲገባ የምስጋናና ባህላዊ የጫወታ ስርዓት ነዉ

በኦሮሞው የገዳ ስርዓት ከባድና የጥሞና ወቅት ተደርጎ ከሚወሰደው ወርሃ ክረምት ወደ የተስፋ እና ልምላሜ ምልክት የፀደይ ወራት ሲታለፍ የተለያዩ መልእክት ያላቸው የምስጋና እና ባህላዊ የጫወታ ስርዓቶች አሉ፡፡
ለታላቁ የምስጋና እና የመሰባሰቢያ በዓል እሬቻ መዳረሻነት በወጣቶች ጫወታ የሚዘወተረው የሽኖዬ እና ጎቤ የወጣቶች ባህላዊ ጫወታ ከዚህ አንጻር ተጠቃሽ ነው፡፡
ይህ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለይም ከተሞች ላይ እየተመናመነ እየተዘነጋም መጥቷል ያሉት ወጣቶች ተሰባስበው በዓሉን በፌስትቫል መልክ በማክበር መልሶ ወደ ሚታወቀው ባህል ለመምጣት ተንቀሳቅሰዋል፡፡
ክረምት ስመጣ ወንዝ ስለሚሞላ አባ ገዳዎች እንደ ሽምግልና እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ለመስጠት ስለሚቸገሩ ከሰኔ 30 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 16 አርዳ ወይም ሜዳላይ አንድ እንጨት ተክሎ እርጥብ ሽንብራ ይዞ ከአከባቢው ራቅ ወዳለ ተራራ በመውጣት ጊና ወይም ንሰሃ ገብቶ ዋቃ-ፈጣሪን ክረምቱን በሰላም አሳልፈን የተራራቀውን ዘመድ አዝማድ ክረምቱን በጤና ጠብቀህ አገናኝን፤ ፍቅር እና አንድነትን ስጠን በማለት ይለምናሉ:: የጭለማ ምልክት የሆነው የወርሃ ክረም መውጣትን ተከትሎ የልምላሜ እና የተስፋ ወራት ቢራ ሲመጣ ግን ወንድ ወጣቶች ጎቤ እያሉ ሴት ወጣቶች ደግሞ ሽኖዬ ወይም አባቢሌ እያሉ ከቤት ቤትም እየተዘዋወሩ የአዲሱን ዓመት መልካም ምኞታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በውል የሚታወቀው ይህ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዋጠ እየመነመነ መምጣቱ አሳስቦናል ያሉት ወጣቶች ጎቤ እና ሽኖዬን በፌስትቫል መልክ በማክበር እንዲንሰራራ ካቀዱ አሁን ሶስት ዓመት ሆናቸው፡፡ የዛሬው መሰናዶያችንም በቅርቡ ለሶስተኛ ጊዜ በተሰናዳው በዚሁ ፌስቲቫል ላይ ያተኩራል፡፡
ባህሉን ለመታደግ እና ለማስተዋወቅ ነው ያሉት ወጣቶች ለሁለት ሳምንታት ገደማ በአዲስ አበባ እና አቅራቢያው ላይ ወዳሉ ከተሞች ተንቀሳቅሰው ባህላዊ ጫዋታውን ሲያቀነቅኑ ከርመው ለማጠቃለያ መርሃ ግብራቸው በኦሮሞ ባህል ማዕከል ተሰባስበዋል፡፡


ወንዶች በጎቤ ሴቶች በሽኖዬ ወይም አባብሌ ባህላዊ ጭፈራዉን ያቀልጡታል፡፡የጎቤ የአዲስ ዘመን ብስራት ባህላዊ ጨዋታውን ወንዶቹ 
ዳማን ፋርዳ ገርቡ ኛቴ
ያጎፍታኮ በገ ነገያን ባቴ…
ያዱሬሳኮ አርጌ (2)
እልመዩ ሆላ
ቢነስ ሂን ኛቱ 
ቢኔሳ ማና - አና ሲፍ ወያ እያሉ ይጫወታሉ ::
የልጃ ገረዶች የዘመን መለወጥ የብስራት ጨዋታ በሆነው ሽኖዬም ያላገቡ ልጃገረዶች ሰው ለአዲስ አላማ ላዲስ እቅድ በሚነሳሳበት፤ ምድሪቱም የተዘራባትን ዘር ቡቃያ በማብቀል ለገበሬው ተስፋ በምትሰጥበት በዚህን ወቅት፤ ያለከልካይ ማንም ሳይተኗኮላቸው ቁኒ /እንግጫ/ ነቅለው እንሾሽላ አስረው ፀጉራቸውን አደ- ጀሌ አሰርተው ከቤት ቤት ሄደው ቁኒ እየሰጡ በውብ ባህላዊ ጫዋታቸው መልካም ምኞታቸውን ይገልጻሉ::
ሺኖዬ ያሺኖዬ ቃሜ ያመስቀሎዬ
ወላሌ ወላሌ ሮቤ ያ ኮሎሌ
ያጋዲሴ ዱርባ ያጆሌ- ቃሜን ጌሴ 
በማለት አዲሱን ዘመን በአደባባይ እና ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ የሚቀበሉበት እና በሳምንቱም ለወራት ሳይገናኝ ተራርቆና ተነፋፍቆ የከረመን ዘመድ አዝማድ ወደሚያሰባስበው ታላቁ የኢሬቻ የምስጋና ቀን የሚያመሩበት በአዲሱን ዓመት የመጀመሪያ ወር የገዳው ስርአቱ ቱባ ባህላዊ እሴት አንድ አካል አድርገው ይከውኑታል፡፡
ቦራቲ አርት ፕሮሞሽን ከኦሮምያ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባር ይህን ጎቤ እና ሺኖዬ የተሰኙ የአዲስ ዓመት የአደባባይ የወጣት ወንዶች እና የልጃገረዶች ጨዋታ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ3ኛ ጊዜ ከጳጉሜን 2 እስከ መስከረም 09 ቀን 2014 የሺኖዬ እና ጎቤ ዓመታዊ ፌስቲቫል በማዘጋጀት በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ በማክበር የመዝጊያ ስነስርዓቱን መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በኦሮሞ ባህል ማዕከል  አከናውነውት ነበር፡፡ የሃሳቡ አመንጪና የቦራቲ አርት ፕሮሞሽን ስራ አስከያጅ ወጣት ብሩክ ግርማ “ኢትዮጵያ የራሷ የሆኑ ቱባ ውብና ባህላዊ እሴቶች እያሏት የሰው በሆነው የሪችት ማፈንዳት አዲስ ዓመትን መቀበል አይጠበቅባትም” ሲል ለአገር ባህል መሰጠት ያለበትን ትኩረት በአጽእኖት ያነሳል፡፡ ሌላዋ የፌስትቫሉ አስተባባሪ ወጣት ደራርቱ አራርሳ እንደምተለው ከፌስትቫሉ አንክዋር አላማዎች አንዱ እየጠፋ የመጣውን ባህል ከመታደግ ሌላ በተለያዩ አከባቢዎች በተበታተነ እና ባህላዊ እሴቱን ባልጠበቀ የሚከናወነውን ይህን ጫዋታ ወደ ተቀናጀ መንገድ ማምጣት ነው፡፡

የፌስትቫሉ ሀሳብ አመንጪ እና አስተባባሪ ወጣት ብሩክ ግርማ “ኢትዮጵያ አዲሱን ዓመት የምትቀበልበት መልክ ከተዘነጉ ሀገራዊ የዘመን መለወጫ ባህላዊ ክዋኔዎች የተቀዱ እንዲሆን እና ለተቀረው ዓለም ልናሳየው የምንችለው እና መላው ኢትዮጵያዊ ወደ አድባባይ ወቶ በራሱ ማንነት መነሻ በኢትዮጵያዊ ህብር ያጌጠ እና የህዝቦችን አንድነት እና ፍቅር የሚያጠናክር የዘመን መለወጫ ባህላዊ ክዋኔዎች እንዲኖረን ማስቻል ከመነሻ ውጥናቸው አንዱ” መሆኑን ያነሳል:: ይህ የዘመን መለወጫ የአደባባይ ጨዋታ ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት የሚቀበሉበት ትልቅ ፌስትቫል ሆኖ መላው ኢትዮጵያውያንን ከመሳብ አልፎ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት ዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ አገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን እስከ ማስቻል ያለሜም ነው ሲል አክሏል::
ይህን የወጣቶችን ባህላዊ ጭፈራ እና የመልካም ምኞት መግለጫ ስርዓት ከኢትዮጵያ ወጣቶችም አልፎ የአፍሪካ ወጣቶች ባህላቸውን የሚያንፅባርቁበት መድረክ እንዲሆን የማስቻል ዓለማ መያዙንም ነው የፌስቲቫሉ አዘጋጆች የሚገልጹት፡፡ እስከ መስከረም 9 በአዲስ አበባ ሁሉም ክ/ከተሞች እና በሁሉም የልዩ ዞን ከተሞች እንዲሁም ቢሾፍቱ እና አዳማ በመዘዋወር መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በኦሮሞ ባህል መዕከል መጠቃለያውን ባገኘው ሶስተኛው ዙር የሽኖዬ እና ጎቤ ባህላዊ የወጣቶች ጭፈራ ፌስትቫል ተገኝተው ለወጣቶቹ ምስጋና ያቀረቡት የቀድሞ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ ፌስትቫሉ የደበዘዘውን ባህል በማንሰራራት ረገድ ያለውን ፋይዳ አስረዱ፡፡
በፌስትቫሉ መዝጊያ ፕሮግራም ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ እውቅና ተሰጥቷል፡፡ ወጣቶቹ በማጠቃለያ መርሃግብራቸው የችቦ ደመራ ማብራት እና ሁሉቆ ስርዓትንም አከናውነው ተመራርቀው የዓመትም ሰው ይበለን ብለው ተለያይተዋል፡፡ 
 


ስዩም ጌቱ 
አዜብ ታደሰ 
 

Audios and videos on the topic